>

ሃይማኖትና ፖለቲካ፤ በኢኦተቤክ ዓውድ (ከይኄይስ እውነቱ)

ሃይማኖትና ፖለቲካ፤ በኢኦተቤክ ዓውድ

ከይኄይስ እውነቱ

ብዙዎች ፖለቲካን የሚረዱት ከሥልጣንና ከመንግሥት ጋር አቈራኝተው ነው፡፡ ትክክል ነው፡፡ ፖለቲካን ለጥቅምና ሥልጣን ሽሚያ ከሚደረግ ትግል ጋር ማያያዙ ለፖለቲካ በተለይም ለሥልጣን ፖለቲካ አግባብነት ያለው ነው፡፡ ይህ ጠበብ ያለ የፖለቲካ ብያኔ ነው፡፡ ግን ይህ የተሟላውን የፖለቲካ ምንነት ሥዕል አያሳየንም፡፡ በቃሉ ምንነት ላይ አንድ ወጥ ስምምነትም የለም፡፡ እንዲያውም የሚያከራክር ፅንሰ ሐሳብ ነው፡፡ እንደ አንድ ዓለማዊ የዕውቀት ዘርፍ (discipline) ፖለቲካ የምንለው እሳቤ ከሃይማኖት ጋር አንዳች ግንኙነት እንደሌለውና በብያኔም ደረጃ ሃይማኖታዊ አመለካከትን በምንም መልኩ የማይጨምር አድርጎ ማየቱ የተሳሳተ ግንዛቤ ነው፡፡ ፖለቲካ የሚለው ቃል ውስጠ-ዘ አንደምታ ያለው፤ ከተራ ፍቺው የዘለለ አዎንታዊ/አሉታዊ ተጨማሪ ትርጕም ያለው (loaded term) ሐሳብ ነው፡፡ ሰፋ ባለ መልኩ ስናየው ባገር ጉዳይ አስተያየት መስጠትና መሳተፍ ፖለቲካ ነው፡፡ በቅጡ ሳናውቀውና ሳንረዳው በዕለት ተዕለት ሕይወታችን የምንሳተፍበትና ተጽእኖ የሚያደርግብን አስተሳሰብ ነው፡፡

በተቃራኒው ሃይማኖት ፖለቲካ የሚባለውን አስተሳሰብ የማይጨምርና ምንም ግንኙነት እንደሌለው አድርጎ ማሰብም ስሕተት ነው፡፡ ሃይማኖት የእግዚአብሔርን መንግሥት ብቻ የሚመለከት ሳይሆን ምድራዊ ሕይወታችንንም በሥርዓት የምንመራበት ሐሳብ ነው፡፡ ባለንበት ዘመን ሃይማኖት/እምነት ከሰው ልጆች መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ጋር ተያይዞ የሕሊና ነፃነት በሚለው ጥቅል ሰብአዊ መብቶች ውስጥ የሚታይ ከመሆኑ አንፃር፣ ይህንን ነፃነት ባግባቡ ለማስጠበቅ ሲባል በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች እና በአገራት የበላይ ሕግጋት ውስጥ የመንግሥትና ሃይማኖት መለያየት ድንጋጌዎች ቢቀመጡም ሃይማኖት ወይም የሃይማኖት ተቋማት ባገራዊ አጀንዳዎች አያገባቸውም ማለት አይደለም፡፡ መንግሥት ግን ምድራዊ ተቋም ነው፡፡ እንደ ክርስትናው/ቅዱሳት መጻሕፍት አስተምሕሮ እግዚአብሔራዊውን አመራር አልፈልግም ብሎ በዓመፃ የመጣና የተቋቋመ የሕዝብ አስተዳደር ተቋም ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በምርጫ ተሰይሞ ሥልጣን ይያዝ ወይም በጉልበት ተሰይሞ አምባገነናዊ አገዛዝ ቢሆንም ሁሌም ጎዶሎ ነው፡፡ የዓመፃ ውጤት በመሆኑም ምክንያት በዓለማዊው ሕገ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ እንዲፈተፍት አይፈቀድለትም፡፡ ለዚህም ነው አሁን ባለንበት ዘመን ዘመናዊው መንግሥት የሃይማኖትን ጉዳይ በሚመለከት ገለልተኛ በመሆን አንዱን ሃይማኖት ወይም እምነት ከሌላው ለይቶ ከመደገፍ ወይም ከመቃወም የመቆጠብ መርህ (secularism) ተቀባይነት አግኝቶ ተግባራዊ እየሆነ ያለው፡፡ ይህ አጠቃላይ መርህና አዝማሚያ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ መንግሥታዊ ሃይማኖት የሚከተሉ ‹መንግሥታት› መኖራቸው አይካድም፡፡ 

አንዳንድ አምባገነኖችም ለዕድገትና ልማት እንቅፋት ናቸው በሚል ነባር ሃይማኖቶችንና የሃይማኖት ተቋማትን በማጥፋት የራሳቸውን ‹‹መንግሥታዊ ሃይማኖት›› ለመትከል ድብቅ አጀንዳ እንዳላቸው በስፋት ሲነገር ይደመጣል፡፡ በዚህ ረገድ ስማቸው ከሚነሣው መካከል የጐሠኛው የዓቢይ አገዛዝ አንዱ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ወያኔ የተከለው የማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥት› መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ እንደሆነ፣ ሃይማኖታዊ መንግሥት እንደማይኖር ቢደነግግም (አንቀጽ 11) ጐሠኞቹ ሰነዱ መኖሩን የሚያስታውሱት ለጥቅማቸው አስፈላጊ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ ሰውየው ይከተለዋል የሚባለው፣ የፖለቲካ ድርጅቱም እንዲከተል የሚፈልገውና ባገር ላይም በጉልበት ለመጫን የሚያስበው የ‹‹ብልጽግና ወንጌል››* በአሜሪካ ስውር ጥንቆላ ባህል (occult tradition) ውስጥ ረጅም ዕድሜ ያለው የፕሮቴስታንት እምነት አንድ ዘርፍ ሆኖ፣ በሃይማኖት ሽፋን ስውር ጥንቆላን (occult) የሚያራምድ አስተሳሰብ ነው፡፡ አስተምሕሮው ባጭሩ የክርስትናን እምነት ከሀብት፣ በተለይም ከፋይናንስና ምድራዊ ስኬት ጋር እኩል የሚያደርግ ንቅናቄ ነው፡፡ እንደሚነገረው ይህን ንቅናቄ ነው ይሄ ያበደ ሰውዬ ወደ ኢትዮጵያ ምድር አምጥቶ በጐሣው ሥርዓት ላይ ሊደርብ ያሰበው ‹ቡትቶ›፡፡ በቡሃ ላይ ቆረቆር እንደሚሉት ኋላ ቀር በሆነው የድንቊርና ጐሣ ሥርዓት በአጋጣሚ የተረፉ ኢትዮጵያዊ የእሤት ሥርዓቶችን (value systems) ከምዕራቡ ዓለም በተዋሰው ‹እምነት› በሚመስል ስውር የጥንቆላ ሥርዓት ነው ሊያጠፋ የሚያስበው፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ንቅናቄ ሃይማኖት አይደለም፡፡ ሃይማኖትም ተብሎ ሊጠራ አይገባውም፡፡ ‹የክርስቲያን ሳይንስ› የሚባሉት ክፍልፋዮች የ‹ብልጽግና ወንጌል› አንዱ መገለጫ ሲሆን፣ ራሳቸውን የሚገልጹት ክርስቲያን በሚል ሳይሆን የ‹አዲስ እሳቤ› (“new thought”)/ ወይም በ19ኛው መቶ ክ/ዘመን የጤናማ ሕይወት የሚመጣው ከጤናማ አስተሳሰብ ነው በሚል ስብከት (“mind cure”) የተደረገ ንቅናቄ አራማጆች ብለው ነው፡፡ እነዚህ ጉዶች ከስውር ጥንቆላው በተጨማሪ የሳይኮ-ቴራፒ መሠረት ያለውና ‹በመናገር የሚገኝ ፈውስ› (“talking cure”) የሚባለው ‹ማደንዘዣ› ሌላው መገለጫቸው እንደሆነ ይነገራል፡፡ እዚህ ላይ የአገዛዙ አማካሪዎች የእነ ምሕረት ደበበን ሚና ያስተውሏል፡፡ ሰውየው ሐዘንና ርኅራኄ ከሚባሉ ሰብአዊ ስሜቶች ተራቊቶ ዜጎችን በገፍ እየገደለና እያስገደለ፣ እንደ ቆሻሻ በግሬደር ዝቆ በጅምላ እያስቀበረ በፓርክ የሚዝናናው፤ በዜጎች መከራና ስቃይ የሚደሰት በሽተኛ የመሆኑ አንዱ ምክንያትም የዚህ ‹ጥንቆላ› አስተምሕሮ ውጤት ነው፡፡

