ከይኄይስ እውነቱ
ኢፍትሐዊነትን ይዞ መቀጠል በዓለማዊውም ሆነ በመንፈሳዊው ሕግ ሰዋዊ ጠባይ አይደለም፡፡ በየትኛውም መመዘኛ የሞራል ልዕልናን አያመለክትም፡፡ የቅድስናም መገለጫ አይደለም፡፡ ከ50 ዓመታት ያልተቋረጠ እልቂትና ጥፋት በኋላ ወደ ቀልባችን/ኅሊናችን ተመልሰን ‹ሰው› መሆን ካቃተን በሰማይም በምድርም ተወቃሾች ነን፡፡
በቅርቡ አንድ ከፍተኛ ቁም ነገር ያዘለ ግሩም ጽሑፍ እንደ ወትሮው ከወንድማችን ፕሮፌሰር ግርማ ብርሃኑ አነበብሁ፡፡ ርእሱ ‹‹ Targeting the Amhara Intelligentsia: Killings, Detentions, and the Legal Threshold of Genocide under International Law›› የሚል ሲሆን÷ በጥቅሉ ሲተረጐም፤ ‹‹የዘር ማጥፋት ወንጀል ሕጋዊ መመዘኛ በዓለም አቀፍ ሕግ፤የዐምሐራ ምሁራን ላይ ያነጣጠረ ግድያና እስር›› የሚለውን መልእክት ይሰጠናል፡፡›› የዐምሐራ ምሁራን በተለይ ኢትዮጵያውያንእውነተኛ ምሁራን ባጠቃላይ ካላችሁ፤ አንዳንዶቻችሁ ከሚያስደነግጥ ዝምታ÷ ቊጥራችሁ ቀላል የማይባል ከጐሣ ፖለቲካ ተዋናይነት÷ ከፊላችሁ ንስሓ ገብታችሁ ከዚህ ክፉ ዓለም በምትሰናበቱበት ዕድሜአችሁ ከጐሣ ፋሺስቶች ጋር አገር በማጥፋት ተባባሪ የሆናችሁ፣ሌሎቻችሁ በጊዜያዊ እሰጥ አገባና ጥቅማ ጥቅሞች ተጠምዳችሁ እጅግ የከፋ አደጋ ላይ የሚገኝ ሕዝባችንን እና አገራችንን የበለጠ ከሚጎዳ ጥፋት ውስጥራሳችሁን ነጥቃችሁ የምታወጡበት ጊዜ ዘግይቷል ካልተባለ መቼ ይሆን? ላገርም ሆነ ለዐምሐራው ማኅበረሰብ ተጠሪ ተጠያቂ ሊሆኑ የሚችሉ ሊቃውንት ባሉበት እየታደኑ እልቂት የሚፈጸምባቸው ከሆነ መጨረሻችን ምንድን ነው?
እስቲ ለአብነት የዘር ማጥፋት ገጽታዎችን በጥቂቱ እንይ፡፡ የዘር ማጥፋት ወንጀል ብዙ ዓይነት ገጽታዎች አሉት፡፡ አፈጻጸሙም ዘርፈ-ብዙ ነው፡፡ ለምሳሌ የአንድን ማኅበረሰብ ወይም ቡድን ባህል ማጥፋት (cultural genocide) አንዱ ገጽታ ነው፡፡ ይኸውም ቋንቋን፣ ቅርስን፣ ትውፊትን፣ ማንነትን በማጥፋት ይገለጻል፡፡ አንድ ማኅበረሰብ የራሱን ቋንቋ፣ ልማድ እንዲተው ማስገደድን ይመለከታል፡፡ አንድን ጐሣ/ነገድ በቊጥርም ሆነ በሥልጣን የበላይ ነኝ በሚለው ጐሣ በማስገደድ ባህሉን እንዲቀበል ማድረግ ሌላው የባህላዊ ጄኖሳይደ መገለጫ ነው፡፡ ይህን ዓይነቱን የዘር ማጥፋት ፋሺስታዊው የጐሣ አገዛዝ በዐምሐራው ሕዝብ፣ በጉራጌውና በጌዴዎ ማኅበረሰቦች ላይ በግልጽ ፈጽሞታል፤ አሁንም ቀጥሏል፡፡
ሌላው የዘር ማጥፋት ገጽታ አንድን ቡድን፣ ነገድ ወይም ማኅበረሰብን ዒላማ ያደረገ ከቤት ንብረት ማፈናቀል፣ ከሥራ ማፈናቀል፣ ዕድሜአቸው ለትምህርት የደረሱ ሕፃናትና ወጣቶች ትምህርት እንዳያገኙ ማድረግ፣ የጤና አገልግሎት መንፈግ፣ ምግብ በመከልከል ረሃብን መፍጃ መሣሪያ ማድረግ ወዘተ. ይጠቀሳል፡፡ በትምህርት ረገድ ወያኔ በዐዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጀመረው የ42 መምህራን ማባረር ዘመቻ በወራሹ ርጉም ዐቢይ በስፋት ቀጥሎ ‹ዳግም ቅጥር› በሚል በቅርቡ ከ100 በላይየሚገመቱ ከጀማሪ ረዳት መምህራን እስከ /30 ዓመታት አገልግሎት ያላቸውን መምህራን ከሥራ አግዶአል፡፡ ከነዚህ መካከል አንዳንዶቹ መምህራን በተማሩበትና በሠለጠኑበትየትምህርት መስክ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በጣት የሚቆጠሩ በመሆናቸውና እጥረት በመኖሩ እንኳን እነሱን ልናባርርና ልናግድ ቀርቶ ተተኪዎችን በጥራትና በብዛት የምንፈልግበት ነው፡፡ ከታገዱት መምህራን ውስጥ አብዛኛዎቹ ከነገደ ዐምሐራ መሆናቸውን ካነጋገርኋቸው መምህራን ለመገንዘብ ችዬአለሁ፡፡
