>
5:21 pm - Monday July 19, 5356

ማመንና የሳይንስ እውቀት ለየቅል! ማጥላላት አላዋቂነትን አይሸፍንም። (በ አኒሳ አብዱላሂ)

ማመንና የሳይንስ እውቀት ለየቅል!

ማጥላላት አላዋቂነትን አይሸፍንም።

በ አኒሳ አብዱላሂ


ማስታወሻ

ከጥቂት ቀናት በኋላ በ 14 03 2022 ዓ.ም. ስቴፈን ሃውኪንግ ከዚህ አለም በሞት ከተለየ አራት አመት ይሆነዋል። ይህ አራተኛ የሙት አመት ቀን በበርካታ የሙያ ባልደረቦቹ ብቻ ሳይሆን ለተፈጥሮ ሳይንስ መዳበር ያበረከታቸውን ፅንሰ ሃሳቦች እንዲሁም ከሴት ልጁ ጋር በመተባበር ከ 10 አመት በላይ ለሆኑ ልጆች “የአፅናፈ አለም ሚስጢራዊ ቁልፍ 2007 ዓ.ም.” በተሰኘ ተከታታይ ድርሰቶችንና እንዲሁም “ወደ አፅናፈ አለም የማይታመን ጉዞ 2009 ዓ.ም.” ያነበቡ ሁሉ በአድናቆት የሚያስታውሱት እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም።

ስቴፈን ሃውኪንግ ታክሞ ሊፈወስ በማይችል በሽታ መለከፉን በተነገረው ጊዜ የ 21 አመት ወጣትና በወቅቱ የሂሳብና የአስትሮኖሚ ተማሪ ሲሆን ሁለተኛው “አልበርት አይንሽታይን” ይሆናል ተብሎ ከፍተኛ ተስፋ የተጣለበትም ነበር።  ስቴፈን ሃውኪንግ በደረሰበት የማይድን በሽታ በወቅቱ ጤንነቱን የመረመሩ ኃኪሞች ከ 2 እስከ 3 አመት እድሜ በላይ እንደማይኖረው ቢተነብዩበትም እሱ ግን የአካል ጉዳቱን እንደምንም ተቋቁሞ፣ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ትሩፋትን ለቀን ተቀን ኑሮውን ለማሸነፍና ለማህበራዊ ግንኙነት በመገልገል በርካታና በጣም የተደነቁለትን የምርምር ውጤቶችን በ 76 አመቱ ከዚች አለም በሞት እስከተለየ ድረስ ለማበርከት የታደለ ሊቃውንት ነበር። ከበርካታዎች ውስጥ አንዳንዶቹን ለመጥቀስ ያህልም፣

  1. በ 1973 ዓ.ም. በ 31 አመቱ ከሁለት የሙያ ባልደረቦቹ ጋር በመሆን ለታላቁ ፍንዳታ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ በሂሳብ ፅንሰ ሃሳብ ላይ የተመረኮዘ አድናቆትን ያተረፈ የምርምር ጥናታዊ ውጤት አቅርቧል። የከፍተኛ ትምህርት ተማሪ በነበረበት ወቅትም ከአንዱ ክፍል ወደሚቀጥለው ደረጃ ሲያልፍም በየወቅቱ እጅግ በጣም ጥሩ ውጤትን በማግኘት ነበር። እንዲሁም የ ፒ.ኤች.ዲ ዲግሪውን ለማግኘት “እየሰፋ ስለሚሄደው አፅናፈ አለም ጠባይና ምንነት” በተሰኘ ርዕስ ያቀረበው ምርምር በበርካታዎች የተደነቀለት ሲሆን በ 1977 አ.ም. ደግሞ በስበት ፊዚክስ (Gravitational Physics) የፕሮፌሰርነት ማዕረግን ለመላበስ የብቃ ትጉህና ብልህ ሊቃውንት ነበር። 
  2. በ 1974 ዓ.ም. ደግሞ አልጠግብ ባይ የሆነው ጥቁር ጉድጓድ (Black Hole) በአጠገቡ የሚያልፉ ማናቸውንም ቁስ አካላት የሚውጥ ብቻ ሳይሆን በጣም ዝግ ባለ ሁናቴ ጨረርን የሚተፋ፣ ከረጅም ጊዜ በኋላም ተኖ የሚጠፋ መሆኑን ባቀረበው ጥናታዊ ምርምር ይፋ አድርጓል። ጨረሩ ከጥቂት ጊዜ በኋላም ለሱ አክብሮት ሲባል በስሙ “ሀውኪንግ ጨረር” ተብሎ ተሰይሟል። ይህም በበርካታ የአፅናፈ አለም ተመራማሪዎች ዘንድ በከፍተኛ ደረጃ የሚታይ ነው ተብሎ የተደነቀለትና የተሞገሰለት እንደሆነም ይገለፃል። በዚህም Fundamental Physics Prize  2.3 ሚሊዮን ኦይሮ ድጎማን ያቀፈ ከኖቬል ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ሽልማት ሊበረከትለትም የበቃ ነበር።
  3. በ 1965 ዓ.ም. ከሙያ ባልደረባው ፕሮፌሰር ሮጀር ፔኖሮሰ ጋር በመሆን ታላቁ ፍንዳታ በሂሳብ ትምህርተ ፅንሰ ሃሳብ ላይ የተመሰረተ  ማስረጃ ለማቅረብ የቻለ ሲሆን በዚህም (Eddington Medal of Royal Astronomical Soceity) ሜዳሊያም ተሸልሟል። ሌላም ሌላም።

