>

‹‹የቢሮክራሲው አማካሪዎች›› (ከይኄይስ እውነቱ)

‹‹የቢሮክራሲው አማካሪዎች››

ከይኄይስ እውነቱ


ከሀገር-በቀል ሽብርተኞች ጋር አብሮና ተባብሮ አገር በማፍረስ የተጠመደና ለዜጎች ደንታ የሌለው አገዛዝ እንደሠለጠነ ብናውቅም አልፎ አልፎ ዐቢይ ከሆነው አገራዊ አጀንዳ ወረድ ባሉ ርእሰ ጉዳዮች የምንነጋገረው ዘለቄታውን እና ሕዝብና አገር እንደሚቀጥሉ በማሰብ ነው፡፡

ከዚህ ቀደም ‹‹ውሱን የአገር ሀብትን የማባከን አንዱ መገለጫ›› በሚል ርእሰ ጉዳይ በመንግሥት አስፈጻሚ መ/ቤቶች ውስጥ ፋሽን እየሆነ የመጣውና ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት እንደወረደ ተቀድቶ (copy-paste ተደርጎ) ሥራ ላይ እየዋለ ያለ መደበኛና ኢ-መደበኛ መዋቅር ‹‹የውስጥና የውጭ አማካሪ እንዲሁም ቺፍ ኦፍ ስታፍ›› የሚባሉ አደረጃጀቶች መሆናቸውንና በአመዛኙ የሚፈለገውን ውጤት ከሚያስገኙ ይልቅ የሕዝብ ሀብት ብክነትን እና አላስፈላጊ የተንዛዛ አሠራርን (red tape) እንዳስከተሉ በመጠኑ ለመዳሰስ ሞክሬ ነበር፡፡ በዛሬውም ተሐዝቦቴ ይህ ‹‹አማካሪዎች›› የሚለው መዋቅር የቢሮክራሲው መደበኛ አደረጃጀቶችን (የሥራ ክፍሎችን) ከጥቅም ውጭ (redundant/irrelevant) እያደረገ እንዳለ ወይም የሥራ ኃላፊዎች መደበኛ ሥራቸውን በመተማመንና በድፍረት እንዳይወጡ በፍርሃት ሸብቦ መያዙን እንደ ባለጉዳይ ከጎበኘኋቸው ጥቂት መ/ቤቶች ለመገንዘብ ችዬአለሁ፡፡

ይህ አስተያየት ሥራቸውን ባግባቡ የሚወጡትን፣ ብቃቱ ያላቸውን፣ የአማካሪነት ሚናን በቅጡ የተረዱትን፣ ባለጉዳዮችን ጊዜ ሰጥተው አዳምጠው በትህትና የሚያስተናግዱትን አማካሪዎች አይመለከትም፡፡ ባንፃሩም አስተያየቱ አንድ የመንግሥት አስተዳደራዊ ተቋም በተሰማራበት የሥራ መስክ – እንደ ዓላማው፣ ተልእኮውና ሥልጣንና ተግባሩ ስፋት – ብቃት ያላቸው አማካሪዎች በጭራሽ አያስፈልጉትም የሚልም አቋም የለውም፡፡ 

ችግሩ ያለው ሁሉም መንግሥታዊ ተቋም አማካሪ ያስፈልገዋል ወይ፤ የአማካሪዎቹስ ቊጥር በምን መስፈርት ነው የሚወሰነው፤ ሚናቸው የመ/ቤቶችን መደበኛ አደረጃጀት (የሥራ ክፍሎችን) መተካት ወይስ መደገፍ/ማጠናከር ነው፤ በየቦታው የጐሣ ፖለቲካው ባመጣው የተረኛነት መንፈስ እንደ ‹ባለሥልጣኖቹ› በምደባ ተቀምጠው የመደበኛ ሠራተኛውን የመወሰን፣ በራሱ የመተማመንና ሃሳብን አመንጭቶ የበላዮቹን በምክንያታዊነት ለመገዳደር ያለውን ፍላጎት አላጠፋም ወይ፤ ከዚህም አልፎ እላይ እንደጠቀስነው አንድ መ/ቤት የተቋቋመበትን ዓላማ ለማስፈጸም የተደራጁትን የሥራ ክፍሎች አላስፈላጊ እስከማድረግ ደርሷል ወይ፤ ወዘተ. ለሚሉት መሠረታዊ ጥያቄዎች ተገቢውን መልስ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ከታዘብኋቸው መ/ቤቶችና ካነጋገርኋቸው የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ያገኘሁት መልስ ግን ጥያቄዎቹን በአዎንታዊነትና በምክንያታዊነት ደግፎ ለመመለስ የሚያበቃ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡

በመሠረቱ እውነተኛና ቅንነት ያላቸውን ባለሙያ አማካሪዎች ሲጀምር የማስጠጋት ሲቀጥልም የማዳመጥ ፍላጎቱ የለም እንጂ የትኛውም መንግሥት ቢሆን ያለ በጎ መካር አይጸናም፡፡ 

በሌላ በኩል አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች እንደሚሉት የጐሣ ሥርዓት በነገሠበት ባለፉት 31 ዓመታት ትውልዱን ለመግደል ከተደረጉት ግዙፍ ነውሮች አንዱ በትምህርት ሥርዓቱ ባጠቃላይ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተለይ የደረሰው ዝቅጠት ነው፡፡ እንደነዚህ አስተያየት ሰጭዎች ግምገማ ካለጥናትና በቂ ዝግጅት በፖለቲካ ውሳኔ ብቻ በየመንደሩ ስምና ግቢ ብቻ ታቅፈው የተቀፈቀፉት ‹ዩኒቨርስቲ› ተብዬዎች የሚያመርቱት ባብዛኛው ፍሬ አልባ ተማሪዎችን እንደሆነ፣ በየመንግሥት መ/ቤቶች የሚደረገው ምደባ በተለይም በኃላፊነት ቦታዎች ለአገዛዞች (‹ፓርቲያቸው›) ባለ ታማኝነት በመሆኑ እነዚህ መ/ቤቶች በአመዛኙ በዕውቀትና ልምድ ጦመኞች አለፍ ሲልም የታዘዙትን ሁሉ ‹አሜን/እሺ› በሚሉ አጎብዳጆች ተሞልተዋል ነው የሚሉት፡፡ ይህ ሁናቴ ባለፉት አራት ዓመታት አፍጥጦ አግጥጦ የለየለት በመሆኑ ባንዳንድ ተቋማት ‹አማካሪዎችን› አስቀምጦ መሥራቱ የግድ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ተራ የለት ተዕለት ጉዳዮች ሁሉ ‹አማካሪ› በሚባሉት መታየት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ በአንዳንድ የመንግሥት መ/ቤቶች የሥራ ክፍሎችን የሚመሩ ዳይሬክተሮች  (አቅሙና ችሎታው ያላቸው ጭምር) ሽባ እንዲሆኑ ተደርገዋል፡፡ ተረኛ ‹ድኩማኖቹ› እና አጎብዳጆቹ ደግሞ ተሰሚነት እንዲኖራቸው በመደረጉ የደንበኞች ጉዳዮች ፍትሐዊ ውሳኔ እየተነፈጋቸው ይገኛል፡፡ ለዚህ ዓይነተኛ ማሳያ ከሚሆኑ መንግሥታዊ ተቋማት አንዱ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ነው፡፡ አንዳንድ ‹አማካሪዎች› ኮሚሽኑ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶችን እንደሚያስተናግድና ለባለሀብቶች (ሕግና ምርጥ ተሞክሮን መሠረት አድርጎ) ጋባዥና ምቹ ከባቢን እንደሚፈጥር (investor-friendly) ተቋም ሳይሆን ሆን ብለው በትልቁም በትንሹም ባለሀብቶችን እንደ ጠላት ለማጥቃት (antagonize ለማድረግ) የተቀመጡ ይመስላሉ፡፡ 

