>

ወቅታዊ ጉዳዮች (ከይኄይስ እውነቱ)

ወቅታዊ ጉዳዮች

ከይኄይስ እውነቱ


 በዚህ ርእሰ ጉዳይ ሁለት ሰሞናዊ ጉዳዮችን ባጭሩ ለማንሳት እሞክራለሁ፡፡ እነዚህም፤ 1ኛ/ ኦነጋውያን ሙሉ በሙሉ ከተቆጣጠሩት የ‹‹አ.አ.›› ከንቲባ ጽ/ቤት የተላለፈ ሕገ ወጥ ዘዋሪ ደብዳቤ (Circular Letter 1  Circular Letter  እና 2ኛ/ በየቀበሌው ‹‹ለአገር መከላከያ ኃይል›› ድጋፍ በሚል የሚደረግ የመዋጮ ስብሰባ (በማስፈራራት የሚደረግ ቅሚያ)፡፡

ሀ/ ዘዋሪ ደብዳቤው/ሰርኪላር/

    ማንኛውም የመሬት አገልግሎት በውክልና እንዳይሰጥ መከረም 10 ቀን 2015 ራሱን የአ.አ. ከንቲባ ጽ/ቤት ከሚለው የአገዛዙ አካል የተላለፈ እና ‹‹ለመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ››፣ ‹‹ለመሬት ይዞታና ምዝገባ መረጃ ኤጀንሲ››፣ ‹‹ለአ.አ. ከተማ ክፍለ ከተማ አስተዳደር››፣ ለሁሉም ክፍለ ከተሞች እና በግልባጭ ‹‹ለፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት›› እና ‹‹ለወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ›› የተሰራጨ ሕገ ወጥ ዘዋሪ ደብዳቤን (Circular) በሚመለከት የሚከተለውን ለማለት እወዳለሁ፡፡ (ዘዋሪ ደብዳቤው ከዚህ ጽሑፍ ጋር ተያይዟል፡፡)

የከንቲባ ጽ/ቤት ተብየው ዓዋጆችንና ደንቦችን በግልጽ የሚቃረን ዘዋሪ ደብዳቤዎችን አውጥቶ ሲያሰራጭ ይሄ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ ቀደም ሲል ነሐሴ 7 ቀን 2013 ዓ.ም.፤ የቅርቡን ለማስታወስ ኦነጋዊ አገዛዝ በአ.አ. 10ኛ አድርጎ በፈጠረው ክ/ከተማ ማናቸውም መሬትና መሬት ነክ አገልግሎቶች እንዳይሰጡ ያደረገውን ዕገዳ የሚመለከት ዘዋሪ ደብዳቤ የሚታወስ ነው፡፡ በቅድሚያ እነዚህ በየጊዜው የጊዜ ገደብ ሳይቀመጥላቸው በዘፈቀደ የሚወጡ ዘዋሪ ደብዳቤዎች በይዘታቸው ላይ እንደሚሰጠው የሐሰት ምክንያት ወይም ዓላማ (pretext) ሳይሆን ከሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት ጋር አንዳች ግንኙነት የላቸውም፡፡ 

  • ወሮበሎችን እየላከ መሬት ወረራ የሚያደርግ፤ 
  • ዜጎች ከዕለት ጉርሳቸውና ከቤተሰቦቻቸው ጉረሮ ነጥቀው አንድ ቀን የራሴ መጠለያ ይኖረኛል ብለው ለዓመታት የቆጠቡትን ገንዘብ ከቁብ ሳይቆጥር የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በነፃና በጉልበት የሚያድል፤ 
  • ለፈጠራቸውና ሊፈጥራቸው ለሚያስበው የአገዛዙ ባለሀብቶች እንዳሻው መሬትና ቤት እንዲሸጡና እንዲለውጡ የሚፈቀድ አገዛዝ፤ 
  • መሬትና ተያያዥ አገልግሎቶችን እንዲሰጡ ባደራጃቸው ተቋማት  ዜጋውን በቁሙ እንዲገፉ የፈቀደላቸው ተረኞች ባለሥልጣናትና ተራ ሠራተኞች ‹የቀን ጅቦችን› ያሠማራ አገዛዝ፤ ወ.ዘ.ተ. 

