>

በውኑ ኢትዮጵያዊነት ‹‹ጐሠኛነት/ብሔርተኛነት›› ነው? (ከይኄይስ እውነቱ)

በውኑ ኢትዮጵያዊነት ‹‹ጐሠኛነት/ብሔርተኛነት›› ነው?

ከይኄይስ እውነቱ

ኢትዮጵያዊነት ባገር ድንበር የማይወሰን ዓለም አቀፋዊ ጠባይ ያለው ሐሳብ ወይም ፍልስምና አይደለም ወይ? አንድ ታላቅ አገራዊ ዕሴት ብቻ መዝዘን ለመናገር፤ የዓድዋ ድል – ፀረ-ፋሺስት÷ ፀረ-ቅኝ ግዛት ተጋድሎ – የኢትዮጵያዊነት መገለጫ አይደለም ወይ? አንድም ኢትዮጵያዊነት በጐሠኛነት ወይም በሌላ አፍራሽ ምክንያት የሚመጣ ልዩነት አልፎ ተሻግሮ የተለያዩትን ኹሉ አንድ የሚያደርግ የሚያዋሕድ የላቀ ዕሴት (transcendent value) አይደለም ወይ? አንድም ኢትዮጵያዊነት ተቋማዊ ቃል ነው፡፡ ራስን ትቶ ለአገር መኖር ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት እኮ እስልምናን ከመካከለኛው ምሥራቅ፤ ዘጠኙን ቅዱሳን ከሮም፤ እነ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስን ከምስር አምጥቶ ጥላ ከለላ የሆነ ምዕራፍ ነው፡፡ እስከ ጥግ ሔደን ከፍ ካደረግነው ምሥጢሩ ለሚገባው ኢትዮጵያዊነት ከብሔራዊና ዓለም አቀፋዊ ማንነት ልቆ ተሻግሮ ከእግዚአብሔር ቀጥሎ የሚነሣ ታላቅ ስም ነው፡፡

ሰሞኑን አንድ ትኩረት የሚስብ ውይይት በኢትዮ-360 ሜዲያ በሁለት ፖለቲከኞች – በአቶ ኤርምያስ ለገሰ እና በአቶ ልደቱ አያሌው – መካከል ሲደረግ አዳመጥሁ፡፡ ስለ አገር ጉዳይ ስንነጋገር ሰፋ ባለ ትርጕሙ ስንወስደው ዜጎች ሁሉ ፖለቲከኞች ነን፡፡ እኔም የኢትዮጵያ ጉዳይ በእጅጉ ከሚያንገበግባቸው ኢትዮጵያዊ ዜጋ አንዱ ነኝ ብዬ አስባለሁ፡፡ የፖለቲካ ሳይንስ ተማሪ ወይም ተመራማሪ ግን አይደለሁም፡፡ ተወያዮቹ ግን የሥልጣን ፖለቲካ ውስጥ ተሳታፊነት የነበራቸው ፖለቲከኞች መሆናቸውን በመግለጽ ወደ ርእሰ ጉዳዬ እገባለሁ፡፡

ለውይይቱ መነሻ የሆነው አቶ ልደቱ በወቅታዊ የአገራችን ጉዳይ ላይ ያዘጋጀው ወረቀት እንደሆነ ከተወያዮቹ የተረዳሁ ሲሆን፣ የውይይታቸው መሪ ርእስ ‹‹ዶ/ር ዐቢይና የ‹አይተኬነት› ›› ጥያቄ የሚል ነው፡፡ ርእሱን ከተጻፈው ቀጥታ የወሰድሁት በመሆኑ እንጂ እንዲህ ዓይነቱን አገር ያዋረደ ነውረኛ ግለሰብ በክብር መጠራት አለበት ብዬ አላምንም፡፡ የዚህ አስተያየት አቅራቢ አቶ ልደቱ ያዘጋጀውን ጽሑፍ አላገኘሁም፡፡ ሆኖም ውይይቱን ተከታትዬአለሁ፡፡ የእኔ አስተያየት የሚያተኩረው መሪ መወያያ በተደረገው ርእስ ላይ ሳይሆን አቶ ልደቱ ኢትዮጵያ የገጠማትን መሠረታዊ የፖለቲካ ችግር የበየነበትን ሁናቴ ይመለከታል፡፡ ይኸውም በእሱ ቋንቋ ‹ብሔርተኛነት› ብሎ የገለጸውና ኢትዮጵያዊነትንም በዚህ ብያኔ ውስጥ ማካተቱ ነው፡፡ በርግጥ የአገራችንን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ በሚመለከት ባንፀባረቃቸው ሌሎች ጉዳዮች ላይም የምስማማባቸውም ሆኑ የምለይባቸው አቋሞች ቢኖሩም በዚህ ጽሑፍ ‹ብሔርተኛነት› በሚለው ላይ ብቻ አተኩራለሁ፡፡ 