ስቴፈን ሃውኪንግ ስሙ ከአፅናፈ አለም ሚስጢራት (Black Hole, Time and Room) ጥቁር ጉድጓድ፣ የጊዜና ህዋ መፀነስ ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው። የዚህ ብልህ ሊቃውንትና መፅሃፍ ደራሲ ረቂቀ ሚስጢር ከፊዚክስ ፅንሰ ሃሳብ ጋር ጨርሶውኑ ምንም አይነት ግንኙነትም ሆነ በመስኩ እውቀት የሌላቸው ሳይቀሩ በከፍተኛ አድናቆት የሚመለከቱት እጅግ ብልህና አንደበተ ርቱዕ፣ ጥልቅ አዋቂነትን የተላበሰ እጅግ ተወዳጅነትንም ያተረፈ ሊቃውንት ነበር። ስቴፈን ሃውኪንግ ምንም እንኳ በተደጋጋሚ በተፈጥሮ ሳይንስ ምርምር አፅናፈ አለምን ለመፍጠር ፈጣሪ የማያስፈልግ መሆኑን ብቻ ሳይሆን ቀንደኛ ፀረ አማኝ አቴይስት እንደሆነ ቢገልፅም ከ 1996 ዓ.ም. ጀምሮ በሮማው ካቶሊክ ቫቲካን ተቋም ሥር በሚገኘው የሳይንስ አካዳሚ አባል ለመሆን የበቃ ብቻ ሳይሆን፣ አካዳሚው ስብሰባዎችን ባዘጋጁበት ሁሉ በተለያዩ ርዕሶች ከፍተኛ አድናቆትን ያተረፉ የሳይንስ ሊቃውንቶች በክብር እንግድነት በተጋብዙበት የውይይት መነሻ ፅሁፍ በአቅራቢነትም እንደ ሌሎቹ ሁሉ ታሪካዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ከፍተኛ ጥረት ያደረገ ነበር ስቴፈን ሃውኪንግ። በ 02.04.2005 ዓ.ም. ከዚህ አለም በሞት የተለዩት የሮማው ጳጳስ ዮሃንስ ፓውሎስ ሁለተኛ ብቻ ሳይሆኑ በአሁኑ ወቅት በሥልጣን የሚገኙት ጳጳስ ፍራንሲዝኮስም በቡራኬ አዳራሻቸው በክብር እንግድት ለመጋበዝና የሃሳብ ልውውጥ ለማድረግ የወሰኑት እነዚህን ክስተቶች ከግምት በማስገባት ሳይሆን እንዳልቀረ በበርካቶች የሚገመት ነው። ስለዚህ ክስተት ደግሞ በተለይ በኃይማኖትና በተፈጥሮ ሳይንስ መካከል መቀራረብን ያሳየ ተብሎ በበርካታ የታሪክም ሆነ የፖለቲካ ተንታኞች በተለያዩ ጊዜያት አሁንም ድረስ እያቀረቡበት ያለ ሁናቴ ይህንኑ መንፈስ የሚያጠናክር ነው።

የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ የአቶ አሳፍ ፅሁፍን      ለአራተኛው ሙት አመት ቀን መታሰብ እንደ መነሻ በማድረግ በሀገራችንም ሆነ በውጭ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ይህ ብሩህ ሊቃውንት ከመሞቱ በፊት ለቀሪው ትውልድ በቅርስነት ያስተላለፋውን መልዕክት አፈላልገው በጥሞና በማዳመጥ የዚህን በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ክብርና ሞገስን ለመጎናፀፍ የበቃን ሊቃውንት ፈለግ በመከተል በተለያዩ የተፈጥሮ ሳይንስ መዳበር የራሳቸውን አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱ ብቻ ሳይሆን በዚህም በመመርኮዝ ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው ደህንነት ጠቃሚ ሊሆን የሚችል ምርምር እንዲያደርጉ በትህትና ሲጋብዝ በሌላ እንደማይተረጎምበትም የጎላ ተስፋውን ከመግለፅ ጋር ነው።

ይህ ፅሁፍ በዋናነት አቶ አሳፍ በሰጡት አስተያየት ላይ ……..አጭር የህይወት ታሪክ! (አሳፍ ሀይሉ) ቢያተኩርም በመጠኑም ቢሆን ለብዙ አመታት በበርካታ ሊቃውንቶች ዘንድ የኖቬል የክብር ሽልማትን ይጎናፀፋል ብለው ከፍተኛ ተስፋ ቢኖራቸውም ቅሉ ይህንን ካባ ላልተላበሰው እውቁ የሂሳብ ትምህርትና አፅናፈ አለም ሊቃውንት ስቴፈን ሃውኪንግ አጭር የግል ታሪክና በሙያው ለተፈጥሮ ሳይንስ እድገት ስላበረከታቸው ውጤቶች ከላይ እንደቀረበው አጠር ባለ ደረጃ በማስታወስ ጭምርም ነው። 

