>

ጭራቁ ያመከናቸው ግለሰቦች እና ኢትዮጵያዊ እሤቶች (ከይኄይስ እውነቱ)

ጭራቁ ያመከናቸው ግለሰቦች እና ኢትዮጵያዊ እሤቶች

ከይኄይስ እውነቱ


ከዚህ ቀደም ባንድ መጣጥፌ ወያኔ ኢሕአዴግ ለከት ከሌለው ንቅዘቱና ዝርፊያው በተጨማሪ ላገር ለወገን የሚጠቅሙ ግዙፍ ሐሳቦችን÷ ውጥኖችን÷ ዕቅዶችን ሰርቆ ማምከን ዓይነተኛ መለያው እንደሆነ ሁሉ፤ ወራሹ ኦሕዴድ/ኦነግ/ ኢሕአዴግ (ብልግና) ደግሞ ሰዎችን አታልሎ አባብሎና በጥቅም አደንዝዞ በቁሙ ማምከን ዓይነተኛ መገለጫው እንደሆነ አብነት በመንሣት ለማሳየት መሞከሬ ይታወሳል፡፡

ደጋግሜ እንደገለጽሁት እነዚህ ጐሣ ወለድ የወንጀል ሥርዓቶች ሕገ አራዊት ጽፈው፣ መዋቅር ዘርግተውና በጐሣ ቈጠራ ናላቸው የዞሩ ታማኞቻቸውንና አድርባዮቻቸውን ይዘው ላለፉት ሠላሳ ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያ አገራችንን በማዋረድና በማፍረስ፣ ሕዝቧን ደግሞ ጐሣና ሃይማኖትን መሠረት አድርገው በመጨፍጨፍ ላይ ተሠማርተው ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ሀገር አፍራሽ ኃይሎች – አንዱ ጭራቃዊ ቡድን ሳይገባው የያዘውን ሥልጣን ማናቸውም ብሔራዊ ጥቅም ተከፍሎበት ጭምር በማስጠበቅ ወያኔ ትግሬ የፈጠረለትን ‹ኦሮሚያ› የሚባል ተምኔታዊ ‹አገር› እውን ለማድረግ፤ ሌላው አሸባሪ ትግራይን ተቆጣጥሮ ለ27 ዓመት የቆየበትን ዝርፊያና ንቅዘት በማስቀጠል ሕገ ወጥ ጥቅሙን ለማስጠበቅና ቢችል ደደቢት ላይ የተነሣበትን ‹የትግራይ ሪፐብክ› ለመመሥረት – የሕዝብን ልጆች ትርጕም አልባ በሆነ ጦርነት ከማገዱ በኋላ፣ አእላፋት ካለቁ በኋላ፣ ተረኞቹ ባሰማሩት ሽብርተኛና ተከልከስካሽ የኦነግ ኃይል ሕፃናትን÷እናቶችንና አዛውንትን ያለ ጦርነት ማሳረዱን በቀጠለበት፣ በሚሊዮኖች ከቤት ንብረታቸው ከተፈናቀሉ በኋላ፣ የአገር ሀብት ካወደሙ በኋላ፣ ሕዝቡን በዋናነት ሥርዓት ወለድ በሆነ የኑሮ ውድነትና በረሃብ እየጠበሱ ባለበት ሁናቴ ለ21ኛው መቶ ክ/ዘመን ታላቅ ፌዝ የሚሆንና ‹ውስጡን ለቄስ› የሚባል – ሁለት ሽብርተኞች ካብ ለካብ የሚተያዩበት – ‹‹የሰላም ስምምነት›› አድርገን ታርቀናል እያሉ ልፈፋ ይዘዋል፡፡ ይሁዳዊ መተቃቀፍንም አድርገዋል፡፡ ስሙን ሰይጣን ይጥራውና በነዚህ ጭራቃዊ ኃይሎች መካከል ዥዋዠዌ እየተጫወተ ለሁለቱም የጭን ገረድ በመሆን ባጠቃላይ ለኢትዮጵያ በተለይ ደግሞ ለዐምሐራ ሕዝብ የመጨረሻ ጠላት በምንም ሁናቴ ይቅር የማይባል ወንጀል እየፈጸመ የሚገኘው ብአዴን የሚባል ጉድ ማስታወስም ያስፈልጋል፡፡