ለአገርና ለሕዝብ ጥቅም ብሎ የሚያወጣው ሕግ እንዲሁም በደብዳቤ የሚያሠራጨው ክልከላ አለ ብሎ ማመን ተላላነት ነው፡፡ አንዳንዱ አድርባይና ሞኝ በዚህ መልኩ ለሚሠራጩ ዘዋሪ ደብዳቤዎች አገዛዙ እንኳን ለመስጠት ያልደፈረውን የማይረባ ምክንያት ሲሰጡለት ይስተዋላል፡፡ ወያኔ ንብረት እንዳያሸሽና በሽያጭ የሚያገኘውን ገቢ ለጦርነት እንዳያውለው ነው ሲሉ ይገርመኛል፡፡ ኦነጋውያኑ እነ ዐቢይና ወያኔ ትግሬዎቹ እነ ደብረ ጽዮን ምንድን ነው ልዩነታቸው? አንደኛው የአገር ጠበቃ ሌላው ጠላት ይመስላችኋል? በዚህ ጉዳይ ደጋግሜ እኔም ሆንኩ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ደጋግመው ስለጻፉና ስለተናገሩ አልመለስበትም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀብቴ በወያኔው ደብረ ጽዮን ከሚዘረፍ በኦነጉ ዐቢይ ቢሆን ይሻለኛል ብሏል እንዴ? 

ኦነጋዊው የኦሕዴድ አገዛዝ ኢትዮጵያዊ ቢሆን ኖሮ ገና ከማለዳው በኢትዮጵያ ስም ከአገር ውስጥም ሆነ ውጭ ባሉ ኢትዮጵያውያን ተቀባይነት ባገኘበት ወቅት፣ ይህንን ታላቅ የፖለቲካ ካፒታል ስንቅ አድርጎ፣ ባለፉት 5 የሰቈቃ ዓመታት በከንቱ ከተከፈለውና እየተከፈለ ካለው መሥዋዕትነት በፍጹም በማይወዳደር አነስተኛ መሥዋዕትነት የጐሣ ሥርዓቱን እስከነ መዋቅሩና አገር ከሚታመስበት የ‹ደደቢት ሰነድ› ጋር አስወግዶ ለተሻለ ሕዝባዊ ሥርዓት መንገዱን መጥረግ በተቻለ ነበር፡፡ ተረኛነትን ሳይመርጥ፣ በወያኔ ሕወሐት/በኢሕአዴግ የተቀሩት ድርጅቶች የሕዝብን ሀብት በመዝረፍ የተፈጠሩትን የፖለቲካ የንግድ ድርጅቶች እና  (ኤፈርት፣ ጉና፣ ወ.ዘ.ተ.) ልዩ ልዩ ንብረቶች ወርሶ ለሕዝብ ጥቅም (የተፈናቀሉትን ለማቋቋም፣ በተለያዩ አገዛዝ ወለድ በተፈጠሩ ውድመቶች የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋሚያ) ባዋላቸው ነበር፡፡

አሁንም ያለጊዜ ገደብ የወጣው ዘዋሪ ደብዳቤ ለተረኞች ዝርፊያ ምቹ ሁናቴን ከመፍጠር የዘለለ ዓላማ የለውም፡፡ ለምሳሌ ከኢትዮጵያ ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወገኖች ቤት ንብረታቸውን ለመሸጥ ለመለወጥ የግድ አገር ቤት ካልመጣችሁ የሚል የድንቊርና አሠራር ፈጥረዋል፡፡ በዚህም የንቅዘት በሩን በርግደውታል፡፡

በዘዋሪ ደብዳቤው ምክንያት ብለው ያስቀመጡት ሕገ ወጥ የቤት ሽያጭን ለመቆጣጠር የሚል ነው፡፡ የተባለው እውነት እንኳን ቢሆን – ማናቸውንም የንግድ እንቅስቃሴ ባግባቡ ለማካሄድና የንብረት ሽያጭና ማስተላለፍ ቊልፍ የሕግ መሣሪያ የሆነውን በፍትሐብሔር ሕጋችን የተሰጠውን ውክልና ሥልጣን የመስጠት መብትን በተራ ደብዳቤ በመተላለፍ አልነበረም፡፡ በነገራችን ላይ ከሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ውስጥ ከሚሠሩ የውስጥ ዐዋቂዎች ባገኘነው መረጃ መሠረት በመ/ቤቱ ውስጥ የሚገኙ ተረኞች የሐሰት የውክልና ሥልጣን ማስረጃ (fake power of attorney) በገንዘብ የሚሠሩ እንዳሉ ተነግሮናል፡፡ 

