>

ኢትዮጵያዊነት/አምሐራዊነት እንደ ‹ማርያም ጠላት› (ከይኄይስ እውነቱ)

ኢትዮጵያዊነት/አምሐራዊነት እንደ ‹ማርያም ጠላት›

ከይኄይስ እውነቱ


ብዙዎቻችን ስለ አገር ጉዳይ ተጨንቀን ተጠብበን በገባን/በተረዳንው መጠን የምንጽፈው፣ የምንናገረው  የኢትዮጵያን መንበረ ሥልጣን የተቆጣጠሩት ዘረኛ ደናቊርት ወይም አጽራረ ኢትዮጵያውያን ያዳምጡናል ብለን አይደለም፡፡ እነዚህ ‹‹ኢሕአዴግ›› የተባሉ የአጋንንት ስብስብ የሚገባቸው ቋንቋ በሠለጠነ መንገድ መነጋገር፣ መወያየት፣ መከራከር፣ ማምን/ማሳመን፣ በሃሳብ ልዕልና መመራት አይደለም፡፡ ይሄ ከተፈጥሮ ባሕርያቸው ውጭ ነው፡፡ ይልቁንም ባንድ ወገን የኢትዮጵያ አገራዊ ህልውና፣ የሕዝቧ ደኅንነት (አሁን ያለውና የመጪው ትውልድ እጣ ፈንታ ÷ ዕድል ተርታ) የሚያሳስባቸው በርካታ ወገኖች በመኖራቸው፣ በሌላ ወገን ቊጥራቸው ቀላል የማይባል ወገኖች ደግሞ የጐሣ አገዛዙ የወንጀለኞች ሥርዓት በተቆጣጠረው የሕዝብ መገናኛ ብዙኃን ዕለት ዕለት የሚነዛው መርዛማና የቅጥፈት ፕሮፓጋንዳ ሰለባ በመሆን እና መሬት ላይ ያለውን እውነታ የሚያሳውቅ በቂ የዜናም ሆነ የሃሳብ ማሰራጫ አውታሮች በሌሉበት አማራጭ በማጣት መንገዳቸውን የሳቱ በመኖራቸው፤ እውነታውን ለማሳየት፣ የጎደለውን ለመሙላት፣ የተጣመመውን ለማቅናት፣ ጥቂትም ቢሆን የራስን ድርሻ ከመወጣት አንፃር ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ 

ዛሬ ኢትዮጵያዊነት/አምሐራዊነት ከመቼውም ጊዜ በከፋ እንደ ‹ማርያም ጠላት› እየታየ ነው፡፡ እንደሚታወቀው አብዛኛው አምሐራ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ በመሆኑ ለጌታ እናት ለወላዲተ አምላክ ያለው ፍቅርና ክብር የተለየ ነው፡፡ ቦታው ባይሆንም ፀረ-ማርያሞቹን የሚያውቃቸው ያውቃቸዋል፡፡ ስለሆነም በዚህ ጽሑፍ ዐውድ የ‹ማርያም ጠላት› የሚለው ሐረግ ለኢትዮጵያዊነት/አምሐራዊነት ጥልቅ ጥላቻ ያላቸውን ጉዶች ለመግለጽ የተጠቀምንበት አባባል ነው፡፡ የሚገርመውና ታሪካዊው ተቃርኖ የአምሐራው ሕዝብ የደርግን ግፍ፣ ጭቆናና ምሬት አንገፍግፎት እምቢኝ በማለት ወያኔ ሕወሐትን ለሥልጣን ለማብቃት ትልቅ ሚና የነበረው ሲሆን፤ ወያኔን በማስወገድ በተካሄደው ሕዝባዊው ዓመፃ ታላቅ መሥዋዕትነት ከመክፈል ጀምሮ የወያኔ ወራሽ ተረኛ የሆነውን ኦሕዴድ በቀይ ምንጣፍ ተቀብሎ፣ ኢትዮጵያዊ የበግ ለምድ ለብሶ የተገለጠውን የተረኞቹን አለቃ ኦነጋዊ ጭራቅ ሕይወት እስከመታደግ ደርሶ የታመነ ሕዝብ ነው፡፡ ወርቅ ላበደረ ጠጠር እንዲሉ፡፡