ከዚሁ ጋር በማያያዝ ከኃይማኖት እምነት በተለየ የተፈጥሮ ሳይንስ የሰው ፍጡር ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ሁላ መልስ አለኝ ብሎ ባይቀናጣም በሙያዊ ጥናቶቻቸው ባለፉት በ 19 ኛውና 20ኛው መቶኛ አመታት ባብዛኛዎቹ ሊቃውንቶች የተገኙ ውጤቶቻቸው በየጊዜው እየተመረመሩ ትክክለኛ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ወደፊትም ቢሆን ሊታረሙ፣ ሊስተካከሉ፣ ሊዳብሩ የሚችሉ መሆናቸው በተደጋጋሚ እየተረጋገጠ ያለበት ሁናቴ ላይ የሚመሰረት ትንታኔ መሆኑን ከወዲሁ አበክሮ መግለፅ የግድ ይላል። በመሆኑም ሁኔታዎች ተስተካክለው ሲገኙ ስለ ታላቁ ፍንዳታና  ለመከሰቱ እርግጠኝነት ምክንያታዊ ስለሆኑ የምርምር ውጤቶች፣ ስለ ተፈጥሮ ሳይንስ መሰረታዊ የሆኑ ቀኖናዊ አስተምህሮትና ምንጮቻቸው፣  እንዲሁም ኩዋንተን ሜካኒክ ተብሎ ስለሚታወቀው የፊዚክስ ትምህርተ ሀሳብ፣ ስለ ተፈጥሮ ሕግና ቋሚ ቀመሮች ለአንባቢያን ለማካፋል ይሞክራል። በዚህም አንባቢያንን በተለይም ወጣቱ ትውልድ በምናባቸው ወደኋላ 14 ሚሊያርድ አመት ጉዞ እንዲጓዙና የሰው ፍጡር ከየት? ወዴት? ምንስ ይጠበቅብናል? ለሚሉት ወሳኝ ጥያቄዎች አብረን በጋራ ለመዳሰስ እንሞክራለን። ወደ ፅሁፉ እንግባ።

በቅርቡ የድረ ገጾች ታዳሚና የትንታኔ ፅሁፍ አቅራቢ የሆኑት አቶ አሳፍ ኃይሉ በእውቁ ሊቃውንት፣ በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ በ1979 ዓ.ም. የሉካሲያን ፕሮፌሰርነት ማዕረግ የተሰጣቸውና በተለይም ከ 1979 እስከ 2009 ዓ.ም. ለ 30 አመት በፊዚክስ ፅንሰ ሃሳብና ስነ ፈለክ (ኮስሞሎጂ) ዘርፍ ጥልቅ እውቀት ባካበቱት ስቴፈን ሃውኪንግ “ስለ ጊዜ አጭር የታሪክ ዳሰሳ፤ ከታላቁ ፍንዳታ እስከ ጥቁር (ጨለማ) ጉድጓድ “  A brief histoy of Time: From Big Bang to Black holes በተሰኘ ርዕስ የተፃፈ መፅሃፍ አንብበው የተመሰጡበትንና ወደኋላ መለስ ብለውም የራሳቸውን ግላዊ ታሪክ ያስታወሱበትን ባጭሩ ለአንባቢያቸው አካፍለዋል። ሆኖም አቶ አሳፍ በዚህ ብቻ አልተገቱም። በርካታ ጥያቄዎችን የሚያጭሩ የመንፈሳዊ መላክተኛ እስከሚያስመስላቸው ድረስ በውስጣቸው የሚዘዋወረውን የአማኝነት ፍላጎታቸውንም ለማንፀባረቅ ሞክረዋል። አሉታዊና አዎንታዊ ገፅታዎቹን በሚገባ ባልዳሰሱበት እንዲያው በደፈናው የሰው ፍጡር ትሁትነትን እንዴት ሊላበስ የሚያስችለውንም ጎዳናንም ጠቁመዋል። የበርካታ ሊቃውንቶችን ፅሁፍ አንብቦ መረዳት እንዴት ወደ አማኝነት ጎዳና የሚወስድ መሆኑን አበክረውም ገልፀዋል። “የወጣልህ በፈጣሪ አማኝ ያደርገሃል” በማለት ሲገልፁ የሚሰጠው ከዚህ ውጪ ሊሆን አይችልም። ሌላም ሌላም።

