>

አገዛዛዊ ዝርፊያን ሕጋዊ ማድረግ (ከይኄይስ እውነቱ)

አገዛዛዊ ዝርፊያን ሕጋዊ ማድረግ

ከይኄይስ እውነቱ

 

በዓለም ላይ በገዛ አገሩ የራሴ የግሌ የሚለው ኩርማን መሬት የሌለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፡፡ የኦነጎቹ አገዛዝ ደግሞ ይሄም ሳያንሰው ኢትዮጵያዊ አስከሬኑ የሚያርፍበት ግማሽ ክንድ ከስንዝር መሬት ነፍጎታል፡፡

ቀደም ባሉ መጣጥፎቼ በወንጀል አገዛዝ ሥርዓት ውስጥ ሕግ በጉልበት የተገኘን ሥልጣን ማራዘሚያ፣ የአገር ሀብትና ቅርስ መዝረፊያና ማውደሚያ፣ የዜጎች መብትና ነፃነት መንፈጊያ መሆኑን ለመግለጽ ሞክሬአለሁ፡፡ ምላጭ ቢያብጥ በምን ይበጡታል እንደሚባለው በርካታ ‹ሕጎች› ሕገ ወጥ ሲሆኑ ምን ይደረጋል? 

የወንጀል ሥርዓት የሆነው የኦሕዴድ/ኦነግ አገዛዝ ጥር 17 ቀን 2014 ዓ.ም. በነጋሪት ጋዜጣ አትሞ ባወጣው ዓዋጅ ቊ. 1263/2014 አንቀጽ 54 እና ዓዋጁን መሠረት አድርጎ በወጣው ደንብ ቊ. 487/2014 ዓ.ም. መሠረት ‹‹የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ›› የሚባል ተጠሪነቱ ለአገዛዙ ጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት የሆነ ተቋም አቋቁሟል፡፡ 

ባለፉት 32 ዓመታት ባጠቃላይ፣ ባለፉት 4 ዓመታት በተለይ የመንግሥት አስፈጻሚ አካለት የሚባሉ መ/ቤቶች ሥልጣንና ተግባራቸውን ለመወሰን እንደወጣው ዓዋጅ በተደጋጋሚ ሲሻሻልና ሲሻር የቆየ ሕግ የለም፡፡ አገዛዞች በቃዡና የራሳቸውን ፍላጎት ለማስፈጸም በፈለጉ ቊጥር የሚቀያየረው ይህ ሕግ የመንግሥት መ/ቤቶች ተረጋግተው ሥልጣንና ተግባራቸውን ባግባቡ እንዳይወጡ፣ የወደፊቱን በጥናት ላይ ተመሥርተው ተንብየው እንዳይዘጋጁና ለዕቅድና ትግበራ እንቅፋት ከመሆኑ በተጨማሪ ለሀገራዊ ሀብት ብክነት የበኩሉን አሉታዊ ተጽእኖ አድርጓል፡፡ የወታደራዊው ደርግ አገዛዝን ጨምሮ ኢትዮጵያን መቀመቅ የከተቱት የአገዛዝ ሥርዓቶች (ወያኔና ኦነጎቹ የተረኝነት ካልሆነ መሠረታዊ ልዩነት የላቸውም) አንዱ መገለጫ ሆኖ የቆየው ለግለሰብ ባለሥልጣኖች ሲባል በግብር ከፋዩ ዜጋ የሚተዳደር መ/ቤት በዓዋጅ/ደንብ ይቋቋም እንደነበር ከዚህ ቀደም በጻፍሑት ትዝብቴ ጠቁሜአለሁ፡፡

