ኢትዮጵያ ትድግናዋን ከምዕራቡ ዓለም አታገኝም
ከይኄይስ እውነቱ
ካለፉት ሃምሳ ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ የምትገኝበትን ሁለንተናዊ ምስቅልቅል በዓለማዊውም ሆነ በመንፈሳዊው ጥበብ ለመግለጽ አዳጋች ሆኗል፡፡ አንዳንድ ሊቃውንት መያዣ መጨበጫ ቢያጡለት በደፈናው ‹‹ችግርግር ያለ ችግር›› በማለት ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ ቤተ ክህነቱ፣ ቤተ መስጂዱ እና ቤተ መንግሥቱ እንደ ዓይን የጠፉበት አገር ውስጥ ‹‹ችግርግር ያለ ችግር›› ውስጥ መዘፈቁ የሚያስደንቅ ሊሆን አይችልም፡፡ ፋሺስታዊው አገዛዘ በሕዝብ ላይ ጦርነት ዓውጆ በሚሊዮኖች እያለቁና እየተፈናቀሉ ከመሆኑም በተጨማሪ ኢኮኖሚው እንኩትኩቱ ወጥቶ ሚሊዮኖች በቀጠና እና ጠኔ ውስጥ ይገኛሉ፡፡
ጠባያችን ምንኛ አጉል ቢሆን ነው ከሁለት (ከመንፈሳዊውም ሆነ ከሥጋዊው) ያጣ የሆንነው? ምን ዓይነት አዚም ነው በውስጥም በውጭም ያለን ሁላችን ተስተካክለን እንደ ሕዝብም ሆነ እንደ አገር ለራሳችን ራሳችን ጠንቅ የሆንነው? እንዴት ነው ኢትዮጵያውያን ኹለት ሆነን እንኳ ለበጎ ነገር መስማማት ያቃተን? እንዴት ብንበላሽ ነው ዕውቀት፣ ጥበብና ብልሃቱ ያላቸውን ሁሉ ገፍተን (እዚህ ላይ ጋሽ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስን ያነሷል – የወንድማችን እስክንድር ውሳኔ ማስተዋል የተሞላበት ነበር) ‹ምንቸቶች ጋን የሆኑበት› ዘመን ላይ የደረስነው? ለምን ይሆን የግለሰቦችና የጥቂቶች ሐሳብና ፍላጎት መነሻም መድረሻም ካልሆነ ብለን ከዘረኛ ፋሺስታዊ ኃይሎች ባልተናነሰ መልኩ ላገር ጥፋትና ውድመት ሌት ተቀን እየሠራን ያለን? ህልውናችንን ለማስጠበቅና አገርን ከሰይጣናዊ ኃይሎች ለመታደግ በሚል ዓላማ ሕይወታችንን ለመገበር በጦር ሜዳ ተሰልፈን እንኳን አንድ መሆን ካቃተን ምንኛ መረገም ነው? እውነት ነጻነት ርቦናል? ፍትሕ ጠምቶናል? በደል አንገሽግሾናል? በአገርም በዓለምም የደረሰብን የመጨረሻ ውርደት ቆጭቶናል? ንቅስ ተደርጎ በየዓይነቱ የሚፈጸመውን ነውር ተጸይፈናል? በተለይም የእናቶቻችንና የእኅቶቻችን በአረመኔዎች መደፈር አንገብግቦናል? ቢያንስ ከክፉዎች ጋር ላለመተባበር ቊርጥ ውሳኔ አድርገናል? ወዘተርፈ፡፡ ለደረደርኋቸውና ሌሎች መሰል ጥያቄዎች በድፍረት አዎንታዊ መልስ የሚሰጥ ያለ አይመስለኝም፡፡ ለዚህ አመለካከቴ ዋነኛ ማስረጃ የሚሆነኝ ማናችንም በትንሹ እንኳን የታመንን አይደለንም፡፡ ከክፉዎች ጋር ካለመተባበር ዠምሮ በተሰጠን ጸጋ፣ ችሎታና ዐቅም ላገርና ለወገን የበኩላችንን ድርሻ አልተወጣንም፡፡ አንጋጠን ‹መና› ከሰማይ እንዲወርድልን ተጠባባቂዎች