የኢትዮጵያ ሕዝብ የአገሩን ህልውና አስከብሮ ወደ መደበኛ የፖለቲካ ንግግር ለመግባት በቅድሚያ ባለው የጐሠኛነት ሥርዓትና በነውረኛው ዐቢይ እንዲሁም ‹ተቃዋሚ የፖለቲካ ማኅበራት› በሚባሉት ተስፋ መቁረጥ ይኖርበታል ያለው አንዳንዶች ቀደም ብለን ስንጮኽ (ብዙኃኑ ባልባነነበት ሰዓት) የቆየንበት ጉዳይ በመሆኑ ሕዝብን ያነቃል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ አገዛዙንና ጐሠኞቹን ‹አማራጭ በማጣት› የመፍትሔው አካል አድርጎ ማየት ይኖርብናል የሚለው አቋሙ ላይ ጠንካራ ተዐቅቦዬ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከዓመታት በፊት ብዙዎቻችን ስንጽፍበት የነበረውን ሀገር-አቀፍ ውይይት፣ ብሔራዊ መግባባት፣ ብሔራዊ ዕርቅ፣ የሽግግር ፍትሕ (ተጠያቂነትና ለፍርድ መቅረብን ጨምሮ) እንደ መፍትሔ በድጋሚ የመነሣቱን ተገቢነት አምንበታለሁ፡፡ 

‹ብሔርተኛነት› ያለውን ‹ንዑስ ብሔርተኛነት› እና ‹ኢትዮጵያዊነት ብሔርተኛነት› ብሎ ይከፍለዋል፡ የዚህ ክፍፍል መሠረቱ ምን እንደሆነም ብገምትም ግልጽ አይደለም፡፡ የመጀመሪያው ባለፉት 32 ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በሕግና በመዋቅር መሠረት ይዞ የበላይነት ያገኘውን፣ ቀደም ሲል በወያኔ ኢሕአዴግ አሁን ደግሞ በወራሹ ኦሕዴድ ኢሕአዴግ የሚቀነቀነውን የጐሣ ፖለቲካና ሥርዓት ሲሆን፤ ሁለተኛው ‹ብሔርተኛነት› ያለው በሚገርምና በሚያስደነግጥ መልኩ ኢትዮጵያዊነትን ነው፡፡ ሁለቱም ዓይነት ‹ብሔርተኛነት› ጽንፈኛነት፣ጠባብነት፣ እኛ-እነሱ ባይነት፣ አክራሪነት በመሆኑ፣ ከሁለት አንዱን  መርጦ መጓዝ ኢትዮጵያን ሁሌም በሁከት፣ በብጥብጥና ግጭት ውስጥ የሚከት ነው የሚል አመለካከት አለው፡፡ በመሆኑም ሁለቱም ‹ብሔርተኛነት› የራሳቸው በጎ እና መጥፎ ጎኖች ስላሏቸው ለኢትዮጵያ ቀጣይነት የሚጠቅመው በጎውን ወስዶ ሦስተኛና መሐከለኛ መንገድ መፈለግ ነው የሚል አቋም አለው አቶ ልደቱ፡፡ በተጨማሪም በኢትዮጵያዊነት ‹ብሔርተኛነት› ውስጥ ያሉ አንዳንዶች ‹‹ብሔር፣ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች›› የሚለውን ቃል መስማት የማይፈልጉና የሚጠሉም እንዳሉ ተናግሯል፡፡ በነገራችን ላይ አንዳንዶች ሳይሆን አብዛኛው በምክንያት ይህ አመለካከት አለው፡፡ ወረድ ብዬ እመለስበታለሁ፡፡

መቼም የሐሳብ ልዩነት ዕውቀትን መሠረት አድርጎና በጨውነት እስከቀረበ ድረስ የሚከበር ከመሆኑም በተጨማሪ የተሻለና የሚጠቅም ሐሳብ ነጥሮ እንዲወጣ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ ወይም በተቃራኒው አንዳንድ ሐሳቦች መርዛማ ይሆኑና አደጋም ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡ ለማንኛውም እንደ ፈረንሳዮቹ “vive la différence” ልዩነት (በዚህ ዓውድ የሐሳብ ልዩነት) ለዘላለም ይኑር እንላለን፡፡ 

ይህን ካልሁ በኋላ ከአክብሮት ጋር ከአቶ ልደቱ አቋም ጋር መሠረታዊ ልዩነት እንዳለኝ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ ይኸውም ከቋንቋ አጠቃቀም ጀምሮ የፅንሰ ሐሳቦች የተሳሳተ አረዳድ እና የሚያስከትለውም አንደምታ አደገኛነትን ይመለከታል፡፡ የተዛባ የቃላትና የፅንሰ ሐሳብ አረዳድ ያልኹት፤ 