ባንዳንድ ሜዲያዎች እንዳዳመጥሁት እነዚህ ኃይሎች በተለይም የምንይልክን ቤተመንግሥት የተቆጣጠረው ኦነጋዊው ቡድን ክህደት እንደፈጸመ አድርገው ይናገራሉ፡፡ በማን ላይ? ከእምነት ባለፈ በተጨባጭ እነዚህ አሸባሪ ቡድኖች አጽራረ ኢትዮጵያ መሆናቸውን እያወቅን ስለ ክህደት ማንሣት ምን ለማለት ነው፡፡ እነዚህ ኢሕአዴግ የሚባል ሰይጣናዊ ቡድን ውላጆች ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በጋራ የከዱት ከዛሬ ሠላሳ ሁለት ዓመት በፊት ነው፡፡ በተናጥል ከወሰድነው ደግሞ የወያኔን ከዘመነ ደደቢት፣ የኦሕዴድን ከኦነግ ምሥረታ ጀምሮ ካሠላነው ግማሽ ምእት ዓመት ተቈጥሯል፡፡ ስለሆነም ‹አንጋፋ› ከሃዲዎች ናቸው፡፡ የሚያሳዝነው ግን ከትውልዱ ቊጥሩ ቀላል የማይባል እነዚህን አንጋፋ ከሃዲዎች በጭፍን የሚከትል፣ የሚያዳምጥና ከሃዲ እንዳልሆኑ የሚከራከር አለ፡፡ የርግመት ጥግ ከማለት በስተቀር ቃል የለኝም፡፡ ይሄ ግን ዐውቀው ዥዋዥዌ የሚጫወቱትን አድርባዮች አይመለከትም፡፡

እዚህ ላይ አንድ ነገር አስረግጦ መናገሩ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል የሚኖር ከአእምሮው ጋር ያለ ኢትዮጵያዊ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጦርነት ነፃ የሆነና የተረጋጋ ሰላማዊ ሕይወት እንዲመራ የማይመኝ ይኖራል ብዬ አላምንም፡፡ በዚህ ረገድ በማይዘልቀው ‹በውሸት የሰላም ስምምነቱም›› የትግራይ ሕዝብ ለጊዜውም ቢሆን ዕረፍት ማግኘቱ በመልካም የሚታይ ይሆናል፡፡ ሆኖም ጦርነት የለም ማለት ሰላም አለ ማለት አይደለም፡፡ ዛሬ ‹ኦሮሚያ› በሚባለው የኢትዮጵያ ግዛት በተለይም በምዕራቡ ክፍል ነገድና እምነትን መሠረት አድርጎ የሚፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ኢትዮጵያውያን ምን ነካን የሚያስብል ነው፡፡ ከአጽራረ ኢትዮጵያውያን (ከአሸባሪ ኃይሎች) ሰላም ይመነጫል ብሎ ማመን ጨለማ ከብርሃን ጋር ኅብረት አለው ወደሚል ተቃርኖ ይወስደናል፡፡ ባጭሩ በወያኔና በውሉዱ ኦሕዴድ መካከል የተደረገው ‹‹የሰላም ስምምነት አይደለም››፡፡ ኢትዮጵያንና ብሔራዊ ጥቅሟን አግልሎ ባሳዳሪዎቻቸው ምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት – ሥልጣንና ሥልጣንን መሠረት አድርጎ ከሚገኝ ዝርፊያ ውጭ መሠረታዊ ልዩነት በሌላቸው የኢሕአዴግ ፍንካቾች መካከል – የተደረገ ‹‹የንግድ ይዘት ያለው የፖለቲካ ስምምነት›› (business related political transaction) ነው፡፡ የቀረው ወሬ ሁሉ ለአገር ውስጥና ለውጭ ዜና ፍጆታ የሚውል ዝባዝንኬ ነው፡፡

ከዚህ በላይ ያለውን የወንጀል ሥርዓቶቹን ምንነት መሠረት አድርገን፤ አሁን ተረኛ የሆነው የወንጀል ሥርዓት በተለይም አገዛዙን የሚመራው ጭራቅ ሕዝብ የሚያከብራቸውንና ላገር ታላቅ ባለውለታ ይሆናሉ ብሎ የሚያስባቸውን በርካት ኢትዮጵያውያን በተግባር ከኢትዮጵያዊነት አውጥቶ አምክኗቸዋል፡፡ በዚህም ሳያቆም ለወንጀል ሥርዓቱ ዋስ ጠበቃ አድርጓቸዋል፡፡ ምክንያቱ አድርባይነትና በዚህ የሚገኘው ጥቅም ይሁን፣ የወንጀል ሥርዓቱ የእስርና ሞት ዛቻ ተደቅኖባቸው ይሁን፣ ወይም በከፋ መልኩ የወንጀል ሥርዓቱ የሚፈጽማቸውን አገር የማጥፋት ሕዝብን የመጨፍጨፍ ይፋ ድርጊቶች ጥፋቶች ሳይሆኑ ላገር የሚጠቅመው የወንጀል ሥርዓቱ አካሄድ ነው ብሎ በማመንና በመቀበል ይሁን እግዚአብሔር ይወቀው፡፡ 

አቶ ብርሃኑ ደቦጭ ላለፉት 30 የሚጠጉ ዓመታት ወያኔ-ኢሕአዴግና ወራሹ ኦሕዴድ-ኢሕአዴግ አገርና ትውልድ አምካኝ በሆነ የትምሕርት ፖሊሲና ሥርዓት ምክንያት ባገር ላይ የደረሰውን የማይጠገን ክስረት በማስረጃ አስደግፎ በመዘገበበት ‹‹የድንቊርና  ጌቶች፤ ሞገሱን የገፈፉት ዩኒቨርስቲ (1983-2012 ዓ.ም.)›› መጽሐፉ እንዳሳየን የከፍተኛ ትምሕርት ተቋማት አንጋፋው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን ጨምሮ ከመጀመሪያ እስከ ሦስተኛ ድግሪ ወረቀት ታቅፈውና የመከነ ጭንቅላት ተሸክመው የተቀመጡ፣ የከፍተኛ ትምሕርትን ጨምሮ በተለያዩ መንግሥታዊና የግል ተቋማት ተሰማርተው የአገር ሸክም የሆኑ ተከታታይ ትውልዶች መፈልፈያ ሆነዋል፡፡ ትውልድን የማምከኑ ሂደት በከፋ ሁናቴ በተረኞቹ ቀጥሏል፡፡ አሁን ያለው የወንጀል ሥርዓት የማምከን ሰለባ የሆኑት በዋናነት ከተጠቀሰው ጊዜ ቀደም ብሎ ትምህርታቸውን በአ.አ. ዩኒቨርስቲ እና በውጭ ዩኒቨርስቲዎች የተከታተለውን ትውልድ ነው፡፡ በትምህርት ረገድ ያለወ የ30ው ዓመታት ጉዳይ ግን ተከድኖ ይብሰል የሚያስብል ነው፡፡ ያም ሆኖ በዚህ ጊዜ ውስጥ ዕውቀትን ቅድሚያ ሰጥተው በራሳቸው ጥረትና በቤተሰባቸው ድጋፍ ንፍሮ ሆኖ ከመከነው ትውልድ ውስጥ ገንትረው የወጡ፣ ራሳቸውን ያበቁ ኢትዮጵያውያን (ቊጥራቸው ብዙ ባይሆንም) የሉም ለማለት አይቻልም፡፡ የሚያሳዝነው ግን ከነዚህም ውስጥ የአገዛዙ ፖለቲካ ሰለባ የሆኑ ብዙ ናቸው፡፡ 