ከፈጣሪው የተሰጠው ነው ተብሎ በበርካታ አማኞች እንኳ የሚገለፀውን የማሰብ ነፃነቱን ሳይቀር በሚጋፋ መልኩ እንዲያውም በአንዳንዶች አስተያየት አርቆ አሳቢነቱንና አስተዋይነቱን የሚገድብ የበታችነት ስሜት እንዲያንፀባርቅ የሚገፋፋ፣ ራሱን ወደታች ዝቅ የሚያደርግ በሳቸው አገላለፅ “የአላዋቂነቴን ግዝፈት በመረዳት አንገቴን በሀፍረት አስደፋኝ” ሲሉ መግለፃቸው በሌሎች ቀደምት መጣጥፎቻቸው ያስተዋልኩላቸውን ስዕላዊ ገፅታ በዚህኛው መጣጥፋቸው አሽቀንጥረው ሲጥሉ አስገርመውኛል። አሳስቦኛልም በበኩሌ ለምን የመንፈስ ቅናት አድሮባቸው በፖለቲካው መስክ በተደጋጋሚ እንደሚያቀርብት ይቻላልን አንግበው (ወደፊት ይቻል ይሆናል እንዳለው ሃውኪንግ) የበለጠ ለማወቅና ለመረዳት ሌሎች በመስኩ የተፃፉ መፃህፍቶችን በማገላበጥ የእውቀት አድማሳቸውን ለማስፋት መሞከር ለምን እንዳልፈለጉ ሊገባኝ ያልቻለ ነው። ትምህርት ቀመስ በራሳቸው አገላለፅ “ለእንደኔ አይነቱ የቲዎረቲካል ፊዚክስ” ሆነው በሚገኙበት የስቴፈን ኃውኪንግ መፅሃፍ አቶ አሳፍም ሆኑ ሌሎች አንባቢያን ጨዋ እንድንሆን ተብሎ የተፃፈ ነው ሲሉ ስለ እሴቶቻችን አለቦታው መጠቀም በወንጀለኛነት እንኳ ባይሆን በአላዋቂነት የሚያስጠይቅ እንደሆነ ቢረዱ ይጠቅማቸው ነበር። ተስፋ ሰንቆ ባመኑበት ጎዳና መጓዝ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን በማስታወስ ማን ያውቃል ምናልባት ጊዜ አግኝተው ይህንን በበጎ መንፈስ የተከተበ የእርምት መጣጥፍ ካነበቡ በኋላ ወደ ሕሊናቸው ተመልሰው ስህተታቸውን የማረም ውስጣዊ ግፊትም ኃይል ይላበሳሉ የሚል ተስፋ አለኝ። 

በርግጥም የስቴፈን ሃውኪንግ መፅሃፍ የመጀመሪያ እትሙ ለንባብ የቀረበው በ1988 ዓ.ም. በኒው ዮርክ ከተማ በሚገኘው (Bantam Book Publisher) ባንታም ቡክ በተሰኘው ማተሚያ ቤት ከታተመ በኋላ ቢሆንም ተወዳጅነቱ ባብዛኛው እየጨመረ በመምጣቱ፣  በተለያዩ ከ 40 በላይ በሚሆኑ ቋንቋዎች ተተርጉሞ አሁንም ድረስ በአለም አቀፍ ደረጃ (ከ 10 ሚሊዮን በላይ መሸጡ ይነገራል) በብዛት እየተሰራጨና እየተነበበ ይገኛል። አቶ አሳፍ ምናልባትም ያነበቡት በድጋሚ ከተወሰኑ ማስተካከያ ታክሎበት የታተመውን እትም ሳይሆን እንደይማቀር መገመት ይቻላል።

የመፅሃፉ ይዘት በዋናነት ያተኮረው በተፈጥሮ ሳይንስና በከፍተኛ ትምህርተ ሂሳብ እውቀታቸው እምብዛም ለሆኑትና በበርካታ ሚሊዮን ለሚገመቱት ስለ አፅናፈ አለም በትንሹም ቢሆን ለማወቅ ጉጉት ላላቸው አንባቢያን ሁሉ በቀላሉ እንዲረዱት ተብሎ የተዘጋጀ ነበር። ስቴፈን ሃውኪንግ በዚህ ትንታኔው አንድ ልዩ አስተያየት ያደረገውና በመፅሃፉ ውስጥ ያካተተው በአልበርት አንሽታይን የተቀመረውን የኢነርጂ መምሪያ ደንብ  (E = mc2) ቀመርን  ብቻ ነው። 

በበኩሌ ስለ አፅናፈ አለም አፈጣጠር በውስጡ ስለሚገኙት ተፈጥሯዊ ህግጋትና አዳዲስ መረጃዎችን ለማግኘትና በዘርፉ ያለኝን የእውቀት ጥማት በየጊዜው ለማዳበር ሁሌም ጥረት ስለማደርግ አቶ አሳፍ የስቴፈን ሃውኪንግ መፅሃፍ ያሳደረባቸውን መደነቅ የምጋራቸው ነው። መፅሃፉን ካነበብክት የቆየ ቢሆንም አለፍ አለፍ እያልኩ በቅርብ ለሕትመት ከደረሱ ከሌሎች ትንታኔዎች ጋር እያጣመርኩና እያመሳሰልኩ ስለማገላብጠው አሁንም ድረስ ያልተለየኝ ቋሚ ባልደረባዬ ሆኖ ከጠረጴዛዬ ተቀምጦ ይገኛል። በአሁኑ ወቅት ዘመናዊ ስነ ፈለክ (ኮስሞሎጂ) በሚያስደንቅ ፍጥነት እየዳበረ በመምጣቱ በርዕሱ ላይ የታተሙና ለንባብ የቀረቡ ተመሳስይ ይዘት ያላቸው መፃህፍቶች በብዛት ይገኛሉ። በዚህም የተነሳ ፍላጎት ላላቸው አንባቢያን እንደዝንባሌያቸው ስለ ተፈጥሮ ሳይንስ የበለጠ አረዳድ ለማግኘት ካለፉት አመታት በበለጠ በርካታ አማራጮች ይገኛሉና ቢጎበኟቸው ጠቃሚነታቸው የጎላ ይሆናል።