ኢትዮጵያዊነትን/አምሐራዊነትን በተለዋዋጭነት የተጠቀምሁት ሆን ብዬ ነው፡፡ አንድም እውነት ስለሆነ፤ በሌላ ረገድ ባለፉት ሠላሳ ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ ላይ ከሠለጠኑት የወንጀል ሥርዓቶችና አድርባይ አሸርጋጆቻቸው አስተሳሰብ የሚለይ መሆኑንም ለማሳየት በመፈለግ ነው፡፡

ይህ ጥቅል አነጋገር በተሳሳተ መልኩ ግንዛቤ እንዳያገኝ ማብራራት አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ኢሕአዴግ የተባለው ቀድሞ በወያኔ/ሕወሐት አሁን ደግሞ በወራሹ ኦሕዴድ/ኦነግ የበላይነት የሚመራው የጐሠኞች አገዛዝ ለአገዛዛቸው ግምባር ቀደም ተቀናቃኝ፤ በኢትዮጵያ ምድር ለሚታዩ የፖለቲካ፣ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ችግሮች፣ በደሎችና ጭቆናዎች ሁሉ ተጠያቂ ፤ በፈጠራ/ሐሰት ትርክት በሌሎች የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች እንደ ‹ማርያም ጠላት› እንዲታይና በደንጊያ እንዲወገር  የፈረዱበት ሕዝብ ነው – አምሐራ፡፡ 

ጐሠኞቹ ወያኔና ኦነግ መንደርተኝነት መሠረቱ ለሆነው የጐሣ አገዛዝ ድጋፍ ይሆነኛል ያሉትን የጫካ ሕግ ወይም ‹የደደቢት ሰነድ› በኢትዮጵያ ላይ ሲጭኑ፣ በግልጽም በአንደምታም ያመለከቱት ኢትዮጵያ የምትባል ጥንታዊትና ታሪካዊት አገር እንዳልነበረች፣ የሀገረ-መንግሥትነት ታሪክ እንደሌላት፣ ተሠርታ ያደረች አገር እንዳልሆነች፣ ሕዝቧም የጋራ ታሪክ÷ ቅርስ፣ እሤት፣ ሥነ-ልቦና፣ ባጠቃላይ እንደ አንድ ሕዝብ የሚያስተሳስረው ኢትዮጵያዊ ‹እትብት› (common denominator) እንደሌለው ቆጥረው፤  አገርን በመበታተን ዓላማ እነሱ ‹ክልል› ብለው በፈጠሩትና ማባሪያ በሌለው ሁናቴ እየተፈጠረ ባለው የመንደርተኛነት መዋቅር ውስጥ የሚገኙ ጐሣዎች ‹ብሔር፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች› ስምምነት እንደ አዲስ የተበጀች ‹አገር› አድርገው በድቡሽትና ክህደት ላይ የተመሠረተ/የሚመሠረት ‹አዲስ አገር› ለመፍጠር ነው ፍላጎታቸው፡፡ በዚህ ‹አዲስ አገር› ውስጥ አምሐራ ድርሻ የሌለው፣ እነሱ እንደ ከብት ጋጣ በወሰኑለት/በፈጠሩለት ‹ክልል› ውስጥ ብቻ የሚኖር፣ በዛም ውስጥ ምንም መብት የሌለው፣ ከወሰኑለት ‹ጋጣ› ውጭ ከተገኘ እንዲገደል÷ እንዲሳደድና እንዲቅበዘበዝ የተፈረደበት ከ‹ጐሣም› በታች የሚታይ ፍጡር ነው፡፡ የዚህም የጥፋት ተልእኮ አስፈጻሚ ከኃያ ሰባት ዓመታት በፊትም ሆነ ዛሬ ሲጠሩት አቤት ሲልኩት ወዴት የሚለው ዘላለማዊ አሽከር ብአዴን ነው፡፡ መቼም የነውረኞች እጦት የለብንምና ነውረኞቹን አንዳርጋቸውን፣ ታምራትን፣ በረከትን፣ ተፈራን፣ አዲሱን፣ ደመቀን፣ ተመስገንን፣ አገኘሁን፣ ገዱን፣ በየትኛውም ደረጃ ዛሬም ቀደሞም ያሉ ‹አመራሮች› ወያኔ አማራን ለማጥፋት ‹በቤተሙከራ› የሠራቸው ‹መርዞች› ናቸው፡፡  