ርእሰ መጻሕፍቱ ዲያቢሎስን ‹አቡሃ ለሐሰት› (ውሸትን ከራሱ አመንጭቶ የሚናገር የውሸት ፈጣሪ አባቷ) ይለዋል፡፡ የዲያቢሎስ የግብር ልጆች የሆኑት ወያኔና የአሁኑ ተረኞች በኢትዮጵያችን ካነገሡአቸው ክፋቶች መካከል ውሸትና ዜጎች ርስ በርሳቸው እንዳይተማመኑና በጥርጣሬ እንዲተያዩ ማድረግ ነው፡፡ በግብር ከፋዩ ሀብት የሚጫወቱበት የአገዛዙ መገናኛ ብዙኃኖች (የኤሌክቶሮኒክሱም ሆነ የኅትመቱ) እና በነዚሁ የውሸት ‹ፋብሪካዎች› የሚሠሩት አብዛኞቹ ኅሊና ቢስ ነውረኞች የውሸት ማሠራጫና ተራ ፕሮፓጋንዳ መሣሪያዎች ሆነው ሲያገለግሉ እነሆ ሠላሳ ሁለት ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ ሆዳም ቅጥረኞችን አሠማርተው አገር አጥፊ ለሆነ ዓላማ የሕዝብ ሀብት የሚበትኑባቸውን የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃኖችን ሳንቆጥር ስንቱ ዜጋ ይሆን የነዚህ የውሸት መፈልፈያ ሜዲያዎች ሰለባ የሆነው?  

ዛሬ አገዛዙ ተሳስቶ ትክክለኛ ነገር ቢሠራ እንኳን የማይታመንበት ደረጃ ከደረሰ ውሎ አድሯል፡፡ አገዛዙ መሬት ላይ በተግባር በሚፈጽመው አገርና ሕዝብ አጥፊ ሥራ፣ በተቆጣጠራቸው የሕዝብ ሜዲያዎች ዕለት ዕለት በሚያስተላልፋቸው ቅጣ ያጣ ቅጥፈቶች ምክንያት በፍጹም ሊታመን የማይችል መሆኑን መሠረት አድርገን ወደ ሁለተኛው ርእሰ ጉዳይ እናልፋለን፡፡

ለ/ መቆሚያ በሌለው መዋጮ በጠራራ ፀሐይ የሚፈጸም ዝርፊያ

‹‹ለአገር መከላከያ ኃይል›› በሚል ስም በዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለው ዝርፊያ ሌላው ሰሞናዊ ክስተት ነው፡፡

አንድ ዜጋ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን በጠላትነት ለሚያይና ይህንንም በተግባር እየፈጸመ ላለ አገዛዝ በአገራዊ አጀንዳ ስም በየጊዜው አለፈቃዱና አለ ዐቅሙ መዋጮ የሚያደርግበት ምን ምክንያት አለ? ደርግ ዜጎችን እያስገደደ ‹‹በእናት አገር ጥሪ›› ስም የጀመረው መዋጮ በወያኔ/ኦሕዴድ የጐሣ ሥርዓት ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ የደናቊርትና የበታች ወታደራዊ ሹማምንቶች አገዛዝ የነበረው ደርግ ቢመከር ቢዘከር አልሰማ ብሎ የኢትዮጵያ ልጆችን በጦርነት ማግዶ፣ በተቃራኒ የቆመ ከሚመስለው ኢሕአፓ ጋር በመሆን ኤርትራ በወያኔ ትግሬ እገዛ እንድትገነጠል ምቹ ሁናቴዎችን መፍጠራቸው የማይካድ ነው፡፡ 

ኦነጋዊው የኦሕዴድ አገዛዝ ቀደም ሲል ሁለት ዙር ከወያኔ ጋር ተካሄዱ ባላቸው ጦርነቶች ለወያኔ ትግሬ አጋርነቱን አስመስክሯል፡፡ ወያኔዎች በጀግንነታቸው ሳይሆን አገዛዙ በየጊዜው በሚሠራው ሸፍጥና አሻጥር (ሳቦታዥ) – እዚህ ላይ ዘላለማዊውን አሽከር ብአዴንን ያስታውሷል – ምክንያት አ.አ. በር ላይ ሸዋ ሲደርሱ የምንይልክን ቤተመንግሥት እንዳይነጠቅ ሲል ንጹሐን ዜጎችን (በተለይም የአማራውንና የአፋሩን ሕዝባዊ ኃይል) ከማገደ በኋላ፣ በውሸት ድርድር ስም ወያኔን በስንቅና በትጥቅ እንዲደራጅ በተግባርም ሆነ በዳተኝነት ረድቶ እንደገና እንዲያንሠራራ በማድረግ አሁን ለሦስተኛ ዙር ጦር ሜዳውን የሰሜኑ ኢትዮጵያ መሬትና ሕዝብ በማድረግ ሌላ እልቂት ደግሶ ይገኛል፡፡ 