1ኛ/ ‹ብሔርተኛነት› እና ‹ንዑስ ብሔርተኛነት› የሚባሉት ቃላት ወይም ፅንሰ ሐሳቦች ምንን ነው የሚያመለክቱት? ሀገር-በቀል መሠረት አላቸው ወይ? እስከነ አካቴውስ ይታወቃሉ? ከባዕድ በተውሶ የመጡ ከሆነስ ከመጡበት ዓውድ አንፃር ለኢትዮጵያ ልዩ ገጽታ የሚስማሙ መሆንና/አለመሆናቸው በጥናት ተፈትሿል ወይስ እንደወረደ አምጥተን ለማደናገሪያ የሰነቀርናቸው ናቸው? መቼ ነው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ሕይወት ውስጥ ቦታ ያገኙት ወይም የተዋወቁት? መሠረታቸውስ አንዱ ኢትዮጵያዊ ነገድ/ጐሣ ሌላኛውን ጨቁኖታል ከሚል ስሑት ትርክት የመነጨና ግራ ተጋብተው ትውልዱን ግራ ያጋቡት ‹የተማሪ ፖለቲከኞቹ› ‹የብሔረሰብ እስር ቤት› የሚለው ልቦለድ ድርሰት አይደለም ወይ? 

2ኛ/ ኢትዮጵያዊነት የሚለውን ሐሳብ፣ ርእዮት ወይም ፍልስምና እንዴት ነው የምንረዳው? እንደ ድንገተኛ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ ከሠላሳ ዓመት ወዲህ የመጣ አስተሳሰብ ነው ወይስ ከኢትዮጵያ የሺህ ዓመታት የሀገረ-መንግሥትነት ታሪክ ጋር የተሳሰረ? ‹‹ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች›› የሚለው እንግዳ የቃላት ትርምስስ ከየት መጣ? ትርጕሙስ ምንድን ነው? ለምን ኢትዮጵያዊነትን በሚያራምዱ አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ተጠላ? ኢትዮጵያ የብዙ ነገዶችና ጐሣዎች አገር መሆኗን ካለመቀበልና ኢትዮጵያ የምንላትን አገር በጋራ የሠሩና እንደ ኅብረ ቀለማት ያሸበረቁ ማኅበረሰቦችን ዕውቅና ካላመስጠት ወይም መብታቸው እንዳይከበር ከመፈለግ ጋር የተያያዘ ነው? በጭራሽ! እዚህ ላይ ከዚህ ቀደም ያቀረብኹትን መጠነኛ ቅኝት ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡

3ኛ/ ኢትዮጵያዊነት ‹ብሔርተኛነት› ነው ወይ? ካልሆነስ አቶ ልደቱ በምክረ ሐሳብነት ያቀረበው ሦስተኛና መሐል መንገድ የሚባል አለ? ኢትዮጵያዊነት ጐሠኞቹ እንደሚሉት ‹ጨፍላቂነት› ወይም አንድ ወጥነት ነው ወይ? ‹አሐዳዊነት› የሚለውን የተውኹት ቀደም ብዬ ስለጻፍኹበትና ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት ያለው አንድ አማራጭ ቅርፀ-መንግሥት በመሆኑና እንደየ አገሩ ሁናቴ ተመራጭ ሊሆን/ላይሆን የሚችልበት ምክንያት ስለሚኖር ነው፡፡ የጐሠኞቹ ዓላማ ግን አገር ከፋፍሎና ሕዝብ ለያይቶ ለማፍረስ ላላቸው አጥፊ አጀንዳ እንቅፋት ይሆንብናል ከሚል ሥጋት የመነጨ መሆኑን በመናገር አልፈዋለሁ፡፡ 

ጥያቄዎቼን ልቀጥልና፤ ኢትዮጵያዊነት የአንድ ነገድ/ጐሣ መገለጫ ነው ወይ? ኢትዮጵያዊነትን የጐሠኛነት ተወዳዳሪና ተገዳዳሪ አድርጎ ማቅረብ በራሱ ለቃሉም ሆነ ለሚወክለው ግዙፍ ሐሳብ አክብሮት መንሣትና ህልውናዋ በጐሠኞች አገዛዝ አደጋ ላይ ወድቋል ለምንላትና ለምንወዳት አገራችን ኢትዮጵያ ታላቅ ጉዳት (disrespect & disservice) አይደለም ወይ? ነፍሱን በገነት በመንግሥተ ሰማያት ያኑርልንና ጋሽ አሰፋ ጫቦ ‹‹ኢትዮጵያዊነቴ ከጋሞነቴ ጋር ተጣልቶብኝ አያውቅም›› ሲል ኢትዮጵያዊነትን ከጐሣው ማንነቱ ጋር በአቻነት አወዳድሮ የተናገረው ወይስ የሁሉም ኢትዮጵያ ነገዶች/ጐሣዎች አሰባሳቢ ብሔራዊ ጃንጥላ አድርጎና የኢትዮጵያን የጋራ ቤትነት አስቦ? ጋሽ አሰፋ ዛሬ በሕይወት ባይኖርም ትቶልን ያለፈው መጽሐፉና በርካታ መጣጥፎቹ አይመሰክሩም? ኦነጋውያኑ አምርረው ይጠሉት የነበረው ባንድ በኩል በዚህ አቋሙ ሳይሆን ይቀራል?

