ከይኄይስ እውነቱ
በተጠቀሰው ርእሰ ጉዳይ ለመጻፍ ካሰብሁ ቆይቼአለሁ፡፡ ይሁን እንጂ ርእሱ ለአንዳንዶች ካሰብሁት ውጭ ትርጕም እንዳይሰጠው በመሥጋት አዘግይቼዋለሁ፡፡ በሌላ አነጋገር ለጥንቃቄ ስል በራሴ ላይ ማዕቀብ ጥዬ ነበር፡፡ እንደ መፍትሔ የወሰድሁት ቃሉን እኔ ላሰብኹትና ለምፈልገው ዓላማ ብይን በመስጠት መጀመርን ነው፡፡
በዚህም መሠረት ‹‹ባላገር›› የሚለው ቃል አዎንታዊም አሉታዊም ትርጕም አለው፡፡ በምናውቀው አዎንታዊ ትርጕም ባላገር ወይም በግእዙ በዓለ ሀገር ማለት የአገር ባለቤት፣ ባለ ምድር፣ ባለርስትነት፣ ባገር ቤት የሚኖር ሰው፣ አገሬ፣ ያገር ተወላጅ፣ አገር ቤት ማለት ነው፡፡
ባንፃሩም በአሉታዊ ትርጕሙ ባላገር ማለት ዐላዋቂ (ባላገር እንዲህ ይላል እንደሚባለው)፣ ያልሠለጠነ፣ ቅልጥፍና የሌለው፣ ገጠሬ (ዐዲስ፤ ያማርኛ መዝገበ ቃላት፤ አለቃ ደስታ ተክለ ወልድ)ማለት ሲሆን፤ ባንፃሩም ያገሬ የወንዜ ብሎ ዘር ቆጠራ የሚገባ፣ የወንዙ የአካባቢው ተወላጅ ከሆነ ማሰብ ማስተዋል የሚያቆም በጭፍን የሚቀበል÷ በመንደሩ በቀዬው በቀበሌው ልክ የሚያስብ፤ ሥልጣኔ ለቀመሰ ወይም ከተሜ ነው ብሎ ለሚያስበውሰው አስቀድሞ የተሳሳተ ፍርድ የሚሰጥ ወይም የተንሸዋረረ አመለካከት ያለው፤ ‹የጳውሎስ› ‹የኬፋ› ነኝ እያለ ክፍፍል በመፍጠር የአንድነት የኅብረት ፀር የሆነ ተብሎም ይወሰዳል፡፡ ይህ ብያኔ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የሚኖር፣ ፊደል የቆጠረ ይሁን ማይም፣ ዶክትሬት የሚል ሦስተኛ የአካዳሚ ዲግሪ ያዘ ወይም ፕሮፌሰር በሚል ማዕርግ ተጠራ፣ ገጠር ኖረ ከተማ፣ በመደበኛም ሆነ ኢ-መደበኛ ሚዲያ የተሰማራ ይሁን በማናቸውም የሙያ መስክ የሚገኝ ሆኖ አስተሳሰቡን የተሸከመውን በሙሉ ይመለከታል፡፡
በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ‹‹ባላገር›› የሚለውን ቃል በዃለኛው አሉታዊ ትርጕሙ መጠቀሜን አንባብያንን ለማሳሰብ እወዳለሁ፡፡በዚህም መሠረት የ‹‹ባላገር ፖለቲካ›› የሚለውን ቃል የተጠቀምኹት ወያኔ ሕወሓት ከተከለው የዘረኝነት ሥርዓት ጀምሮ ላለፉት 40 ዓመታት ገደማ ያለውን እና በተወራጁ ርጉም ዐቢይ እስካሁንም በኢትዮጵያ ላይ የሠለጠነውን የድንቊርና አገዛዝ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ዃላ ቀር ‹ፖለቲካ› ፖለቲካ የሚባል ከሆነ መሠረት የሚያደርገውና ከዋና መገለጫ ገጽታዎቹ መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፤
