>
5:09 pm - Friday March 3, 4575

ችግርግር ያለ ችግር (ከይኄይስ እውነቱ)

ችግርግር ያለ ችግር

ከይኄይስ እውነቱ

አገራችን ኢትዮጵያ የገጠማት ችግር ተራ ችግር አይደለም፡፡ ምናልባት የችግሩን ጥልቀትና ስፋት ይገልጽልኝ ከሆነ በሚል ነው ርእሴን ‹ችግርግር ያለ ችግር› ያልኹት፡፡ ዛሬ ጦርነት ማድረግ ችግር ነው፤ አለማድረግም ችግር ነው፤ መደራደር ችግር ነው አለመደራደርም ችግር ነው፡፡ ትንሽ ላፍታታው፡፡ 

ባለፉት 32 የግፍና የሰቈቃ ዓመታት በኢትዮጵያችን የሠለጠኑት የወንጀል አገዛዞች አንዳችም ኢትዮጵያዊ ተፈጥሮ እንደሌላቸው በተግባራቸው አስመስክረዋል፡፡ ቀድሞ በወያኔ ትግሬ የሚመራው ኢሕአዴግ አሁን ‹ብልግና› ብሎ ራሱን የሚጠራውና በኦሕዴድ የሚመራው ኢሕአዴግ ቡድኖች መካከል ከስም እና ከአመራሮቹ የጐሣ ማሊያ ቅያሬ ውጭ በዓላማ፣ በሚከተሉት የጐሣ ፖለቲካ፣ እንመራበታለን በሚሉትና በመቃብራችን ላይ ካልሆነ አይቀየርም በሚሉት ‹የደደቢት ሰነድ› አንዳች ልዩነት የላቸውም፡፡ እነዚህ አገራችንን የዋይታ ምድር ያደረጉ ጉዶች አንዱ የአገር ጠበቃ ሌላው አሸባሪ መስለው ደኸውን ገበሬ  በጦርነት የሚማግዱት፣ ሕፃናት እንዳያድጉ፣ ሴቶች እናቶቻችንና እኅቶቻችን በሰላም እንዳይኖሩበት፣ አረጋውያን በለፉበት ምድር እንዳይጦሩ የጦር ሜዳውን ሰሜናዊ የአገራችንን ክፍልና ሕዝብ በማድረግ ለሦስተኛ ጊዜ እልቂትና ውድመት እየፈጸሙ ያሉት ከኢትዮጵያ ሉዐላዊነትና የሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ጋር የሚያገናኘው ጉዳይ ኖሮ አይደለም፡፡ በጭራሽ!!! መሠረቱ ሰሜናዊ የሆነውን የጉራጌ ማኅበረሰብም እየተፈታተኑት ያሉት ያለምክንያት አይደለም፡፡ ዛሬ ይህንን ያገጠጠ እውነት ዐላውቅም አልተረዳሁም የሚል ባገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያለ ኢትዮጵያዊ ካለ ‹አንተኑ ነግድ ለኢትዮጵያ› (አንተ ለኢትዮጵያ እንግዳ/ባዕድ ነህ ወይ?) ከምንለው በቀር ዐውቆ የተኛን፣ ጅልነትን የመረጠውን ወይም እያወቀ ለሆዱ ያደረውን ልንረዳው አንችልም፡፡