ወደ ቀዳሚ ነገራችን እንመለስና፣ በርግጥ ፖለቲካዊው ተቋም መንግሥት እና ሃይማኖት መሠረታዊ ልዩነት አላቸው፡፡ ፊተኛው ምድራዊ ኋለኛው ሰማያዊ፤ ፊተኛው ጊዜያዊ ኋለኛው ዘላለማዊ ባሕርያት አሏቸው፡፡ ሃይማኖት የራሱ ብቸኛ መለያ የሆኑ የእምነትና ተግባራዊ የአምልኮ ሥርዓቶች አሉት፡፡ መሠረተ-እምነት (ዶግማ)፣ አስተምሕሮ (ዶክትሪን)፣ ቀኖና (ካነን)፣ ሥርዓት (ሆሊ ኦርደርስ)፣ መንፈሳዊ ትውፊት (ስፕሪችዋል ትራዲሽን)፣ ወዘተ. አሉት፡፡ ባንፃሩም ሁለቱም የሚጋሯቸው የጋራ ገጽታ እንዳላቸውም ማስተዋል ይገባል፡፡ ለምሳሌ ሰብአዊ መብቶች የምንላቸው ሁለንተናዊ መብቶች ፖለቲካዊ ብቻ ሳይሆን ሃይማኖታዊ ገጽታ እንዳላቸው መዘንጋት የለብንም፡፡

በኢትዮጵያችን የሠለጠነው ወራዳ አገዛዝ ነገ ተነሥቶ እንደ ምዕራቡ ዓለም ግብረ ሰዶምንና ግብረ ገሞራን በሕግ አጸድቃለሁ ቢለን የፖለቲካ ጉዳይ ነው አያገባንም ልንል ነው? ሆን ብሎ ፅንስን ማስወረድ ሕጋዊ ነው ቢለን የፖለቲካ ጉዳይ ነው በሚል አሜን ብለን ልንቀበል ነው? ዛሬ ምዕራቡ ዓለም በሰብአዊ መብቶች ሽፋን በሃይማኖት ፍጹም ተቀባይነት የሌላቸው በርካታ ርኵሰቶችን/ነውሮችን ሕጋዊ አድርጎ ማለማመድ ከጀመረ ዓመታት ተቈጥረዋል፡፡ ከራሳቸውም ሕዝብ አልፈው ነውሮቹ በሌሎች አገሮችም እንዲሰበኩና ተግባራዊ እንዲሆኑ ጥረት ከማድረግ ሳይወሰኑ አንዳንዴም ለሚሰጡት እርዳታና ብድር በቅድመ ሁኔታነት እያስቀመጡ እንደሆነ የምንሰማው የዐደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ሙከራዎቹ በአገራችን የሉም ማለት አይደለም፡፡ በተወሰኑ ሚዲያዎች እና በተግባር በመዲናችን የተካሄዱ ስብሰባዎች እንደነበሩ እናስታውሳለን፡፡