በሌላ በኩል በእኔ አመለካከት አምሐራ የሚባለው ሕዝብ ከጐሣ ሆነም ከነገድ በላይ ነው፡፡ አምሐራ የምለው በሁሉም የኢትዮጵያ ግዛት በወርድና በቁመቷ ተንሰራፍቶ የሚኖረውን ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት አምሐራን ኢትዮጵያዊነት ከሚለው ብሔራዊ ማንነት ጋር  ተመሳሳይ አድርጌ ነው የምወስደው፡፡ ምክንያቱም አምሐራ የሚባለው ሕዝብ በታሪክ አጋጣሚ ከሁሉም የኢትዮጵያ ነገዶችና ጐሣዎች ጋር ተውሕዶ በኢትዮጵያዊነት ውስጥ ቀልጦ ትግሬም፣ ጉራጌም፣ ወላይታም፣ ሶማሌም፣ አፋርም፣ አደሬም፣ ሲዳማም፣ ኦሮሞም፣ ጋሞም፣ ከምባታም፣ ሀዲያም፣ ሽናሻም፣ ጉምዝም፣ በርታም፣ ኮንሶም፣ ሐመርም፣ ሰማንያዎቹንም ሆኗል፡፡ በዚህም ከጐሠና ነገድ በላይ የሆነ ብሔራዊ ማንነት (ኢትዮጵያዊነት) እንዲፈጠር ምክንያት የሆነ ሕዝብ ነው፡፡ የራሱን ማንነት ለጠቅላላው ጥቅም የሠዋ ታላቅ ሕዝብ ነው፡፡ ይህ አገራዊ ውለታው ተዘንግቶ ነው ዛሬ ማንም ወራዳ ያልታረመ አፉን የሚከፍትበት፡፡

በበታችነት ሕማም የሚሰቃዩት ጐሠኞች ምኞት ግን ከዚህ ኢትዮጵያዊነት ማማ ወርዶ እንደነሱ በመንደርተኝነት እንዲርመጠመጥ ነው፡፡ ነፍሳቸውን ይማርና እነ ፕሮፌሰር መሥፍን ወልደ ማርያምና ሃሳባቸውን የሚጋሩ ወገኖች ‹አምሐራ የለም› የሚለውን አገላለጽ የሚረዱት አምሐራዊ ማንነት ያለው ሕዝብ የለም በሚል አድርባዮቹ እነ ብርሃኑ ነጋና አንዳርጋቸው በሚናገሩበት የፍርሀትና ቢደራጅ የሥልጣን ፍርፋሪውን ያስቀርብናል በሚል የማይበገር ተቀናቃኝነት ስሜት ሳይሆን ወዶና ፈቅዶ ራሱን ኢትዮጵያዊ አድርጓል በሚለው መንፈስ ነው፡፡ የራሱን ሰጥቶ የሌሎች ወገኖቹን ባህል ማንነት የራሱ አድርጎ የተቀበለ ሕዝብ ሆኗል ለማለት እንደሆነ እረዳለሁ፡፡ በዚህም ከሌሎች ወገኖቼ የበላይ ነኝ ብሎ የማይኮፈስ፣ በንግሥናውም ሆነ በሀብት ክፍፍሉ እኔ ልቅደም የማይል፣ የዚህ ጐሣ ወይም ነገድ ነኝ ብሎ የአድልዎ ሥነ ልቡና የሌለው፣ ዳኝነትና አስተዳደር የሚያውቅ፣ ለጋስነት ገንዘቡ የሆነ፣ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለው በመሆኑ ለጋራ ጥቅም ከመሰለው ‹ሞኝ› እስኪያስብለው ሌሎች ወገኖቹን ለማመን ዝግጁ የሆነ፣ በአገርና በወገን ላይ ለሚደርስ ጥቃት ደረቱን ለጦር ግንባሩን ለጠጠር ለመስጠት ዝግጁ የሆነ፣ እነዚህኑ እሤቶች በሌሎቹ አጋብቶ፣ እርሱም መልካሙን እሤቶች ከሌሎቹ ወገኖቹ ወርሶና ወስዶ፣ በእኩልነት ታይቶ፣ በጋራ ለማደግና ለመልማት የሚፈልግ፣ የግዛት አንድነቷና ሉዐላዊነቷ የተከበረ ኢትዮጵያ የምትባል ጥንትም የነበረች፣ አሁንም ያለች ወደፊትም የምትኖር አገር የጋራ ባለቤት ነው፡፡ 