ባንድም ሆነ በሌላ መልኩ ዕውቀትን የሚያስጨብጥ ትምህርት ማግኘት ወይም የመማር ውጤቱ በበጎ መልኩ ለመለወጥ ነው፡፡ ለራስም፣ ላስተማረ ሕብረተሰብና አገር መትረፍ ነው፡፡ ከቤተሰብ እስከ አገር ድረስ ያለን ተግዳሮት ለመጋፈጥና ችግር ለመፍታት ነው፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ለራስ የምቾት ጥግ መፍጠሪያና ከወንጀለኞች ጋር አገር ለማጥፋት በመሣሪያነት ለማገልገል ከሆነ ምነው በእናታቸው ማሕፀን ውኃ ሆነው በቀሩ የሚያሰኝ ነው፡፡ 

በጊዜአቸው ተራማጅ የነበሩት ዐፄ ኃይለሥላሴ ለትምህርት መስፋፋት የነበራቸው ርዕይና ፍላጎት፣ በተግባርም የወሰዱት ርምጃ ታላቅነታቸውን የሚያሳይ ነበር፤ የድሀ ልጆችን ከገጠር ጭምር አምጥተው ባገር ውስጥ ሳይወሰኑ በውጭ አገር ልከው አስተምረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከውጭ ተምረው የመጡት ተማሪዎች ተለውጠው ሲመጡ እሳቸውና ዙሪያቸውን የከበቡአቸው ብዙዎቹ መኳንንትና መሣፍንት ባሉበት ሆነው ዓለም ያለበትን ሁናቴ መዋጀት ሳይችሉ ቀሩ፡፡ በዚህም ምክንያት ለውጥ ፈላጊው የተማረው ወገን የጀመረው እንቅስቃሴ ባልተማሩ ወታደሮች ተጠልፎ፣ በዓመፃ የተጀመረው የተማሪዎችም እንቅስቃሴ የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ባህል፣ እምነት፣ ትውፊትና ሌሎች በጎ እሤቶች ባልዋጀና በቅጡ ባልተረዱት የባዕድ ርእዮት በመቃኘቱ፣ በወቅቱ ከነበሩት የፖለቲካ ድርጅቶች የአንዳንዶቹ መሠረትና አስተሳሰብ በጠላት ሻእቢያ የተመራ በመሆኑ (ኢ.ሕ.አ.ፓን ያስታውሷል)፣ ከደርግና ከኢ.ሕ.አ.ፓ. ጋር በርእዮት አንድ ነን የሚሉት ሌሎችም ድርጅቶች የመጨረሻ ግባቸው ሥልጣን መሆኑን በተግባር በማሳየታቸው  (እርስ በርስ ባደረጉት መገዳደል አንድ ትውልድ እምሽክ ብሎ ሊያልቅ ችሏል) ወታደራዊው አገዛዝ የኢትዮጵያ የቊልቊለት መንገድ መጀመሪያ የወንጀል ሥርዓት ለመሆን በቃ፡፡ ይህም የደናቊርቶች ሥርዓት አገዛዙን ያሟሸው እንደ ፋሽስት ጥልያን የተማሩ ኢትዮጵያውያንን የገቡበት ገብቶ በመግደል ነበር፡፡ ወታደራዊው ደርግን የተኩትና ባለፉት 32 ዓመታት በኢትዮጵያችን ላይ የሠለጠኑት የወንጀል ሥርዓቶች ደግሞ (የለየላቸው ባለጌዎችና ወሮበሎች ስብስብ በመሆናቸው) ከፋሽት ጥልያን፣ ከናዚው ጀርመን፣ ከደቡብ አፍሪቃው የዘር መድሎ ሥርዓት (አፓርታይድ) በእጅጉ የከፉ ሆነው ደርግ የጀመረውን የቊልቊለት ጉዞ ወደ ‹በርባሮስ› ለመውሰድ እየተጣደፉ ይገኛሉ፡፡ በዚህ መሀከል ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ለሕዝቧ ደኅንነትና እኩልነት፣ ላገር ሉዐላዊነትና ክብር፣ ዕድገትና ልማት ከልባቸው ሲያስቡ፣ ሲጨነቁ፣ ሲጮኹ፣ የዐቅማቸውን ሁሉ በአፍም በመጣፍም እንዲሁም በተግባር ሲደክሙ የነበሩ ዋነኞቻችን (ለአብነት ያህል ነፍሳቸውን ይማርልንና ፕ/ር አሥራት ወልደየስ፣ ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ፣ ፕ/ር መሥፍን ወልደ ማርያም፣ ሌሎችም በየተሰማሩበት መስክ ላገር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ አንጋፋ ኢትዮጵያውያን) አድማጭ አጥተው ዛሬ ከቀደሙት እውነተኛ አባቶቻችን ጋር ተከማችተዋል፡፡ የኢትዮጵያ አምላክ እግዚአብሔር ዛሬም ባገር ውስጥም ይሁን በውጭ እውነተኛ ኢትዮጵያውያን አሉት፡፡ ሆኖም ፊደል ቆጥረዋል ወይም በዚህች ደሀ አገራችን ጥሪት የተሻለ ተምረዋል የተባሉት (በልዩ ልዩ ሙያ ዘርፍ የሚገኙ) ብዙዎች ለወንጀል ሥርዓቶች በመገዛት ራሳቸውን አምክነው በተግባር ‹ምራጮች› (እብቅ፣ገለባ) መሆናቸውን አስመስክረዋል፡፡ አንዳንዶቹም ወያኔ ሕውሓትን አምርረው የሚጠሉና የውጭ አገር ሕይወት ሰልችቶአቸው የተመለሱ፣ የጐሠኝነቱ ይሁን የጥቅም ሰለባ ሆነው የመከኑ አሉበት፡፡ ስለሁሉም ‹መካኖች› የተጠናቀቀ ዝርዝር ማቅረብ ባይቻልም ስማቸውን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከሁሉም የሚገርመኝ የሕግና የፖለቲካና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁር የሆኑት፣ ወያኔን በማያቋርጥ ብእራቸው ለዓመታት ሲታገሉና ሲያጋልጡ የኖሩት (እንዲያውም ጽሑፌን ብዙዎች ኢትዮጵያውያን እንደ ስብከት ይከታተሉልኝ ነበር እስከማለት የተመጻደቁት)፣ ፕ/ር አለማየሁ ገብረ ማርያም ጭራቁ ከመጣ በኋላ አቋማቸው እንዴት ነው? ለወንጀል ሥርዓቱ ጥብቅና መቆምና መደገፋቸው መብታቸው ነው፡፡ ወያኔ ሕወሓትን አምርሮ በመታገሉ ምክንያት ያልተገደበ ፍቅርና አክብሮት የሰጠውን የኢትዮጵያ ሕዝብ መካዱና ለተረኛው የወንጀል ሥርዓት ቋሚ ለጓሚ ሆኖ በርካታ ኢትዮጵያውያንን በስሕተት መንገድ በመምራታቸው ግን ታሪክና የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቅርታ የማያደርግለት ግዙፍ ጥፋት ፈጽመዋል፡፡ ጭራቁ በመጣበት የመጀመሪያው ወቅት የታየው ዕብደትና ፈንጠዝያ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ያለው አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የተጋራው በመሆኑ (ምንም እንኳን ከምሁራን የሚጠበቅ አርቆ አስተዋይነት ቢኖርም) በዚህ የሚተቻቸው የለም፡፡ ነገር ግን ወያኔ ያሰፈነው የጐሣ ሥርዓት፣ የጐሣ ፖለቲካ፣ የሕገ አራዊት መደላድልና የክልል መዋቅሩ እጅጉን ተጠናክሮ በቀጠለበት በዚህ አምስት ዓመት ውስጥ በኢትዮጵያ ምድር በኦሕዴድ/ኦነግ መራሹ አገዛዝ የተፈጸመውን ግፍና በደል እንዲሁም አገራዊ ምስቅልቅል የታዘበ ሰው ቢያንስ ወያኔን በሚቃወምበትና በታገለበት ግለት መጠን፤ ሲሆን ከዚያም በላይ ግንባር ቀደም ሆነው ብእራቸውን ሊያነሡ በተገባቸው ነበር፡፡ ግለሰቡ ወያኔን ለምንድን ነበር ሲቃወሙ ሲተቹ የኖሩት? እነዚያ ምክንያቶች ዛሬ ላይ በተለይም ባለፉት አምስት ዓመታት የተራራ ያህል ገዝፈው አገርና ሕዝብ ሊያሳጡን አልደረሱም? እንዲያውም ወያኔ ያልሠራው ግፍ በተረኞቹ አልተፈጸመም? ኢትዮጵያና ሕዝቧ የበለጠ አልተዋረዱም? ወንጀልና ኀጢአት የሚባሉትን ሁሉ ንቅስ ጥቅስ አድርገው አልፈጸሙም? ፕ/ር አለማየሁ ለየትኛው ዕድሜ ነው? ሀብት፣ ድሎትና ምቾት እንዳልል በሙያዎ የተከበሩና በገቢ ረገድም ለሌላው የሚተርፉ ኖት፡፡ ዝና ዕውቅና እንዳልል በሙያዎ የታወቁ፣ የተከበሩና በርካታ ሽልማቶችንም ያገኙ ኖት፡፡ በወንጀል ሥርዓቱ አምነውበት እንዳልል ለዓመታት የጻፉዋቸውን የስብከት ያህል ያነበብናቸው ኢትዮጵያዊ ጽሑፎችዎ እንደ ሐውልት ሕያው ምስክር ሆነው አሉ፡፡ ምን ነካዎት? ለእንደዚህ ዓይነቱ 360 ድግሪ የአቋም ለውጥ ምን ዓይነት ምድራዊ ማብራሪያ ሊሰጥ ይቻላል? ትውልዱ ከማን አብነት ይንሣ? ቅዱሳት መጻሕፍት እንደመዘገቡት ‹በኋለኛው ዘመን› ሰይጣን ብርሃናዊ መልአክ እስኪመስል ተአምራትን ያደርጋል የሚለው ትንቢታዊ ቃል እየተፈጸመ ካልሆነ ጭራቁና አጋንንታዊ ቡድኑ ምን ዓይነት ሰይጣናዊ ድርጊት ፈጽመው ይሆን ‹የተሻሉ› የሚባሉትን ኢትዮጵያውያን ማምከን የያዙት? ጭራቁ ያመከናቸውን የቀሩትን ቤት ይቊጠራቸው፡፡ 

