>

ፖሊስ በጦማሪና መምህር ስዩም ላይ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ጠየቀ

ጋዜጠኛ ኢዩኤል ፍስሃ ዳምጤ

በአምቦ ዩኒቨርስቲ ወሊሶ ካምፓስ መምህር የሆኑት አቶ ስዩም ተሾመ ከትላንት በስቲያ የካቲት 29 ቀን 2010 ዓ.ም በቁጥጥር ስር መዋላቸው የሚታወቅ ነው። አቶ ስዩም በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ወደ ማዕከላዊ የተወሰዱ ሲሆን ትላንት የካቲት 30 ቀን 2010 ዓ.ም በአራዳ መጀመሪያ ደረጃ የጊዜ ቀጠሮ ፍ/ቤት ቀርበዋል።

ፖሊስ አቶ ስዩም ኦሮሚያ ውስጥ የተቀሰቀሰውን አመፅ ለማደራጀት ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ገልፆ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ጠይቆባቸዋል። ፍ/ቤቱ ፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ በመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ለመጋቢት 14 ቀን 2010 ዓ.ም ሰጥቷል።

ዛሬ መጋቢት 01 ቀን 2010 ዓ.ም በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ (ማዕከላዊ) አቶ ስዩምን ለመጠየቅ ተገኝተው እንደነበር አቶ ፋሲካ አዱኛ ገልፀዋል ። አቶ ፋሲካ አዱኛ ስማቸውን አስመዝግበው ከገቡ በኋላ ከአቶ ስዩም ጋር መገናኘት መቻላቸውን ለዚህ ዜና ፀሐፊ ገልፀዋል። አቶ ስዩም በወሊሶ ከተማ በቁጥጥር ሥር በዋሉበት ወቅት በመከላከያ ሰራዊት አባላት መያዛቸውንና ድብደባ እንደተፈፀመባቸው እንደገለፁላቸው አቶ ፋሲካ አስረድተዋል። ድብደባው የተፈፀመውም የላፕቶፖቻቸውን ፓስወርድ እንዲሰጡ በማስገደድ መሆኑን አቶ ስዩም ገልፀዋል። በድብደባው ብዛትም የላፕቶፖቻቸውን ፓስወርድ እንደሰጡ አቶ ስዩም አስረድተዋል። በመኖሪያ ቤታቸው መያዛቸውን የገለፁት አቶ ስዩም የመከላከያ ሰራዊት አባላቶቹ በቤታቸው የሚገኙ ንብረቶቻቸውን ማውደማቸውን ገልፀዋል። ከቤታቸውም 3 ላፕቶፖችን እንደወሰዱባቸው አያይዘው ገልፀዋል።

አቶ ስዩም ተሾመ ባሳለፍነው ዓመት የታወጀውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ በጦላይ የፖሊስና ወታደራዊ ማሰልጠኛ ታስረው መለቀቃቸው የሚታወስ ነው። በጦላይ በታሰሩበት ወቅትም ከፍተኛ ድብደባ ተፈፅሞባቸው እንደነበር ይታወቃል።

Filed in: Amharic