በአሁኑ ወቅት ትኩረቴ በዚሁ ርዕስ በተመሳሳይ ሁኔታ ባለፉት 20 እስከ 25 አመታት ውስጥ በተደረጉ የአካላዊ ንጥረ ነገሮች ላይ የተደረጉ የምርምር ውጤቶችና ስለ አፅናፈ አለም ያለንን እይታ የሚያዳብሩትን በማካተት የተፃፉና ለንባብ  በቀረቡት በርካታ መፃህፍቶች፣ መግለጫዎችና የምርምር ውጤቶች ላይ ነው። አቶ አሳፍም በአንድ መፅሀፍ ላይ ብቻ ሳይወሰኑ  አለፍ አለፍ ብለው በነዚህ ላይ ቢያተኩሩ የበለጠ ይጠቅማቸዋል እንጂ አይጎዳቸውም።። በበኩሌ እንደ አቶ አሳፍ የመሰሉ ለተፈጥሮ ሳይንስ የምርምር ውጤቶች በሚመለከት ህሊናቸውን ክፍት የሚያደርጉ ኢትዮጵያዊያን ዝንባሌያቸውን ወደዚህ ቢያደርጉ በጣም ደስተኛ እንደሚያደርገኝ መግለፁ በአሉታዊ እንደማይተረጎምብኝ ተስፋዬ የጎላ ነው።

ወደ አቶ አሳፍ ጽሁፋቸው ስመለስ ትኩረቴን ስቦ ይህንን መጣጥፍ ለመፃፍ ያነሳሳኝ ስለ ትኩረት የሰጡት አስተያየት ነው። ለመሆኑ ግን ትሁትነት ምንድን ነው? የሚሰጠን ግንዛቤስ ምን ይመስላል? ትሁትነት የአንድ ሕብረተሰብ አባላት እርስ በርስ ተከባብረው የቀን ተቀን ተግባሮቻቸውንና ማህበራዊ ግንኙነታቸውን በአግባቡ ለመምራት ከሚጠቀሙባቸው እሴቶች መካከል አንዱ ነው። በዚህም የአንድ ግለሰብ ጠባይ በአዎንታውና በአሉታዊ መልኩ የሚያንፀባርቁ ገፅታዎችም የሚገለፅበት ነው። ጉረኛነት፣ ሁሉን አውቃለሁ ባይነት፣ ትዕቢተኛ፣ እብሪተኛ፣ ቀደም ቀደም ማለት፣ ሳይጠየቁ በማናቸውም ውይይት ጣልቃ ገብነት፣ እኔን ብቻ ስሙኝን ጠባይ ማንፀባረቅ፣ ራስ ወዳድነት ተገቢም ሆነ ተገቢ ባልሆነ ሁናቴ እውቅናን ሆነ ምስጋናን ለግል ብቻ መሻት እና ሌሎችም በአሉታዊ ገፅታቸው ማህበራዊ ግንኙነትን አደፍራሽ በመሆናቸው የነዚህ መሰል ጠባዮችን የሚያንፀባርቅ ግለሰብ ተወዳጅነት ሆነ አክብሮትን ስለሚነፈጋቸው በጎሪጥ የሚታዩ ናቸው። በዚህም የተነሳ ባይተዋርነት ስሜት እንዲሰማቸው የሚያደርግ ክስተት በበርካታ ጥናቶች የተረጋገጡ ናቸው። 

ትሁትነት ባጠቃላይ ደስተኝነትን፣ እርካታን የማግኘት ችሎታ ነው። ትሁትነትን የተላበሱ ሰዎች ደስተኛ ብቻ ሳይሆኑ ከውጭ በሚከሰት ማንኛውም እንከን የማይገቱ ነፃነትንም የተላበሱ ናቸው።  ስለ ትህትና አዎንታዊና አሉታዊ ገፅታዎቹ ትምህርት ሰጪዎች ፈላስፋዎች ብቻ ሳይሆኑ የኃይማኖት እምነት ተቋማትም በአስተምህሮታቸው ላይ የሚመሰረት ትሁትነትን የሚገልፁበት የየራሳቸው አረዳድ ይኖራቸዋል።

ትሁትነትን መላበስ የራስን መልካም ጠባዮችንና በጎ ተግባራት እንዲሁም በራስ ጥረትና ድካም የተገኙ አዎንታዊ የሥራ ውጤቶችን ማሳነስ ጨርሶ ሊሆን አይችልም። ይህ ማለት አሉታዊ የሆኑትን ከማስወገድና ወደፊትም እንዳይደገሙ ጥረት አለማድረግ ማለት አይደለም። አስፈላጊ ሆኖ በሚገኝበት ሁናቴም ለግልፅነትና ለሀቀኝነት በፅኑ አለመቆም ማለት ከቶዉንም አይደለም። በራስ አለመተማመንም ጨርሶ ሊሆን አይችልም። እንዲያውም ይበልጡኑ ከስህተት ለመማር ዝግጁነት እንዲኖር የሚያበረታታ ለዚህም ብርታትን የሚሰጥ እንደሆነ በርካታ ጥናቶች የሚጠቁሙት እንደሆነ ይታወቃል። ሰው በተፈጥሮው ሁሉን አዋቂ ሊሆን ከቶም አይቻለውምና።

