>
5:18 pm - Sunday June 15, 1614

በአማራ ደም የጨቀየችው ወለጋ ዛሬም " በአራጅ ልጆቿ የደም ግብሯ ገብቶላታል....!(ዘሪሁን ገሰሰ)

በአማራ ደም የጨቀየችው ወለጋ ዛሬም ” በአራጅ ልጆቿ የደም ግብሯ ገብቶላታል….!

ዘሪሁን ገሰሰ

ይህና በየጊዜው የምናየው እስከ አፍንጫው የታጠቀና ለይስሙላም ቢሆን “አሸባሪ” ተብሎም የተፈረጀ ኃይል ፥ ላለፉት አመታት እንዲህ እንደልቡ በየከተሞቹ እየተንቀሳቀሰ ፣ አካባቢዎችንና ተቋማትን እየተቆጣጠረ ብሎም በየጊዜዉ በገፍ አሰልጥኖ እያስመረቀ ጭፍጨፋና ሽብር መፈፀሙን አጠናክሮ  የቀጠለው ፥ ኬንያ ወይም ኤርትራ ወይ ደግሞ ኤርትራ በረሀ ላይ ሆኖ ሳይሆን “መንግስት አለሁ!” በሚልበት የኢትዮጵያ ሉአላዊ ግዛት እምብርት ላይ ሆኖ ነው!

የአንድ መንግሥት ተቀዳሚና በምንም መልኩ የማይዘነጋ ተግባሩ ከዜጎች ግብር ሰብስቦ የፀጥታ ተቋማትን ገንብቶ የዜጎችንና የሀገርን ደህንነትና ሉአላዊነት ማስጠበቅ መቻል ነው፡፡

ይህን መፈፀም ያቃተው ስርአት ካለ አይቆጠርም፡፡ ከጅምሩ የወደቀ ስርአትም ነው፡፡ የዜጎችን በሰላም ወጥቶ የመግባት ፥ የመንቀሳቀስና የመኖርን ዋስትና ያላስከበረ ፥ የሀገርን ሉአላዊነት መጠበቅ ያልቻለ ስርአተ መንግሥት ስለሌሎች የልማትም ሆነ የተቋማት ስራ የማውራት የሞራል ልዕልናው የለውም፡፡

መንግሥት ይሄን ያፈጠጠ ገሀድ ተቀብሎ ስህተቶቹን በአጭር ጊዜ ማረም ባለመቻሉ ፥ በተለይም የኦሮሚያ ክልል (ምስራቅ ወለጋ) የሚገኙ አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የእልቂት ማእከል ሆነው በንፁሐን የደም ዋበላ የሚታጠቡ የሰቆቃ ምድር ሆነዋል፡፡ ቤኒሻንጉል  የነበረው እልቂት በጋምቤላ በዜጎች ላይ ከሚፈፀመው ጭፍጨፋ ባሻገር ከክልላዊ መንግስቱን ለመቆጣጠር ከጫፍ እስከመድረስ የደረሱት የአሸባሪው ኃይሎች በዚቹ “መንግስት አለ!” በሚባልባት ሀገር በነፃነት እየሰለጠኑና እየታጠቁ መሆኑም የአደባባይ ሀቅ ነው፡፡

በነገራችን ላይ የኢትዮጵያውያን የመከራና የግፍ ፅንስን አርግዞ የወለደው ትህነግ ፥ በለስ ቀንቶት የሀገረ መንግስቱን ስልጣን ይዞ በቆየባቸው በእነዚያ የተረገሙ አስርት አመታት ውስጥ በጥሩነቱም ውሰዱት በመጥፎ ፥ ብቻ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ አይደለም በቀበሌ በጎጥ ውስጥ እንኳ አንድም የታጠቀ ሀይል የሚንቀሳቀስበት ሁኔታ ተፈጥሮ አያውቅም ነበር፡፡

ከኢህአዴግ አብራክ የተወለደው ገዢው የብልጽግና መራሹ መንግሥት ሀገረ-መንግስቱን ከተቆጣጠረበት ሰአት ጀምሮ አማፂያን ቡድኖች መሀል ሀገር ሆነው በትጥቅና በሰው ሀይል እየተንሰራፉና እየደረጁ ሀገሪቷን በደም የጨቀየች ምድር ሲያደርጓት  ፤ በተለያዩ ጊዜያት ” ተደመሰሱ ፥ ወደጎረቤት ሀገር ተሰደዱ ፤ አንድም ቀበሌ አልተቆጣጠሩም ፣ መሪዎቻቸው ተያዙ ፣ ተበተኑ ፣ ….ወዘተ” የሚል መሬት ላይ ካለው እውነታ በተቃራኒ የሆነ ፕሮፓጋንዳ ከመስራት  ፥ “የገነባሁት በአፍሪካ ተገዳዳሪ የሌለው ሰራዊት ነው” ሲል ያሞካሸውን ሀይል ተጠቅሞ እንኳ የዜጎችን በህይወት የመኖር መብት እንኳ ሊያስከብር አልቻለም፡፡

እልቂቱን ማስቆም ፥ መንግስታዊ ሀላፊነቱን መወጣት ያልቻለው ይህ ስርአት ወርዶ ወርዶ በንፁሀን ላይ ፍጅት ሲፈፀም መረጃ እንዳይወጣ ኔትወርክ ወደማጥፋት ደረጃ ዝቅ ብሎ ይገኛል፡፡ ወለጋም በየደቂቃው ኤልፎች የሚፈጁባት ፣ አስርት ሺዎች የሚፈናቀሉባት የደምና የግፍ ምድር ሆና ቀጥላለች፡፡

እኛም አቤት የሚል በሌለበት ” ኧረ መንግስት ሆይ ወዴት አለህ?” እያልን አምስት እረፍት አልባ የሰቆቃ አመታትን ልንደፍን ነው፡፡

ኦ ወለጋ በንፁሐን ደም የጨቀየች ምድራዊ ሲኦል….!

Filed in: Amharic