>

ትኩረት በወለጋ ለሚገኙ የአማራ ወገኖቻችንን!  (ከአማራ ወጣቶች ማህበር በባህር ዳር)

ትኩረት በወለጋ ለሚገኙ የአማራ ወገኖቻችንን!

ከአማራ ወጣቶች ማህበር በባህር ዳር

የአማራን ህዝብ ላለፉት አራት አመታት ረፍት እንዲያጣ ከተደረገበት ጉዳይ አንዱ በወለጋ በሚገኙ አማራ ወገኖቻችንን ላይ የሚፈፀመው አሰቃቂ የሆነ የዘር ማጥፋት ፥ማፅዳት ነው ።መንግስታዊ እውቅና እና ድጋፍ ባለው ገዳይ ቡድን ላለፉት አራት አመታት በወለጋ በርካታ ህፃናት ፣ሴቶች ፣አሮጊቶች ፣አባቶች በአጠቃላይ አማራ የተባለ ሁሉ በግፍ ታርዷል ። በህይወት የተረፉት ለአስከፊ ስደት ፣መፈናቀል ፣እንግልት እና ከፍተኛ የሆነ የስነ -ልቦና ስብራት ደርሶባቸዋል ።

ከሰሞኑ ደግም <<ኦፌኮ >> በተባለ የኦሮሞ የፓለቲካ ድርጅት እየተቀሰቀሰ ወይም እየተጠራ የሚገኘው የዘር ማጥፋት ጥሪ በወለጋ የሚገኙ የአማራ ወገኖቻችን ላይ ከፍተኛ ስጋት ላይ እንዳሉ ከአካባቢው በደረሱን መረጃዎች ተረድተናል ።የተደረገባቸው ከበባ ፣በአካባቢው የተፈፀመው የስልክ ኔትወርክ የማቋረጥ ተግባር እና የተሰሙት የድረሱልን የሲቃ ድምፆች በአካባቢው የሞት ድግስ እንደ ተደገሰ ተገንዝበናል ።

ስለሆነም እንደ ኦፌኮ አይነት ሃላፊነት የማይሰማቸው ፣በወለጋ ለሚጨፈጨፉ ንፁሃን አማራ ወገኖቻችንን ደንታ የሌላቸው እና የሞት ነጋሪት የሚጎስሙ የፓለቲካ ድርጅቶች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ እያሳሰብን ።በተደጋጋሚ ጊዜ የሚጠሩት የሞት ድግስ ፣የሃሰት ውንጀላ ፣የአማራን ህዝብ ጥላሸት የመቀባት ተግባራቸው እና እንቅስቃሴያቸውን እንዲታቀቡ መልዕክታችን እናስተላልፋለን ።

በመሆኑም በአማራ ህዝብ ስም የተደራጃችሁ የሲቪክ ማህበራት ፣የፓለቲካ ድርጅቶች እንዲሁም የአማራ ህዝብ ጉዳይ የሚያሳስባችሁ አደረጃጀቶት ሁሉ በአሁኑ ወቅት የድረሱልኝ ጥሪ እያሰሙ ለሚገኙ በወለጋ (በተለይም አንገር ጉትን ተብሎ በሚጠራው ስፍራ) የሚገኙ አማራ ወገኖቻችንን የሚመለከተው አካል ንፁሃን አማራ ወገኖቻችንን ከመታረዳቸው በፊት እንዲደርስላቸው ድምፅ ልንሆናቸው ይገባል ።ይህንን ሳናደርግ ከተጨፈጨፉ በኃላ የሃዘን መግለጫ ጋጋታ የሚፈይደው አንዳች ነገር የለም ።

በወለጋ የሚገኙ አማራ ወገኖቻችንን ህይወት እጅጉን ያሳስበናል ።

የአማራ ወጣቶች ማህበር በባህር ዳር

Filed in: Amharic