  • ከአዲስ አበባ ውጭ ክፍላተ ሀገራቱን በቅጡ ለማስተዳደር የተሣነው አገዛዝ ባለበት፤
  •  በኢትዮጵያ ታሪክ ተሰምቶ በማይታወቅ ሁናቴ የውጭ ወራሪ ኃይል የአገራችንን ድንበር ጥሶ ገብቶ ሕዝባችንን እየገደለ÷ እየዘረፈና ንብረት እያወደመ ተንሠራፍቶ በተቀመጠበት፣ በዚህም የአገርን ሉዐላዊነትና ግዛታዊ አንድነት ከውጭ ጠላቶች ማስጠበቅ አቅቶት አገርን ያዋረደ አገዛዝ ባለበት፤ 
  • በዘረጋው የጐሣ አስተዳደራዊ መዋቅር ምክንያት ዜጎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው መሥራት እንዳይችሉ ብቻ ሳይሆን ‹መጤ› ናችሁ ተብለው በሚሳደዱበትና በሚፈናቀሉበት አገር፤ 
  • ባገዛዙና በቅርብ ባለሟሎቹ አማካይነት ቅጥ ያጣ አገራዊ ሀብት በሚዘረፍበትና ንቅዘት በነገሠበት፤ 
  • አገራዊ ኢኮኖሚው ባመዛኙ አገዛዝ ወለድ በሆኑ ችግሮች ምክንያት አፈር ድቤ በበላበት የጐሠኞቹ ሥርዓት፤ 
  • በኑሮ ውድነት  ዜጎች የሚላስ የሚቀመስ አጥተው በረሃብ በሚጠበሱባት ኢትዮጵያ፤
  • የአማራው ሕዝብ በወለጋና በሌሎችም ወያኔ ‹ኦሮሚያ› ብሎ በፈጠረው የኢትዮጵያ ግዛት በአገዛዙ አሸባሪ ኃይል በግፍ በሚጨፈጨፉበት አገር፤ 
  • ባጠቃላይ አገዛዙ መደበኛ የሆነውን የመንግሥት ሥራ – የሕዝብን ሰላምና ጸጥታ ማስከበር፤ አገርን ከውጭ ወራሪዎች የመጠበቅ ተግባር – መሥራት  አቅቶት ሥርዓተ አልበኝነት በሰፈነበት አገር፤ 
  • በአገር መከላከያ ስም የተደራጀው ሠራዊት የአገዛዙ ሥልጣንና ጥቅም ጠባቂ ሆኖ በጐሣ መሠረትነት በተደራጀበት (በተለይም አገራዊ ፍቅር ባለመኖር፣ በዕውቀትና በልምድ እጦት የማይታሙት የጦሩ መሪዎች ካንድ ጐሣ ተመርጠው በተረኛነት በተሾሙበት)፤ 

ለየትኛው ጦርነት ነው ዜጋው መዋጮ የሚያደርገው? በሌላ አነጋገር የአገር መከላከያ የተባለው ኃይል በዋናነት የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ወይም የኦነግ ምልምሎች ስብስብ አይደለም ወይ? ሳይወድ በግዱ በጦርነቱ ተካፋይ የሆነው የአማራው ሕዝባዊ ኃይል (ፋኖ) ከአራጁ፣ አፋኙና አሳዳጁ የኦነግ ጦር ጋር አይደለም እንዴ ወያኔን እንዲዋጋ በዐውደ ግንባር የተሰለፈው? ምን ዓይነት መሪር ምፀት/ስላቅ ነው?