4ኛ/ በጽሑፉ መግቢያ ላይ ያነሣኋቸውና ከተራ ቊጥር 1 እስከ 3 የአቶ ልደቱን ሐሳብ  በጥያቄ መልክ ለመሞገት በቀረቡት ሐሳቦች ውስጥ የተንፀባረቁት የአቶ ልደቱ ሐሳቦች ለፖለቲካ ትክክለኛነት ሲባልና በሥልጣን ላይ ያሉትንም ሆነ ሌሎች የጐሣ ፖለቲከኞች ለማስደሰት በሚል የቀረቡ ‹የመቻቻል› አቋሞች ናቸው ወይስ ከልቡ የሚያምንባቸው? ካለን የቆሸሸ ፖለቲካና የሚያም አገራዊ ተሞክሮ በመነሣት ፖለቲካን እንደ ሞያ የያዘን እና ለሥልጣን ፖለቲካ የሚታገልን ሰው እንዳምን አልገደድም፡፡ አንዱ የውድቀታችን ምልክት ባገዛዞችም ይሁን በሌሎች ምክንያቶች በተራ ዜጎች መካከል የነገሠው አለመተማመን አይደለምን? ፖለቲከኞችንማ ለበለጠ ምክንያት አለማመናችን ምን ያስደንቃል?

ከዚህ በመቀጠል ከፍ ብዬ ለመሟገቻ ያነሣኋቸውን ነጥቦች በመጠኑም ቢሆን ጠቅለል ባሉ ሁለት አንኳር ነጥቦች ለማየት እሞክራለሁ፡፡

1ኛ/ ‹ብሔርተኛነት/ጐሠኛነት› የሚለውን ቃል መደበኛ ትርጕም እና ከ32 ዓመት ወዲህ የተነሡት የጐሣ ፖለቲከኞች ቃሉን የተጠቀሙበትን አግባብ እናያለን፡፡ ይህ መሠረታዊ ጉዳይ እንጂ ተራ የቃላት ጨዋታ (semantics exercise) ተደርጎ ሊታይ አይገባም፡፡

‹ብሔር› የሚለው ቃል የግእዝ ሲሆን አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በመዝገበ ቃላታቸው ምድር፣ ሀገር፣ ከተማ፣ገጠር፣ አውራጃ፣ ግዛት፤ታላላቅ ክፍል በስምና በሹም በወሰን በድንበር የተለየ፤ ቦታ፣ ሰፈር፣ ስፍራ ሲሆን፤ በሌላም በኩል ሰው፣ወገን፣ ሕዝብ ተብሎም ይፈታል፡፡ ሲበዛ ብሔራት/በሓውርት ይሆናል፡፡ ሀገር-በቀል ፅንሰ ሐሳቡ ይህ ነው፡፡ እገሌ ዘብሔረ ቡልጋ ቢባል የቡልጋ አገር ሰው ነው ማለታችን ነው፡፡ ‹ብሔረ ሰብእ› ካልን ደግሞ አገርና ሰው ተጣምሮ የተገለጸበት ቃል ነው፡፡ የሰዎች አገር/የአገር ሰዎች እንደማለት፡፡ በመሆኑም የፖለቲካ ሥርዓት መገለጫ ወይም ባንድ አገር ውስጥ ያለ ማኅበረሰብ ማንነት መለያ ሆኖ አገልግሎ አያውቅም፡፡ ‹ሕዝቦች› የሚለው ቃልም ላንድ አገር ሕዝብ የማይነገር ጸያፍ አባባል ነው፡፡ ‹ሕዝብ› በራሱ ብዙ ነውና፡፡ በዚህም ምክንያት ነው ‹ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች› በማለት በወያኔ የማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥት› የተካተተው ትርጕም አልባ ተራ የቃላት ግብስብስ ወይም የቃላት ዘባተሎ ሆኖ የሚታየው፡፡ በመሆኑም ጐሠኛነት ወይም በተለምዶ ‹ዘረኛነት› የሚባል ቃል እንጂ ‹ብሔርተኛነት› የሚባል ሀገር-በቀል የቃል አጠቃቀም የለም፡፡ ጐሠኛነትን ተክቶ የጐሣ ፖለቲከኞች ሊያስተዋውቁት የሞከሩት ያለቦታው የተሰነቀረ ቃል ነው፡፡ ዘረኞቹ ቃሉን የተረጐሙት በእንግሊዝኛው ‹‹nationalism›› የሚለውን ከሆነ ትልቅ ስሕተት ሠርተዋል፡፡ ይህ ቃል አንድ አገር በውጭ ኃይል ወይም ሙሉ በሙሉ በታሪክም፣በባህልም፣ በዕሤት ሥርዓቶች እንዲሁም በሥነ ልቦና በማይመሳሰለው ኃይል በጉልበት ተይዞ ራሱን ከባርነት ነፃ ለማውጣት የሚያደርገውን ንቅናቄ የሚወክል ፅንሰ ሐሳብ ነው፡፡ በተጨማሪም በዓለም ታሪክ ተመዝግቦ እንደምናነበው በርካታ መንግሥታትን ወይም አገራትን ባንድነት ጠቅልለው የሚገዙና ባንድ ዘውዳዊ አገዛዝ ወይም ሉዐላዊ መንግሥት ጥላ ስር የሚተዳደሩ ሰፊ ግዛቶች (empire) በነበሩበት ዘመን፤ ለምሳሌ እንደ ሮማዊው ግዛት፣ የብሪቲሽ ግዛት፣ የራሺያ ግዛት፣ የቱርኩ ኦቶማን ግዛት፣ ወዘተ. በውስጣቸው አገራትንና መንግሥታትን ይዘው ይገዙ ነበር፡፡ በነዚህ ሰፋፊ የንጉሣውያን ግዛቶች ውስጥ የነበሩ ራሳቸውን የቻሉ መንግሥታት ወይም አገራት በኃይል ጠቅልሎ ከሚገዛቸው አገዛዝ ነፃ ለመውጣትና ሉዐላዊነታቸውን ለማስከበር ያደረጓቸው ንቅናቄዎች ‹ናሽናሊዝም› በሚለው ፅንሰ ሐሳብ ይገለጻሉ፡፡ ይህ ዓይነቱ ክስተት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አልተመዘገበም፡፡ ወያኔ ትግሬና ኦነጋውያኑ የፈጠሩት (መጽሐፍ የጻፉለት፣ በመጽሔት ያሳተሙት፣ ሐውልት የቀረፁለት፣ ሰፊ ፕሮፓጋንዳ የሠሩለት ‹የቅኝ ግዛት›፣ ‹የብሔሮች ጭቆና› ወዘተ. የሚል) የሐሰት ትርክት የለም ማለት ግን አይደለም፡፡ አቶ ልደቱ ‹ብሔርተኛነት› ሲል ይህንን ዓለም አቀፍ ንቅናቄ አይመስልም፡፡ ካልሆነ ደግሞ ‹ብሔርተኛነት› የሚለውን ቃል ‹ጐሠኛነት› (“tribalism”) ለሚለው ቃል በተለዋዋጭነት የተጠቀመበት ይመስላል፡፡ 

