>
5:21 pm - Tuesday July 21, 7361

ምርኮኞች ህዝብን ነፃ አያወጡትም! (ቬሮኒካ መላኩ)

የጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን የነፃነት ትግል መሪ ኔልሴን ማንዴላ በእስር ቤት በነበረበት ሰአት ነጭ አሳሪዎቹ እስርቤት በስብሰህ ከምትሞት ያቀረብንልህን offer ተቀበል ባሉት ጊዜ “Only free man can negotiate; prisoners cannot enter into contracts ” ብሏቸው ነበር።

የአማራ ህዝብ ታሪክ ሰሪ ነው። ከአምስት ሺህ ዘመናት በላይ በቆየው የነፍጠኞች ታሪክ ውስጥ ፈሪዎች እና የጦር ምርኮኞች ህዝብን መርተው፣ ታግለው እና አታግለው ፣ ለድል አብቅተው አያውቁም። የኢትዮጵያ ህዝብ የነፃነት ታሪክ የተፃፈው በነፍጠኞቹ በላይ ዘለቀ፣ አሞራው ውብነህ ተሰማ፣ ሀይለማሪያም ማሞ፣ አበበ አረጋይ ፣ ገረሱ ዱኪ እና መሰል አርበኞች እንጂ ሀገር ጥለው በሸሹ ፈሪዎች ወይም ጠላት ጋር በተባበሩ የእንቁላል ሻጭ የባንዳ ልጆች እና አስካሪሶች አይደለም።
ምርኮኞቹ ብአዴን እና ኦህዴድ አፈግፍገዋል። ብአዴን እና ኦህዴድን ህዝቡ ከህውሐት ምርኮ ነፃ ሊያወጣቸው እየሞከረ ቢሆንም እነሱ ግን አሁንም ህውሐትን እየተለማመጡ የሚኖሩ የምርኮኞች ክበብ መሆንን መርጠዋል። በብአዴን እና ኦህዴድ ውስጥ ያሉ ለውጥ ፈላጊዎችን ማበረታታት የስርዓቱን መሰረት ለማናጋት አንዱ ስትራቴጂ ሊሆን ቢችልም እነዚህን ሃይሎች የለውጡ መሪ ተዋናይ አድርጎ ማቅረብ ግን risky ነው። ህሊናቸውን ሽጠው ይህን ስርአት ሲያገለግሉ የኖሩ ግለሰቦች በቅፅበት የባህሪ ለውጥ አድርገዋል ብሎ ማሰብ መና ከሰማይ ይወርድልናል ብሎ ተስፋ ማድረግ ነው። በብአዴንም ይሁን ኦህዴድ ውስጥ ያሉት አብዛኛዎቹ አመራሮች የትግራይን የበላይነት ለማስቀጠል በህውሐት ተቀጥረው የሚሰሩ ቅጥር ነፍሰ ገዳይ መሆናቸው መዘንጋት የለበትም። በአማራ እና ኦሮሚያ አካባቢ የህዝቡ ቁጣና አመፅ አሁን ካለበት ሁኔታ በባሰ መልኩ ገንፍሎ እንዳይወጣ ከህዝቡ ጎን የቆሙ በመምሰል የማረጋጋት ስራ እየሰሩ ያሉት እነዚህ ብአዴን እና ኦህዴድ የተባሉ ተለጣፊ ድርጅቶች ናቸው። ገዱም ሆነ ለማ በተለሳለሰ አንደበት ህዝቡ መስማት የሚፈልገውን ነገር እየተናገሩ የማረጋጋት ስራ ከመስራት የዘለለ በተጨባጭ ያስመዘገቡት ውጤት የለም። በህውሐት ኢህአዲግ ውስጥ ያለውን የርስበርስ ሽኩቻ እና ልዩነት ማስፋት ጠቃሚ ነው። የነ ለማ እና ገዱ(በጣም ፈሪ ሰው ነው) ቡድን የትግሉ ግብአት ሊሆኑ ይችሉ ይሆን እንጂ የትግሉ መሪ ተዋናይ አይደሉም።
ምርኮኞች ህዝብን ነፃ ሊያወጡ አይችሉም። ህዝቡ ግን ምርኮኞችንም ጭምር ነፃ ያወጣቸዋል
Filed in: Amharic