በሌላ በኩል ኢትዮጵያን ለማፍረስ ወያኔና ኦነግ የተከሉት የማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥት› በሌሎች አገሮች ሕግጋተ መንግሥት ያልታየ ‹‹ሃይማኖት በመንግሥት ጣልቃ አይገባም›› የሚል ድንጋጌ ሰንቅሯል፡፡ ይህ ድንጋጌ በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይነት የሌለው የሃይማኖትን ባሕርይ በፍጹም ያልተረዳ የደናቊርት ሐሳብ ነው፡፡ ሃይማኖት በምድር ያለ የእግዚአብሔር መንግሥት ከሆነ በክርስትናውም ሆነ በሌሎች እምነቶች ያሉ አስተምሕሮዎች፣ እሤቶች ጋር ተቃራኒ አባባል ነው፡፡ የሃይማኖት ተቋማት ወይም መሪዎች መንግሥት የተባለው ሰው ሠራሽ ተቋም ‹‹ደሀ ሲበድል ፍርድ ሲያጓደል›› (ባጠቃላይ ግፍና ጭቆና ሲፈጽም) የመንግሥት ጉዳይ ስለሆነ ጣልቃ አንገባም ብለው እጃቸውን አጣጥፈው ይቀመጡ ወደሚለው ትርጕም የለሽ መደምደሚያ ይወስደናል፡፡ የሃይማኖት አስተምሕሮ – ለምሳሌ የኢኦተቤክ ብንወሰድ – ለመሪዎቹ አባቶች የሞራል ሥልጣን (moral authority) ይሰጣል፡፡ እንዲያወግዙ፣ እንዲገሥፁ፣ ተከታዩ/ምእመኑ እምቢ አልገዛም እንዲል የማድረግ በጉልበት ከሚፈጸመው ምድራዊ ሕግ የበለጠ ሥልጣን ይሰጣል፡፡ ሰማዕታቱ አቡነ ጴጥሮስና አቡነ ሚካኤል ለጠላት ጥልያን ሕዝቡም ምድሪቱም እንዳይገዙ ሲያወግዙ እና አርበኛውን ሲያበረታቱ የፈጸሙት ይህንን ከአምላክ የተሰጠ ሥልጣን ነው፡፡ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ የሚጠይቀው መንፈሳዊ ጥንካሬና በሃይማኖትና ፖለቲካ መካከል ያለውን ግንኙነት በውል መረዳት ብቻ ነው፡፡

የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ጥራዞች በተጻፉበት ርእሰ ጉዳይ ላይ ምሁራዊ ትንተና ለመስጠት አይደለም፡፡ የሙያውም የዘርፉ ዕውቀት ባለቤትም አይደለሁም፡፡ ባገራችን ዓውድ ከተራው ሕዝብ ጀምሮ ፊደል ቈጥረናል፣ ከዚህም ከፍ ባለ ሁናቴ ምሁራን ነን በሚሉ ባንዳንዶችም ዘንድ የተሳሳተ ግንዛቤ በማስተዋሌ ነው፡፡ ይህ የእምነት ተቋማት መሪዎችንም ይመለከታል፡፡ ምናልባት ‹ፖለቲካና ኮረንቲ ከሩቁ› የሚለው አጉል ልማዳዊ አባባል ስር በመስደዱም ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ የተሳሳተ ግንዛቤ ሊታረም ይገባዋል፡፡ አባቶቻችን ጥቁር ልበሱ ብለው ባዘዙን ሰሞንና ከሱባኤውም በኋላ ባሉት ቀናት ከል በመልበሴ አንዳንድ ክርስቲያኖችና ከእምነቱም ውጭ ያሉ ትውውቆቼ በሩቅ ሲሸሹኝ አስተውዬአለሁ፡፡ የ‹ፖለቲካ› ተቃውሞ ምልክት በማድረግ፡፡ ትእዛዙ በቤተክርስቲያን የተሰጠ ቢሆንም  አንድ ሰው የመረጠውን ልብስ ዓይነት መልበስ (የሥራው ሁናቴ በተለይ የሚያስግድደው ካልሆነ በቀር) መብቱ ነው፡፡ መብትም ሆነ ነፃነት ደግሞ ከፖለቲካ ጋር የተቈራኘ ነው፡፡