ለአገርና ለሕዝብ ብርሃን ሊሆኑ የሚችሉትን ሊቃውንት ነገድና ሃይማኖትን መሠረት አድርጎ መጨፍጨፍ ተልእኮው ምንድን ነው? ጠላት ጥልያን በሁለተኛው ወረራ ወቅት ዓለማውያንም ሆኑ መንፈሳውያን ሊቃውንትን ጨፍጭፎ አገርን ያለተጠሪ ሕዝብን ያለ መሪ ለማስቀረት ያደረገው ሙከራ በታሪክ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ‹‹ጥቁሮቹ ጥልያኖች›› ግን ከባዕዳኑም ንጽጽር በሌለው ሁናቴ ሕዝብና አገርን በአረመኔነት እያጠፉ ነው፡፡በተለይም የዐምሐራውን ነገድ እያልን ያፈጠጠ ያገጠጠውን የምናነሳው በጎላው ለመናገር እንጂ ሌላውም ሕዝባችን ከዚህ ጥፋት ነፃ አይደለም፡፡ የዐምሐራውን ለየት የሚያደርገው ባለፉት የደርግና የወያኔ አገዛዝ የተጀመረው የጥፋት ውጥን እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በጥቂት አረመኔ የኦሮሞ ጐሠኞች ላለፉት 8 ዓመታት የሠለጠነው የፋሺስታዊ ጐሣ አገዛዝ በታቀደና በተጠና መልኩ ‹የአገዛዙን የአስተዳደር መዋቅር› መሠረት አድርጎ ሁለንተናዊ የህልውና ጥፋት እየተፈጸመበት የሚገኝ መሆኑ በሁሉም ዘንድ የሚታወቅ በመሆኑ ነው፡፡ ይህንን ጥፋት ምዕራባውያኑ ‹የሰብአዊ መብት ተሟጋች› የሚባሉት ድርጅቶችም በሚገባ ያውቁታል፡፡ ለመሆኑ እነዚህ ተቋማት ሕግና መርሆዎችን በየትኛውም ቦታ ያለምንም አድልዎ ወጥነት ባለውና ባንድ ዓይነት ሁናቴ ተግባራዊ ያደርጋሉ ወይስ ባልተጻፈ ሕግ የምዕራባውያኑ መንግሥታትና ተቋማት ጉዳይ አስፈጻሚዎች ናቸው? መልሱ ግልጽ ይመስለኛል፡፡
በሕዝቡም ሆነ የሕዝቡ አካል በሆኑት ‹ምሁራን› ላይ እየተፈጸመ የሚገኘው እልቂት ‹የዘር ማጥፋት› የሚባለው አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ወንጀል ውስጥ ይወድቃል የሚለው የሕግ ፍረጃን ለጊዜው ወደ ጎን አድርገን፣ እልቂቱ ሥርዓታዊና መዋቅራዊ መሆኑ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም፡፡ ድርጊቱ በሕግ የዘር ማጥፋት ቢባል ከታሪክ ምዝገባ ባለፈ አሁን ባለው ኢፍትሐዊና ጉልበት-መር በሆነው የዓለም አቀፍ ሥርዓት ለውጥ ይኖረው ይሆን? የርእሴ ዋና ጉዳይ በመሆኑ ወደ ኋላ እመለስበታለሁ፡፡ በዐምሐራው ሕዝብ እና በሌሎችም የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች ላይ ለግማሽ ምእት ዓመት በአገዛዞች ሲፈጸም የቆየው የሕዝብና የአገር ጥፋት መጠኑና የጭካኔው ልክ በፍልስጥኤም በሱዳንና በሌሎችም የዓለም ክፍሎች ከሚታየው ጥፋት የሚበልጥ ሆኖ ሳለ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በቂ ሽፋን ያልተሰጠው ለምን ይሆን? ወይስ ይህም ጉልበት አምላኪ ከሆነው ዓለም አቀፍ ሥርዓት ጋር የተያያዘ ይሆን?
