ጋዜጠኛና የታሪክ ምሁሩ ታዲዎስ ታንቱ
ጋዜጠኛና የታሪክ ምሁሩ ታዲዎስ ታንቱ ከእስር ተፈቱ ተብሎ በማኅበራዊ ሚዲያዎች እና በተለያዩ አካላት እየተሰራጨ የሚገኘው መረጃ ፍጹም ሐሰት ነው ።
የታሪክ ምሁሩና ጋዜጠኛው ታዲዎስ ታንቱ፤ ግንቦት 10 ቀን 2014 ዓ.ም በአገዛዝ ሥርዓቱ የጸጥታ ኃይሎች በግፍ ታፍነው ለግዞት እስር ከተዳረጉበት ጊዜ ጀምሮ፣ ላለፉት ዓመታት በእስር ላይ ሆነው የፍርድ ሂደታቸውን ሲከታተሉ ቆይተዋል። ሂደቱን ሲያካሂድ የቆየው የአገዛዙ የፍርድ አስፈጻሚ አካልም በጥቅምት ወር 2017 ዓ.ም ላይ የ6 ዓመት ከ3 ወር የጽኑ እስራት ፍርድ በይኖባቸዋል።
ጥቅምት 12 ቀን 2017 ዓ.ም. በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት፣ ፍርድ ቤቱ የአቶ ታዲዎስን የፍርድ ማቅለያ ተመልክቶ ውሳኔ ለመስጠት ቀጠሮ ይዞ ነበር። በእለቱም አቶ ታዲዎስ የሚያቀርቡት የቅጣት ማቅለያ ካለ እንዲያቀርቡ በፍርድ ቤቱ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር።
ነገር ግን ዕድሜያቸውን ሙሉ ለእውነት የቆሙት አረጋዊው ጋዜጠኛና የታሪክ ጸሐፊ፣ ችሎቱ ፊት በቆራጥነት በመቆም የሚከተለውን ታሪካዊ እና ኃይለኛ ምላሽ ሰጥተው ነበር ፤
“እኔ ተፈጥሮ በሰጠችኝ የማመዛዘን ሕሊና መሠረት ለተበደሉ ዘሮች ወይም ማንነቶች ላይ ሚዛናዊ ሀሳብ በመስጠቴ ምንም ዓይነት የጥፋተኝነት ስሜት አይገባኝም! በጠበቆቼ በኩል ማቅለያ ለፍርድ ቤቱ እንዳቀርብ የቀረበልኝን ጥያቄ አልተቀበልኩትም፤ ምክንያቱም የቅጣት ማቅለያ ማዘጋጀት ማለት ‘አጥፍቻለሁ’ የሚል የጥፋተኝነት ድምዳሜን ስለሚያሳይ፣ ተፈጥሮ የፈቀደችልኝን መብት በሕግ አልቀይረውም! የሰናፍጭ ቅንጣት የምታክል ወንጀል ስለሌለብኝ ውሳኔውን አልቀበለውም፤ ይህ አቋሜ ነው።” ብለዋል።
ጋዜጠኛ ታዲዎስ ታንቱ በመቀጠልም፦ “ፍርድ ቤቱ የፈለገውን ውሳኔ ይወስን፤ እኔ በዚህ ዕድሜዬ—በ74 ዓመቴ ለወጣቶች መልፈስፈስን አላስተምርም!” በማለት የጸና አቋማቸውን በሙሉ ድፍረት ለችሎቱ አሰምተዋል ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ከአንድ ዓመት በፊት የቀድሞው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ ከፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጋር በመነጋገር “ይቅርታ ጠይቀው ከእስር መፈታት ይችላሉ” በማለት፣ የይቅርታ ጽሁፍ ተዘጋጅቶ በጠበቆቻቸው በአቶ ሰለሞን ገዛኸኝ እና በአቶ ታለማ ገዛቸው በኩል ለአቶ ታዲዎስ መልዕክት ደርሷቸው ነበር።
ነገር ግን አቶ ታዲዎስ፦ “በፍጹም ይቅርታ አልጠይቅም! የሠራሁት ምንም ወንጀል የለም!” በማለት በመንግሥት በኩል የቀረበላቸውን የይቅርታ ጥሪ በጽኑ ውድቅ አድርገውታል።
በአሁኑ ወቅት ጋዜጠኛና የታሪክ ፀሐፊ ታዲዎስ ታንቱ አሁንም በግፍ እስር ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ከእስር ተፈተዋል ተብሎ የሚሰራጨው መረጃ ሙሉ በሙሉ ሐሰት ነው ።
በተጨማሪም ሰሞኑን ከይቅርታ ሂደቱ እና ከእስረኞች መፈታት ጋር በተያያዘ፣ ለእሳቸው የቀረበ አዲስ የይቅርታ ፎርም የሌለ ሲሆን፤ አሁን ላይ የይቅርታ ፎርሙን ከፈረሙትም ሆነ ለመፈረም ፈቃደኛ ካልሆኑት እስረኞች ስብስብ ውስጥ እሳቸው እንደማይገኙበት ታውቋል።
@RasMinilik (Etorika)





