አንዳንድ የሃይማኖት ሰዎች ወይም መሪዎች በሃይማኖትና ፖለቲካ መካከል ግልጽ መስመር በማስመር አምባገነንና ዘረኛ መንግሥት የሃይማኖት ተቋማትን ለመቆጣጠር ወይም ለማጥፋት (ድብቅ አጀንዳቸውን ማስፈጸሚያ ለማድረግ) መዋቅሩንና ኃይልን በብቸኝነት ለመጠቀም (monopoly of violence) በሕግ የተሰጠውን ሥልጣን አላግባብ ተጠቅሞ በሃይማኖታዊ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት የሚያሳድረውን ግዙፍ ተጽእኖ ለመቋቋም ከሚደረግ መንፈሳዊ ተጋድሎ ማፈግፈጊያ ወይም መደበቂያ ዋሻ አድርጎ ማየት ታላቅ ስሕተት ነው፡፡ ወደድንም ጠላንም ፖለቲካ የምንለው ሐሳብ ሰፋ ባለ ትርጕሙ ስናየው የእያንዳንዳችን የዕለት ተዕለት የሕይወታችን ክፍል ነው፡፡ 

ኢትዮጵያ ባለፉት 50 ዓመታት በጉልበት የሠለጠኑ አገዛዞች እንጂ መንግሥት ኖሯት አያውቅም፡፡ በተለይም ባለፉት ሦስት ዐሥርታት የመንግሥትነት ባሕርይ ያለመኖሩ ዓይነተኛ መገለጫዎች አገዛዙ እገዛዋለሁ የሚለውን ሕዝብ ነገዱንና ሃይማኖቱን መሠረት አድርጎ በጠራራ ፀሐይ እየጨፈጨፈና እያስጨፈጨፈ (የዘር ፍጅት፣ በሰብአዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች፣ የጦር ወንጀሎች) እያፈናቀለና እንዲፈናቀል እያስደረገ ሲፎክርና ሲያቅራራ፣ የግፍ ጽዋው ሞልቶ እየፈሰሰ ተጠያቂነት የሚባል ነገር በምድሪቱ መጥፋቱ፤ አገር እገዛለሁ በሚሉ ስብስቦች ብልግና (ሽብርተኝነት፣ በሐሰት ትርክት ላይ የተመሠረት ጥላቻ፣ ውሸት፣ ቅጥፈት፣ ክህደት፣ ንቅዘት፣ ወሮበልነት፣ ሥርዓተ አልበኝነት ወዘተ.) መንገሡ፤ ዳኝነት፣ ፍትሕና ባጠቃላይ የሕግ የበላይነት አለመኖሩ፤ በሰሜን ምዕራብና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የአገር ዳር ድንበር በባዕዳን ጠላቶች ጭምር ተይዞ (ዜጎች ሲገደሉ፣ ሀብት/ንብረታቸው ሲቃጠልና ሲዘረፍ) በዝምታ ከማየት አልፎ ዜጎችን በማስፈራሪያነት እየተጠቀመበት ነው፤ በአገዛዙ እየታወቀ ለዓመታት ታፍኖ ተቀምጦ፣ አንድ ኢትዮጵያዊ ጐሣ በጠላት ተፈጅቶ ከ50/60 የጐሣው አባለት ቀሩ ሲባል ከመስማት የበለጠ ምን የሚያስደነግጥና የሚያበሳጭ ጉዳይ ይኖር ይሆን? ቅድመ አያቶቻቸው ከዛሬ 500 ዓመታት በፊት ከ20 በላይ የሚሆኑ ነባር የኢትዮጵያ ጐሣዎችን ከምድረ ገጽ ላጠፉ ልጆች ዜናው ምንም ላይመስላቸው ይችላል፡፡  ባጭሩ አገዛዙ እገዛዋለሁ የሚለውን አገርና ሕዝብ ከታሪኩ፣ ከእሤቶቹ፣ ባህሉ፣ ቅርሱና ማንነቱ ጋር ጠራርጎ ለማጥፋት መነሣቱ ጎልተው የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ መንግሥት የሚባል የአገርን ዳር ድንበርና የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት የሚጠበቅ አካል ቢኖር ኖር ሌላውን ሁሉ ትተን ይህ በሥልጣን የሰከረና አንደበቱ ያልታረመ ሰውዬ ባደባባይ ሳያፈራና ሳያፍር ሕዝብ በሕዝብ ላይ እንዲነሣ፣ የሃይማኖት ተቋማትን እና የሃይማኖት መሪ አባቶችን የሚያዋርድ ንቀትና ትእቢትን የተሞላ ከፋፋይና የጥላቻ ንግግር በማድረጉና በሃይማኖት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባቱ ብቻ ከሥልጣን መሰናበት ነበረበት፡፡ ለጊዜው በጐሠኛነት ላይ ባዋቀረው ሠራዊቱ ብዛት ተመክቶ በማናፋት ላይ ነው፡፡ ይህ እስከ መቼ ይዘልቃል?