ነን፡፡ አንዳንዶቻችንም በሚያስደነግጥ ዝምታ ውስጥ ነን፡፡ ሌሎች ደግሞ ከርሣቸውን ቀዳሚ አድርገው ከክፉዎች ጋር አብረው ተሰልፈዋል፡፡ አንድ ወንድሜ ደጋግሞ እንደሚያነሣው እኔን ጨምሮ ‹ነጻ አውጪዎች› ጠባቂዎች ነን፡፡ የስንፍናችን ጥግ ዓይነተኛ ማሳያ መካከል አንዱ በእምነት ሽፋን ባርነትን ለመቀበል ዝግጁ መሆናችን ነው፡፡ ፈጣሪውን ጥግ የሚያደርግ ሰው መቼም ቢሆን የራሱን ድርሻ አይዘነጋም፡፡ ምክንያቱም በአምላክ የቸርነት ሥራ ውስጥ ሁሌም ቢሆን የሰው ልጆች ድርሻ አላቸውና፡፡ የምናመልከው ስንፍናንና ሐኬትን የሚጸየፍ አምላክ ነው፡፡ እስካሁን ባለው ሒደት ባርነትን ተቀብሎ ለመኖር (የሚያስኖረውም ያለ አይመስለኝም) ራሱን በማመቻቸት መጥፎ ምሳሌ እየሆነ ያለው አብዛኛው የዐዲስ አበባ ሕዝብ ነው፡፡ የሚገርመው ደግሞ ‹ነጻ አውጪዎች› የምንላቸው ራሳቸው ተቸግረው ነጻ አውጪ ሲፈልጉ ማየታችን የሚገርም ጉድ ነው፡፡ አንድ በጽኑ የታመመ÷ ግራ ገብቶት ግራ የሚያጋባ÷ በሚዲያ ላይ መቅረብ የማይገባው÷ ነውርን ገንዘቡ ያደረገ ዘመድሁን የተባለ ዱርዬ እያዳመጡ ራሳቸውን ለልዩነት ሲያመቻቹ ማየት በእጅጉ ያምማል፡፡ የፈለገው የተደራጀ ሆዳም ከፋፋይ ይኑር በዓላማ አንድ ሆነው ለዛ ዓላማ ውድ ሕይወታቸውን ለመስጠት ጨርቄን ማቄን ሳይሉ ዱር የገቡ ወንድማማቾች ልዩነታቸውን በመነጋገር ፈተው፣ ዕርቅ አውርደው፣ ትልቁን አገራዊ ሥዕል እየተመለከቱ ኅብረት÷ አንድነትና ድርጅት መፍጠር ካልቻሉ መከራችን ገና ነው ማለት ነው፡፡ ወንድማማቾች ይቅር ካልተባባሉ ክርስትናውም ሆነ እስልምናው የይስሙላ ነው ማለት ነው? እውነት አገር ወዳድ÷ ሕዝብና አገርን የሚያስቀድሙ ምሁራን አሉን? በጥቅሉ ለመናገር እንጂ በጣት የሚቆጠሩትን ዘንግቼ አይደለም፡፡ ነፍሳቸውን በአፀደ ገነት ያኑርልንና አንጋፋው የአደባባይ ምሁር ፕሮፌሰር መሥፍንና ጓደኞቻቸው ከተለዩን በኋላ ባገር ደረጃ ትልቅ ክፍተት ተፈጥሮአል፡፡ እነዚህን ምድር ላይ ከዘረኛ ፋሺስቶች ጋር የሚፋለሙ ጀግኖች ወገኖቻችንን በመልካም ምክር፣ በአደረጃጀት፣ በተጠናና በታቀደ መልኩ ዘላቂውን ፍኖት በማሳየት አሁን ካላገዙአቸው ለመቼ ነው የሚሆኑን? እስከመቼ ስድብና ሃሜት ፈርተን እንደ ሰጎን ራሳችንን ‹አሸዋ› ውስጥ ቀብረን እንኖራለን? ምን ዓይነት ኅሊና ነው ይሄንን ዝምታ የሚፈቅድ? በትግሉ ውስጥ ካሉትም መካከል ከጋራ ዓላማው አፈንግጦ ለጠላት ራሱን ያመቻቸውንና ተመክሮ ተዘክሮ አልመለስ ያለውን ለጠቅላላው ጥቅም ሲባል መለየት የግድ ነው፡፡ የግል ምኞቱን መከተል ሲፈልግ ያን ጊዜ ራሱን አስቀድሞ ለይቷልና፡፡