1/ ‹‹የጐሣ ብሔርተኝነት››፤ ቢገባውም/ባይገባውም የነገድ/የጐሣ ‹ብሔርተኝነትን› እንደ መሪ ርእዮተ ዓለም አድርጎ መቀበል፤በተግባር ግን የርእዮተ ዓለም አመራር አክትሞ የፖለቲካ ፓርቲ የሚባሉት የፖሊሲ መሠረት ያላቸውን መድረኮች እርግፍ አድርጎ በመተው የጐሣ ማንነትን በመከላከል ላይ መጠመድ፤
2/ የዜሮ ድምር አስተሳሰብ፤ አንደኛው የጐሣ ቡድን የሚያገኘው የፖለቲካ የበላይነት/ጥቅም በሌላው የህልውና አደጋ እና የማይቀር ውድቀት ላይ የተመሠረተ መሆን፤
3/ ‹‹እኛ እና እነሱ›› የሚል ክፍፍል፤ ኅብረተሰቡን ነባርና መጤ በሚል ግልጽ የተቃርኖ መስመር በመክፈል ‹‹እኛ›› እና ‹‹እነሱ›› የሚል ክፍፍል መፍጠር፤
4/ የሀብት እጥረትን ለበላይነት መሣሪያ አድርጎ መጠቀም፤‹የጐሣ ልሂቃን› ነን የሚሉት እንደ መሬት፣ የመንግሥት ሥራ እና የመንግሥት ገንዘብ ያሉትን ውሱን ሀብቶች ላይ ውድድር መፍጠርን መሣሪያ አድርጎ መጠቀም፤
5/ የፈጠራ ትርክቶችና ታሪካዊ ቊርሾዎችን መሣሪያ ማድረግ፤ በፈጠራ ትርክቶችም ሆነ በታሪክ ተፈጽመዋል ተብለው የሚነገሩኢፍትሐዊ ሁነቶችን እና ጠባሳዎችን በመቀስቀስና እነዚህን በመጠቀም ዐዳዲስ ቅሬታዎችን በማቀጣጠል ታሪካዊ ቊርሾዎችን መሣሪያ ማድረግ፤
6/ ‹‹የበላይ ጠባቂነት/የጡት አባትነት›› ሥርዓት መንገሥ፤የመንግሥት ሀብት፣ ሥራዎች እና ከፍተኛ ገንዘብ የሚያወጡ የፕሮጀክቶች ውሎችን በችሎታ ሳይሆን በጐሣ ታማኝነት የሚፈጸምበት ‹‹የበላይ ጠባቂነት›/‹የጡት አባትነት› ሥርዓትመኖር፤
7/ ቊልፍ የመንግሥት ተቋማትን መቆጣጠር፤ እንደ ዳኝነት፣ ጦር ሠራዊት፣ ፖሊስ ያሉ ቊልፍ የመንግሥት ተቋማትን የበላይነት ባገኘው የጐሣ ቡድን መቆጣጠር፤
8/ የሕግ የበላይነት አለመኖር፤ ሕጎችን በአድልዎ ተፈጻሚ ማድረግ – አጋር የተባሉትን መጠበቂያ፤ የፖለቲካ ተቀናቃኝ የሆኑትን ማሳደጃ በማድረግ የሕግ የበላይነትን መሸርሸር፤
9/ ብሔራዊ የዜግነት ማንነትን ማዳከም/ማጥፋት፤ ብሔራዊ ዜግነትን ለጐሣ ማንነት እንዲገዛ በማድረግ ብሔራው ምልክቶችን ትርጕም በማሳጣት ብሔራዊ የሲቪክ ማንነትን ማዳከም፤
10/ የጥላቻ ንግግር እና ሰብእናን ማዋረድ፤ ብዙኃን መገናኛዎች እና የፖለቲካ ቅስቀሳዎች ኃይልንና ዓመፃን በሚጋብዙ የጥላቻ እና ሰብእናን በሚያዋርዱ ንግግሮች መሞላት፤
11/ ፍርሃትን መንዛት፤ መሪዎች የምርጫ መሠረት የሆናቸው ማኅበረሰብ እና አካባቢ ህልውና ከሌሎች ቡድኖች በማያቋርጥ ሥጋት ውስጥ መሆኑን በማሳመን ሆን ብለው የተጋነነ፣ አሳሳች ወይም የሐሰት ፍርሃትን መንዛት፤
12/ ፀረ-ምሁርነት፤ አመክንዮአዊ የሆኑ ሕዝባዊ ክርክሮች በደም በሥጋ ቋጠሮ እና በነገድ ጥራት ላይ በተመሠረተ ስሜትን በሚነኩ ንግግሮች እንዲተኩ በማድረግ ፀረ-ምሁርነትን ማራመድ፤
