>

ከደመወዝ/ደሞዝ ጋ የተያያዘ ታሪክ እና በዓሉ ግርማ "የተሸነቆረ ወጪት ነህ" ያለው ትውልድ (ክፍሉ ሁሴን)

ከደመወዝ/ደሞዝ ጋ የተያያዘ ታሪክ እና በዓሉ ግርማ “የተሸነቆረ ወጪት ነህ” ያለው ትውልድ

ክፍሉ ሁሴን
የጃንሆይ ደመወዝ ስንት ነበር? “ሰማይ አይታረስ፤ ንጉስ አይከሰስ” በሚባልበት አገር የጃን ምንዳ መጠየቅ ነውር ነው ከተባለ እሺ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የክቡር አቶ አክሊሉ ደመወዝ ስንት ነበር? ያ ከይሲ መንግስቱ ኃይለማሪያምስ ስንት ይበላ ነበር? ያ መናጢ መለስ ዜናዊስ?
የደመወዝ/ደሞዝ ነገር ሲነሳ በየካቲት 1966 ወቴ ጠብመንጃውን ወድሮ ጃን ደሞዝ ጨምሩ ብሎ ያፋጥጣል። ጃም ይጨምራሉ። የአቅሙን መጎልበት የጃን አቅም መኮሰስ የተረዳው፤ እንዲሁም ጭማሪው ያላመረቃው ወቴም በድጋሚ ጭማሪ ብሎ ፍጥጥ ይላል። የዚህን ጊዜ አክሊሉ ሀብተወልድ ለጃ “እንጨምር ብንል እንኳ አገሪቱ ፈጽሞ ገንዘብ የላትም!” ብለው የብሄራዊውን ቋት መሟጠጥ እቅጩን ያስታውቃሉ። ልዕልት ተናኘወርቅ የጃ ልጅ (አማሪካ ገና ልዕልት ኢቫንካ ትረምፕ ሳይኖራት በፊት እኛ የራሳችንን empowered ኢቫንካ አፍርተን እንደነበር ልብ ይሏል) ቀበል አድርጋ “ኤዲያ! ውሻ ጆሮውን ቆርጠው ቢጥሉለት ስጋ የሰጡት መስሎት ይበላዋል፤ ስለዚህ ጭማሪውን እንፍቀድና ታክስ ወዲያው እንጣል!” ስትል ወይም እሜቲቱ ሲሉ ምክረ ሃሳብ እንደሰነዘሩ የቤተመንግስቱን መዋዕል ዋቢ አድርገው ብዙዎች ሸቅጠውበታል።
ወቴ በዚህ መልክ ዳግመኛ ደመወዙን አስጨምሮ ለጃ ታማኝ ነኝ እያለ ነቅሎ ከወጣበት ካምፕ ለመመለስ ሲዳዳ ተመሳሳይ የደሞዝ ጭማሪ ጥያቄ የነበረውን የሲቪሉን ማህበረሰብም ብሶት ለማስተጋባት ጳውሎስ ኞኞ ከአንባቢ የተላከለት አስመስሎ በጠይቁን አምድ፦
“ጥያቄ፦ ከቢኤ ዲግሪ እና ከኤምኤ ዲግሪ የቱ ይበልጣል?
መልስ፦ ኤምዋን ይበልጣል ደሞዝ ያስጨመረው።” ሲል ያትማል።
ይህ ትክዝ ያለኝ “በ400 ዶላር ደሞዝ ሰፈርህን ሁሉ እንድጠብቅልህ ትፈልጋለህ?” ወይ ብሎ አብይ አህመድ ዱባይ ላይ ምስኪን ሀበሾችን ሰብስቦ ሲደነፋ ስላየሁት ነው። በእድሜዬ የታዘብኩትን ይህን የታሪክ ምፀት ይበልጥ ወዝ ባለው መልክ እያነጻጸረ ይሄድበታል ብዬ የ50፣ የ60፣ የ70 ትውልድ ነኝ ብሎ “ግሩፕ” ከፍቶ ለጋበዘኝ ብሰድለት ጽሁፌን አንስቶ እኔን በማገድ በዓሉ ግርማ ደራሲው በተሰኘው መጽሐፉ “ከአፍንጫው አርቆ የማያስብ የተሸነቆረ ወጪት” ሲል የገለጸው ትርፍራፊ መሆኑን ግልጽ አደረገልኝ።
Filed in: Amharic