ጭቆናን እና ጨቋኝን እምቢ የሚል የአንድ አገር ሕዝብ ከዚህ ዓይነቱ የግፍና በደል አገዛዝ ነጻ ሆኖ ለሕዝብ ሁሉ የእኩልነትና የፍትሕ ሥርዓት በማምጣት ሕዝብና አገርን ወደ ዕድገትና ልማት ጎዳና ሊመራ የሚችለው አገር ውስጥ በሚካሔድ ትግል ነው፡፡ በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ (ዜግነቱን የቀየረው ጭምር) አስተዋጽኦ እጅግ ውሱን ነው፡፡ እንደኔ በውጩ በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጌ የምወስደው አገር ውስጥ የሚካሔደውን ትግል በመከፋፈልም ሆነ የተለያዩ አፍራሽ አጀንዳዎች በመያዝ ከማዳከም መቆጠብን ነው፡፡ ከተቻለ ደግሞ (እስካሁን እንዳደረጋችሁት) ትግሉን በዐቅም መደገፍና በፋሺስታዊ ኃይሎች እልቂትና ጥፋት እየደረሰበት ያለውን ሕዝብና አገር መልሶ ለማቋቋም የድርሻን መወጣት ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ፈረንጆችን ደጅ በመጥናት የሚገኝ አንዳች በጎ ነገር የለም፡፡ የሩቁን ትተን ያለፉት ሃምሳ ዓመታት ተሞክሮዎች ካላስተማሩን የዋሆች ሳንሆን ሞኞች ነን፡፡ በዚህ ረገድ በምዕራቡ ዓለም በስደት የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ፊደል ቈጠርሁ የሚለው ጭምር (በነሱ የሚብስ ይመስለኛል) በአመዛኙ አእምሮው በምዕራባውያን አስተሳሰብ ቅኝ የተገዛ በመሆኑ ባርነትን በመንፈስም በተግባርም ይዞ ከሚመጣ በቀር የፈየደውም ሆነ የሚፈይደው በጎ ነገር የለም፡፡ ‹ያ በሚባለው ትውልድ› አማካይነት የምሥራቁ ዓለም አልቦ እግዚአብሔር የሚል ኮሚኒስታዊ ነቀርሳ ተክሎብን የጥፋቱን መንገድ ጀመርን፤ ከዚያም ምዕራባውያኑ ኢትዮጵያን ለማጥፋት ወያኔ ትግሬን ነቀርሳ አድርገው ተከሉብን፤ አሁን ደግሞ የወያኔ ውላጅ የሆነው በኢትዮጵያ፣ በተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ በነባሩ እስልምና፣ በዐምሐራው ሕዝብ፣ በነባር መንፈሳዊ ባህላዊ እሤቶችና ቅርሶች ጥላቻ የሰከረ የለየለት ሰይጣናዊ ቡድን ነጮቹ ለወያኔ የሰጡትን አጋንንታዊ ተልእኮ እስከ ጥግ ድረስ ለመፈጸም ቃል ገብቶ በዓለም ታይቶ ተሰምቶ የማይታወቅ አረመኔያዊ ድርጊት በየዕለቱ በመፈጸም ኢትዮጵያን ምድራዊ ሲዖል አድርጓታል፡፡
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግስት ጀምሮ ላለፉት ሰባ ዓመታት በላይ አብዛኛው ምዕራባውያን መንግሥታት አጋንንታዊ መሆናቸውን በተግባር አስመስክረዋል፡፡ በእጅ አዙር ሳይሆን በቀጥታ ቅኝ አገዛዝ ለማለት በሚያስደፍር ሁናቴ ለማይረካ የሀብት ማጋበስ/ዝርፊያ በዚህም የሚገኘውን የኢኮኖሚና ወታደራዊ የበላይነትን ይዞ ለመቀጠል ዓለምን እያመሱ ይገኛሉ፡፡ እነሱ ጣልቃ ገብተው ሁከትና ብጥብጥ የሌለበት አገር