እውነቱን ለመናገር የአገርና የሕዝብ አንድነትን፣ ሥልጣኔን፣ የጋራ መልካም ዕሤቶችንና ቅርሶችን ከሚያወድም ፋሺስታዊ የጐሣ አገዛዝ ጥፋት ተዘልሎ የሚቀር የሕዝባችን ክፍል ይኖር ይሆን? የጊዜና ቅደም ተከተል ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር፡፡ዐምሐራው የጥፋቱ ግምባር ቀደም ገፈት ቀማሽ፣ ህልውናውም አደጋ ላይ የሚገኝ በመሆኑ በተናጥል የሞት ሽረት ትግል በማድረግ ላይ ቢገኝም፣ የሁላችን መብት በእኩልነት ተከብሮ እንደ አንድ ሕዝብና አገር መቀጠል ካለብን የገጠመን ፈተና የዚህኛውን ሕብረተሰብ ክፍል ብቻ ይመለከታል ብለን ወር ተራችን እስኪደርስ የምንጠብቅ መሆን የለብንም፡፡ በመሆኑም ምሁራን የሕዝባችንን እና አገራችንን ዘላቂ ህልውና የሚያረጋግጥ፣ ዘላቂና ተግባራዊመፍትሔ ሊያመጡ የሚችሉ ጥናታዊ ጽሑፎችን ሕዝባችን በሚረዳበት ቋንቋ በማዘጋጀት ለውይይት ማቅረብ፣ ማስተማርና ማንቃት ይጠበቅባችኋል፡፡ ይሄ ከምሁራን ብቻ ሳይሆን ‹ፊደል ከቆጠረ› ሁሉ ይጠበቃል፡፡ ትምህርት፣ የሥራና የሕይወት ልምድ በዚህም የሚገኘው ዕውቀትና ጥበብ ሕዝብና አገርን አስወድዶ ሕዝብና አገርን የሚጠቅም መልካም ለውጥ ካላስገኘ፤ በተቃራኒው የሕዝብና የአገርን አንድነት የሚያናጋ፣ የማኅበረሰብን ትስስር የሚበጣጥስ፣ ልዩነትን አስፍቶ ለርስ በርስ እልቂትና ጥፋት፣ አልፎ ተርፎም ለባዕዳን ጣልቃ ገብነት የሚዳርግ ከሆነ ዕውቀትም ጥበብም ሊባል አይገባውም፡፡ ዕውቀታቸውንና ልምዳቸውን ለዚህ ዓይነቱ ሰይጣናዊ ዓላማና ተግባር የሚያውሉ ‹ፊደል ቆጣሪዎች› የትኛውንም ዓይነት የአካዳሚ ማዕርጋት ቢይዙ ትክክለኛ መጠሪያቸው ‹ደናቊርት› የሚለው ቃል ነው፡፡አለመታደል ሆኖ እንደነዚህ ዓይነቶቹ – መነሻቸውና መድረሻቸውን ከርሣቸውን ያደረጉ – ጉዶች በውስጥም ሆነ በውጭ እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡
ወደ ርእሰ ጉዳዬ ጭብጥ ልመለስና ኢትዮጵያ ውስጥ ላለፉት ስምንት ዓመታት አገራችን ላይ በታሪኳ ታይቶ የማይታወቅ ምስቅልቅል እየፈጠረ ባለው ፋሺስታዊ የጐሣ አገዛዝ በዐምሐራው ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል (ጄኖሳይድ) ተፈጽሟል ወይ? የሚለው ጥያቄ በሕግም ሆነ በማኅበራዊሳይንስ ጠበብት ዘንድ ብዙ ተብሏል፡፡ ዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት የሚባለውን ተቋም ውሳኔ ካላገኘን ወንጀሉ አልተፈጸመም ካላልን በስተቀር ሕጉ ባስቀመጠው መለኪያ (ስታንዳርድ) መሠረት ሁሉም መሥፈርቶች ተሟልተው የሚገኙበት በሕጉ ምሁራን ዘንድ የመጽሐፉን ብያኔ በሚያሟላ መልኩ (text book