ከሰው ምክነት ወጣ ብለን አገራዊ መልካም እሤቶቻችን ላይ ሆን ብለው ዐቅደው እየፈጸሙ ያሉትን ጥፋት ስንመለከት ኦነጋውያን ጐሠኞቹ በሚያስቡትስ ተምኔታዊ ‹አገር› ምን ዓይነት ማኅበረሰብ ሊያኖሩበት እንዳሰቡ አምላክ ይወቀው፡፡ የአንድ አገር ዋናው ሀብቱ በትምህርት፣ በመልካም ሥነ ምግባርና መልካም እሤቶች የታነፀ ዜጋ/ሕዝብ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ ባህላዊና የእምነት መሠረት ያላቸው ዘመን ተሻጋሪ መልካም እሤቶች ያሏት አገር ነች፡፡ ትልቁ ጥሪቷም ባንድ ሕዝብነት አብሮና ተሳስቦ በመኖር፣ በመረዳዳት፣ ‹በሕግ አምላክ› ብሎ ሕግና ሥርዓትን በማክበር፣ ሐዘንና ደስታን በጋራ በመካፈል፣ ሥራን በመተጋገዝ (ደቦ፣ ጅጌ፣ ወንፈል)፣ ያለውን በማካፈል፣ እንግዳን በመቀበል፣ ቃልን በማክበር/በመተማመን፣ በሕይወት ተሞክሮ የለዘብ የሽማግሌን ቃል በማዳመጥ፣ ተገቢ ይሉኝታን ገንዘብ በማድረግ፣ ለሞተ ወገኑ አስከሬን ክብር በመስጠት፣ ብሔራዊና ዓለም አቀፍ መገለጫዎቹ ለሆኑት ሰንደቅ ዓላማና የሕዝብ መዝሙር ፍጹም ታማኝነትና አክብሮት በማሳየት፣ የአገር ጠላትን በጋራ በመመከት፣ ሐሰት÷ ስርቆት÷ ክህደት÷ጐሠኝነት የመሳሰሉ ነውሮችን ሁሉ በመጠየፍ፣ ወዘተ. የሚገለጹ ማኅበራዊ ጥሪቶች ባለቤት የሆነ ሕዝብ ነው፡፡ ዛሬ እነዚህ እሤቶች ተሸርሽረው አደጋ ላይ ወድቀዋል፡፡ ይህም በዋናነት የወንጀል ሥርዓቶቹ ከሕዝቡ ታሪክ፣ ባህልና እምነት ውጪ የፈጠሩት የጐሣ ሥርዓትና መዋቅር ውጤት ነው፡፡ ዛሬ አገር በጉልበቴ እገዛለሁ ከሚለው ‹በሽተኛ› ግለሰብ ጀምሮ የወንጀል ሥርዓቱና ይኸው አገዛዝ ያመከናቸው ሰዎች አንዳች መሳቀቅ ሳይታይባቸው ውሸትን መናገር መደበኛ ሕይወታቸው አድርገውታል፡፡ የወያኔ ትግሬ አለቃ የነበረው ባንዳው መለስ ሌብነት ባህል እንዲሆን በዐደባባይ ሳይሰቅቀው ይናገርና ያበረታታ እንደነበረው የመንፈስና የግብር ልጁና ወራሹ ዐቢይ የወንጀል ሥርዓቱ የፈጠራቸውን ሌቦች በዐደባባይ ሲያበረታታ ተደምጧል፡፡ በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም በዕርጥባን ያገኘውን በሚሊዮኖች የሚቈጠር ዶላር ለፈለገው ጉዳይ ባውለው ማንም አያገባውም በማለት በዐደባባይ በትእቢት ሲደነፋ ሰምተነዋል፡፡ በዚህም የአገዛዙን ንቅዘት ከመመስከሩም በተጨማሪ ለዜጎች የሌብነት ምሳሌ ሆኗል፡፡ ይህ በሕዝብ ደም መላ ሰውነቱ የረከሰ፤ በሚያራምደው የጐሣ ሥርዓት ሕዝብን ለያይቶ ባላገሩን ስደተኛ ተቅበዝባዥ ያደረገ፤ አገራችንን ተወዳዳሪ በሌለው ንቅዘት በክሎ ዜጎችን የሚላስ የሚቀመስ ያሳጣ፤ አእላፋት ኢትዮጵያውያን ለተሠዉለት ሰንደቅ ዓላማ ቅንጣት ክብር የሌለው፤ ብሔራዊ መለያችን የሆኑ ተቋማትን ርቃናቸውን ያስቀረ፣ ለባዕድ አሳልፎ የሰጠና ለመስጠት የተዘጋጀ፤ በኢትዮጵያ ታሪክ የአገር ሉዐላዊነትን አስደፍሮና ጠላት ያገራችንን ድንበር ውስጥ ተቀምጦ እየገደለና እየዘረፈ ተቀምጦ ወዳጃችን እያለ ዜጋውን ለማስፈራሪያ የሚጠቀም፤ ሕፃናትን በማሳረድ÷ ሴቶች እኅቶቻችንና እናቶቻችንን በማሳረድና በማስደፈር÷ በመጦሪያቸውና በመከበሪያቸው ዘመን አዛውንቶችን በማስጨፍጨፍ÷ ቤት ንብረታቸውን በማዘረፍና እንዲቃጠል በማስደረግ እንዲሁም በማፈናቀል የኢትዮጵያን እናቶች ደም እምባ ያስለቀሰ፤መቅጠፍ መዋሸት የዕለት ተዕለት ተግባሩ ያደረገ፤ ጐሠኛነት ከደሙ የተዋሐደው፤ ላሰከረው ሥልጣን ሲል ብሔራዊ ጥቅማችንን ሁሉ ለባዕዳን አሳልፎ ለመስጠት የተዘጋጀ፤ ዓላማ በሌለውና በአሻጥር በተሞላ ጦርነት አእላፋት የሕዝብ ልጆችን ማግዶና አገራዊ ሀብትና ንብረት አውድሞ ሲያበቃ የግብር አባቱ ከሆነው በኢትዮጵያ ጥላቻ ካሳደገውና እሱ እንደሚመራው አሸባሪ ቡድን ከምድረ ገጽ መጥፋት ከሚገባው ሌላ አሸባሪ ቡድን (ወያኔ/ሕወሓት) ጋር ይሁዳዊ መተቃቀፍ በማድረግ ለሌላ ዙር መዓት እያዘጋጀን ያለ ‹ሰው› ነው የኢትዮጵያ መንበረ መንግሥት ላይ ተቀምጦ የሚያምሰን፡፡ 

እነዚህ ለምድር ለሰማይ የሚከብድ ወንጀል ከፈጸሙ ጭራቃዊ ቡድኖች (ኢሕአዴግ ከሚባለው አጋንንታዊ ቡድን ፍንክትካቾች) ለኢትዮጵያ ሰላም ይወርዳል ብሎ የሚያሰብ ሰው   ካለ መከራችን ማብቂያም አይኖረው፡፡ ካንድ ሳምንት በፊት ‹‹አማራው የመቀሌውን ሽርሽር እንዴት ማየት አለበት?›› በሚል ርእስ በጭራቁ አፍቃሪ የተጫረ በማር የተለወሰ ሬት አስተያየት አይቼ ነበር፡፡ የግለሰቡ ዋና መልእክት የዐምሐራ ሕዝብ አሳቢ መስሎ ‹‹አንተ ስትጠነክር ያኔ ዶር አቢይን ከጎንህ ታገኘዋለህ፡፡›› በማለት ኢትዮጵያ እንዴት ልገላገለው ብላ የምታስበውን የአገር ጠንቅ መድኃኒት/ፈውስ ተደርጎ እንዲታይ ያለመ ነው፡፡ እንደነዚህ ዓይነቶቹን በየቦታው ተልእኮ ተሰጥቷቸውም ይሁን በድንዛዜ ውስጥ ያሉ ‹ሕሙማን› እግዚአብሔር ከመድኃኒቱ ያገናኛቸው ከማለት ውጭ እሰጣ ገባ የሚያስፈልግ አይመስለኝም፡፡ ጽሑፋቸው ለሙግትም የሚበቃ አይደለምና፡፡ ለዐምሐራ ሕዝብ ግን ንቀት ነው፡፡

Filed in: Amharic