አናገኝም፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የሚባለው ድርጅትና ቅርንጫፎቹ፣ የዓለም አቀፉ የፋይናንስና የዓለም ባንክ የተባሉት ድርጅቶች እንዲሁም የነዚሁ ተቀጥላ የሆኑት ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የምዕራቦቹ አገሮች ኤምባሲዎች፣ የምዕራባውያኑ ወኪሎች በመሆን ዘመናዊውን የባርነት አገዛዝ በዓለም ላይ በተለይም በአፍሪቃ፣ በእስያና ላቲን አሜሪካ አገሮች በማስፈን የነርሱ ነውረኛ ባህልና አስተሳሰብ ማራገፊያ ወደቦች አድርገዋቸዋል፡፡ ከነዚህ አገሮች ጋር ባላቸው ዓለም አቀፍ ግንኙነት የቀረፁአቸው የውጭ ግንኙነት ‹‹ቋሚ›› ፖሊሲዎች አገሮቹንና ሕዝቦቻቸውን የደሀ ደሀ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ሁሌም በርስ በርስ ጦርነት፣ ግጭት፣ የረሃብና በሽታ አዙሪት ውስጥ በመዝፈቅ ዕውቀት፣ ዕድገትና ልማት እንዳይኖር አጥብቀው በመሥራት ላይ የተመሠረቱ ናቸው፡፡ ይህንንም የሚያስፈጽሙት የገዛ ሕዝባቸውን ቁም ስቅል የሚያሳዩ ሰይጣናዊ አገዛዞችን በቅጥረኝነት በማስቀመጥ ነው፡፡ በዚህ አጋንንታዊ ግብር ሰለባ ከሆኑት ግንባር ቀደም አገሮች መካከል ሕያው ምሳሌ የሆነችው አገራችን ኢትዮጵያ ናት፡፡ ለምሳሌ አሜሪካ ኢትዮጵያን አስመልክቶ የምትከተለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሄንሪ ኪሲንጀር በሚባል የአጋንንት ውላጅ ተቀርፆ ለዘጠና ዓመታት ገደማ አሁንም ድረስ ሥራ ላይ ይገኛል፡፡ ሰነዱ በአሁኑ ጊዜ ምሥጢራዊነቱ አብቅቶ በይፋ ባደባባይ የሚገኝ ነው፡፡
ቴድ ቬስታል የተባለ የኦክላሆማ ግዛት ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር አሜሪቃ በኢትዮጵያ ላይ ስለምትከተለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የሚከተለውን ጽፎአል፡፡ ኋላ የአሜሪቃ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበረው እና እ.አ.አ. በ1972 ዓ.ም. የፕሬዚዳንት ኒክሰን የብሔራዊ ጸጥታ ዋና አማካሪ የነበረው ሄንሪ ኪሲንጀር ይህንን አማክሯል፤ ‹‹ ይህ በኢትዮጵያ መጻኢ ሁናቴ ላይ የቀረበ ምሥጢራዊ ሪፖርት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በምትባለው አገር ላይ አሜሪቃ ልትከተለው የሚገባ የውጭ ፖሊሲ የአገሪቱን ስስ ብልት ማለትም ጐሣን፣ ሃይማኖትን በመጠቀም እና በመከፋፈል በማያቋርጥ የውስጥ ግጭት ውስጥ በማቆየት ያልተረጋጋች እንድትሆን ማድረግ ያስፈልጋል በማለት የፖሊሲ ሐሳብ አቅርቧል፡፡››
⇐ ሰነዱን አንብቡት፡፡ ምን ያህል በቂም በቀል፣ በዘረኝነትና በጥላቻ የተሞላ እነደሆነ ትረዳላችሁ፡፡ ፖሊሲው ተግባራዊም ሆኖ እስካሁን ዘልቋል፡፡ ይህንን አቋም በሰላማዊ ሰልፍና በጩኸት ማስቀረት ይቻላል? እኔ በግሌ ባላምንበትም እንኳ እስከዛሬ በአሜሪካና በአውሮጳ በተደረጉ ሰላማዊ ሰልፎች ይህንን ጉዳይ አጀንዳ አድርጎ በጽሑፍም በተቃውሞም የገለጸ አለ? ከተሳሳትሁ እታረማለሁ፡፡ በእኔ ዕውቀት ግን ያለ አይመስለኝም፡፡ ለወቅታዊ ጉዳዮች ጮኾ ከመመለስ በቀር፡፡ ጨክነን እንናገር ካልን ላንድ ዐምሐራ ማኅበረሰብ በየግዛቱ የተቋቋመው የማኅበራት ጋጋታ ለዓመታት የፈየደው የለም፡፡ አባላቱን አንድ አድርጎና አስተባብሮ ለአንድ ዓላማ አሰልፎአል ለማለት አይቻልም፡፡ በእኔ ትሁት ምልከታ ከልማቱ ጥፋቱ አመዝኖ ይታየኛል፡፡ አልፎ አልፎ የሚታዩ (ያውም በወጣት ልጆች) የግል ጥረቶችን ግን ሳላደንቅና ሳላከብር አላልፍም፡፡
‹‹የትግል ሚዲያ›› በሚባሉትም ያለው እንቅስቃሴ ‹‹የእሳት አደጋ›› ዓይነት አሠራር እንጂ በዕውቀት፣ በጥናት፣ በሙያ ያልታገዘ፤ ዘላቂውን የማይመለከት የዕለት ተዕለት ጉዳዮችና መረጃዎች ላይ የሚያተኩር፣ የአንድ ወይም የሁለት ግለሰቦች ስሜታዊ ጩኸት የጎላበት (በጊዜያዊ ፈንጠዝያና ልቅሶ የተሞላ)፣ ዐዋቂዎችን በበቂ ሁናቴ የማያሳትፍ፣ በትርፍ ጊዜ የሚሠራ፣ ውጭ ተቀምጦ ትግሉን ለመምራት የሚቃጣው፣ ለወታደራዊ ጉዳዮች ሁሉ መመሪያ ለመስጠት የሚዳዳ፣ የሚዲያ መደበኛ ፎርማት የሌለው ግርግር ነው፡፡
ከፋሺስታዊው አገዛዝ ወዳጅነት ‹‹ምልሶች›› የሆኑት ሚዲያዎች ‹‹የትግል ሚዲያ›› የተባሉትን ጠባያት ባብዛኛው የሚጋሩ ሆነው፤ አቋም የለሾች፣ አንዳንዶቹም ከፋሺስታዊው አገዛዝ ጋር በኅቡዕ የሚሠሩ፣ በዋናነት ለሆዳቸው የተሰለፉ ወይም ገንዘብ መቃረምን መሠረታዊ ዓላማቸው ያደረጉ ሆነው ይታያሉ፡፡ በሕዝብ የግብር ገንዘብ ስለሚተዳደሩት ‹‹የመንግሥት ተብዬዎች›› እና ለአገዛዙ ዘብ የቆሙ አጋር ሚዲያዎችን በሚመለከት ብዙ ተብሏል፡፡ ባጭሩ አገር በማፍረሱ፣ ሕዝብን በማስጨፍጨፉ እና በማፈናቀሉ፣ ብሔራዊ ቅርሶችን እና እሤቶችን በማጥፋቱ ሒደት ግንባር ቀደም ተዋናዮች ናቸው፡፡ በውስጡም የተሰገሰጉት ሆዳቸው አምላካቸው የሆኑና ከኅሊናቸው የተፋቱ ግለሰቦች ናቸው፡፡
በዝርወት በውጭ የሚኖረውና ቊጥሩ ቀላል የማይባል ‹ኢትዮጵያዊ› የምዕራቡን መንግሥታት ጠባይ፣ ዓላማና ‹ብሔራዊ ጥቅም› ባለመረዳት ይሁን ወይም ዝም ከማለት ይሻላል በሚል አስተሳሰብ አልፎ አልፎ በቤተ መንግሥታቸው፣ በየምክር ቤቶቻቸውና በኤምባሲዎቻቸው በአለፍ ገደም ጩኸት ማሰማቱ ለውጥ ያመጣ ይመስል ሲደክሙ ይስተዋላል፡፡ በየትኛውም አገር ቢሆን በጎ ሰዎች አይጠፉም፡፡ እንደ ሰው ልጅ የሌሎች በደልና መከራ ሊሰማቸው ይችላል፡፡ ሐሳባችንን፣ ስሜታችንን ሊጋር ይችሉ ይሆናል፡፡ ሊያዝኑና በመንፈስ አጋርነታቸውን ሊያሳዩን ይችሉ ይሆናል፡፡ ከእኛ ስንፍና ጋር ተደምሮ ትርጕም ያለው እገዛና ለውጥ መጠበቅ ግን የዋኅነት ነው፡፡ ከዕብደቱ ወጥተን ወደ ዐቅላችን ብንመለስ እኛ ለራሳችን አናንስም ነበር፡፡ ለአሜሪካ ፕሬዚዳንትነት ወይም ምክር ቤትና ሴኔት አባልነት የሚወዳደሩ እጩዎችን በመደገፍ ወይም በመቃወም ለኢትዮጵያ ጠብ የሚል በጎ ነገር ያለ ይመስላችኋል? በጭራሽ ራሳችንን አናታልል፡፡ በዚህ ረገድ አውሮጳም ተመሳሳይ ሳይሆን አንድ ዓይነት አቋም ነው ያላት፡፡ የነሱ ደግሞ ከቅኝ ግዛት ዘመን ጀምሮ ስር የሰደደ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ላይ ሲያራምዱ ለቆዩትና አሁንም ለሚያራምዱት ሰይጣናዊ ፖሊሲ ንድፉን (ብሉ ፕሪንቱን) ያዘጋጀው ሎርድ ማኩሌይ የተባለ እንግሊዛዊ መሠሪ የፖርላማ አባል የዛሬ 190 ዓመት ገደማ እ.አ.አ. ፌብሯሪ 2/1835 ለእንግሊዝ ፓርላማ የሚከተለውን ንግግር አድርጓል፡፡
‹‹በአፍሪቃ ከጫፍ እስከ ጫፍ ተጓዝሁ፤ ሀብት የተትረፈረፈባት፣ ደሀና ሌባ የሌለባት፣ ከፍተኛ ግብረ ገብ ያለው ሕዝብ ኢትዮጵያ በምትባል አገር አየሁ፤ እንዲህ የላቀ ችሎታ ያለው ሕዝብ ባለቤት የሆነን አገር አከርካሪውን ማለትም መንፈሳዊና ባህላዊ ቅርሶቹን መስበር ካልቻልን መያዝ የሚሞከር አይደለም፡፡ ስለዚህ እኔ የማቀርበው ሐሳብ የዚህችን አገር ጥንታዊ የትምህርት ሥርዓት እና ባህሏን በመቀየር የውጭ እና የእንግሊዝ የሆነ ሁሉ ከነሱ እንደሚበልጥ እንዲያስቡ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ በዚህም ክብርና ኩራታቸውን እንዲሁም ሀገር-በቀል ባህላቸውን እንዲጥሉ በማድረግ እኛ እንደምንፈልገው – በእኛ የበላይነት የሚመራ አገር ማድረግ እንችላለን፡፡››
ከዚያም ይህ አገር አጥፊ ፖሊሲ በነ ሮማን ፕሮሀዝካና ደቀመዛሙርቱ (Roman Procházka – “Ethiopia: the Powder Barell” ደራሲ) እና በየዘመኑ በተነሡ የምዕራቡ አገር መሪዎች ግዘፍ ነሥቶና ተግባራዊ ሆኖ በቅብብሎሽ ቀጥሏል፡፡
ከፍ ብለን ያነሣነው ኦስትሪያዊው ሮማን ፕሮሀዝካ በዓድዋ ድል እርር ድብን ብሎ የዛሬ 90 ዓመት ገደማ – በ2ኛው የጥልያን ወረራ ዋዜማ – የጻፈው መርዘኛ ድርሰት ምዕራባውያን ኢትዮጵያ ላይ ለሚከተሉት የውጭ ፖሊሲ መሠረት ሆኗል፡፡ በዚህ ጽሑፉ (ጩኸቴን ቀሙኝ እንደሚባለው) የኢትዮጵያን ዘውዳዊ ሥርዓት ‹የአቢሲኒያ ኢምፔሪያሊዝም› ብሎ ከመክሰሱም በተጨማሪ፣ ሥርዓቱ በዐምሐራ ነገድ የበላይነት የሚመራና ሌሎቹን ጐሣዎች ሁሉ ጨቁኖ የሚያስተዳድር መሆኑን ገልጾ፣ ዛሬ ያለው የኢትዮጵያ የዓፄዎቹ ግዛት