ከዚህ ቀደም በጻፍሑት መጣጥፍ እንዳነሣሁት ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት የተቋቋመ መ/ቤት የበላይ ኃላፊዎች (‹አማካሪዎች›ን ጨምሮ) ቢሮዎች በተቻለ መጠን ለባለሀብቶች ክፍት ሊሆኑ ይገባል፡፡ በሥርዓት፣ በቅደም ተከተልና እንደ ጉዳዩ ክብደት ለማስተናገድ እንዲቻል በጸሐፊዎች አማካይነት ቀጠሮ መያዝ በቂ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ከዚህ አልፎ ‹ቺፍ ኦፍ ስታፍ› እያልን አላስፈላጊ ‹አጥር› መደንቀር ተገቢ አይደለም፡፡ ለሁሉም ቦታ አለው፡፡ የበላይ አመራሩም የሥራ አመራር ብቃቱን እና በመስኩ የሚያስፈልገውን ጠቅላላ ዕውቀት የሚያዳብረው ከሚመለከተው አማካሪ ጋር በጋራ በመሆን ባለጉዳዮችን ሲያወያይ ነው፡፡ ሌላው ያስተዋልሁት ችግር አንድ ኃላፊ በተለያዩ ምክንያቶች ሥራ ቦታው ላይ ባይገኝ በምክትሉ ወይም እሱ በሚወክለው ባለሙያ አማካይነት በመተካት መደበኛ ሥራ መስተጓጐል ደንበኞችም መጉላላት የለባቸውም፡፡ በተለይም አገልግሎት በሚሰጡ ተቋማት እገሌ የሚባል ኃላፊ ወይም ኦፊሰር የለም በማለት ከሳምንት እስከ ወራት የሚመላለሱበት አጋጣሚ ጥቂት አይደለም፡፡

በአንዳንድ መንግሥታዊ መ/ቤቶች ስንቀሳቀስ ካየሁት በጎ ነገር የሥራ ከባቢውን ምቹ አድርጎ ማስተካከል፣ ለሠራተኞችም ሆነ ለደንበኞች ማራኪና ሳቢ ማድረግ ከጠንካራ ተዐቅቦ ጋር (strong caveat) በበጎነት አይቼዋለሁ፡፡ ያገኘሁት መረጃ በማስረጃ መደገፉ እንደተጠበቀ ሆኖ በአንዳንድ ቦታዎች የሕንፃ የውስጥ ክፍሎችን ለማሳመር ተብሎ የወጣው ወጪ ሌላ የተሻለ አዲስ ሕንፃ ከሚያሠራም በላይ እንደሆነ ስንሰማ አገራዊ ሀብት በመባከኑ (በሚሊዮን የሚቈጠሩ ዜጎች በተፈናቀሉበት፣ በጦርነት በተጎዱበትና በረሃብ በሚሰቃዩበት አገር ውስጥ) እጅጉን ያመናል፡፡ መልካም ዕይታችንንም ያደበዝዘዋል፡፡ የሥራ ከባቢን ምቹ ማድረግ መልካም መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በቅድሚያ የሰው ኃይሉን በዕውቀት፣ በልምድና በበጎ ሥነ ምግባር ማነፁ ላይ በብርቱ መሥራት ይገባል፡፡ 

ለማጠቃለል ‹አማካሪዎች› ተብለው በየመንግሥት አስተዳደር ተቋማት በመዋቅርም ሆነ ከመዋቅር ውጭ የምናገኛቸው ግለሰቦች፤

1ኛ/ በቅድሚያ በተረኝነትና ለጥቅም በመጓተት የመጡ አለመሆናቸውን ማረጋገጥ፤ በተቻለ መጠን የሚያገለግሉትን ተቋም ጠንቅቀው የሚያውቁ፤ በሚመደቡበት ተቋም የሚኖራቸው ሚና ምን ድረስ እንደሆነ አጥርተው የሚያውቁ፤ በትምህርትም ሆነ በሥራ ልምድ እንዲሁም ሕዝብን በቅንነት በማገልገል ከዚህ ቀደም በሥራ አፈጻጸማቸውም ሆነ ባስገኙት ውጤት መልካም ስም ያስመዘገቡ፤ ምራቃቸውን የዋጡ መሆናቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ 

2ኛ/ የአማካሪዎቹ ተግባር በየትኛውም ሁናቴ የተቋሙን መደበኛ የሥራ ክፍሎች ተግባርና ኃላፊነት የማይተካ፤ ይልቁንም የሚደገፍ/የሚያጠናክር፤ በዋናነት ፖሊሲ ነክ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡

3ኛ/ አማካሪዎች በተቋሙ ውስጥ የራሳቸውን ደሴት ሠርተው ሳይቀመጡ ዕውቀትና ልምዳቸውን ለተቋሙ መደበኛ ባለሙያዎች በማስተላለፍና ከተቻለም የሥልጠና መርሐ ግብር በመቅረፅ ተተኪዎችን በማፍራት ተቋማት ራሳቸውን ችለው የሚንቀሳቀሱበትን የሰው ኃይል የማጠናከር ሚና እንዲጫወቱ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

Filed in: Amharic