አሁን በሥልጣን ላይ ያለው ኢሕአዴግ የሚባል ጭራቅ ቡድን ፍንካች (ኦሕዴድ/ኦነግ) ወያኔ ትግሬን ለማጥፋት ፍላጎት የለውም፡፡ ኢትዮጵያዊ አጀንዳ ያለው ቢሆን ኖሮ ወያኔዎች በመጀመሪያው ጦርነት – ርእሰ መጻሕፍቱ እንደሚለው – ‹ለይኩኑ ከመ ጸበል ዘቅድመ ገጸ ነፋስ› (ከነፋስ ፊት እንዳለ ትቢያ) ይሆኑ ነበር፡፡ ሁለት ዙር በተደረገው ጦርነት የአማራን ሕዝባዊ ኃይልና ኢትዮጵያዊውን የአፋር ማኅበረሰብ ይዞ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሕወሓትን ከኢትዮጵያ ምድር ማጥፋት ይቻል ነበር፡፡ በዚህም የትግራይን ሕዝብ ነፃ ከማውጣቱ ጋራ ኢትዮጵያን ማዳን ይቻል ነበር፡፡ የሁለቱ ግጭት ሥልጣንና በዚህም የሚገኘው አገራዊ ዝርፊያ ነው፡፡ ታዲያ ንጹሐን ዜጎች ለዚህ ዓላማ ማገዶ የሚሆኑበት ምን ምክንያት አለ? ለማለት የፈለግሁት ሁለቱም ኃይላት አሸባሪዎች ናቸው፡፡ እነዚህ አሸባሪ ኃይሎች የበላይነታቸውን ለማስጠበቅ በሚያደርጉት ፍልሚያ በኑሮ ውድነት የሚማቅቀው ደሀ ሕዝብ (የትግራይ፣ የአፋርና የአማራ) የሚያልቅበት ምን ምክንያት አለ? ከአጋንንቱ ማኅበር ቀደም ብለው የተደመሩት ‹ኢዜማ/ግንቦት 7›ም ሆነ ሳይወለድ የጨነገፈው ‹አብን› የሚባል የብአዴን ‹ታናሽ ወንድም› የአሸባሪዎቹ ግብር አበሮች በመሆናቸው ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል ሁሉ ማዳመጥ ሳይሆን ሊጸየፋቸው ይገባል፡፡ ኦሕዴድ የሚባል የነውረኞች ቊንጮ ከዚህ ቀደም በተደረጉት ጦርነቶችም ሆነ አሁን እየተካሄደ ባለው ትርጕም አልባ ጦርነት ጊዜ የሽብር ክንዱን (አንድ አምሳል አንድ አካል የሆኑትን የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ብሎ ያደራጀውን እና የኦነግ ሠራዊትን) በወለጋ እና ከ30 ዓመት ወዲህ ወያኔ በፈጠረላቸው ‹ኦሮሚያ› በሚባል የኢትዮጵያ ግዛት የሚኖረውን ኢትዮጵያዊ (በተለይም የአማራውን ሕዝብ) አረመኔያዊ በሆነ የዘር ማጥፋት ጅምላ ጭፍጨፋ ‹በማጽዳት› ተጠምዶ ይገኛል፡፡ ይኸው የሚጨፈጭፈውን ሕዝብ በአገር መከላከያ ስም ካደራጀው (ሲመረመር ግን የኦሮሚያ ልዩ ኃይል አካል ከሆነ ቡድን ጋር) ጎን ለጎን ተሰልፎ ወያኔን እንዲዋጋ ማድረግ የክፍለ ዘመኑ ታላቅ ስላቅ ነው፡፡ ይህን ተልእኮ አስፈጻሚና አሰማሪው የዓለሙ ሁሉ ማፈሪያ የሆነ ብአዴን የተባለ የአሳሞች ስብስብ ነው፡፡ አባቶች በሬ ካራጁ የሚሉት እንዲህ ዓይነቱን ሸፍጥ ነው፡፡ 