ትሁትነት ሰዎች በሂደት ከተቀበሏቸውና ካዳበሯቸው ሌሎች እሴቶቻቸው ጋር በማጣመር በመካከላቸው ሊኖር ስለሚችለው ግንኙነት ጠልቆ ማሰብን፣ አብሮነታቸው እንዴት መጠናከር እንደሚችል ማሰላሰልን፣ ልዩነቶቻቸውን ማለዘብ፣ ሰላምና እፎይታ አግኝተውም በክፉም በደጉም ኑሯቸውን የሚገፉበት ሁኔታ ለማመቻቸት የሚጠቀሙባቸው እንጂ ሌላ ምንም ተአምር የላቸውም። እርስ በርስ ተደጋግፎ የሕይወት ኑሮን መግፋት፣ ሕሊናን ክፍት አድርጎ አንዱ ከሌላው እየተማረ የራስን የተፈጥሮ እውቀት ማሳደግ ጠቃሚ እንጂ ጉዳት እንደሌለው የሰው ፍጡር የሚገነዘበው ነው። ለዚህም አጥብቆ የሚታትር ነው። “የሰው ፍጡር አላዋቂ መሆኑን ለመረዳት የግድ ወደ ፈጣሪው ተንጠራርቶ መመልከት አይጠበቅብህም” ተብሎ ምከር መለገስ የመንፈሳዊ ትምህርትና አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙትን በርካታ ወንጌላዊያን በበኩሌ ለነሱ ጠበቃ መሆን ባይዳዳኝም በተሰጠው ምክር ለዘብ ባለ ገለጻ ቅር እንደሚሰኙ አቶ አሳፍ ግን ሊታወሳቸው አልቻለም። በርግጥም ለታላላቅ እውቀት ባለቤት ለሆኑ፣ የብዙ አስደናቂ ፀጋ ባለቤቶች ለሆኑ ሰዎችም እኮ በሁሉም መልኩ ከነዚሁ የበለጡ ሊኖሩ እንደሚችሉ ለምን ከግምት ማስገባት ያቅታል? አቶ አሳፍ ግን  በሙሉ ልብነት “እመነኝ ናሽናል ጂኦግራፊክ ፈጣሪ በኪነጥበቡ ወደዚች ምድር ያመጣቸውን ጉድ የሚያሰኙ ፍጡራን እያሳየህ የወጣልህ በፈጣሪ አማኝ ሰው ያደርገሃል“  በማለት ተፈጥመው ሲያበቁ ስቴፈን ሃውኪንግ ይህንን እምነታቸውን አደበላለቀብኝ በማለት ፈንታ በትሁትነት አሳበው ሊሸፋፍኑ ይውገረገራሉ። በበኩሌ አቶ አሳፍ ተማሪ ወይንም አስተማሪ ይሁኑ ባይገልፁም የቲዎረቲካል ፊዚክስ ትምህርት ቀመስ እንደሆኑ ግን የጠቀሱት ከስቴፈን ሃውኪንግ ጋር የማይስማሙበትን ፅንሰ ሃሳብ በማስረጃ እየሞገቱ ቢያስነብቡን ኖር ለግንዛቤያችን አዎንታዊ አስተዋፅዖ ባበረከቱ ነበር። ለዚህ ግን ድፍረቱ ስለጎደላቸው ይሁን አይሁን ባይገለፅም ይህንን ለባለሙያዎች ትተውታል። ምክንያቱም የፅሁፋቸው ዋናው መልእክት ቀደም ብሎ እንደተገለፀው በተዘዋዋሪ ሰዎች ወደተሳሳተ ኢአማኝነት እንዳይነጉዱ እንጂ ሌላ አይደለም። ይህን መሞከር መብታቸው ቢሆንም ምንም አይነት ማስረጃ ለማረቅብ ባልጣሩበትና የአዕምሮ ጂምናሲትክ ባልሰሩበት ልፋታቸው ከንቱ ሆኖ ይቀራል። ቀርቷልም። ለእውቀት መዳበር ጥርጊያ መንገድ ባለማሳየታቸው የፅሁፋቸው ጭብጥና ምክር ልገሳቸው ከንቱ ልፋት በመሆኑ ተመልሰው ቢያስቡበት መልካም ይሆናል።