ይህ ሕዝብ ነው ባለፉት 32 ዓመታት በወያኔ ሕወሐትና በወራሹ የኦሕዴድ/ኦነግ የወንጀል ሥርዓቶች ከኢትዮጵያዊነቱ ዝቅ የሚያደርግ አዲስ ማንነት ተፈጥሮለት፣ ከዚህ መለስ የሚል አጥር ታጥሮለት፣ ኢትዮጵያዊ ነኝ በማለቱ እንዲሁም አብዛኛው በሚከተለው የርትዕት (ኦርቶዶክስ) ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይነቱ ምክንያት በተጠናና በአገዛዙ መርነት በጅምላ እየተጨፈጨፈ፣ በጅምላ እየተቀበረ፣ የዘር ማጥፋት/ማጽዳት እየተፈጸመበት፣ አገዛዝ ፈጠር በሆነና ሸፍጥ በተሞላበት ጦርነትም እየተማገደ፣ የጦር ወንጀል እየተፈጸመበት፣ ከቤት ንብረቱ በሚሊዮኖች እየተፈናቀለ፣ እየተሰደደ፣ የደሀ ደሀ ተደርጎ ለህልውና ጥፋት እየተዳረገ ያለው፡፡ 

እስከ መጨረሻው ጥግ የተገፋና የተበደለ ሕዝብ፣ በማንነቱና በእምነቱ እየተሳደደ እንዲጠፋ የተፈረደበት ሕዝብ በማናቸውም መንገድ ህልውናውን ማስከበር ቅድሚያ ተግባሩ ሊሆን ይገባል፡፡ ይህንንም ለመፈጸም ተደራጅቶ አንድ ሊሆን ያስፈልጋል፡፡ ድርጅቱ ግን የፖለቲካ ማኅበር መሆን የለበትም፡፡ ይህ በጐሠኞቹ ወጥመድ ውስጥ መግባት ነው፡፡ በአንዳንዶች ዘንድ እሾኽን በእሾኽ ነው በማለት የስንፍና ንግግር ይሰማል፡፡ መነሻውም መድረሻውም ጥፋት በሆነ የጐሣ የፖለቲካ አደረጃጀት የሕዝብን ህልውና መታደግም ሆነ የኢትዮጵያን ህልውናና አንድነት ማስከበር አይቻልም፡፡ የአምሐራን ሕዝብም ሆነ የኢትዮጵያን ህልውና በጐሠኛነት መንፈስ መታደግ አይቻልም፡፡ እዚህ ላይ ብርቱ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ አገራችን ስትኖር እኛም እንኖራለን፣ አገራችን ህልውናዋ ተጠብቆ እንዲኖር ደግሞ የአምሐራው ሕዝብ አጥፊዎቹ ሰፍረው ቈጥረው በሰጡት ግዛት ሳይወሰን ‹በአምሐራዊነቱ› ህልውናውን ማስከበር የነገ ተግባር አይደለም፡፡ ርእሰ መጻሕፍቱ ‹የድኅነት ቀን› ዛሬ ነው እንዲል፡፡  