13/ የኃይል ቅስቀሳዎች፤ ለማስመሰል የሚደረጉ የምርጫ ድራማዎች በመጡ ቊጥር የጐሣ ልሂቃኑ ኢ-መደበኛ የሆኑ ሚሊሻዎችን፣ ወጣት ወሮበሎችን (እንደ ጀዋርና ሽመልስ ‹ቄሮ› ዓይነት) ወይም የአገዛዝ ጸጥታ ሠራተኞችን በማሰማራት ተቀናቃኝ ቡድኖች ካሉ በማስፈራራትና ድብደባም በመፈጸም የኃይል ቅስቀሳዎችን ማድረግ፤
14/ በገዢው ቡድን ውስጥ የሚኖሩ የልዩነት ሐሳቦችን/አቋሞችን ማፈን፤ በዛው በገዢው የጐሣ ቡድን ውስጥ ለዘብተኛ ድምፆች ካሉ ጸጥ ማድረግ፣ በከሃዲነት መፈረጅ ወይም በማግለል የማስገደድ ተግባራትን መፈጸም፤
15/ የሀብት ክፍፍል፤ የሀብት ክፍፍልን በሚመለከት የዘመድ አዝማድ/ወገንተኝነት እና በጐሣ የጡት አባትነት/የበላይ ጠባቂነት የሚመራ አሠራር መሠልጠን፤
16/ የግጭት አፈታታ፤ የግጭት አፈታትን በሚመለከት በማስፈራራት፣ በኃይል እና መንግሥታዊ ጭፍለቃ/ማስገደድ የሚፈጸም አሠራር፤
17/ የፖለቲካ ፓርቲ አቋም፤ በጐሣ ማንነት የሚዘወር መሆን፤
18/ የሥልጣን መስተጋብር፤ ሥልጣንን አንድን ጐሣ እንወክላለን በሚሉ ጉልበተኞች ሙሉ በሙሉ መቆጣጠርና ሌላውን ማግለል፤ወዘተ…
ከፍ ብዬ በዝርዝር ያቀርብዃቸውን ‹የባላገር ፖለቲካ› መገለጫዎችን የተጠቀምሁት በዐምሐራ ፋኖ ለሚመራው የዐምሐራ ሕዝብ ህልውና ትግል ነቀርሳ ሆኖ ለርጉም ዐቢይ አገዛዝ ስላደረው ብአዴን የተባለ የጠላት ኃይል እና በዐምሐራ ፋኖ ውስጥ ከተራ አባልነት እስከ አመራርነት ተሰግስገው የሚገኙ ብአዴናዊ ግርፎች ትግሉ በጠንካራ ድርጅታዊ መዋቅር ታግዞ ለውጤት እንዳይበቃ ለሚፈጽሙት አፍራሽ ድርጊት ዐውድ ለመስጠት ነው፡፡
ብአዴን ስለሚባለው ጭንጋፍ ድርጅት ብዙ ተብሏል፡፡ ትንሹ እርሾ ብዙውን ሊጥ ያቦካል እንደሚባለው ሁሉ፣ ብአዴን ማለት መላ ‹ሊጡን› የሚያበላሽ መርዛማ እርሾ ነው፡፡ በፋኖ ትግል ውስጥ ብአዴናዊ እርሾ ኖሮ ትግሉ ይሠምራል ማለት እጅግ ከባድ ነው፡፡ ርጉም ዐቢይን መንቀል ቢቻል እንኳን የሚተከለው ሥርዓት ለአገርና ለሕዝብ የተሻለ ተስፋና ዕድል የሚሰጥ ስለመሆኑ ዋስትና የለም፡፡ ጦርነት ወይም ውጊያ መቻልና የአመራር ዕውቀት ለየቅል ናቸው፡፡ ርእዮተ ዓለሜ ‹‹የዐምሐራ ብሔርተኝነት›› (Amhara Nationalism) የሚል ድርጅት (ለስልት/ለስትራቴጂነ ነው የሚል ሰንካላ ምክንያት የሚሰጥ ቢኖርም እንኳን) ጤናማ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ ይህንን አቋም ማቄን ጨርቄን ሳይል እግሩን ለጠጠር ደረቱን ለጦር ለመስጠት የወጣው አብዛኛው የዐምሐራ ፋኖ ተቀብሎት ነው ለማለት ይከብደኛል፡፡ የነገዱን ህልውና አስከብሮ ኢትዮጵያ አገሩን በዓለት ላይ ለመመሥረት ዱር ቤቴ ማለቱ ይታወቃል፡፡ ታዲያ ለምን የአገሩን ስም ከመዳረሻው አወጣ? ይሄ የግለሰቦች ጉዳይ አይደለም፡፡ የዓላማ እና የእምነት ጉዳይ እንጂ፡፡ ዓላማና እምነት ደግሞ በቃልም በመጣፍም በተግባርም መገለጽ ይኖርበታል፡፡ ማንም ተነሥቶ ስለ ፋኖ ትግል አያገባህም/ያገባሀል የማለት መብት የለውም፡፡ ነገደ ዐምሐራ በተለይ፣ ኢትዮጵያዊ ባጠቃላይ ያገባዋል፡፡ ጦር ያነሣ ሁሉ እንደ ወያኔ ‹‹ሺሕ ዓመት የመንገሥ መብት›› አለኝ ማለት አይችልም፡፡ ግፍና በደል የደረሰበት ማኅበረሰብ የሚያደርገው ፍትሐዊ ትግልህልውናውን አስከብሮ እንደዚህ ዓይነቱን አመለካከት ለማስቀረት ካልሆነ መጨረሻው የፈላጭ ቆራጭነት/አምባገነንነት አዙሪት ውስጥ የሚዘፍቀን መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ በመሆኑም ጭንቀታችን እስካሁን ባሳለፍነው መንገድ ለመንቀል ብቻ ከሆነና በቀጣይ ስለምንተክለው ከመንቀሉ በላይ በእጅጉ ተጨንቀን ካላሰብንበት በሥልጣን አረቄ የሰከሩ ደናቊርት ‹‹የባላገር ፖለቲከኞች›› መጫወቻ ከመሆን አናመልጥም፡፡ ስለሆነም እነሱ ሁሉን ያውቃሉ እንተውላቸው የሚለውና ደጋግመን በሚዲያ የምንሰማው ንግግር አንድም በትጥቅ ትግሉ ጊዜያዊ አመራርነት ላይ ያሉትን ላለማስቀየም የሚደረግ ካልሆነ በቀር ትግሉን አይጠቅምም፡፡ በሕይወት ልምድ ከለዘቡም፣ ከእውነተኛ ሕዝባዊ ምሁራንም ምክርን መስማት በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ በዓለም ላይ የተካሂዱ ፍትሐዊ የትጥቅ ትግል ታሪኮች እንደሚያስተምሩን የተገፋው ሕዝብ ሁሉ ተነሥቶ ጦር ሜዳ አይውልም፡፡ እያንዳንዱ የተለያየ ድርሻ አለው፡፡ መጥፎ የሚሆነው በአብዛኛው ኢትዮጵያውያን በአገር ውስጥ ሆነ በውጭ በሚገኙ ዘንድ እንደምናስተውለው ተዘልለው አያገባኝም ብለው በሌሎች መሥዋዕትነት የተሻለ ሕይወት ለመምራት የሚያስቡ ወገኖች መኖራቸው ነው፡፡ ይሄ አደገኛ አመለካከት ነው፡፡ ምጣችንንም ያረዘመው ይሄ ክፉ የሐኬተኝነት አመለካከት ነው፡፡ ቢያንስ አገር ከሚያፈርሱና ሕዝብን ቁም ስቅል ከሚያሳዩ ጋር ባጠቃላይ ከክፉዎች ጋር አለመተባበር በራሱ በጎ አስተዋጽኦ ነው፡፡ ነግ በእኔ ብሎ ከተበደለው ወገኑ ጋር በአጋርነት የማይቆም ማኅበረሰብና ኅብረተሰብ አገዛዝን መንቀል ቢቻል እንኳን ነገን የተሻለ የማድረግ ራእይና ራእዩን በተግባር የመተርጐም ብቃትም ሆነ ዐቅም አይኖረውም፡፡ የትጥቅ ትግል በሕዝብ እምቢተኝነት መታገዝ ይኖርበታል፡፡ የእምቢተኝነት ትግል ደግሞ አገርን ከሚያፈርሱ ሕዝብን ከሚበድሉ ጋር አልተባበርም በማለት በትንሹ ከመታመን ይጀምራል፡፡ በትንሹ ያልታመነውን ለትልቅ ቁም ነገር ማን ያጨዋል?