ባንፃሩም ባለፉት 32 ዓመታት ይህን የቃላት ዘባተሎ ሳይገባቸው በሌላ አገር፣ በሌላ የታሪክ ዓውድ በቀድሞው ሶቭዬት ኅብረት ሰፊ ግዛት ውስጥ (ከፍ ብለን እንደገለጽነው በርካታ አገራትን/መንግሥታትን በሥራቸው ሲገዙ የነበሩ) ለነበሩ ራሳቸውን የቻሉ ‹አገሮች› እና ኅዳጣን የሆኑ ማኅበረሰቦችን መብት ለማስከበር የተቀረፀውን የፖለቲካ መፍትሔ የኢትዮጵያን ሕዝብ የጋራ ታሪክ፣ ባህል፣ ሥነ ልቦና፣ እምነት፣ ባጠቃላይ የተለየ የሀገር ግንባታ ሂደትና ልዩ ገፅታ ግምት ውስጥ ሳይገባ፣ የሐሰት ትርክት ፈጥሮ ሕዝብን በማጭበርበር የፖለቲካ ሥልጣን ለመያዝና በዚያም የሚገኘውን ዝርፊያ ለማጋበስ ‹nation, nationalities and people› የሚለውን ፅንሰ ሐሳብ ‹ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች› ከሚለው የቃላት ድሪቶ ጋር አቻነት በመፍጠር፣ ሐሳቡን እንደወረደ አምጥተው በሕዝብ ላይ በመጫን፣ ኅብረተሰባችን የተሠራበትን ድርና ማግ በመበጣጠስ በዚህም ማኅበራዊ ሥሪቱን በማናጋት ዛሬ አገራችን በመፍረስ ጣር ላይ እንድትገኝ አድርገዋል፡፡ እነዚሁ ጐሠኞች ይህንኑ የቃላት ዘባተሎ በሕግና በመዋቅር ከመትከል አልፎ አገር ለማጥፋት ዓላማቸው በተቆጣጠሩት የሕዝብ መገናኛ ብዙኃን በፕሮፓጋንዳ መልክ ደግመው ደጋግመው በማስጮኽና ሕዝብ ውስጥ እንዲሠርፅ በማድረግ በጐሠኛነት ላይ ያዋቀሩትን ፖለቲካና ሥርዓት ‹ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች› በሚለው የቃላት አርቲ ቡርቲ እያጭበረበሩ ይገኛሉ፡፡ ሆኖም  ይህ የማጭበርበሪያ መጋረጃ ዛሬ ላይ ተገፏል፡፡ ባጭሩ ይህ የቃላት ቡትቶ የኢትዮጵያን ምድር ሲረግጥ ‹ጐሠኛነት› በሚለው ቃል ይጠቃለላል፡፡ አዎን! ይህ ትርጕም የሌለው የቃላት ዘባተሎ ይዞት የመጣውን ጥፋት ነው የምንጠላው እንጂ ማኅበረሰቡማ (ከ80 በላይ የሆኑት ጐሣዎች) የነበረ፣ ያለና ለወደፊትም ከጐሣው ሥርዓት ስንላቀቅ እንደ ቀድሞው ተሳስቦ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ እውን አቶ ልደቱ ‹ንዑስ ብሔርተኛነት› ያልኸው ጐሠኛነት ከሠላሳ ዓመት በኋላ የኢትዮጵያን ነገዶች/ጐሣዎች መብት ያስከበረ ነው ብለህ ከልብህ ታምናለህ? ራሳቸውን ማስተዳደር ችለዋል? አራት ኪሎ ያለው ጨካኝ አምባገነን አይደለም እንዴ ለሱ ታዛዥ የሆነ ሰው እየመረጠ የሚያስቀምጥላቸው፤ በፈለገም ጊዜ አንሥቶ የሚቀይርላቸው? መቼም የተለመደውን የአጭበርባሪ ፖለቲከኞች የማይረባ ምክንያት የሆነውን ‹የአፈጻጸም ችግር› ነው ወይም የጐሠኞቹ አለቃ ብቃት ማነስ ነው እንደማትለኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ጐሠኛነት የጐሣ ፖለቲከኞቹ አጣመሙት/አላጠመሙት  እንደ ፖለቲካ ሥርዓት ከመነሻውም ጠማማና በጎ ጎን የሚባል የሌለው ‹ድውይ ፍጥረት› ነው፡፡ ‹የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች› በዓል በማለት በዓመት አንድ ጊዜ ዐደባባይ ወጥተው እንዲጨፍሩ ስላደረገ የመብት መከበር አድርገን ከቆጠርነው ተላላዎች ነን ማለት ነው፡፡ ይህ በጐሣዎች ስም የሚነግደው አገዛዝ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያን በደቡብ ሱዳን አስወርሮ አንድ ኢትዮጵያዊ ጐሣ አልቆ 50/60 አባላት ብቻ ነው የቀሩት ብሎ አምኖ የተናገረ አይደለም እንዴ? 