በታሪክ ቀዳሚውን ሚና በመያዝ ብሔራዊ ማንነትን ቅርፅ ያስያዘው የአምሐራ ሕዝብ  በዜግነት ፖለቲካ ሽፋን ጐሠኞች ሥር እንደሚርመጠመጠው ኢዜማ ወይም ለፍርፋሪ ጭራውን በመቁላት በጐሠኛነት መንፈስ ሳይወለድ እንደጨነገፈው የብአዴን ታናሽ ወንድም ‹አብን› ያልሆነውን ለመሆን መሞከር የለበትም፡፡ አሁን ቀዳሚው አጀንዳ ምን ዓይነት ሥርዓት ያስፈልገናል የሚለው አይደለም፡፡ የራሱንም ሆነ የኢትዮጵያን ህልውና ለማጥፋት ሌት ተቀን የሚሠሩ ‹ክፉ ሠራተኞችን› የኢሕአዴግ መንጋዎችን ማጥፋት ነው፡፡ የቅድሚያ ቅድሚያ ግን ብአዴን የሚባለውን የሙታን ስብስብ ከ‹መቃብር ጠባቂነት› አንሥቶ መቃብር ውስጥ ለመክተት ያልተዘጋጀ የአምሐራ ሕዝብ ትግል ፍጻሜው አያምርም፡፡ በግፈኞች የፈሰሰውን የሕፃናቱን፣ የእናቶቻችንን፣ የአረጋውያኑን ደም እና አሁንም እየተከፈለ ያለው መሥዋዕትነት ከንቱ እንዳይሆን የምንሻ ከሆነ አምሐራዊነትን ከኢትዮጵያዊነት ጋር አንድ አካል አንድ አምሳል አድርጎ መንቀሳቀስ የግድ ይሆናል፡፡ የዚያን ጊዜ በየክፍላተ ሀገሩ በጐሠኛነት አመድ የተዳፈነውን ፍሕም እንዲያመርት እንዲያጎመራ ማድረግ ይቻላል፡፡ 

የወየኔ ወራሽ የሆነው የተረኞቹ ጐሠኞች አገዛዝ ሥልጣን በያዘ ማግስት የኢትዮጵያን ሕዝብ ለማነሁለል አስቦም ቢሆን ኢትዮጵያዊነትን በልቡ ክዶ በአፍኣ/በቃል ከፍ ለማድረግ ሲሞክር የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ከጐሠኞቹ በስተቀር በአብዛኛው ኢትዮጵያ መንፈስ ካገር ቤት እስከ ውጩ ዓለም ምን ያህል እንደናኘ አሁን ያለው ትውልድ ሁሉ ምስክር ነው፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያዊነት ለጊዜው የተዳፈነ ፍሕም እንጂ አመድ አይደለም፡፡ እንደ ቅዱስ መስቀሉ ጠላቶች ተራራ እስኪመስል የዘረኛነት ቆሻሻ ክምር ተከምሮበታል፡፡ አመድ ለማድረግ የሚሠሩትን አጽራረ ኢትዮጵያውያን አስቀድሞ አመድ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም አምሐራዊነት በብሶት በሚፈጠር የጐሠኛነት ስሜት ሳይሆን በጥንተ ተፈጥሮው በአምሐራዊነት/ኢትዮጵያዊነት ጸንቶ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ ያኔ ሰማዩም ከእኛ ጋር ይሆናል፡፡

አምላከ ኢትዮጵያ ሳንበድላቸው የበደሉንን፣ ሳንጣላቸው የተጣሉንን የማይመለሱ አጽራረ ኢትዮጵያን አጥፍተህ፣ ሥልጣንህን ገልጸህ ግፉዐንን ለመርዳት ተነሣ፡፡ ክፉ ሊያመጡብን የሚመክሩት ሁሉ አድጎ አነስ አድሮ አነስ ይሁኑ፡፡ ሀገረ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ለማጥፋት የሚሹ ሁሉ ይፈሩ ይዋረዱ፡፡ በዓይነ ምሕረትሕ ጎብኝተህ ትድግናህን እንድታቀርብልን ለእመ አምላክ በገባህላት ቃል ኪዳን እንማፀንሐለን፡፡

Filed in: Amharic