ወደ ፅሁፋቸው በመቀጠል ከሁሉ በላይ  ልዩ ጥያቄ የሚያጭር ሆኖ ያገኙት የተፈጥሮ ሳይንስ ተመራማሪ ሊቃውንቶች በትምህርተ ሂሳብ ከፍተኛ እምነት ያላቸው መሆኑ በአቶ አሳፍ ላይ በጣም ከፍተኛ አግራሞትን መጫሩ ነው። አልፈው ተርፈውም “ቁጥርን እንደ እግዜር ሊያምኑት ምንም አይቀራቸውም” በማለት እየተሳለቁ “ለምንድን ነው በቁጥር ሁሉ ነገር ላይ እንደርሳለን ብለው የልብ ልብ የተሰማቸው” በማለት ሊቃውንቶቹን በሌሉበትና በማይውሉብት ቦታ ሊከሱ ይዳዳቸዋል። መች ይህ ብቻ። በተፈጥሮ ሳይንስ የምርመራ ውጤት ይሁን ወይንም በተመራማሪዎቹ ላይ አለበለዚያም ለፈጣሪያቸው ከወዲሁ ጠበቃ አቁመው ለመከራከር ይሁን “ቁጥርን ከእግዜሩ በላይ ለማመን” የሚል በምሁር ደረጃ የማይጠበቅ የስላቅ ጥያቄ በመሰንዘር በእውቅት የለሽ መድረክ ይውገረገራሉ። መች ይህ ብቻ። ላለፉት በርካታ አመታት ቋቅ እስከሚልና እስከሚሰለች ድረስ በብዙ ደርዘን ክርክሮች በደጋፊም ይሁን በተቃውሞ ጎራ ከፍተኛ ውይይት የተደረገበትን የታላቁ ፍንዳታ እንደ አዲስ ማቅረባቸው በርዕሱ ለነገሩ አዲስ መሆናቸውን ያሳብቅባቸዋል። ታላቁ ፍንዳታን ከወዲሁ እንደ ጭራቅ የፈሩት ይመስላል። ታላቁ ፍንዳታ ፅንሰ ሃሳብ(ቲዎሪ) ሳይሆን ጥልቀት ባለው ተደጋጋሚና በርካታ ጥናታው ምርምሮች የተረጋገጠ እውነታ ነው። የሚገርመው ግን ማንኛውም ጥናታዊ ምርምር ገደብ ሳይደረግበት በነፃ ሊከናወን መብት መሆኑ ተረስቶ ሃሳባቸውን ለማጠናከሪያ የሚረዳ መስሏቸው የፖላንዱ ተወላጅ የነበሩትና ለሮማ ካቶሊክ ርዕሰ ጳጳስ በነበሩት ብፁዕ ዳግማዊ ጳውሎስ ሁለተኛ ሮማ ከተማ ለሁለተኛ ጊዜ በተደረገው የስነ ፈለክ የጥናት ጉባኤ ላይ ስለ ታላቁ ፍንዳታ አትመርምሩ በማለት ምክር ይሁን ትዕዛዝ ስላቀረቡ ስቴፈን ሃውኪንግ ተሳለቀ በማለት ያልሆነ ታሪክ ለምን መተረክ እንዳስፈለጋቸው ግን ግራ የሚያጋባ ነው።

እስቲ ራሱ ስቴፈን ሃውኪንግ ስለዚህ ሁናቴ ራሳቸው አቶ አሳፍ አነበብኩት ከሚሉት መፃሃፍ የከተበውን አስተያየቱን ቃል በቃል ሳይሆን በግርድፉ ወደ አማርኛ በመተርጎም እንመልከተው። “በበኩሌ” ይላሉ ጳጳሱ ጳውሎስ ሁለተኛ “ከታላቁ ፍንዳታ በኋላ ስለተከሰተው የአፅናፈ አለም እድገት ምርምር ማድረጋችሁን አልቃወምም። ታላቁን ፍንዳታ ራሱን ግን ለመመርመር መሞከር የናንተ ተግባር አይደለም። ይህ የተፈጥሮ መጀመሪያና የፈጣሪ ሥራ ነው።” በማለት በመግለፃቸው ስቴፈን ሃውኪንግ ይህንን አስመልክቶ የራሱ አስተያየት እንደሚከተለው ያቀርባል። “እኔ በቅርቡ በስብሰባው ላይ ስላቀረብኩት ትንታኔ የተገለፀላቸው ወይንም ያወቁ አይመስለኝም። ስለ ሕዋና ጊዜ (Space and time finite) መሆን፣ ወሰን የለሽ መሆናቸው የሚሰጠው ግንዛቤ መጀመሪያና ለፈጣሪ መኖር ቦታ አይሰጥም። በበኩሌ የሃሳብ መጣጣም ከተቆራኘሁት በተለይም ጋሊሌዮ ከሞተ ከ 300 አመት በኋላ የተወለድክት እኔ የሱን ፅዋ ለመጋራት ጨርሶ ፍላጎት የለኝም” (ገፅ 148) የሚል አስተያየት ነው ያቀረበው። ታዲያ በምን ማጠየቂያነት ነው ይህ አስተያየት በአቶ አሳፍ በስላቅነት የሚተረጎመው? እንዲያውም በሕይወቱ አራት ጳጳሳትን ለመገናኘት የታደለ አንደበተ ርቱዕ የነበረው ስቴፈን ሃውኪንግ የሃሳብ ልዩነት ቢኖረውም ከበሬታን እንጂ ስላቅነት የግንኙነቶቹ ሁሉ የመገለጫ ጠባይ አይደለም፣ አልነበረም።