በዚህ ክፍል የተመለከተውን ሐሳብ በጥያቄ እንጀመርኹት በጥያቄ እቋጨዋለሁ፡፡ በተግባር ቋንቋን መሠረት አድርጎ እንደ ከብት ጋጣ የታጠረው ‹ክልል› የሚባል መዋቅር ኢትዮጵያን የዜጎች ባጠቃላይ የነገድ/የጐሣዎች በተለይ እስር ቤት አላደረገም ወይ?

2ኛ/ ኢትዮጵያዊነት ‹ብሔርተኛነት› ነው ወይ? በሚል ከፍ ብዬ ጥያቄ አንሥቼ ነበር፡፡ ኢትዮጵያዊነት የሚባለው እሳቤ ከበቂ በላይ የታወቀ ነው፤ እሳቤውንም ለማስረዳት ማንም መድከም የለበትም፤ ከነፍሳችንና ከደማችን የተዋሐደ የጋራ ማንነታችን ነው በሚል ለዘመናት በውስጡ የያዘውን የደለበ ዕሤት በቅጡ ሳንገነዘብ ነበር፡፡ አገር ሊያሳጣ በሚችል ደረጃ መገፋቱ እጅግ አሳሳቢ ቢሆንም፣ ባለፉት ሠላሰ ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያዊነት በአገዛዞች ከፍተኛ ጥቃት ከደረሰበት በኋላ፣ ቅርንጫፎቹና ቅጠሎቹ ሁሉ ተመልምለው ግንዱን ለመገዝገዝ ዳር ዳር በሚሉበት ሰዓት ኢትዮጵያውያን በመጠኑም ቢሆን የባነንን ይመስላል፡፡ ፈጣሪ በሰጠን ኢትዮጵያ በተባለች የተቀደሰችና ቅዱሳን በኪደተ እግራቸው የባረኳት ምድር፣ የተለያዩ ቤተ-እምነቶች ተከባብረው በሚኖሩባት በዚህች የጋራ ቤተመቅደሳችን ኢትዮጵያዊነት የጋራ ነፍሳችን፣ በደም ሥራችን የሚፈስ የጋራ ደም፣ ባንድ ሕዝብነት የሚያስተሳስረን ጅማታችን፣ አጥር ቅጥር ሆኖ የሚጠብቀን የጋራ አጥንታችን ነው፡፡ ከዚህ የነፍስ ንግግር ወጣ ልበልና የጀመርኹትን ሐሳብ ማሠሪያ ላብጅለት፡፡