አበው ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም እንዲሉ የወያኔ ሕውሓት አሽከር ሆኖ የዐምሐራን ሕዝብ ሲበድል የኖረውን ገዱ የተባለ ብአዴናዊ ጉድ ‹ኮራሁበት› የሚል ቃል ብዙዎች ከሚያከብሩት ሰው በሚዲያ መስማት በእጅጉ ያማል፡፡ አንዳንድ ጊዜ እንደነዚህ ዓይነት ‹አደገኛ› ምስክርነቶችን ከአደባባይ ይልቅ በግላችን ብናቆያቸው በተለይ ለተናጋሪው የሚጠቅም ይመስለኛል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያን ታርቋትና ታድጓት ርጉም ዐቢይ አለቃ የሆነበት የኦሕዴድ/ኦነግ አገዛዝ ቢነቀል፤ ወደፊት በሽግግር ፍትሕ የሚፈጸሙ ሥርዓቶች እንደተጠበቁሆነው፣ ኢትዮጵያ ላይ የጐሠኝነት አገዛዝ ተክለው አገር ያፈረሱናሕዝብ ላይ ሰቆቃ የፈጸሙ በጐሣ የተደራጁ የፖለቲካ ማኅበራት/ቡድኖች እና አመራር ግለሰቦች (ወያኔ ሕወሓት፣ ኦነግ/በተለያየ ስያሜ በጫካም ሆነ በከተማ ያለው/፣ ኦሕዴድ፣ ብአዴን፣ ደሕዴን፣ ሌሎችም ‹ኢሕአዴግ› በሚለው ማጭበርበሪያ ጥምረት ውስጥ የነበሩ ድርጅቶች በሙሉ፣ ‹ክልል› በተባለው የጐሣ አጥር ፖለቲካን በዘር አደራጅተው ወንጀል ሲፈጽሙ የነበሩ ድርጅቶች በሙሉ) እንደ ወንጀለኛ ድርጅት በጋራ፣ አመራሮቹ ደግሞ እንደ ግለሰብ በተናጥል በሕግ በሚወሰን ጊዜ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ሕይወት መታገድ እንዳለባቸው በጽኑ ከሚያምኑ ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ነኝ፡፡ ይህ ውሳኔ ተግባራዊ ቢሆን ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ ከሚሰጠው ዘርፈ ብዙ ጥቅም መካከል የግፍ አዙሪትንና የዘር ፖለቲካን ለመዝጋት ጥሩ ምሳሌነት ይኖረዋል፡፡ በሕግ ፊት እንዲጠየቁ በማድረግ ከ5 ዐሥርታት በላይ የዘለቀውን ተጠያቂነት ያለመኖር አደገኛ ባህል (culture of impunity) ለመዝጋት እና ለሚሊዮኖች ግፉአን ፍትሐዊ መዝጊያ ሆኖ በማገልገል ለዐዲስ ምዕራፍ ያዘጋጃል፡፡ የሚል እምነት አለኝ፡፡ በሌላም በኩል ወንጀለኛ ድርጅቶቹን በተለያየ ደረጃ ሲመሩ ለነበሩ ግለሰቦች ጥፍጣፊ ሕሊና ካለቸው የማሰላሰያና የንስሓ ጊዜ እንደሚሰጣቸው፣ አልፎ ተርፎም ዕድሜው ካለ የበደሉትን ኅብረተሰብ ለመካሥ በተራ ዜግነት ዕድል እንደሚሰጣቸው ይታመናል፡፡ ገዱና ሌሎችም በሀገር ውስጥና በውጭ ተደብቀው ያሉ ጓዶቹ፣ አሁንም ብአዴን በሚባለው ጭንጋፍ ውስጥ በተለያየ ደረጃ አመራር ሆነው ይህንን አንድ ሐሙስ የቀረው የርጉም ዐቢይ አገዛዝን በማገዝ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሰቆቃ የሚያራዝሙ ሕሊና ቢሶች ቀድሞ የወያኔ አሁን ደግሞ የኦሕዴድ/ኦነግ ጨንገር ሆነው ላለፉት 40 ዓመታት በዐምሐራው ነገድ ላይ ለተፈጸሙት ዘርፈ ብዙ የዘር ጭፍጨፋና ማጽዳት ወንጀሎች በግምባር ቀደም ተጠያቂነት የምንፈልጋቸው እንጂ ልናቆለጳጵሳቸው የትኛው የግብረ ገብና ሥነ ምግባር ሚዛን ይፈቅድልናል?
ዛሬ በምንገኝበት የዲጅታል ዘመን ‹የጋዜጠኝነት ሞያ› ማንም ደናቊርት እንደ አህያ ዦሮ የሚጎትተው ተራ ‹ንግድ› ሆኗል፡፡የዲጂታሉን ዓለም ከሚመሩ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ለሚጣልላቸው ርጥባን ራሳቸውን መሼጦ አድርገዋል፡፡ ከተራው ዱርዬ አንሥቶ ዓለምን ናቅሁ እስካለው መነኩሴ በዚህ ተግባር ተሰማርተዋል፡፡ በጣት ከሚቆጠሩ በቀር በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ (አገዛዙ ያሰማራቸውም) ሆኑ ንክኪ ያላቸው እና በግላቸው የሚንቀሳቀሱ፣ ማኅበራዊ ሚዲያውን የጩኸትና የግርግር መድረክ ያደረጉ የተለያየ የፖለቲካ ፍላጎትና አጀንዳ ያላቸው ግለሰቦች (በተለይም በውጩ ዓለም የሚገኙት ከጥቂቶች በስተቀር) የዐምሐራ ፋኖን ትግል በእጅጉ እየጎዱት ይገኛሉ፡፡ ከነዚህም ከፊሉ ጥንስሳቸው (‹ጌሾና ብቅላቸው›)‹ኢሕአዴጋዊ› ነው፡፡ የፋኖ ጊዜያዊ አመራር ነን የሚሉትም አንዳንድ ግለሰቦች አንድም ብአዴናዊ መሠረት ከመኖር÷ አንድምከብስለት ጉድለትና ከርካሽ ዝና ፍለጋ ሊሆን ይችላል በአመዛኙ እኔ ‹የጳውሎስ ነኝ› እኔ ‹የኬፋ ነኝ› በሚል ጥልና ክፍፍልን ለሚያራምዱ ማኅበራዊ ሚዲያዎች የተመቻቹ ሰላባዎች ሆነው ተገኝተዋል፡፡ የግለሰቦች ፈቃድ የሚፈጸምበት ገና በውጥን ያለና የጠራ ስምምነት የሌለበት ‹ድርጅት መሼጦ ሊኑን በሚችሉ ጥቂቶች የመጠለፍ አዝማሚያ ካለ ጭንጋፍ ከመሆን ያለፈ ዕጣ ፈንታ አይኖረውም፡፡
ቤተሰቤ ነው፣ ዘመዴ ነው፣ ጓደኛዬ ነው፣ ጎረቤቴ ነው፣ የወንዜ ልጅ ነው ቢያጠፋኝም እታገሠዋለሁ ወዘተ. የሚል ‹የባላገር ፖለቲካ› አጥፊ ነው፡፡ ቢያንስ ከአራቱ ክፍላተ ሀገር (ሺዋ፣ ወሎ፣ ጎዣም እና ጎንደር) ብአዴንን እንደ ድርጅት እና ታሕተ ሰብአ አመራሮቹን (በየደረጃው ያሉትን) እንደ ግለሰብ ማስወገድ ያልቻለ የዐምሐራ ፋኖ እንኳን ለመላ ኢትዮጵያ÷ ህልውናው በቋፋ ላለው የዐምሐራ ሕዝብ እንዴት ታዳጊ ይሆናል? እነዚህ የጭቃ ውስጥ እሾኾች ናቸው እኮ ሕዝባችንን ቁም ስቅል እያሳዩ ያሉት፡፡ የዐምሐራ ፋኖ አስቀድሞ የመቀመጫዬን እንዳለችው እንስሳ በቅድሚያ በወታደራዊውም ሆነ በፖለቲካው መስክ ራሱን በዓለት ላይ መመሥረት ይኖርበታል፡፡ በጥቂት አመራሮቹ ያልጠራ አቋም ተይዞ መዝለቅ አይቻልም፡፡ ርጉም ዓቢይንና አገዛዙን