ጭፈራውን በልክ…?!?
ታምሩ ገዳ
የዘንድሮ ምርጫን ምንም ይሁን ምንም ውጤቱ አገር አሻረጋሪ ነው ሲባል ነበር። በዚህ መሰሉ ምርጫ አገር ወዴት እንደምትሻገር ውለን አድረን ማየት ነው። ከዚያ በፊት ምርጫው ዲሞክራሲያዊ እንደሆነ ገዢው ፓርቲ በተሳካ መንገድ ተወዳድሮ እንዳሸነፈ አድርጎ ማቅረብ ትርፉ ትዝብት ነው። ቢያንስ አዲስ አበባ ላይ እስከ ሌሊቱ ሰባት ሰዓት ተናንቆ የመረጠውን ሕዝብ ድምጹን ተዘርፎም ባታበሳጩት ጥሩ ነው። ለገዢው ፓርቲ ድምጽ ለመክፈልና በተቃዋሚ ስም ተቃዋሚን ለማዳከም ከሮጡት ውጪ ሕዝብ የሰጠው ድምጽ ሲሰረዝና ሲደለዝ ከርሞ ለመጣ ውጤት ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት ከትዝብት በላይ ይዞት የሚመጣ ጣጣ መኖሩን ውሎ አድሮ እናየዋለን።
የገዢው ፓርቲ ደጋፊዎች ተረጋጉ ይሄ ሕዝብ ሁሉን ይታዘባል።ለጊዜውም ቢሆን የሥልጣን ጥማትን ሺህ አይነት ሕገ ወጥ ተግባር በተፈጸመበት ምርጫ ይሄን ያህል ማቅራራት ዋጋ እንደሚያስከፍል ከቀደሙት አለቆቻችሁ ብትረዱት ጥሩ ነው።
አንዳንዱ ደግሞ ግንባሩን ሊያስመታ ይሮጣል። ለመጀመሪያ ጊዜ የግል ተወዳዳሪዎች ፓርላማ ገቡ ብለው ሰውን የሚያሳቅቁ ለአደርባይነታቸውም ቃላት የማይመርጡ አሉ። የሚታዘብ ሕዝብ አለና በሰረቃችሁት ሳይሆን ጭፈራው ድምጽ በሰጣችሁ ልክ አድርጉት።
ይልቅ ይሄን ያህል ገዢውን ፓርቲ ትወዱት እና ይሰማችሁ ከሆነ በግፍ ያሰርካቸውን ፍታ፣የፖለቲካ ቁርሾን በድርድር እና ውይይት ለመፍታት ቁጭ በል፣በዚህ የምርጫ ሒደት ብቻ ራስህን አታጃጅል፣ ሁሉን አቀፍና እውነተኛ ውይይት አድርግ ብላችሁ ምከሩ። እንዲያ ሲሆን ቢያንስ ጨፍሮ ከማፈር ያ ሁሉ የመረጠን የት ገባ ይሄ ሁሉ ተቃውሞ ከየት መጣ የሚባልበት ጊዜ እንዳይመጣ መስጋት ይገባል።