>
10:12 pm - Sunday August 7, 2022

የከሚሴ፣አጣዬ፣ካራቆሬና የማጀቴ ጥቃት እና ሴራዉ  … (ውብሸት ሙላት)

የከሚሴ፣አጣዬ፣ካራቆሬና የማጀቴ ጥቃት እና ሴራዉ  …
ውብሸት ሙላት
በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ራሱን የማስተደዳር ሥልጣን ያለዉ አካባቢ ነዉ፡፡ በወረዳዎች ተከፋፍሎ…. እስከ ባቲ ድረስ አፋርን እያዋሰነ ይዘልቃል፡፡ በዚህ ዞን፣ ስፍር ቁጥር የሌላቸዉ ባለሥልጣኖችም ሆነ መደበኛ ሠራተኛ የሚመጣዉ ከአንድ አካባቢ ብቻ ነዉ-ከወለጋ፡፡
ራሱን ችሎ በልዩ ዞንነት መተዳደር በጀመረበት ወቅት ገደማ የኦነግ ታጣቂዎች በአካባቢዉ ችግር ሲፈጥሩ እንደነበር ይታወቃል፡፡
በዚህ ዞን ዉስጥ፣ የክልሉ የሰላምና ደኅንነት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ብርጋዴር ጀኔራል አሳምነዉ ጽጌ እንደገለጹትም ጭምር፣ የተደራጀ የጦር ካምፕና ማሠልጠኛ አለ፡፡ ኃላፊዉ ይፋ ካደረጉት እንኳን ወራት ተቆጥረዋል፡፡
በመሠረቱ፣ በምእራብ ና ሰሜን ጎንደር ዞኖች ዉስጥ የነበረዉ፣ በቅማንት ኮሚቴ ሽፋንና ተገን፣ ከከሚሴዉ ጋር ተመሳሳይ ነዉ፡፡ በጎንደር የነበረዉን በቀጥታም በቁሳቁስም (በትጥቅና ስንቅ) ስፖንሰር አድራጊዋ “አማራን ሳናጠፋ አንሞትም” ብለዉ የመጨረሻ ጣራቸዉን የሚጣጣሩት በጣት የሚቆጠሩ የሕወሃት ቁንጮዎች ናቸዉ፡፡ ይህን ግባቸዉን ለማሳካት በሱዳን፣በደቡብ ሱዳን፣በኬንያ፣በሶማሊያ እና በጂቡቲ ያላቸዉን ሃብት ጥቅም ላይ እያዋሉ ነዉ፡፡ ባለ በሌለ አቅማቸዉ እየተወራጩ ነዉ፡፡
እነዚህ በጣት የሚቆጠሩ የሕወሃት ሰዎች፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሁለተኛ ዙር አማራን የማጥቃት ዘመቻቸዉን ጀምረዋል፡፡ ዋና ተባባሪያቸዉ ደግሞ እንዲሁ በገንዘብ የተሸጡ እና በዓላማ የሚመሳሉ (አማራን የማጥፋት ተመሳሳይ ግብና እቅድ ያላቸዉ) ኦነግ ዉስጥ ያሉ ቡድኖች ናቸዉ፡፡
ከሚሴ እና በዙሪያዉ የሚንቀሳቀሰዉ የኦነግ ጦር በትጥቅ ደረጃ ከአነስተኛ የጦር መሳሪያ በላይም ቀላል መሳሪዎች (Light weapons) (ለማንቀሳቀስ ከአንድ ሰዉ በላይ የሚያስፈልጋቸዉ) ጥቅም ላይ እየዋሉ ነዉ፡፡ በተለይ አጣዬና ማጀቴ አቅራቢያ ላይ በሰፊዉ ጥቃት ሲፈጽሙባቸዉ ነበር፡፡
ይሄ የጥቂት ሕወሃት እና የኦነግም ዉስጥ የተወሰነዉ ቡድን በአንድነት ሆነዉ አገሪቱን እያተራመሷት ነዉ፡፡ የሰኔ 16ቱ የግዲያ ሙከራ፣ ወለጋ ላይ የነበረዉ ጦርነትን እንደምሳሌ ማንሳት ይቻላል፡፡ ይሔዉ የሕወሃት ቡድን የቅማንት ኮሚቴ በሚል ሰበብና ሽፋን በሱዳን በኩል በቦቴ ስፍር ቁጥር የሌለዉ የጦር መሳሪያ ሲያስገባና ለማስገባት ሲሞክር መያዙም ይታወቃል፡፡ ነገር ግን የፌደራል መንግሥት ምንም ዓይነት እርምጃ እየወሰደ አይደለም፡፡ አልወሰደምም፡፡ ከሚሴ አካባቢም እንደ ቋራው የጦር ምሽጎች መኖራቸዉን እየሰማ የፌደራል መንግሥት እርምጃ አልወሰደም፡፡ ግጭት እስኪከሠት ይጠብቃል፡፡