ኢትዮጵያዊ መንግሥት ቢኖረን ኖሮ ዜጋው ከወያኔ ትግሬም ሆነ ከውጭ ወራሪ ኃይል ጋር ለሚደረግ ፍልሚያ አይደለም ከትርፉ ‹ትዳሩን› ሁሉ በሰጠ ነበር፡፡ አንዳች የመንግሥትነት ጠባይ በሌላቸው በወያኔ ትግሬና በወራሹ ኦሕዴድ/ኦነግ ግን ለዘራፊዎች ሲሳይ የሚሆን መዋጮ (ያውም በማስፈራራትና ያለ ዐቅም) በየጊዜው ተደርጓል፤ አሁንም እየተደረገ ነው፡፡

በመንግሥት መ/ቤቶችና ተቋማት የገንዘቡ መጠን የሚወሰነው በውስጥ በተሰገሰጉ የአገዛዙ ተወካዮች ሲሆን፤ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ አገዛዙ በሚዘውረው ‹ሴኔቶች›፤  የአገዛዙ ባልሆኑ ነጋዴዎችና በነዋሪው ላይ ደግሞ ከቀበሌ እስከ ከፍተኛው አስተዳደራዊ ዕርከን በሚገኙ የአገዛዙ ተረኛ ካድሬዎች ነው፡፡ በየቀበሌው ባሉና ቤት ለቤት በሚዞሩ ተረኛ ካድሬዎች እየታዘብን ያለነው ደግሞ የሚገርም ነው፡፡ ‹ኮታ› ተሰጥቶናልና ይህን ያህል መስጠት አለባችሁ እያሉ ሕዝቡን እያስጨነቁት ነው፡፡ ዐቅም የለንም ሥራ ላይ አይደለንም የሚሉ ወገኖችን ደግሞ ቢያንስ ከመቶ ብር ያላነሰ ገንዘብ ያለ ደረሰኝ እየተቀበሉ ይገኛሉ፡፡ 

ለመሆኑ አንድ ዜጋ ከፍ ብለን በጠቀስነው በአገዛዙ አለመታመንና ብልሹነት ምክንያት በጦርነቱ አላምንበትም፤ ስለሆነም ምንም ዓይነት መዋጮ አላደርግም ብሎ በድፍረት ቢጋፈጥ ‹‹የአገር ጠላት፣ የወያኔ ተባባሪ›› ተብሎ ሊፈረጅና ሊታሠር ነው? መጨረሻችን ምን ይሆን? አልናፈቃችሁም? ይህንን ጽሑፍ የምናገርበት ዓውድ ያልገባው ሰው በቅርቡ ‹‹ችግርግር ያለ ችግር›› በሚል የጻፍሑትን አስተያየት ቢያነብ መልካም ይመስለኛል፡፡

ለማጠቃለል ደጋግሜ በጽሑፎቼ ሁሉ እንደገለጽሁት፤ ዝቃጩ ብአዴን፣ ወያኔ/ሕወሐት እና ተረኛው ኦሕዴድ/ኦነግ እንዲሁም ኢሕአዴግ/‹ብል(ጽ)ግና› የተባለው ነውረኛ ስብስብ ውስጥ የሚገኙ ድርጅቶች በሙሉ የኢትዮጵያና ሕዝቧ ጠላቶች ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ አንዱን ከሌላው መለየት ትርጕም የለውም፡፡ የአገዛዙ ደጋፊና የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ሰለባ ካልሆነ በቀር እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ጠላቶቹን ተደራጅቶ መፋለም እንጂ የላቡን ውጤት በፈቃዱ ለጠላቱ የሚሰጥበት አንዳች ምክንያት የለም፡፡ ጠላቶቹን ለመፋለም አንዱና ዋናው ቅድመ ሁኔታ ደግሞ ኢሕአዴግ/ብል(ጽ)ግና በሚባለው ስብስብ ውስጥ የሚገኙ ድርጅቶችንና አባላቱን ሁሉ አለማመን ነው፡፡ በተለይም የአጋንንት መጋለቢያ ፈረስ የሆነውን ዐቢይ ፈጽሞ አለማመን ነው፡፡

ሁሌም ቢሆን አገራችን ኢትዮጵያን የሚመለከቱ አስተያየቶቼን ለእግዚአብሔር አምላክ ተማጽኖ በማቅረብ ለመደምደም አስብና ምን አንደበት፣ ምን እሱ ፊት የሚቀርብ ሕይወት አለኝ ብዬ እተወዋለሁ፡፡ ግን እኮ ባለቤቱ እኛ የማናውቃቸው ሰዎች አሉት፡፡ አምላከ ኢትዮጵያ ስለሚያውቃቸው ‹ምርጦቹ› ብሎ ከገባንበት መዓት ያውጣን፡፡

 

Filed in: Amharic