እኔ የማዝነው ኢትዮጵያ፣ ሉዐላዊነቷን እና የግዛት አንድነቷን በተግባር በማረጋገጥ፤ ለዚሁ ዓላማ ሕዝብን አደራጅቶ ለማንቀሳቀስ ዝግጁ በሆኑ የፖለቲካ ማኅበራት፤ የሙያ ማኅበራት እና የማኅበረሰብ ድርጅቶች (ሲቪክ ማኅበራት) ረገድ የወላድ መካን መሆኗ ነው፡፡ ይህ በእጅጉ ያማል፡፡ እነዚህ ተደራጅተው ሕዝብን ያደራጃሉ የሚባሉ ማኅበራት በወንጀል ሥርዓቶቹ ወሮበሎች ቊጥጥር ሥር ከሆኑ ለሕዝቡ ታዳጊ ከየት ይምጣ? እንደ መና ከሰማይ ይውረድ ወይስ አሸባሪዎችን እየረዱ ወዳሉት ነጮች እንጩኽ? ወይስ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ተካክለን በበደልንበት (ኵሉ ዐረየ ወኅቡረ ዐለወ እንደተባለው) እና ለእግዚአብሔር በማይመች አካሄዳችን ወደ ላይ እናንጋጥ? ምን ነካን ጃል? እንዴት እንዲህ በሥጋዊውም በመንፈሳዊውም ጥፍት እንላለን? ብቸኛ የቀረን ጥጋችን እምነትና በሱ ያለ ተስፋ ቢሆንም፣ አነዋወራችን እኮ ለመለኮታዊ ጣልቃ ገብነትም አልተመቸም፡፡ እንደ አገርና ሕዝብ ‹አልሞትንም ብለን ባንዋሽም› እንደ ወንጀል ሥርዓቶቹ አሸባሪዎች የጥፋት አሠራርና ፍላጎት ጨርሶ አለመጥፋታችንም በባለቤቱ ቸርነት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በጫርኋቸው ጽሑፎች የወንጀል ሥርዓቱ ፍንካች የሆኑ አገራዊ ችግሮችን እያነሣሁ ለመዳሰስ ስሞክር አገር ለማጥፋት የሚንቀሳቀሱት የወንጀል ሥርዓቱ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ሕዝብን ለማገልገል በየተቋማቱ ተቀጥረው የሚሠሩ፣ በንግዱ ዓለም ተሠማርተው ደኸውን ሕዝብ የሚገፉ፣ ቊጥራቸው የሚያስደነግጥ ወገኖች ዜጎችን በማጉላላትና በንቅዘት ተጠምደዋል፡፡ እነዚህ መናጢዎች ነውራቸው አላንስ ብሎ ጣራ የነካ ንቀታቸውን ስትታዘቡ እንደ ዓይን ጥፍት ማለታችንን ትረዳላችሁ፡፡ ሳትፈልጉም የቀቢፀ-ተስፋ ስሜት ይጎበኛችኋል፡፡

ወደ ቀደመ ነገሬ ልመለስና፤ አገዛዙ አገር በማጥፋት ረገድ የወያኔን የሽብር ተግባር ያስከነዳ በመሆኑ ከወያኔ ትግሬ (ሕወሓት) ጋር የኢትዮጵያ የጋራ ጠላት ነው፡፡ ኢሕአዴግ/‹ብልግና› በሚባለው የአጋንንት ስብስብ መካከል ምርጫ የለንም፡፡ በየትኛውም መመዘኛ ስናየው የወንጀል ሥርዓት የሆነው የኦሕዴድ አገዛዝ ኢትዮጵያን ወክሎ ከወያኔ ትግሬ ጋር ለመፋለምም ሆነ ለመደራደር ቢያንስ የሞራል ብቃት የለውም፡፡ በዚህ ምክንያት ነው ጦርነቱም ሆነ ድርድሩ የማይሠራው፡፡ ወያኔ ዕርቅና ድርድር በመዝገበ ቃላቱ ውስጥ የሌሉ ከይሲ ቡድን መሆኑንን ለዓመታት በተግባር ያስመሰከረ ነው፡፡ የቸገረው ርጕዝ ያገባል እንዲሉ አንዳንዶች ኦሕዴድም ሆነ ሕወሓት የመጨረሻ ቀጣፊዎችና የማይታመኑ መሆናቸውን እያወቁ፣ ዜጎች በከንቱ ከሚያልቁ የውሸት ድርድር ቢደረገ ይሻልል ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ወያኔ ትግሬና ኦነግ ኦሕዴድ ካንድ ከተረገመ ‹ማሕፀን› የተገኙ የጥፋት ኃይሎች ከነጓዛቸው ከኢትዮጵያ ምድር መጥፋት አለባቸው፡፡ እነሱና ጭፍሮቻቸው ባሉበት እውነተኛና ዘላቂ ሰላም ማሰብ ነፋስን እንደ መጐሰም፣ ጉምን እንደ መዝገን ይሆናል፡፡ ይህ አቋሜ እስኪታክተኝ ለዓመታት ያንፀባረቅሁትና በሕይወት እስካለሁ አብሮኝ የሚዘልቅ ነው፡፡ ቀድሞ ወያኔ ትግሬ መር በሆነው ኢሕአዴግ፤ ላለፉት 5 ዓመታት ደግሞ በወያኔ ወራሽና ወር ተረኛ በሆነው ኦሕዴድ መር ‹ኢሕአዴግ/ብልግና›፡፡ ‹መጥፋት አለባቸው› ስንል ቡድኖቹና ድርጅቶቹ ከፈጠሩት የጐሣና የወንጀል ሥርዓት ጋር የታሪክ ቆሻሻ ቅርጫት ውስጥ መጣል አለባቸው ማለት ነው፡፡ ድርጅቶቹን ወንጀለኛና አሸባሪዎች መሆናቸውን በይፋ በማወጅ፤ አባላቱ ደግሞ ከኢትዮጵያ የሥልጣን ፖለቲካ ሕይወት ለተወሰኑ ዓመታት እንዲገለሉ ማድረግን ይጨምራል፡፡ ይህም ሲደረግ አመራሮቹና ተራ አባላቱም እንደ ወንጀላቸው መጠን ለፍርድ እንዲቀርቡ ማድረግ፤ የዘረፉትን አገራዊ ሀብት በተቻለ መጠን እንዲመለስና የሕዝብ ሀብት የማድረግ፤ በግብረ አበርነት የሚታዩትም እንደ ወንጀል ድርጊታቸው ወይም ዳተኝነታቸው መጠን በፍርድና በእውነተኛ የዕርቅ ሂደት ውስጥ የሚያልፉበትን ሥርዓት ማመቻቸት ማለት ነው፡፡ ይህ የሚሆነው የወንጀል ሥርዓቱ ያቋቋመው የጎሣ ፖለቲካ እስከነ መዋቅሩና ለዚህም መሠረት ሆኖኛል የሚለው የማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥት› ተወግዶ አገር ለመደማመጥ ዕድል ስታገኝ ነው፡፡ 

