>

የመለስ ዶሴ (ደረጀ ደስታ)

እየሆነ ያለውን ታውቅ ዘንድ ገንዘቡን ተከተል ይባላል።
ህወሃት ባለቤታቸውን በክብር እሳቸውን በቁም እየቀበረ ይመስላል። ድርጅታቸው ያሽቀነጠራቸው አዜብ “ሰፊውን ህዝብ” መሆን እየጀመሩ ይሆን? ባለፈው ሳምንት በአንዲት ሀብታም ወዳጃቸው ልቅሶ ላይ ከሥላሴው ቤተክርስቲያን ተገኝተዋል። አሜሪካ ከርመው አዲስ አበባ የገቡትም በዚያው ሳምንት ነበር። የድርጅታቸው ደህንነቶች አዜብ ከአገር ለቀው በወጡና በገቡ ቁጥር ሻንጣቸውን አንድም ሳያስቀሩ እያራገፉ መበርበር ጀምረዋል። በቪ.አ.ይፒ ክብር ያገኙትን ሁሉ እየተቆጡና እያሽቆጠቆጡ በተመላለሱበት ኤርፖርት ይህ መድረሱ “ወይ ጊዜ!” እሚያሰኝ ነው። ሻንጣቸው መበርበሩ እሳቸውን ለማበሳጨት የተደረገ ብቻ አይመስልም። የአዜብ ወዳጅ ዘመድ የሆኑ በሙሉ ስለ አዜብ ሀብትና ንብረት መረጃ እንዲሰጡ እየተጠየቁ መሆኑ እየተነገረ ነው። የአዜብ ሀብት ይህን ያህል ከዓይን ተሰውሮ ለመርማሪ ያስቸገረ ነገር ሆኖ ነው ወይስ ሰዎቹ ከሳቸው እሚፈልጉት ሌላ ነገር አላቸው?
ባለቤታቸው መለስ ዜናዊ ኦክቶበር 17 2008 የምኒስትሮች ምክር ቤት የመንግሥት ባለሥልጣን የሀብት ምዝገባን በተመለከተ መዘጋጀቱን ለፓርላማቸውና ለህዝብ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል። ከአራት ዓመት በኋላም ዲሴምበር 29 2012 ላይ የፌደራል የጸረ ሙስና ኮሚሽኑ ፣ የባለሥልጣናቱ ሀብትና ንብረት ዝርዝር ከሁለት ወር በኋላ ለህዝብ ይፋ ይደረጋል ብሎ አወጀ። ኮሚሽኑ ያንን ሲያውጅ ቀርቶ አቶ መለስ ራሳቸው መመዝገብ እንጀምራለን ብለው ሲያውጁ ዝርዝሩን በእጃቸው ሳያስገቡ አይደለም። የባለሥልጣናት ሀብትና ንብረት ቀርቶ፣ እያንዳንዷን ዝርዝር ታሪክና ውሏቸውን እሚያውቀው ሰነድ ከአቶ መለስ መሳቢያ ውስጥ መኖሩን መገመት እሚያቅተው ሰው የለም። የአቶ ጌታቸው የደህንነት ቢሮ፣ በእየለቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ እሚያቀርበው ሪፖርት አለ። አቶ ጌታቸው አሰፋ ራሳቸው የላኩት ሪፖርት ስለሆነ ያ ቅጂው እሳቸውም ዘንድ ስለሚገኝ ችግር የለውም። ይሁን እንጂ አቶ መለስ የደህንነት ሪፖርት እሚያገኙት ከአቶ ጌታቸው ቢሮ ብቻ አይደለም። ከመከላከያው ደህንነትና ከጀኔራል ሳሞራም ያገኛሉ። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ በራሱ በኩል ከምኒስትሮች ከሚያሰባስበውም መረጃ ያገኛሉ። ተጠሪነቱ ለአቶ መለስ ብቻ የሆነም የራሳቸው መስመር አላቸው። እነዚህ ሁሉ ሰነዶች አቶ መለስ ሲሞቱ አብረው የሞቱ ሰነዶች አይደሉም። የትና በማን እጅ ናቸው?
ወ/ሮ አዜብ በሚስትነታቸው ለሚስጥሮቹም ሆነ ለሰነዶቹ ቅርብ መሆናቸው እሚጠበቅ ነው። በዚያ ላይ ስለ ኤፈርት ብዙ ብዙ እሚያውቁት ነገር አለ። እንደ ስብሐት፣ አርከበ፣ ስዩም፣ አባይ ፀሐዬ፣ ስለመሳሰሉ ሰዎች ሀብትና ንብረትም ከሳቸው በላይ እሚያውቅ የለም። በአንዳንዶቹ ወዳጆቻቸው እየተመከሩም አንዳንድ ሰነዶችን ሳያሸሹና ለክፉ ቀን ሳያስቀምጡ እንዳልቀሩም እየተነገረ ነው። አምስት ሳንቲም የለኝም እያሉ እሚምከነከኑት ሴትዮዋ፣ ያን ያህል እውቀቱም ሆነ ተንኮሉ ኖሯቸው ሰነዱን ይጠቀሙበታል የሚል ጥርጣሬ ባይኖርም፣ አሁን ካሉት ባለሥልጣናት ለማን አካፍለውታል፣ ካልሆነም ወደፊት ምን ያደርጉታል እሚለውን ስጋት መፍጠሩ አልቀረም። ሴትዮዋን በሙስና ገድሎና አዋርዶ መቅበሩ አማራጭ ያልተገኘለት ጨዋታ ይመስላል። አዜብን የመምታቱ ጨዋታ ግን ከፍትሕ ጥማት የመጣ አይደለም። ሰዎቹ ሙስንና አስታከው እንዲመቱ እሚፈልጓቸው የኦህዴድና የብአዴን ሰዎች አሉ። ጨዋታው ወቅቱን በአሸናፊነት ለመወጣት፣ ደርቦና አስመስሎ የመምታት ጨዋታ ነው። አሁን በሥልጣን ላይ ያሉትን የህወሃት ባለሥልጣናት እማይነካ ሙስና ማንንም ነጥሎ መንካቱ አያምርበትም። የአቶ መለስ ዶሴ ቢለቀቅ ደግሞ ሁሉንም ነገር ያሳየን ነበር።
የፀረ ሙስና ኮሚሽን የመዘገበው የባለሥልጣናት ሀብት በአስቸኳይ ይለቀቅ! እሚል መፈክር ግን ወቅታዊ ሳይሆን አቀርም። የታሰሩ ሰነዶች ሁሉ ይፈቱ!!!

Filed in: Amharic