definition of genocide) ተፈጽሟል፡፡ በምሁራኑና ፊደል በቆጠሩት እንዲሁም በማኅበረሰቡ ዘንድ ተጽእኖ ፈጣሪ በሆኑት ዐምሐሮች ላይ በተበታተነ መልኩ ነገር ግን ሆን ብሎ ታቅዶ የነገድና ሃይማኖት ማንነትን መሠረት አድርገውየሚፈጸሙ ያላቋረጡ ግድያዎችን በሚመለከት፣ እዚህም እዚያም የተፈጸሙትንና የሚፈጸሙትን አንድነት÷ ወጥነት÷ተከታታይነትና ግንኙነት የሌላቸው የሚመስሉ የተነጣጠሉሁነቶችን አጠቃላይ አካሔድ በሕዝብ ደረጃ በሚፈጸም የዘር ማጥፋት ወንጀል ዓውድ አስገብቶ ማጥናትን ይጠይቃል፡፡ እዚህ ላይ ለማንሣት የምፈልገው ነጥብ በሕጉ መሠረት የዘር ማጥፋት ወንጀልን የሚመመሠርቱ መሠረታዊ መመዘኛዎች ተሟልተው ቢገኙ ቀጣዩ ርምጃ ምን ሊሆን ነው? በፈጻሚዎቹና ግብር አበሮቻቸው ላይ ዓለም አቀፍ ክስ ልንመሠርት ነው? የዚህ አስተያየት አቅራቢ ቊልፍ ጥያቄ በሕግ ሳይሆን በጉልበት በሚመራው ዓለም አቀፍ ሥርዓት፣ ይህንንም በሚያረጋግጡት ምዕራባውያን መንግሥታትና ተቋሞቻቸው እንዲሁም በነሱ ቊጥጥር ሥር ውሎ ፈቃዳቸውን በሚያስፈጽመውና በወረቀት ነብርነት በሚመሰለው የመንግሥታቱ ድርጅትና ቅርንጫፎቹ ጋር ደጅ መጥናቱ በጅምላም ሆነ በተናጥል የሚፈጸመውን ግድያ ያስቆመዋል? ወይስ በውስጥ የሚደረገውን ትግል ሊያግዝ የሚችል ዲፕሎማሲያዊና ግንዛቤ የመፍጥር ጥረት ተደርጎ እንዲታይ ነው? እነዚህን ጥያቄዎች የማነሣው የዘር ማጥፋትና መሰል ወንጀሎችን ጥናትን መሠረት አድርጎ ግንዛቤን መፍጠር፣ ማጋለጥና ከተቻለም በወንጀሉ ተጠያቂ የሆኑትን ሁሉ ፍርድ ፊት እንዲቀርቡ በማድረግ ጥፋቱን ለማስቆምና እንዳይደገምለማድረግ ከዚህ ቀደም የተደረጉም ሆነ በቀጣይ የሚደረጉ ጥረቶች አስፈላጊ አይደሉም አይጠቅሙም ከሚል መነሻ አይደለም፡፡ በምዕራባውያን የጉልበት የበላይነት የሚመራውን ዓለም አቀፍ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ባለማመን እና በእነሱ መልካም ፈቃድ የሚዘጋጁ ዓለም አቀፍ ሕግጋት እስከነ ጉድለታቸው በእኩልነት ሊፈጸሙና ተግባራዊ ሊሆኑ እንደማይችሉ በተግባር ከሚታየውና ከሚሰማው በመረዳት እንጂ፡፡
ከ2ኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ነግሦ ያለውና ጉልበት ትክክል ነው የሚለው የምዕራባውያኑ መርሆ በሌሎች የዓለማችን ክፍሎች የፈጠረውና እየፈጠረ ያለው ምስቅልቅል እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ርስ በርሳቸውም እያቃረናቸው የቃላት ጦርነቱን ከጀመሩ ከራርመዋል፡፡ ጥሉ እውነተኛ ነው ወይስ የማስመሰል የሚለውን ጊዜ ይገልጠዋል፡፡ በአፍሪቃ፣ በላቲን አሜሪቃ፣ ባብዛኛው የእስያ አገሮች የሚገኙ አምባገነንና