የኢኦተቤክ ‹አገር› እንደሆነች በወዳጆቿም ሆነ በጠላቶቿ የታወቀ ነው፡፡ አገር ያልናት ባደረገችው መተኪያ የሌለው አበርክቶዋ ነው፡፡ በያዘችው አገራዊ ቅርስና እሤቶች ነው፡፡ ዝርዝሩን ከቀደመ ጽሑፌ ማየት ይቻላል፡፡ ሊታዘዛት ዝግጁ የሆነ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ይዛለች፡፡ ይህ ታላቅ ሀብት ነው፡፡ የቤተክርስቲያኒቱን ተቋማዊ አንድነትና ልዕልና ከማስከበሩ ጎን ለጎን አገራዊ ኃላፊነት አለባት፡፡ አገር ከሆነች ደግሞ አገርን የማዳን/የመታደግ ታላቅ ኃላፊነት አለባት፡፡ አገርን፣ ሃይማኖትን/ቤተክርስቲያንን የሚያጠፋ ዓላዊ ሲነሣ ዝም ብላ መመልከት ተገቢ አይደለም፡፡ አይመለከተኝም ማለት አትችልም፡፡ የኢኦተቤክ አሁንም ላለፉት ሠላሳ ሁለት ዓመታት በዳተኝነት ከሠራችው ግዙፍ ጥፋቶች የተማረች አይመስልም፡፡ ከጸሎት ባለፈ በእግዚአብሔር የተሰጣትን መንፈሳዊ ሥልጣን ሥራ ላይ ማዋል (exercise ማድረግ) አለባት፡፡ ምእመኑ እናቴ ቅድስት ተዋሕዶ አለሁልሽ የሚላት መሠረትና ጉልላቷ ክርስቶስ ስለሆነ እንጂ በደካማ ሰው ታምኖ አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ አባቶቹን ያከብራል፣ ይታዘዛልም፡፡ ባለቤቱ ደግሞ ቸር ሰው ወዳጅና የሰውን ድካም የሚያውቅ አምላክ ነው፡፡ የጐሣው ሥርዓት ባመጣው ሁለንተናዊ ጥፋት ቤተክህነቱ በከፍተኛ ምስቅልቅል ውስጥ ያለና አሁንም ያልጠራ መሆኑን አብዛኛው ምእመን ያውቃል፡፡ ይሄ ያበደ ሰውዬ ቀድሞ በሎሌነት ያደረለትን እና አሁን ደግሞ በጌትነት የሚገዛው የጐሠኞች አገዛዝ በቤተክህነቱ ያደረሰውን ጥፋት ከጽሑፈ ተውኔቱ እስከ ተዋናይነት የተሳተፈበት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት አንዳንድ አባቶችን በሰይጣናዊ ተንኰሉ ከገንዘብ/ሀብት ወይም ሌሎች ነውሮች ጋር በተያያዘ ምስጢር አጋልጣለሁ በሚል ለማስፈራረቱ (blackmail ለማድረግ) መሞከሩ የኖረበት ተግባር ነው፡፡ በፈጠራ ክስ ሰዎችን የሚወነጅል ቆሻሻ ሥርዓት ውስጥ ነው ያለነው፡፡ ምናልባት ባንዳንዶች ላይ ያዝኹ የሚለው ምስጢር ቢኖር እንኳን (ከሕገ ወጦቹ ጥፋት ተነሥቶ ምእመኑ መደናገር ውስጥ ስለገባ) ሥልጣነ ክህነትን የሚያፈርስ ‹ነውር› እስካልሆነ ድረስ በንስሓ የሚስተካከል ነውና ለአጥፊ ዓላማው በጭራሽ መንበርከክ አይገባም፡፡ እኛ ልጆቻችሁ (መሠረተ-እምነት፣ ቀኖና ቤተክርስቲያን እና ሥርዓተ ቤተክርስቲያን እስከተጠበቀ ድረስ) ዛሬም ነገም እስከ ሁሌም እናከብራችኋለን፣ እንታዘዛችኋለን፡፡ እንደ መንፈሳዊ አባትነታችሁ ከምንጠይቃችሁ መሠረታዊ ጥያቄዎች መካከል፤ 1ኛ/ ባኮራችሁን ጥበብ የሞላበት አመራርና አቋም ፀንታችሁ የቤተክርስቲያናችንን ተቋማዊ ልዕልናና አንድነት እንድታስከብሩና በዓላዊው የተንኰል ወጥመድ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ዳግም እንዳትወድቁ (እንኳን 26ቱ 3ቱም ሕገ ወጦች በቤተክርስቲያናችን ጉዳይ የመጨረሻ ውሳኔ ሰጭ የሆነው አካል ተቀላቅለው አገዛዙ የሰጣቸውን ተልእኮ እንዲፈጽሙ በጭራሽ መፍቀድ የለብንም)፤ 2ኛ/ አባቶችና ልጆቻችሁ መመካከር ይኖርብናል፡፡ በተጥባባተ ነገር ለመሄድ ከማሰብም አይደለም፡፡ እንደምታውቁት የምንተሳሰብበት፣ እግዚአብሔርን የምንፈራበት፣ የኢትዮጵያዊ ጨውነት ዘመንና እሤቶች ተሸርሽረው መለ መላችንን እየቀረን ነው፡፡ አዲሱ ትውልድ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን እንዲጠላ ተደርጎ እያደገ ነው፡፡ ክቡሩን የሰው ሕይወት ሲያጠፋ ትንኝ የገደለ የማይመስለው ጨካኝ ትውልድ በዚህች የተቀደሰች ምድር በቅሏል፡፡ ጥፋቱ የጐሠኛነት ሥርዓት የተከሉት ብቻ ሳይሆን የሁላችንም ነው፡፡ በሚያስደነግጥ ዝምታችን አገርና ቤተክርስቲያናችንን በማጥፋቱ ተባባሪ ሆነናል፡፡ ለሥጋችን አድልተናል፡፡ ተካክለን በድለናል፡፡ ይሄ እውነት ነው፡፡ 3ኛ/ ካለፈው ተምረንና ተፀፅተን ከእንግዲህ ወዲህ በየትኛውም የአገራችን ክፍል ደሀ ሲበደል ፍርድ ሲጓደል፤ ወገኖቻችን ባገዛዙ በሚታዘዙ ኃይሎችና ሽብርተኞች ደማቸው በከንቱ ሲፈስ (በወለጋ፣ በጎጃሙ መተከል እንዲሁም አገዛዙ ኦሮሚያ በሚለው የኢትዮጵያ ግዛት) ዝም ማለት የለብንም፡፡ በየዕለቱም ቢሆን ከማውገዝ ጀምሮ ለሟቾች ጸሎተ ፍትሐትን እና ሥርዓት ያለው የክብር ቀብርን፣ ለሚፈናቀሉ ዘመዶቻቸው መጽናናትንና ምእመናንን አስተባብረን ድጋፍ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ በዚህም ሳንወሰን እንዲህ ዓይነት አገራዊ ጥፋት የሚፈጽመውን አካል/አገዛዙን ያለምንም ፍርሀት ተው! ማለት ያስፈልጋል፡፡ እምቢ ካለና በነውሩ ከቀጠለ ምእመናን እንዳይታዘዙት እስከ ማውገዝ መሄድን ይጠይቃል፡፡ በተቃራኒው በእስካሁኑ ዝምታ እንዘልቃለን፤ ቤተመንግሥቱ ሲጎትተን እየተንፏቀቅን ለጥፋቱ ቡራኬ በመስጠት እንቀጥላለን ካላችሁ አገርም ቤተክርስቲያንም አይኖረንም፡፡ በዚያ በኩል ያሉት ሰዎች የኢኦተቤክ እና አገርን ለማጥፋት ዐቅደው፣ ሠራዊትና የአገር ሀብት ሁሉ አሰልፈው 24/7 እየተጉ ነው፡፡ አሁን ካልባነንን መቼም ከድባቴአችን የምንወጣ አይመስልም፡፡ ጆሮአችንን እና ዓይናችንን ከፍተን በንቃትና በትጋት እንከታተል፡፡