ከአቶ ልደቱ ንግግር የተረዳሁት ‹ብሔርተኛነት› ማለት ጐሠኛነት መሆኑን ነው፡፡ ይህ ከሆነ ኢትዮጵያዊነትን በጐሠኛነት እየከሰሰ ነው፡፡ ጉድ በል ሸዋ!!! አጀብ!!! የሚያሰኝ ነው፡፡ መከራችን ገና ማለቂ የለውም ማለት ነው፡፡ በየትኛውም አገር ቢሆን ብሔራዊ ማንነት እኮ መጠኑ ይለያይ እንጂ መሥዋዕትነት ተከፍሎበት የምንደርስበት፣ ነገድ/ጐሣ ዘለል የሆነ፣ የጋራ እምቅ ዕሴቶችን የያዘ ገለልተኛ የአንድ አገር ሕዝብ የጋራ ማንነት ነው፡፡ ዜግነታዊ ማንነት ነው፡፡ በተቃራኒው ኢትዮጵያዊነት ‹ብሔርተኛነት/ጐሠኛነት› ነው ካልን ዜግነት ጐሠኛነት መሆኑን እየገለጽን ነው፡፡ ታዲያ የዜግነት ፖለቲካ የምትሉ ፖለቲከኞችና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ምን ይሻላችኋል? የሠለጠነና ዘመናዊ ያላችሁት የዜግነት ፖለቲካ ወደ ድንጋይ ዘመን ከሚወስደን የጐሣ ፖለቲካ ጋር አንድ አካል አንድ አምሳል ነው ከተባለ እውነትም አቶ ልደቱ እንዳለው ሦስተኛና መሐል መንገድ የተባለው አማራጭ ሳያስፈልገን አይቀርም፡፡ በድጋሚ ጉድ በል ሸዋ!!!

ስላቁን ወደ ጎን አድርገን፣ ኢትዮጵያዊነት ባገር ድንበር የማይወሰን ዓለም አቀፋዊ ጠባይ ያለው ሐሳብ ወይም ፍልስምና አይደለም ወይ? አንድ ታላቅ አገራዊ ዕሴት ብቻ መዝዘን ለመናገር፤ የዓድዋ ድል – ፀረ-ፋሺስት÷ ፀረ-ቅኝ ግዛት ተጋድሎ – የኢትዮጵያዊነት መገለጫ አይደለም ወይ? አንድም ኢትዮጵያዊነት በጐሠኛነት ወይም በሌላ አፍራሽ ምክንያት የሚመጣ ልዩነት አልፎ ተሻግሮ የተለያዩትን ኹሉ አንድ የሚያደርግ የሚያዋሕድ የላቀ ዕሴት (transcendent value) አይደለም ወይ? አንድም ኢትዮጵያዊነት ተቋማዊ ቃል ነው፡፡ ራስን ትቶ ለአገር መኖር ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት እኮ እስልምናን ከመካከለኛው ምሥራቅ፤ ዘጠኙን ቅዱሳን ከሮም፤ እነ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስን ከምስር አምጥቶ ጥላ ከለላ የሆነ ምዕራፍ ነው፡፡ እስከ ጥግ ሔደን ከፍ ካደረግነው ምሥጢሩ ለሚገባው ኢትዮጵያዊነት ከብሔራዊና ዓለም አቀፋዊ ማንነት ልቆ ተሻግሮ ከእግዚአብሔር ቀጥሎ የሚነሣ ታላቅ ስም ነው፡፡ ይህ ምኞትና ግነት የሚመስለው ቢኖር አልፈርድበትም፡፡ ሆኖም በውስጥ ባንዳዎችና ቅጥረኞች፣ በውጭ በምዕራባውያን መንግሥታትና ዓለም አቀፍ ተቋሞቻቸው የማያቋርጥ የጥቃት ዒላማቸው የሆነበትን ምክንያት አንባቢው መርምሮ ይድረስበት፡፡

ኢትዮጵያን ለማስተዳደር ዕድሉን ያገኙ ቀደምት ኢትዮጵያውያን ነገሥታት ባብዛኛው አማኞች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያን ከሕዝባቸው ነጥለው አያዩም ነበር፡፡ አገሩን በማስከበር፣ ሕግና ሥርዓት በመጠበቅ ሕዝቡን ለሕግ መገዛትንና ተከባብሮ መኖርን ያስተማሩ ናቸው፡፡ ከውጭ የመጡት ቅዱሳንም ሕዝቡ ፈሪሃ እግዚአብሔር እንዲያድርበት በጎ ተጽእኖ አሳድረውበታል፡፡ ወደ ቅርቡም እነ አቡነ ጴጥሮስ ዘመን ስንመጣ የአገር ፍቅርን እና ጀግንነትን በተግባር አስተምረዋል፡፡ እነዚህና ሌሎች በጎ እርሾዎች ናቸው ዕብደትን ከድንቊርና አስተባብረው እና የባዕዳን ቅጥረኞች በመሆን ጭምር አገራችንን ለማፍረስ እየገዘገዟት ካሉ የጥፋት ኃይሎች እየተንገዳገደችም ቢሆን ያቆዩአት፡፡ በታሪካችን ውስጥ በተለይም በቀደመው ዘመን አገርን የገዙ ነገሥታት ጊዜውና ንቃተ ኅሊናቸው የፈቀደላቸውን ሠርተው፣ ባገር ግንባታው ሂደት የራሳቸው አሻራ አሳርፈው ኢትዮጵያን ከነ ሙሉ ክብሯና ኩራቷ አውርሰውናል፡፡ በዚህ ሂደት ልማትም ጥፋትም ይኖራል፡፡ ልንመዝናቸው ከፈለግንም በኖሩበት ዘመንና ሥርዓት መለኪያ እንጂ በ21ኛው መቶ ክ/ዘመን መሥፈርት ሊሆን አይችልም፡፡ የተሰበረውን መጠገን፣ የጎደለውን መሙላት፣ የጠመመውን ማቅናት የወራሹ ትውልድ ግዴታና ኃላፊነት ነው፡፡ መልካሙን ተከባክቦ ማቆየት፣ ክፉውን ማረም ማስተካከል አሁን ያለው ትውልድ ድርሻ ነው፡፡ የኋላውን፣ እንኳን በሐሰትና ፈጠራ ክስ ተነሥቶ ይቅርና እውነትንም መሠረት አድርጎ መውቀስና መክሰስ የትውልድን ክሽፈት የሚያሳይ ረብ የለሽ ነውረኛነት ነው፡፡