ሆኖም ስቴፈን ሃውኪንግ የጋሊሌዮ ፅዋ በኔ ላይ እንዲደርስብኝ አለፈልግም ማለቱ አለምክንያት አልነበረም። በወቅቱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን መሬት እምብርት ሆና ፀሃይና ጨረቃዎች ሌሎቹ ፕላኔቶችም በሷ ዙሪያ የሚሽከረከሩ ናቸው በማለት ለብዙ አመታት የነበራቸውን አመለካከት ጋሊሌዮ ስህተት መሆኑን በጥናት ማጋለጡ ብቻ ሳይሆን በወቅቱ በነበረው የመገናኛ ቋንቋ በጣሊያንኛ ማሳተሙ፣ በርካታው ሕዝብ የምርምሩ ተካፍይ እንዲሆን ፈር መቅደዱ ያልተዋጠላቸው፣ ራሳቸውን የእውነት ጠበቃ በሚቆጥሩ የበፊቱ እይታ አቀንቃኞች ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ በማሰብ የምርምሩን ውጤት እንዲያስተካክል ቢጠይቁትም በጥናቱ እርግጠኝነት ሙሉ እምነት ያደረበት ሊቃውንት ግን አሻፈረኝ በማለቱ ለቁም እስር ተዳረገ። ንትርካቸው እየጋለ በሄደበት ወቅትና የጋሊሊዮም ግትርነት ታክሎበት ከሞት ቅጣት ሕይወቱን ለማትረፍ ሲል ሃሳቡን እንዲቀይር ተገደደ። የቁም እስር ቅጣቱ ግን እስከለተሞቱ ድረስ ፀንቶ ቆይቷል። 

ዛሬ ከብዙ መቶ አመታት በኋላ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ለብዙ አመታት ስትከተለውና አስተምህሮቷን ስታስፋፋበት የነበረውን እይታና ጋሊሌዮ ላይም ተወስዶ የነበረ የፍርድ ውሳኔ ስህተት መሆኑን በይፋ በጳጳሱ ዮሃንስ ጳውሎስ ሁለተኛ ተገለፀ።  ከዚህ ውሳኔ ለመድረስ የተቻለውም በጳጳሱ አነሳሽነት ተመስርቶ የነበረው አጣሪ ኮሚቴ ከ 13 አመት በኋላ በደረሰበት ውጤት ላይ በመመስረት ነበር። የሊቃውንቱ ትክክለኛነት በገሃድ ተረጋገጠ፣ እውነትም ከተረገጠችበት ቦታ ራሷን ቀና አድርጋ ማንነቷን በይፋ ገለፀች። በዚህም እርምት ጋሌሊዮንም  ለተፈጥሮ ሳይንስና ለቀጣዩ ትውልድ በእምነትና በሳይንስ መካከል የመገናኛ ድልድይ መስራች ተብሎ ምስጋና ተችሮት በታሪክ ከሚገባው የክብር ቦታ ላይ እንዲቀመጥ ተደረገ። በኖቬምበር 1992 ዓ.ም. በይፋ መልካም ስሙ ከታደሰለት በኋላ በ2009 ዓ.ም ደግሞ ለጋሊሌዮ ታላቅ የፀሎት አከባበር ተዘጋጅቶለት ለሱ ያላቸውን ከፍተኛ አክብሮት እንዲቸርለት ተደረገ። ይህ ክስተት በኃይማኖትና በተፈጥሮ ሳይንስ መካከል መልካም ግንኙነት ለመፍጠር ጥርጊያ መንገድ የከፈተ ነው ተብሎ በምሳሌነት የሚጠቀስና የሚነገርለት ቢሆንም በተገቢው ደረጃ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ገና ፈታኝ እርምጃ ከፊታቸው እንደተደቀነ ግን መሸሸግ አይቻልም። መሰል ክስተት ወደፊት ላለመከሰቱም ምንም አይነት ዋስትና የለም ተብሎ ጥርጣሬን ማሳወቅ በርግጥም ከእውነት መራቅ አይሆንም። በተፈጥሮ ሳይንስና በኃይማኖት እምነት መካከል በተለያዩ ርዕሶች  ላይ ያለውን አለመግባባት ከግምት ሲገባ በጎሪጥ የመተያየት ስጋት አሁንም ድረስ እያንዣበበ መሆኑን መካድ አይቻልምና። 

በበኩሌ ሁሌም የሚገርመኝ በፈጣሪ መኖር አለመኖር ጎራ ለይተው የሚነታረኩ በራሳቸው በተለይም በአማኞቹ በኩል የሚሰለፉት እውቅናን ያተረፉ ሊቃውንቶችን እርዳታ ለምን እንደሚሹ ነው። አቶ አሳፋም እምብዛም ባይገፉበትም ዳርዳር እንዳላቸው የስላቅ ትርከታቸው ያሳብቅባቸዋል። ስቴፈን ሃውኪንግ የሰው ፍጡር አስገራሚና አስደናቂ የሆኑ ተግባራዊ ውጤቶች በማግኘት ደረጃ በጉልህ ምሳሌነት የሚጠቀስ ነበር። ማንም ሰው የራሱ በግሉ የሚያጋጥሙት በርካታ ችግሮች ይኖሩታል። ሆኖም መልካምና ጥሩ ውጤቶች ለማምጣት የሚችል ነው። ስቴፈን ሃውኪንግ ለተፈጥሮ ሳይንስ ከፍተኛ ባለውለታ ነው። ባለውለታ ብቻ ሳይሆን ባደረበት የፀና በሽታ ሳይበገር ለመልካም ተግባር መገኘት በምሳሌነት የሚጠቀስ ነበር። በዚህም ሁልጊዜ ሲታወስ ይኖራል። 

ይቀጥላል።

Filed in: Amharic