ሁሉ ነገር ከእጃችን ከወጣ በኋላ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨቱ አይጠቅመንም፡፡ ቢረፍድም ወደ ቀልባችን ተመልሰን፣ እግዚአብሔርን ይዘን በጾም፣ በጸሎት፣ በልቅሶ በምህላ እርሱን ተማፅነን ከእስካሁነ የከፋ ጥፋትን ማስቀረት፣ ወደ ቀደመ ክብራችን መመለስ እንችላለን፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የተቀደሰ ተግባር ቊርጥ ሕሊናን እና የተናበበ ድርጊትን ይጠይቃል፡፡ ቤተክርስቲያናችን በሁለት በኩል የተሳሉ ልጆቿን ይዛ በራሷ መንፈሳዊና አስተዳደራዊ ዕቅድ እንጂ ቤተመንግሥቱና ተላላኪዎቹ በተለሙላት ትልም አትጓዝም፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ እንዳስተማረን እግዚአብሔርን እሺ በጄ እንለዋለን፤ በዓላውያን አድሮ የሚፈታተነንን ሰይጣን ደግሞ እምቢ ወግድ ማለት ይኖርብናል፡፡

ለተዋሕዶ እምነት ተከታዮች እንኳን ለጾመ ኢየሱስ (ዐቢይ ጾም) በጤናና በሕይወት አደረሳችሁ፡፡ ሱባኤውን ጾመ ሥርየት ጾመ ድኅነት ያድርግልን፡፡ ላገራችን ሰላምን፣ ቤተክርስቲያናችን ከተቃጣባት ፈተናና መከራ ሰውሮ በአንድነትና በሉዐላዊነቷ እንዲያፀናልን፣ ለሕዝባችን ፍቅርና አንድነትን እንዲሰጥልን ጸሎቴና ምኞቴ ነው፡፡

Filed in: Amharic