አዎ! የጐሣ ፖለቲካና ሥርዓት የኢትዮጵያ መሠረታዊ ችግር መሆኑ ጥያቄ ውስጥ አይገባም፡፡ ኢትዮጵያዊነት በሚለው ብሔራዊ ማንነት ውስጥ በታሪክ በተወሰኑ ነገዶች/ጐሣዎች ላይ በአገዛዞች መደባዊ በሆነ መልኩ ሆን ተብሎም ይሁን ባለማወቅ የተፈጸመ በደል ካለ መፍትሔው ማረምና ማስተካከል እንጂ ያለፈውን ጊዜና የጐሠኞቹን ስሑት ትርክት ጎትቶ አምጥቶ ኢትዮጵያዊነት ጐሠኛነት ወይም ‹ብሔርተኛነት› ነው ማለት ሥልጣን ላይ ያሉት ዘረኞች የዐምሐራውን ሕዝብ ለዘመናት ገዥ ሆኖ ሲበድል ኖሯል በማለት ከቀሪው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር ለማጣላት የፈጠሩትን የሐሰት ትርክት እና  ሕጋዊና መዋቅራዊ ጥቃት በመፈጸም ያደረሱትን የጅምላ ፍጅትና መፈናቀል ማፅደቅ ይሆናል፡፡ አንድም መድኃኒቱን በሽታ አድርጎ ከመቊጠር ልዩነት የለውም፡፡

ለማጠቃለል ጐሠኛነት/‹ብሔርተኛነት›/ መሠረቱ ጥላቻና መለያየት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የአብሮነት ጠንቅና ደዌ ነው፡፡ በመሆኑም በየትኛውም መለኪያ በጎ ገፅታ የለውም፤ ሊኖረውም አይችልም፡፡ የነገዶችን ወይም ጐሣዎችን መብቶችና ጥቅሞች ለማክበር የጐሣ ፖለቲካና የጐሠኛነት ሥርዓት አያስፈልግም፡፡ ይህ ቢሆንማ ለ32 ዓመታት እንደ ቤተሙከራ ‹አይጥ› የሆነችው አገራችን መድኃኒት ባገኘች ነበር፡፡ በተቃራኒው ጐሠኛነት በደዌ ላይ ደዌ ጨምሮባት የማይድን ነቀርሳ ነው የሆነባት፡፡ ባንፃሩም ኢትዮጵያዊነትን ከጐሠኛነት/‹ብሔርተኛነት›/ ጋር የሚያዛምደው አንዳች ነገር የለም፡፡ ኢትዮጵያዊነትን እንደ ሉዐላዊ ሐሳብና ፍልስምና ይዞ በሠለጠነ የዜግነት ፖለቲካ – በሕግ እና በመዋቅር (ተቋማት) – የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ እንዲሁም በነገድ/ጐሣ ማንነት የሚታወቁ ማኅበረሰቦችን መብትና ጥቅም (ባህል፣ ቋንቋ፣ እምነት፣ ራስን ማስተዳደር) ማስከበር ግን ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያዊነት የሚያመጣው የአገርና የሕዝብ አንድነት፣ የሚፈጥረው ማኅበረሰባዊ መስተጋብርና ኢኮኖሚያው ትስስር የኢትዮጵያ ነገዶችና ጐሣዎችን ብዝኀነት የሚያጠናክርና የሚያሟላ እንጂ ገሸሽ ያደርጋል የሚለው አመለካከት ጤናማ አይመስለኝም፡፡ ባጭሩ ኢትዮጵያዊነት የብዙ ነገዶችና ጐሣዎች አገር ለሆነችው ኢትዮጵያ በውስጥም በውጭም የነፃነትና የደኅንነት ዋስትና ከመሆኑም በተጨማሪ ለዘመናት ካፈራቸው ድልብ ዕሴቶቹ አኳያ የሁላችን መኩሪያና መከበሪያ ልዕልና ያለው አስተሳሰብ ነው፡፡

Filed in: Amharic