የወንጀል አገዛዝ ሥርዓቶቹ አመራሮችና ተከታዮቻቸው  (አድርባዮቹን ጨምሮ) በይፋ ዋሾና ሌቦች/ዘራፊዎች በመሆናቸው፣ ቊጥሩ ቀላል የማይባል የኅብረተሰባችን ክፍል እነዚህን ነውሮች እንደ ክብር መለያ እንዲቀበላቸው ከማድረግ በተጨማሪ የ‹ስኬት› አቋራጭ መንገዶች መሆናቸው በመንግሥት አስተዳደር መ/ቤቶች፣ በልማት ድርጅቶች እና በግሉም ዘርፍ መደበኛ አሠራር እስከመሆን ደርሰዋል፡፡ በግለሰቦችም ደረጃ መጥፎ ልማድ ሆኗል፣ አልፎም ‹ባህል› መስሏል፡፡ ሥልጣንን ተጠቅሞ የሕዝብን ሀብትና መሬትን ለራስ ጥቅም የሚያወሉ የወንጀል አገዛዞችን ነጮቹ የሌቦች አገዛዝ (kleptocracy) ይሉታል፡፡

ወደ ቀደመ ነገሬ ስመለስ፣ በዚህ ጽሑፍ መግቢያ ላይ የጠቀስኩት  ተቋም (የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ) መቋቋም ለምን አስፈለገ? በዓዋጁና በደንቡ የተመለከቱት ዓላማዎች፣ እንዲሁም ለተቋሙ የተሰጡት ሥልጣንና ተግባሮች ለተቋሙ አስፈላጊነት በቂ ምክንያቶች ናቸው? ይህን ተቋም ማቋቋም ሳያስፈልግ በሕጎቹ የተመለከቱትን ‹ዓላማዎች› (የሚታመንባቸው ከሆኑ) ማሳካት አይቻልም? አገራችን አገዛዙ (ሽብርተኞችን አሰማርቶ) በፈጠረው የሰላም እጦት፣ ዜጎች ባሉበት በሕይወት የመኖርና ካንዱ ክ/ሀገር ወደ ሌላው በነፃነት ተንቀሳቅሰው ለመሥራት በማይችሉበት ሁናቴ፣ በገፍ ተፈናቅለው ሜዳ ላይ ፈሰው እያሉ፣ በቢሮክራሲው፣ በልማት ድርጅቶች፣ በንግዱና በሌሎችም የኢኮኖሚ ዘርፎች ለዜጎች እኩል የመወዳደሪያ ሜዳ በሌለበት እና ኢኮኖሚው በዋናነት አገዛዝ-ወልድ በሆኑ ምክንያቶች ተንኰታኩቶ በሚገኝበት ወቅት፣ በግብር ከፋዩ ገንዘብ የሚተደደር የቢሮክራሲ መ/ቤት ማቋቋም ጤነኝነት ነው? በእነዚህ ጥያቄዎች መመዘኛነት በርካት የቢሮክራሲውን መ/ቤቶች ብንፈትሻቸው ከፍተኛ የሕዝብ ሀብት ብክነት ማሳያ ከመሆናቸውም አልፎ የሚያስቆጡና የሚያስገርሙም አሉበት፡፡ በወያኔ አገዛዝ አሽከሮች የነበሩት ያሁኑ ‹ተረኞች› ወያኔ በርካታ የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን (የሕዝብ ሀብቶች) በ‹ፕራይቬታይዜሽን› ሽፋን ለራሳቸው ሰዎች ወይም የዝርፊያ ተካፋዮቻቸው በ‹ነፃ› እንደመስጠት በሚቆጠር ዋጋ ከማስተላለፋቸውም በላይ አገዛዝ-ወለድ ‹ሞኖፖሊ› እንዲፈጠር ማድረጋቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ ፕራይቬታይዜሽን የሚመራበት ከዓዋጅ እስከ መመሪያ ሕግ ነበረው፡፡ በሕግ የተቀመጠውን ሥልጣንና ተግባር ያስፈጽማል ተብሎ የተቋቋመ መንግሥታዊ መ/ቤትም ነበረው፡፡ የውሸት ጨረታም ይካሄድ ነበር፡፡ ዝርፊያው በአገዛዙ የተደገፈ ስለነበር ማንም ሊያስቀረው አልቻለም፡፡ ስለሆነም ሕግ፣ ተቋም፣ የአሠራር ሥርዓት በወንጀል አገዛዝ ሥርዓት ውስጥ ለሕዝብና ላገር ዋስትና አይሆኑም፡፡ ይልቁንም የዝርፊያን ሂደት ሕጋዊ መልክ እንዲኖረው ያደርጋሉ፡፡

ከመነሻው ከፖሊሲ አኳያ እንዴት መንግሥት በኢኮኖሚው ውስጥ እስከ ችርቻሮ ንግድ ድረስ ገብቶ ዋና ተዋናይ ይሆናል? የሥራ አመራርና በሕግ ቊጥጥርና ክትትል የማድረጉን ዐቅም እስኪያጠናክር ድረስ ስትራቴጂክ ጠቀሜታ ያላቸውን የልማት ተቋማት ለጊዜው ይዞ ይቀጥል የሚለው አስተሳሰብ ተቀባይነት ቢኖረው እንኳ ይሄ ምናልባት የሚሠራው አገርና ሕዝብን በሚወድ ‹ቸር ዲክታተር›፣ (Benevolent Dictator) አገዛዝ ውስጥ ነው፡፡ የዋሾና ዘራፊዎች አገዛዝ ያልተጻፈ ‹የኢኮኖሚ ፖሊሲ› የአገዛዙን ሥልጣን የሚያስቀጥሉ፣ በንቅዘት የተበላሹ ‹አዳዲስ ሀብታሞችን› (“les nouveau riches”) በመፍጠር የወንጀል ሥርዓቱን የኢኮኖሚ ጡንቻ ማፈርጠም ነው፡፡ በወያኔና በወራሹ አገዛዞች የታየውና የቀጠለው ይሄ ነው፡፡ ብሔራዊ መለያና ኩራት የሆኑትን የቴሌኮሙኒኬሽንን እና የአየር መንገድ ድርጅቶችን ከዜጋም ለባዕዳን አሳልፎ ለመስጠት የተሰማማ አገዛዝ፣ የልማት ድርጅቶችን ዐቅም ላላቸው ዜጎችና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ንቅዘት፣ አድሎና ሸፍጥ በሌለበት ግልጽና ተጠያቂነት ባለበት አሠራር  ለምን አያስተላልፋቸውም? እንዲህ ዓይነቱ ሕግን መሠረት ያደረገ አሠራር አሁን ባለው የተረኞቹ አገዛዝ አይታሰብም፡፡

‹‹…በፌዴራል መንግሥት ሥር የሚገኙ ሀብቶች በባለቤትነት ማስተዳደርና የመንግሥትን ሀብት ባግባቡ በመጠቀም የኢንቨስትመንትን ውጤታማነት ለማሳደግ…ተጨማሪ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ…›› (የዓዋጁ አ.54 /2/) በሚል የሐሰት ምክንያት ውሱን የሕዝብ ሀብት የያዙ ድርጅቶችን ባንድነት በማሰባሰብ ለዝርፊያ ምቹ ማድረግ የሌቦች አገዛዝ ዓይነተኛ መገለጫ ነው፡፡ የአገዛዙ አለቃ በዜጎች ስም በርጥባን ስለተገኘ ገንዘብ ሲጠየቅ በዐደባባይ ማንም አያገባውም፣ አልጠየቅም ያለ ነውረኛ ነው፡፡ ለመሆኑ ሕዝብ ባልመረጠበትና ውክልና ባልሰጠበት የመንግሥት ሀብት የሚባል አለ? በዚህ ጽሑፍ ባነሳናቸው የአገዛዝ ሥርዓቶች ‹መንግሥት› እና ‹ሕዝብ› የሚለው ቃል ሆን ተብሎ የተምታቱበት ዘመን ነው፡፡ የአገሩና የሀብቱ ባለቤት የሆነው ሕዝብ እስከ መቼ የመንግሥትነት ባሕርይ ለሌለው የሌቦች አገዛዝ መናጆ ሆኖ ይኖራል? ደርግ ‹መሬት ላራሹ› ብሎ ገበሬውን የካድሬዎች ጭሰኛ አደረገው፡፡ ወያኔና ወራሹ ኦሕዴድ መሬትን የግል ሀብታቸው በማድረግ እንደፈለጉ ይሸጣሉ/ይለውጣሉ፤ ለአፍራሽ ተልእኮአቸው ተባባሪ ለሆኑ እየሸነሸኑ ያድላሉ፡፡ አሁንም እዚህ ጋር በድጋሚ አነሣዋለሁ፡፡ በዓለም ላይ በገዛ አገሩ የራሴ የግሌ የሚለው ኩርማን መሬት የሌለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፡፡ የኦነጎቹ አገዛዝ ደግሞ ይሄም ሳያንሰው ኢትዮጵያዊ አስከሬኑ የሚያርፍበት ግማሽ ክንድ ከስንዝር መሬት ነፍጎታል፡፡ ዕብደትና ድንቊርና ሲነግሥ፣ ልጓም የሚሆኑ መልካም እሤቶች ተሸርሽረው ሰዎች ኅሊናቸውን በከርሳቸው ሲቀይሩ የተለየ ውጤት መጠበቅ አይቻልም፡፡

ለአሁኑ ጽሑፌ ቆስቋሽ የሆነኝን አሳብ በማንሣትና አስተያየት በማከል አጠቃልላለሁ፡፡ ለዚህ ጽሑፍ መነሻ አሳብ ያገኘሁት በቅርቡ እ.አ.አ. በጁላይ 31/2022 እትሙ ‹ካፒታል› የተባለው ጋዜጣ ‹‹Feasibility Heightens for EIC to Join EIH Umbrella›› በሚል ርእስ የጻፈው ዜና ነው፡፡ EIC የሚለው ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መጠሪያ ምሕፃረ ቃል ሲሆን፣ EIH ደግሞ ርእሰ ጉዳያችን ለሆነው ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ መጠሪያ ምሕፃረ ቃል ነው፡፡ የሆልዲንጉን ዓላማና ተግባር ለመወሰን በወጣው ደንብ የትርጕም ክፍል ‹‹የመንግሥት ሀብት›› የሚለውን ሐረግ እንዲህ አስቀምጦታል (የደንቡ አ.2/2/) ፤

‹‹ ‹የመንግሥት ሀብት› ማለት ሙሉ በሙሉ ወይም አብዛኛው የአክሲዮን ድርሻው በፌዴራል መንግሥት ባለቤትነት የተያዘ የመንግሥት የልማት ድርጅት ፤ የአክሲዮን ማኅበር ወይም የመንግሥት የፋይናንስ ድርጅት፤ በመንግሥት ባለቤትነት ወይም ይዞታ ሥር ያለ መሬት ወይም ሕንፃ፤ እንዲሁም ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በመንግሥት ባለቤትነት ሥር ያለ ግዙፍነት ያለው ወይም ግዙፍነት የሌለው ሀብት ነው፡፡››

የዚህ ጽሑፍ ዓላማ በንቅዘት የበሰበሰው የወንጀል ሥርዓት በሚያወጣቸው ሕጎችና በሚያቋቁማቸው ተቋማት ሕጋዊ ሽፋን በመስጠት የሕዝብ ሀብት እንዴት እንደሚባክን በማሳያነት ማቅረብ ቢሆንም፣ EIH የተባለው ተቋም አስፈላጊነት አጠያያቂ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የመንግሥት አስተዳደር መ/ቤት (regulatory agency) በመሆኑ ከፍ ብለን በጠቀስነው ‹‹የመንግሥት ሀብት›› ትርጓሜ ውስጥ አይወድቅም፡፡ በትርጓሜው የማይሸፈን ከሆነ ደግሞ በሆልዲንጉ ሥር የሚተዳደር ተቋም ሊሆን አይችልም፡፡

Filed in: Amharic