በቅርቡም፣ በሰሜን ሸዋ፣ ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ወደ 50 ኪሎ ሜትር ያህል የኦነግ ወታደር ገብቶ ግጭት ከፈጠረም በኋላ የፌደራል መንግሥት ምንም እርምጃ አልወሰደም፡፡
ከእነዚህ ጥምር ቡድኖች በተጨማሪ ደግሞ፣ አንዳንድ የዋህ ሰዎች፣በተለይ ወሎን በሚመለከት፣የእነዚህ ሁለት ቡድኖች የትሮይ ፈረስ በመሆን እያገለገሉ ነዉ፡፡ ከትሮይ ፈረሶቹ ባለፈ ግን በሚዲያ በኩል አጋር ቡድኖችም አሉ፡፡ የእነዚህ በጣት የሚቆጠሩ የህወሃት እና የኦነግ ጥምር ቡድኖች! የፌስቡክ ገጻቸዉን ተመለከቱ! የከሚሴዉ አካባቢ ግጭት እንዲፈጠር ከመቼ ጀምረዉ ያሟርቱም ይሰሩም እንደነበር! ከህወሃት በኩል ያሉት ሁለት ዓመታት አልፏቸዋል፡፡ አሁን ግን በተደራጀ መልኩ መጥተዋል፡፡ እንደዉም አርሲና ባሌም ሌላ ግጭት እንደሚኖር እየጠቆሙ ነዉ፡፡
የአማራ ክልልን የግጭት ማሰሮ (Cauldron of Violence) ለማድረግ በበቀል ስሜት የሚሠራን ቡድን ምንም ዓይነት እርምጃ አለመዉሰድ፣በተግባር ከእዚህ ቡድን ጋር መተባበር ነዉ፡፡ በየእለቱ የሰዉ ሕይወት እየጠፋ፣ የአማራ ክልልን የግጭት ቀጠና እንዲሆን የፌደራሉም መንግሥት እየተባበረ ነዉ፡፡ ምክንያቱም አገር አተራማሾቹን፣ግጭት አምራቾቹን እያወቀ አዲስ አበባና መቀሌ ላይ ተቀምጠዉ (እነዚህ በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች) ሰዉን እያጫረሱ ነዉ፡፡ ይሔንንም የፌደራሉ መንግሥት እያወቀ፣ቢያንስ ለሕግ ባለማቅረብ፣ከለላ አድርጎላቸዋል፡፡
ለእነ ጌታቸዉ አሰፋ ሲሆን በሕግ መጠየቅ የለም፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪም በቅርቡ በድጋሜ እንደገለጹት ፖለቲካዊ መፍትሔን ስለተመረጠ ነዉ ብለዋል፡፡ ይሄን ሁሉ ወንጀል እየሠሩ፣ የሰዉ ህይወት እንደ ቅጠል እየረገፈ፣ ለአንዱ ፖለቲካዊ መፍትሔ በሚል ይዘቱም ዉጤቱም የማይታወቅ መንገድን መርጦ፣ ሌሎች የኦነግ አመራሮችን ደግሞ ሆቴል እየቀለቡ መኖር መንግሥታዊ ተግባር ነዉ ማለት አስቸጋሪ ነዉ፡፡ አገር በመንግሥት ጸሎት አትመራም፡፡ አገር በመንግሥት ምክር አትመራም፡፡ ጸሎትና ምክር የመንግሥት ተግባር አይደለም፡፡ ከመንግሥትም አይጠበቅም፡፡
መንግሥት ከአገር አተራማሾች ይልቅ ለዜጎች መከታና ከለላ ይሁን! መንግሥት የአማራ ሕዝብ ላይ የተደራጀ፣ የታቀደ፣ጠቀነባበረ ጥቃት ፈጻሚዎችን ለሕግ ያቅርብ! እርምጃ ይዉሰድ!
(ለመዉጫ፡- አስክንድር ነጋ በራስ ሆቴል መግለጫ እንዳይሰጥ የጸጥታ ስጋት እንደነበር ነግሯል፡፡ የፖሊስ የምርመራ ዉጤቱ ለምን ይፋ አይደረግም እነማን እስክንድር ላይ ጥቃት በመፈጸም ተባብረዉ ነበር? ለምን ይፋ አልሆነም? ለምን ይፋ አይሆንም?)
Filed in: Amharic