የሕዝብ ደም መጣጭ የሆኑ አገዛዞች/‹መንግሥታት› በየአገሮቻቸው ለሚታዩ ሁለንተናዊ ቀውሶችና ‹ጉልበተኞቹ› ጣልቃ ገብተው እንዲያምሱአቸው ሁኔታዎችን በማመቻቸት ረገድ ተጠያቂዎችና ኃላፊ ቢሆኑም፣ በየአገሮቹ የሚታዩ ጦርነቶች÷ ግጭቶች÷ ማኅበራዊ÷ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ምስቅልቅሎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የምዕራባውያኑ ጉልበተኞች እንዲሁም የነሱ ተገዳዳሪ የሆኑት የቻይናና የራሺያም መንግሥታት እንዲሁም የሁለቱ ጉልበተኞች ጭፍሮች ጣልቃ ገብነት መሆኑ ፀሐይ የሞቀው እውነት ነው፡፡ ዓለም በሲያንስና ቴክኖሎጂ ምጥቀት ሽፋን በርኵሰት በመሞላት ከሥልጣኔ ተራቁቶ ዕለት ዕለት እያበደና እየደነቆረ ይገኛል፡፡ ዛሬ እግዚአብሔር አምላክ በየአገሩ ያደለው የተፈጥሮ ሀብት ከበረከትነት ይልቅ ርግማን ሆኖ ለሚሊዮኖች እልቂት ምክንያት እየሆነ ነው፡፡ ዓለም ከእጅ አዙርቅኝ አገዛዝ እንደገና ወደ ቀጥተኛ ቅኝ አገዛዝ እየተሸጋረ ይገኛል፡፡ በዚህ ዓይነቱ ዓለም ውስጥ ነው ሕግና ሥርዓት አለ ብለን ወደ ‹ቅኝ ገዥዎቹ›ና ለነሱ ተጠሪ ወደሆኑት ተቋማት ደጅ የምንጠናው? መልሳችን አማራጭ የለንም ከሆነ የመሸነፍና ተስፋ የመቁረጥ ይሆንብናል፡፡ መፍትሔው አገር ውስጥና በእጃችን ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ግንኙነቱንም ሆነ ንግግር እንዳስፈላጊነቱ በጊዜው ጊዜ እንደርስበታለን፡፡ በቅድሚያ የመቀመጫዬን እንዳለችው እንስሳ እንደ ሰውና ሕዝብ እንዲሁም እንደ አገር ህልውናችንን በመሥዋዕትነት ማረጋገጥ ይኖርብናል፡፡ይህንን የተቀደሰ ተግባር (ፈተናው ቢበዛበትም) የዐምሐራው ሕዝብ ጀምሮታል፡፡ ፋሺስታዊውን አገዛዝ ከፕሮፓጋንዳ በስተቀር በተግባር መለ መላውን አስቀርቶታል፡፡ ታዲያ ዐምሐራ ጀግና አጥቶ ነው ይህንን ቆሻሻ አገዛዝ ቀብሮ መገላገል ያቃተው? በጭራሽ! ትግሉን የሚያስተባብርና የሚመራ ድርጅትና መሪ ማቋቋምና ማውጣት አቅቶት ነው? አይመስለኝም፡፡ እስኪታክተን እንደተናገርነው ዘላለማዊ አሽከር ሆኖ ሌሎች እያሰቡለት ከከርሡ ውጭ የሚያውቀው የሌለ የታሕተ ሰብእ ስብስብ የሆነው ብአዴን የተባለ ወያኔ ሠራሽ ‹ፍጡር› መኖር እና በዚህ ጭንጋፍ ‹ፍጡር› ላይ የማያዳግም ርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ የሆነ አመራር መጥፋቱ ይመስለኛል፡፡