የራሱን ፖሊሲ ለማመንጨትና ለመከተል አሁንም ሆነ ምናልባት ለመጪዎቹ ብዙ ዐሥርታት ብቁ አይደለም፤ ይህንንም እንዲሞክር መፍቀድ ከሠለጠነው ዓለም ጥቅም ጋር በእጅጉ የሚፃረርና የዓለምን ሰላም በከፋ መልኩ አደጋ ላይ የሚጥል ነው ብሏል፡፡ በተጨማሪም ከሕዝቡ አብዛኛውን ቊጥር የሚይዙት ዐምሐራ ያልሆኑት የኢትዮጵያ ነገዶች የአቢሲኒያ ኢምፔሪያሊዝም ሰለባ በመሆናቸው፣ የኢምፔሬያሊዝም ተቃዋሚ የሆናችሁ ሁሉ እነዚህን በጉልበት ተስፋፊዎች የሆኑ የኤምፔሪያሊስት ኃይሎችን እንደተጨቆኑ በመቊጠር ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው አድርጎ መውሰዱ ስሕተት መሆኑን በመጽሐፉ መቅድም ላይ ተናግሯል፡፡ በዚህም ምዕራባውያን ኢትዮጵያ በጥልያን ስትወረር ጀርባቸውን እንዲሰጡ የአንበሳውን ሚና ከመጫወቱ ባሻገር ለፋሺስት ጥልያን እና ለቡችሎቻቸው ወያኔዎች ጐሠኛነት መርዛማ ዘር ትቶ አልፎአል፡፡ (ዝርዝር ሐሳቡን ለመረዳት የእንግሊዝኛውን ትርጕም ወይም በአርቲስት ደበበ እሸቱ የተዘጋጀውን የዐማርኛ ትርጕም ማንበብ ይቻላል)
በምዕራባውያን በኩል ለሚታየው ሥር የሰደደ ጥላቻ፣ ዘረኛነትና ንቀት መሠረቱ የሰው ልጅ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እኩል መሆኑን ያስመሰከረውና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች ፈርጥ የሆነው፣ በፀረ ቅኝ ግዛትና ፀረ ፋሺስታዊ ተጋድሎ ያንፀባረቀው የዓድዋ ድል ሲሆን፤ ነጻነታችንን አስከብሮ ለማቆየት ዓይነተኛ ሚና የነበራት፣ የአብዛኛውን ሕዝብ ብሔራዊ ሥነ ልቦናዊ ውቅር የሠራች፣ አገራችን ከቆመችባቸው አዕማድ ቀዳሚና ዋነኛዋ የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮና እሤቶቿ ናቸው፡፡ ምዕራባዊ አሳዳሪዎቻቸውም ሆኑ ቅጥረኞቹ ዒላማ ያደረጓት ያለምክንያት አይደለም፡፡ ለዚህ የጥፋት ተግባር ደግሞ በውስጥ በውጭም የሚገኙ አብዛኛዎቹ (ከመንፈሳዊነት የተራቆቱ) ከፊሉም ክህነታቸውን ያፈረሱ ‹እነ አባ ለከርሡ› ከፋሺስቶቹ ባልተናነሰ እየተባበሩ ይገኛሉ፡፡ የምእመኑን ገንዘብ ብቻ የሚፈልጉት አባ ለከርሡዎች ምእመኑ በቤተ ክርስቲያኒቱ ህልውና አያገባውም ብለው በድፍረት ከመናገር አልፈው ሲዘልፉም ይሰማሉ፡፡ ባንፃሩም የበዓል ክርስቲያን ሆኖ የሚታየው በርካታ ምእመንም ግዕዛን እንደሌላቸው እንስሳት በመሆን፣ አንዳንዱም ክርስትናውን በቅጡ ባለመረዳት ጽድቅና ማክበር እየመሰለው እነ አባ ለከርሡ ለፋሺስቶች አሳልፈው የሚሰጡትንና ለሕዝብ መጨፍጨፊያ የሚውለውን ሀብትና ንብረት የ‹ቴሌቶን› መድረኮች በሆኑት የንግሥ በዓላት ብቻ ሳይሆን በአዘቦቱም ቀን በካድሬዎች ጩኸትና