ለማስወገድ ከሚታገሉ ኢትዮጵያውያን ኃይሎች ጋር ካልሆነ ከጠላት ኃይሎች ጋር ‹አጋርነት› በጭራሽ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ከለየለት ጠላት ጋር እንዲህ ዓይነቱን ‹ውሽምነት› ለመመሥረት መሞከር ዓላማ እናግብ እንዳይሳካ የሚያግድ ራስን የማጥፋት ድርጊት (self-defeating exercise) ሆኖ ይታያል፡፡ ባልጸና እና ውንክርክር እያለ ባለ ‹ድርጅት› መሠረታዊ በሚባሉ የሕዝቡን ህልውና፣ የፋኖን ህልውናና አቋም በሚነኩ፣ በዓላማ፣ በአጋርነት ወዘተ. ጉዳዮች በጥቂት አመራሮችም ሆነ አመራሮቹ በሚቆጣጠሩአቸው ‹ቡድኖች› ቊልፍ ውሳኔ የሚሰጥበት ጊዜ ላይ አይደለንም፡፡ብአዴናዊ የአሽከርነት ልቦና ይዞ ድርጅትን በቅጡ መምራት አይቻልም፡፡ ለዘመናት ሰቆቃ ሲያደርሱ ከቆዩና በዚሁ ከቀጠሉ ጠላት ኃይሎች ጋር እንኳን መነጋገር ማሰቡም ትክክል አይደለም፡፡ ይህን ለማድረግ የሚዘጋጁ ሁሉ እንደ ወያኔ ‹ኢሕአዴግ› ባሉ የውሽት ጥምረቶች ውስጥ በ‹ገረድ ደንገጥርነት› ታማኝ ሎሌዎች ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩ (በንጽጽራዊ ዘይቤ) በአመዛኙ ‹ፖለቲካዊ የስቶኮልም ሲንድረም› በሚባለው የሥነ ልቡና ቀውስ ስለመያዛቸውና የዚህ ሕማም ሰለባ ስለመሆናቸው ከፍተኛ ጥርጣሬ ውስጥ ስለሚከት የዚህ ሕማም ሰለባ ሊሆኑ የሚችሉ ኃይሎች ራሳቸውን ሊፈትሹ ይገባል፡፡ ‹ስቶኮልም ሲንድረም› የሚባለው ጠቅለል ባለ አነጋገር አንድ ሰው ጉዳት ለሚያደርስበት ወይም ለሚበድለው አካል ወይም ለጠላቱ አሳቢነት፣ ፍቅርወይም አጋርነት ማሳየት የሚጀምርበት የሥነ ልቡና ሁኔታ ነው።
በፋኖ የሚመራው የዐምሐራ ሕዝብ ትግል ላለፉት 40 ዓመታትገደማ በኢትዮጵያ ላይ ሠልጥኖ ከቆየው የዃላ ቀርና ድንቊርና ‹የባላገር ፖለቲካ› ካልተላቀቀ፣ የጐሣ ፋሺስታዊውን የርጉም ዐቢይ አገዛዝ መንቀል ቢቻል እንኳን የምንመኘውን በብሔራዊ ዜግነት ላይ የተመሠረተ፣ መሠረታዊ ሰብአዊ መብቶች የሚከበሩበት፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ያለበት፣ የሕግ የበላይነት የሰፈነበት የእኩልነት ሥርዓት ለመትከል በእጅጉ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡























