>

ትምህርት እንደ ‹‹ኮሪደር ጥፋት››፤ማንበብ የማይችሉ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች አስደንጋጭ ቊጥር

ትምህርት እንደ ‹‹ኮሪደር ጥፋት››፤ማንበብ የማይችሉ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች አስደንጋጭ ቊጥር

 

ከይኄይስ እውነቱ

 

ድንቊርና ሲሠለጥን ትምህርትም በቅዠት እንደሚሠራው ‹‹የኮሪደር ጥፋት›› ሆኗል፡፡

 

አፍ የፈቱበትን እና አፍ የፈቱበትም ባይሆን የሚነጋገሩበትን የአገራቸውን ብሔራዊ ቋንቋ ማንበብ የማይችሉ ከዓፀደ ሕፃናት እስከ አንደኛ ደረጃ ትምህርት የሚገኙ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ቊጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ ባስደንጋጭ ሁናቴ እየጨመረ ይገኛል፡፡ የሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና የፈተናዎች ኤጀንሲ በሚባለው የአገዛዙ ተቋም በቅርቡ ተደረገ በተባለ ጥናት (አገዛዙ በቊጥር ረገድ የሚሰጠው መረጃ ተአማኒነት ባይኖረውም እንኳን) 56% (ሃምሳ ስድስት ከመቶ) የሚሆኑ የ3ኛ እና የ4ኛ ክፍል ተማሪዎች አንድ ቃል እንኳን ማንበብ እንደማይችሉ ይፋ አድርጓል፡፡ ስታቲስቲክሱን ትተን ቢያንስ ይህ አስደንጋጭ እውነታ ታምኗል፡፡ ይህም ጸሐፊ ስለ ኢትዮጵያዊ ዕሤቶች እና መንፈሳዊ ትምህርቶች ለልጆች መጠነኛ ግንዛቤ ለመስጠት እንደሚጥር ዜጋ የተጠቀሰውን እውነታ ቀደም ብሎ ከወያኔ ትግሬ ዘመን  ጀምሮ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ እዚህም ደረጃ የተደረሰው አገዛዛዊና ትውልድ ገዳይ በሆነ የትምህርት ፖሊሲና ኢትዮጵያንና ሕዝቧን በሚጠሉ ፋሺስታዊ አገዛዞች ሆን ተብሎ በዕቅድ በሚመራ ሥርዓታዊ/መዋቅራዊ በሆነ መንገድ ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡

በመሠረቱ ቋንቋ መግባቢያ መሣሪያ ነው፡፡ ቋንቋን ማወቅ በራሱ ግብ ባይሆንም ዕውቀትን ለመግብየት ግን ወሳኝ መሣሪያ መሆኑ እሙን ነው፡፡ አንድ አገር እንደ ሕዝቡ የነገድ/ጐሣ ስብጥር በየአካባቢው የሚነገሩ በርካታ ቋንቋዎች ሊኖሩት ይችላል፡፡ ባለ ብዙ ነገድ የሆነችው ኢትዮጵያም ከሰማንያ በላይ ቋንቋዎች እንደሚነገሩባት ይታወቃል፡፡ ያም ሆኖ በታሪክ አጋጣሚ ሁላችንንም በአራቱም ማዕዝናት የሚያግባባ ዐማርኛ የተባለና በአፍሪቃ ብቸኛ የሆነ የራሱ የጽሑፍ ፊደላት ያሉት ብሔራዊ ቋንቋ ማዳበር ችለናል፡፡ የቀሩት የአገራችን ቋንቋዎች የራሳቸው የተለየ የጽሑፍ ፊደል ባይኖራቸውም እንደተናጋሪው ብዛት ሰፋ ባሉ ወይም በውሱን አካባቢዎች ይነገራሉ፡፡ እነዚህም ቋንቋዎች አብዛኛው ሕዝብ የተለማመዳቸውንና የሚያውቃቸውን የብሔራዊውን ቋንቋ ፊደላት በመጠቀም በአካባቢያዊ አስተዳደር፣ በማዕከላዊ መንግሥት እና በቋንቋው ተናጋሪ ምሁራን ድጋፍና ጥረት በሥነ ጽሑፍ ሊዳብሩና ሊስፋፉ ይገባል፡፡ 

ባጠቃላይ በአሁኑ ጊዜ በመላው ዓለም ላይ የሚገኙ ሉዐላዊ መንግሥታት እንድ አገርና ሕዝብ የሚግባቡበት አንድ ብሔራዊ ቋንቋ አላቸው፡፡ በጣት የሚቈጠሩቱ ደግሞ ሁለት ወይም ሦስት ብሔራዊ ቋንቋዎች ይነገርባቸዋል፡፡ የኢኮኖሚ ዐቅም ስላላ ብቻ ካንድ በላይ የብሔራዊ ቋንቋ መኖር አስፈላጊ አይሆንም፡፡ ብሔራዊ ቋንቋ እንደ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ሁሉ ታሪካዊ መሠረት ይዞ፣ ባንድ ወገን የሕዝብ አንድነት÷ ኅብረትና የጋራ ዕሤቶች መገለጫ፤ በሌላ ወገን የነፃነትና ሉዐላዊነት መለያ ምልክት ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት በተባለው የዓለሙ ድርጅት 193 አባል መንግሥታት አሉ፡፡ ይሁን እንጂ ድርጅቱ የሚጠቀምባቸው ኦፊሴላዊ ቋንቋዎች ስድስት ብቻ ናቸው፡፡ ብሔራዊ ቋንቋን የምንፈልገው በእኩልነት መገለጫነት ሳይሆን፣ በዋናነት ለጋራ ጠቀሜታው፣ ኑሮን/ሕይወትን ስለማቀላጠፉ ነው፡፡ ባንድ ቋንቋ የሚግባባ ሕዝብ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና  ፖለቲካዊ ሕይወቱን በዐቅድ ለመምራት ትልቅ መሣሪያ ሆኖ ያገለግለዋል፡፡ የጐሣ ፖለቲካ ከመነሻው ዕብደትና ድንቊርና በመሆኑ ዘመንን ዋጅቶና መልካም ዕሤቶችን ጠብቆ ለሚመራ የሠለጠነና ዘመናዊ ሕይወት ታላቅ እንቅፋት ነው፡፡

ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና፣ በዘመነ ወያኔ የጀመረውና በውላጁ ኦሕዴድ/ኦነግ በእጅጉ ከፍቶ የዘለቀው የፋሺስታውያኑ አገዛዞች መገለጫ – ለነባር የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህል፣ ዕሤቶችና ቅርሶች ያላቸው የመረረ ጥላቻ ነው፡፡ ከነዚህም መካከል ዒላማ የሆነው ብሔራዊ ቋንቋችን ዐማርኛ ሲሆን፣ በዚህም ከዐምሐራው ሕዝብና ከአስገኝዋ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር በይፋ መዋቅራዊ/ሥርዓታዊ በሆነ መልኩና አሁን ደግሞ ጦርነት ታውጆ አገር የማፍረሱ ጥፋት ከተጀመረ እነሆ ድፍን ሠላሳ አራት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

ፋሺስታዊው አገዛዝ እስትንፋሱን ያራዘመው በኢትዮጵያ ሕዝብ ሀብት በተቆጣጠራቸው መደበኛ እና ዲጂታል ሚዲያዎች ‹የፕሮፓጋንዳ ወሬ› ጥቂት ከርሣሞች ብቻ ነው፡፡ ለዚህም ጥፋቱ እንኳን መሣሪያ አድርጎ የሚጠቀመው የሚጠላውንና አጠፋዋለሁ የሚለውን የዐማርኛ ቋንቋ ነው፡፡ ሕፃናት ከሙዓለ ሕፃናት ጀምሮ መልክአ ፈደልን፣ ድምፀ ፊደልን በመለየት ፊደላትን በማሰካካት ቃላትን ብሎም ዓረፍተ ነገርን መመሥረት የተማሩ ቢሆን ኖሮ ከስድስትና ሰባት ዓመታት በኋላ ማንበብ አይችሉም የሚል አሳፋሪ (አሳፋሪ ያልሁት ለተቋማቱ ነው) ቃል ባልተነገረ ነበር፡፡ ወላጆችስ ምን እየሠሩ ነው? ጥቂት ጥሪት አለን፣ ‹ዘመናዊ ነን› የሚሉቱ ፊደል የቆጠሩቱም ሆኑ ማይምኖቹ ዋነኛ ፍላጎታቸው ልጆቻቸው ‹የፈረንጅ አፍ› እንዲለምዱላቸው ነው፡፡ ዐቅም የሌላቸውና ማንበብ መጻፍ የማይችሉቱ ት/ቤት በሰደዷቸውና ከሕፃናቱ ከፍ በሚሉ ተማሪ ልጆቻቸው አማካይነት ክትትል ማድረግ ይቻላል፡፡ እንደ ዱሮ ደብዳቤ አንብቡልኝም በመቅረቱ ልጆቻቸው ማንበብ ስለመቻላቸው እንኳን የሚያውቁበት መንገድ ያለ አይመስልም፡፡

የፋሺስታዊው አገዛዝ ተልእኮ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ዛሬ በዚሁ በአገራችን ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ዐማርኛ ቋንቋን በእንግሊዝኛ ለማስተማር የሚዳዳቸው ‹‹የግል ት/ቤቶች›› እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ተማሪዎች ዐማርኛ ቋንቋ እንዳይናገሩ እስከመከልከል የደረሱና እንግሊዝኛ ቋንቋን ግብ አድርገው እየሠሩ ያሉ የግል ት/ቤቶች ቊጥር ቀላል አይደሉም፡፡ ንቅዘቱ ሥር የሰደደ በመሆኑ በሕግ ሥልጣንና ተግባር ተሰጥቶአቸው ክትትልና ቊጥጥር እንዲያደርጉ በየደረጃው የተቋቋሙ አካላት የችግሩ እንጂ የመፍትሔው አካል አይደሉም፡፡ አንድም የአገር ጥፋቱ አካል፣ በሌላም ወገን ሆዳምና ደናቊርት በመሆናቸው፡፡ 

አብዛኛዎቹ የግል ት/ቤቶች የሚመሩት ወይም በባለቤትነት የተያዙት አእምሮአቸው በምዕራባውያኑ ቅኝ በተገዙ ግለሰቦች በመሆናቸው ሁሉም ለማለት በሚያስደፍር ሁናቴ ስያሜአቸው የባዕድ ከመሆኑ በተጨማሪ ልጆቹን የሚሰብኩትና የሚያዘጋጁት ውጭ አገር ሔደው እንዲማሩ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ብዙ ወላጆች (በተለይም ዐቅም የሌላቸው) ከልጆቻቸው ጋር ‹‹ጦርነት›› ውስጥ ይገኛሉ፡፡ አንባብያን እስቲ እነዚህን ስሞች አስተውሉአቸው፡፡

  • Lion Heart Academy
  • Gibson Academy
  • Vision Academy
  • Diamond Academy
  • School of Tomorrow
  • Harmony Hills
  • South West School
  • Mald School
  • Deliverance School
  • Trillium School
  • Fountain of Knowledge
  • Young Roots
  • Cambridge International School
  • Flipper International School
  • One Planet International School 

ዝርዝሩ ረዥም ነው፡፡ ከውጭ አገር የማኅበረሰብ ት/ቤቶች (Foreign Community Schools) በስተቀር ባንድ አገር ውስጥ የሚገኙ የግልም ሆኑ የመንግሥት ት/ቤቶች አገራዊ ቋንቋ ወይም አገራዊ ማንነትን የማያንፀባርቁ ስያሜ መስጠት ለምን አስፈለገ? የዚህ ትርጕም ምንድን ነው? መብትና ነፃነት አለኝ በማለት ብቻ ማንነትን ዘንግቶ ልቅ መሆን ምን ይሉታል? ለልጆቻችን ምን እያስተማርናቸው ነው? አንድ ስሙን የማልጠቅሰው የግል ት/ቤት ከትምህርት ጋር የተያያዘ መልካም ሀገር-በቀል ስም ሰይሞ ሲያበቃ ተማሪዎች አልመዘገብ አሉኝ በሚል ምክንያት ስያሜውን ለመቀየር እንደተገደደ አንድ ወዳጄ አጫውቶኛል፡፡ እዚህ ደርሰናል፡፡ ሥርዓት የሚያስይዝም የለም፡፡ ፈረንጅ አምላኪነት ማለት ከዚህ የተለየ ትርጕም የለውም፡፡ በአእምሮ ቅኝ መገዛቱ እንደ ተላላፊ በሽታ ከትልልቆቹ ወደ ሕፃናቱ ወርዷል፡፡

 ስለ አገር ታሪክ፣ ባህል፣ ብሔራዊ ማንነትና የጋራ ዕሤቶች መሠረት የሚጣልበትን የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ለባዕዳኖችና አእምሮአቸው ቅኝ ለተገዛ የባዕዳን ቅጥረኞች አሳልፎ የሰጠ የነፃነት ታሪክ አለኝ የሚል አገር ከኛ ውጭ ስለመገኘቱ መረጃ የለኝም፡፡ የትኛው አገር ነው በትምህርት ኢንቨስትመንት ረገድ የአንደኛ ደረጃ ትምህርትን ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት የሚያደርግ? ይሄ የተረገመ ሰውዬና ግብር አበሮቹ በወያኔ ዘመን እንኳን ዝግ የነበረውን ብርግድ አድርገው በመክፈት አገሪቱን ባለቤት አልባ አድርገዋታል፡፡ 

መፍትሔው ምንድን ነው?

ሥርዓታዊና መዋቅራዊ ለሆነ ችግር ዋናው መፍትሔ ፋሺታዊ የጐሣ አገዛዙን እስከነ መዋቅሩ ማስወገድ ብቻ ነው፡፡ ከዚያ በመለስ ትውልድ መጥፋት የለበትምና በዋናነት ወላጆች ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ልጆችን ት/ቤት መላክ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ምን ተማርሽ/ተማርህ? እስቲ አንብቢልኝ/አንብብልኝ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ከፍ ብዬ እንደጠቀስሁት ማንበብና መጻፍ ባይችሉ እንኳን በታላላቅ ወንድምና እኅቶቻቸው አማካይነት ወይም በጎረቤት ልጆች ጭምር ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ቀጥሎ ት/ቤቶች ከወላጆች ጋር በጋራ ሆነው መምከር ይኖርባቸዋል፡፡ ለስሙ በየት/ቤቱ የወላጆች ኮሚቴ የሚባል ቢኖርም፣ ከዚህ ቀደም ባንድ መጣጥፌ እንደገለጽሁት ጥቂት የማይባሉቱ (ስለ ትምህርቱ ሥርዓት/የመማር-ማስተማር ሒደት፣ በተማሪና መምህራን እንዲሁም ተማሪዎቸ ርስ በርሳቸው ስላላቸውና ስለሚኖራቸው ግንኙነቶች፣ ት/ቤቶቹ ተማሪዎችን ስለሚያንፁበት አገራዊ ዕሤቶች ወዘተ. በኃላፊነት ስሜት ሊሠሩ ቀርቶ)  ከት/ቤቱ አመራሮች ጋር ንቅዘት ውስጥ የሚገኙ አሉ፡፡ ሌላው ትምህርት ነክ በሆኑ ዓላማዎች ላይ የተሰማሩ ሀገር-በቀል የሲቪክ ማኅበራት (በተለይም የገንዘብ ምንጫቸው ባገር ውስጥም ሆነ በውጭ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ብቻ የሆኑ) ካሉ ቤተ መጻሕፍት በማቋቋም ብቻ ሳይወሰኑ ሕፃናት ልጆችን ንባብ በማለማመድ እገዛ ማድረግ የግድ ይላል፡፡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትም በዚህ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ መጻሕፍቱም በዋናነት የአገራችንን ታሪክ፣ ባህል፣ ትውፊትና መልካም የጋራ ዕሤቶችን መሠረት ያደረጉ መሆናቸውን ማረጋጥ ያስፈልጋል፡፡ ከተረታ ተረት ጀምሮ ካልጠፋ ሀገር-በቀል ጽሑፍ የባዕድ መጻሕፍት እየተረጐምን የልጆችን አእምሮ ወዳልተፈለገ አፍቃሬ ፈረንጅነት ለምን እንስባለን? በራሳችን ጽሑፍ ውስጥ እኮ እምነት አለ፣  ትውፊት አለ፣ ባህል አለ፣ የጋራ ዕሤት ወዘተ. አለ፡፡ የዐማርኛ መዝገበ ቃላትን አጠቃቀም እንዲያዳብሩ በማድረግ የቃላት ክምችታቸውን መጨመር፣ ካዳዲስ ቃላት ጋር እንዲተዋወቁ በማድረግ የማንበብ ችግራቸውን ማሻሻል፤ በዚህም እሳቤአቸውን፣ ሐሳባቸውን፣ ፍላጎታቸውን በተሻለ ብቃት እንዲገልጹ ማድረግ ይቻላል፡፡ የቋንቋ ትምህርት አንዱና መሠረታዊ ክህሎት ማንበብ ሆኖ ሳለ ይህንን ሳይችሉ ተማሪዎች እንዴት ከክፍል ወደ ክፍል ሊሻገሩ እንደቻሉ አይገባኝም፡፡

 ነገሬን ከማጠቃለሌ በፊት የቅርብ ትዝብቴን መዝግቤ ልለፍ፡፡ አገርና ሕዝብን በሚጠሉ ‹‹የጐሣ ፖለቲከኞች›› ትውልድን በብልሹ የትምህርት ሥርዓት አማካይነት የመግደሉ ሒደት ከተጀመረ ከርሟል፡፡ 

ባሁኑ ጊዜ ርጉም ዐቢይ በአፍሪቃ ቀዳሚ ስፍራ የነበረውን፣ በበርካታ ምሁራን የዓመታት ጥረት በዓለም የተከበረውን፣ በርካታ ሊቃውንትን ለአገር ብቻ ሳይሆን ለዓለም ያፈራውን፣ ስመ ጥር የነበረውን የዐዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ባንድ ‹ዶ/ር› ሳሙኤል በሚባል ቀትረ ቀላል ካድሬ (ትምህርት ሚኒስቴርን ሲያምስ የነበረ) አማካይነት (በወያኔ የተጀመረውን የማፍረስ ተግባር) ግብዓተ መሬት ለመፈጸም ጥድፊያ ላይ ይገኛል፡፡ ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የዐማርኛ ጥናት፣ የታሪክ ትምህርት ክፍል የመሰሉ አንጋፋ የምርምር ተቋማትን አጥፏል፡፡

አሁን በቅርቡ ደግሞ የውጭ ቋንቋዎች ጥናት (ILS) የተባለውን አንጋፋ የምርምር ተቋም አጥፏል፡፡ የ‹ኮሪደር ልማት› እያለ እንደ ልጆች ጨዋታ አገርን ምስቅልቅሉን በሚያወጣበትና ሕዝብን እንደሚያፈናቅልበት ብልጭልጭ የቅዠት ተግባር በትምህርቱም መስክ ያለአንዳች ጥናት በፖለቲካ ውሳኔ ብቻ ቀደም ሲል የጠቀስሁት ቀትረ ቀላልና ተርመጥምጦ ራሱን ውዳቂ ያደረገውን ብርሃኑ ነጋን ‹በመዶሻነት› በመጠቀም በዩኒቨርስቲው ካምፓሶች ሥር የሚገኙ አንጋፋ የትምህርት/የምርምርና ጥናት ተቋማትን እያፈራረሰ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም ርጉም መለስ እንዳደረገው የሚገዳደሩትን አንጋፋ መምህራንን ለኹለተኛ ጊዜ ለማባረር ዝግጅቱን አጠናቅቋል፡፡ በትምህርት ‹ሬሳ ሳጥን› ላይ የመጨረሻውን ምስማር መምታት የሚሉት ይህንን ዓይነት የጥፋት ፍጻሜ ይመስላል፡፡ ድንቊርና ሲሠለጥን ትምህርትም በቅዠት እንደሚሠራው ‹‹የኮሪደር ጥፋት›› ሆኗል፡፡

አገር መፍረስ ማለት ከዚህ ውጭ ትርጕም ይኖረው ይሆን? አቡነ ሉቃስ እንዳሉት አንድ ባለጌ ወፈፌ ማስወገድ አቅቶን ሁላችን ‹ሬሳ› እንሁን? ‹የሚንቀለቀለውን ሰደድ እሳት› ካጠፋን በኋላ ወደ መሠረታዊው የሥርዓት ለውጥ መሸጋገር ይቻል ነበር፡፡ 

መነሻችን ያገራችን ልጆች ትምህርት ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ነው፡፡ ልጆቻችንን ት/ቤት ብንሰድም በከፊል ማይምኖች ሆነዋል፡፡ ዳግማዊ ‹መሠረተ ትምህርት ለዕውቀት ዘመቻ› ሳያስፈልገን ይቀር ይሆን?

Filed in: Amharic