እንደ አንድ አገር ሕዝብ የእኩልነት ራእይ ይዘን ለመኖር የምናስብ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል የምንገኝ ኢትዮጵያውያን በሙሉ (ዘረኞች የከለሉልን የጐሣ አጥር ሳይገድበን፣ የተቆጣጠሩትን አገዛዛዊ መዋቅር ተጠቅመው ታሪክን በማዛባት የፈጠሩትንና ያሠራጩትን የሐሰት ትርክቶች በማስተዋል መርምረንና ሐሰቱን ለሌሎች ወገኖቻችንም አጋልጠንና አሳውቀን) ባንድነት ተባብረን ቆሻሻውን የጐሣ አገዛዝ ነቅለን ለሁላችን የሚበጅ የእኩልነት ሥርዓት ተክለን መኖር የማንችልበት ምክንያት የለም፡፡ ይህንን ሁሉ ለመሸከም የሚያቅት ጥፋት ካየን በኋላ ነፃ አውጪ ወይም ተአምር የምንጠብቅ ከሆነ እንደ ሰው፣ እንደ ቤተሰብ፣ እንደ ማኅበረሰብ፣ እንደ ሕዝብና እንደ አገር የለንም ማለት ነው፡፡ በደልና ጭቆና ባጠቃላይ ኢፍትሐዊነትን ይዞ መቀጠል በዓለማዊውም ሆነ በመንፈሳዊው ሕግ ሰዋዊ ጠባይ አይደለም፡፡ በየትኛውም መመዘኛ የሞራል ልዕልናን አያመለክትም፡፡ የቅድስናም መገለጫ አይደለም፡፡ ከ50 ዓመታት ያልተቋረጠ እልቂትና ጥፋት በኋላ ወደ ቀልባችን/ኅሊናችን ተመልሰን ሰው መሆን ካቃተን በሰማይም በምድርም ተወቃሾች ነን፡፡ ወገኔ! የኛን የዘመናት ችግሮችና ተግዳሮቶች ባዕዳን ምዕራባውያን ሆኑ ሌሎች ‹ጉልበተኞች› እንዲፈቱልን ደጅ መጥናቱ ዝቅ ሲል የዋህነት ከፍ ሲል ሞኝነት ነው፡፡ አንዳንዶች ‹ምሁራን› ተብላችሁ ‹‹የምክክር ኮሚሽን›› እያላችሁ ከፋሺስቶች ጋር እጅና ጓንት ሆናችሁ የምትርመጠመጡ መቼ ይሆን የምትባንኑ? ወይስ ከኢትዮጵያ ሌላ አገር እና የተለየ ማንነት ይኖራችሁ ይሆን? ሌላው ቢቀር የሙያ ክብርና ስም አለን እንዲሁም ትተን ለምናልፈው ታሪክ እንጨነቃለን የምትሉ ከሆነኅሊናችሁን አዳምጡ፡፡ መቼም እንዲህ ዓይነቱ ወራዳ ተግባር ውስጥ የገባችሁት አምናችሁበት ወይም የጠመንጃ አፈ ሙዝ ተደቅኖባችሁ አይመስለኝም፡፡
ነገሬን ለመቋጨት በቅድሚያ በድንቊርና ርስ በርስ መናቆራችንን አቁመን የቤት ሥራችንን በኅብረት እንሥራ፡፡ ለሚሠሩትም እንቅፋት አንሁን፡፡ ያኔ እንደ እምነታችን ሰማዩም ይጨመርበታል፡፡ ወንድማችን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ግርማም ጥረትህን ቀጥል፡፡ እግዚአብሔር ይርዳህ፡፡ ሌሎች እውነተኛ ምሁራን/ሊቃውንት የወንድማችንን አሠረ-ፍኖት እንድትከተሉ ትመከራላችሁ፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያንን ባንድነት መብላት፣ ባንድነት ማለቅ፣ ባንድነት የሚያስደነግጥ ዝምታ ውስጥ መገኘት፣ ባንድነት ባርነትን መሸከም፣ ወዘተ ብቻ ነው የሚያስተባብረን? ለምንድን ነው ኅብረት አንድነታችን ለክፋት ብቻ የሆነው? መቼ ይሆን ባንድነት በጎ ለመሥራት፣ ባንድነት ለሕዝብና ላገር የሚጠቅም ልዕልና ላለው ተግባር ለመሰለፍና ባጠቃላይ ባንድነት ለፍትሕና ለእኩልነት ለመቆም የምንነሣው?
