ከንቱ ውዳሴ እየተመራ በትኖ መሔዱ የዓመታት አሳዛኝ ትዕይንት ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ዛሬ እግዚአብሔር ባወቀ በበርሃ ወድቀው ላገር ለወገን ከሚለምኑ አባቶችና እናቶች እንዲሁም አንዳንድ መንፈሳዊ ምእመናን በስተቀር የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በቤተ ክህነቱ ሰው የላትም፡፡ ድፍረቱ ሰማይን በርግጫ መምታት ደርሷል፡፡
ጽሑፌን ለመቋጨት ምዕራባውያን መንግሥታት እኛን ኢትዮጵያውያንን የሚቤዡ ወይም የሚታደጉ ሳይሆኑ በተቃራኒው ሌት ተቀን ለውድቀታችን የሚሠሩ ናቸው፡፡ ይሄ አስተያየት ሳይሆን መሬት የያዘ መሪር ሐቅ ነው፡፡ አሁን ያለንበት ኢ-ፍትሐዊ ዓለም የሚመራው ‹ጉልበት ትክክል ነው› በሚለው አጋንንታዊ መርህ ነው፡፡ የሚያከበርውም አሸናፊ ጉልበተኛውን ብቻ ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ብንዘገይም የያዝነው የተቀደሰ ዓላማ – የሕዝባችንን ህልውና ማስከበርና የአገር አንድነትን መታደግ – ሲሆን፣ እያካሔድን ያለነውም ፍትሐዊ ጦርነት/ትግል ነው፡፡ ለዚህ የተቀደሰ ዓላማ ለመሞት ጀግንነቱ፣ ቆራጥነቱ አልጎደለንም፡፡ የጎደለን ኅብረት፣ አንድነትና ድርጅት ነው፡፡ ይህንንም በዕውቀትና በብልሃት መምራት ነው፡፡ ከፋሺስታዊው ዘረኛ አገዛዝ በበለጠ ዐቢይ እንቅፋት የሆኑብንም በውስጥና በውጭ የሚገኙ ከሃዲ ባንዳዎች በመሆናቸው እነሱን ያለርኅራኄ ማጽዳት ይጠበቅብናል፡፡ ይህን አድርገን ከባርነት ነጻ ከወጣን በድሉ ማግስት ነጮቹ ሳንጠይቃቸው ለራሳቸው ብሔራዊ ጥቅም ሲሉ ተሽቀዳድመው ይመጣሉ፡፡ ያኔ እኛም ብሔራዊ ጥቅማችንን መሠረት አድርገን የውጭ ግንኙነታችንን መስመር እናስይዛለን፡፡ ይህም ሲባል ከወዲሁ በዲፕሎማሲውና ዓለም አቀፍ ግንኙነት፣ በሴኩሪቲና ስትራቴጂ መስክ ዕውቀቱና ልምዱ ያላቸው አገርና ሕዝብን የሚወዱና የሚያስቀድሙ (እንደ ጋሽ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ ያሉ) በሳል ኢትዮጵያውያን በኩል ተከታታይነት ያለው ጥረት ማድረግን ይጠይቃል፡፡ ስለሆነም በአገር ቤት ያለው ኢትዮጵያዊ (የፋሺስታዊው አገዛዝ ግንባር ቀደም ገፍት ቀማሽ ከሆነው የዐምሐራ ሕዝብ ውጪ ያለው ባጠቃላይ) ለጥፋት የተደገሰለትን ወር ተረኛነትና ነጻ አውጪ ሳይጠብቅ ሲችል ተደራጅቶ፣ ካልቻለ ደግሞ የየግል ድርሻውን መወጣት ይጠበቅበታል፡፡ በዝርወት የሚኖረው ማኅበረ ግዩራኑም (ዳያስጶራው) በደመ ነፍስ ከሚመራ እንቅስቃሴ ወጥቶ ዘላቂውን ግምት ውስጥ ያስገባ በዕውቀትና ጥናት ላይ የተመሠረተ፣ የውስጡ ትግል በቶሎ መቋጫ የሚያገኝበት እገዛ ላይ ቢጠመድ መልካም ይመስለኛል፡፡