ስለሆነም ይህ መልካም ምኞት እውን እንዲሆን ከተፈለገ ባራቱም ማዕዝናት የሚገኝ ኢትዮጵያን አገሬ፤ ሕዝቧን ወገኔ የሚል ዜጋ ሁሉ ትግሉን ወይም ‹ጦርነቱን› ከወያኔ ትግሬ ጋር ብቻ ሳይሆን በአገዛዝነት ከተቀመጠው የወያኔ ውላጅ ኦሕዴድ/ኦነግ ጋር መሆኑን በሚገባ ዐውቆ በሥነልቦና ብቻ ሳይሆን ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ መዘጋጀት፣ መደራጀት ይኖርበታል፡፡ 

ቀደምት መንፈሳውያን አባቶች ብዙ ሕዝብ እግዚአብሔር ነው ይላሉ፡፡ ሀገረ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ከውስጥ ከሃዲዎችና ከውጭ ጣልቃ ገቦች ነፃ ለማድረግ በሚደረገው ትግል ውስጥ ባንድነት ተነሥቶ ለራሱም ሆነ ለቀጣዩ ትውልድ አዲስ ዛሬን እና የተሻለ ነገን ገንዘብ ማድረግ ከፈለገ የእግዚአብሔር ጽኑዕ ክንድ አትለየውም፡፡ በተቃራኒው ትግሉን የአማራና የአፋር ሕዝብ ብቻ በማድረግ ለወንጀል ሥርዓቱ ለመገበር ራሱን ለባርነት (ለገርባ/ገበሮነት) የሚያመቻች ካለ ግን ወያኔና ወራሾቹ ያበጁለትንም ‹ክልል› የተባለ ጋጣ እንደሚያጣ መንገሩ ከነቢይነት አያስቆጥርም፡፡ ማንም አገር ከዳተኛ የዱርዬ ስብስብ እንደ ሰም አቅልጦ እንደ ገል ቀጥቅጦ እንዲገዛን መፍቀድ ወይም አስፈላጊውን መሥዋዕትነት በመክፈል ነፃ የሆነችና ሁላችን እኩል ባለቤት የምንሆንባት አገር የመገንባት ምርጫው በእጃችን ነው፡፡ በምናደርገው ምርጫና ውሳኔ ላለፉት 32 ዓመታት ግፍና ጭቆናን አንቀበልም በሚል በወንጀል ሥርዓቶቹ የተሰዉትን እንዲሁም አገዛዝ-መር በሆነ ሽብርተኝነት ያለምንም በደላቸው በጅምላ ተጨፍጭፈው ያለቁትን ንጹሐን ዜጎች እናከብራለን ወይም መሥዋትነታቸውንና ሞታቸውን ከንቱ እናደርጋለን፡፡ ‹‹እሳተ ወማየ አቅረብኩ ለከ፤ ደይ እዴከ ኀበ ዘፈቀድከ›› (እሳትና ውኃን ከፊትህ አኑሬአለሁ፤ እጅህን ወደ መረጥኸው ስደድ)፡፡

Filed in: Amharic