ማንኛውም ዓይነት የአምባገነኖች አፈና የባልደራስን ትግል ሊያስቆም አይችልም…!
ከባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ የተሰጠ መግለጫ
አንድነቷ የተጠበቀባት እና ዲሞክራሲ የሰፈነባትን ኢትዮጵያን ለማየት ከቆምንለት ዓላማ ዝንፍ አንልም!!!
ባልደራስ በፓርቲነት ከመቋቋሙ በፊት በባለአደራ ም/ቤት እንቅስቃሴ በሚያድርግበት ጊዜ፣ በህዝብ ጥያቄ መሠረት ወደፓርቲነት እራሱን ለመቀየር በተንቀሳቀሰበት ወቅት እና ፓርቲም ከሆነ በኋላ በገዥው ፓርቲ ለቁጥር የሚያታክቱ ተፅእኖዎች ሲደረግበት ቆይቷል።
የባልደራስ ለዕውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የቀድሞ ፕሬዘዳንት አቶ እስክንድር ነጋ ከማንም በፊት በኢትዮጵያ ውስጥ የዘር ማጥፋት እኩይ ተግባር ሊፈጸም የሚያስችሉ ምልክቶች እየታዩ መሆናቸውን ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ አስታውቀዋል፡፡
ባልደራስ ‹‹አዲስ አበባን ማዳን ኢትዮጵያን ማዳን ነው›› የሚል መፈክር አንስቶ የአዲስ አበባን ሕዝብ ቀስቅሷል፡፡ በዋና ከተማችን የነበሩ የማንነታችን ገላጭና ዕድሜ ጠገብ የሆኑ ቅርሶች በተረኞቹ ባለስልጣናት እንዲወገዱ ሲወሰንባቸው እንዳይፈርሱ ከፍተኛ ተጋድሎ አድርጓል፡፡ የአዲስ አበባ ኗሪዎች ዝንተ – ዓለም ከኖሩበት ቤታቸው በግፍ ሲባረሩ ባልደራስ አግባብ አለመሆኑን በመጥቀስ ደጋግሞ ጮኋል፡፡
ሀገር በእኩያኑ የህወሃት ሰዎች ስትወረር ባልደራስ ወራሪዎቹን ተቃውሞ የተለያዩ መግለጫዎችን አውጥቷል፡፡ ጦርነቱ ጋብ ሲልም በተለያዩ ደረጃዎች ያሉ የባልደራስ የአመራር አባላት አናብስቶቹ የአፋር ተዋጊዎች እና ቆራጦቹ የፋኖ አባላት አገርን ለመታደግ ለከፈሉት ዋጋ አሉበት ቦታ ድረስ በመሄድ አድናቆት እና ምስጋና አቅርበዋል፡፡ የባልደራስ አባላት በሰሜኑ ጦርነት ሳቢያ በተለያዩ የአማራና የአፋር ክልሎች ለተጎዱ ወገኖች የምግብና የአልባሳት ድጋፍ አድርገዋል፡፡ ፓርቲያችን ለማሳያነት ከጠቀሳቸው ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች በተጨማሪ በርካታ ሃገራዊ ተግባራትን አከናውኗል፡፡
ባልደራስ ለዕውነተኛ ዲሞከራሲ ፓርቲ ከምሥረታው አንስቶ እስካሁን ድረስ በሚያከናውናቸው ተግባራቱ የኦህዴድ ብልጽግና ፓርቲ እና በሥሩ በሚቆጣጠራቸው ተቋማቱ ከፍተኛ ጭቆናና በደል እያደረሱበት ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል በ2012 ዓ.ም. ወርሃ የካቲት ላይ የመጀመሪያ ጠቅላላ ጉባኤውን ለማካሄድ ገንዘብ ከፍሎ በተከራየው የሆቴል አዳራሽ እንዳይሰበሰብ የገዥው ፓርቲ ካድሬዎች በፈጸሙት ክልከላ ስብሰባውን በሜዳ ላይ ለማካሄድ መገደዱ አይዘነጋም፡፡ አሁን ሰሞኑን እንኳ ባልደራስ በኢትየጵያ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ውይይት ለማካሄድ የሆቴል አዳራሽ ተከራይቶ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ፈቃድ ስለተከለከለ ስብሰባውን ማድረግ ሳይችል ቀርቷል፡፡ የፊርማ ድጋፍ ለማሰባሰብ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፍቃድ አግኝቶ ድንኳን ጥሎ ቅስቀሳ ማድረግ እንዳይችል የገዥው ፓርቲ ካድሬዎች ድንኳኑን አስነስተውታል፡፡
የፓርቲው የወቅቱ ፕሬዘዳንት አቶ እስክንድር ነጋ፣ የድርጅት ጉዳይ ሓላፊው አቶ ስንታየሁ ቸኮል እና ሌሎች አባላቱ የሃሰት ክስ ተመሥርቶባቸው ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር በወህኒ ቤት ታስረው ሲንገላቱ ቆይተዋል፡፡
የጥቁር ህዝብ መኩረያ በሆነው የአድዋ በዓል ላይ በንቃት የተሳተፉ፣ የካራማራ የድል በዓል ለማክበር የወጡ እና በነፃነት ሃወልት አበባ ለማስቀመጥ የሄዱ የባልደራስ አባላት በተለያዩ የማጎሪያ ቤቶች ታስረው ተንገላትተዋል፡፡ የእነአቶ እስክንድር ነጋን የፍርድ ችሎት ለመከታተል የሄዱ የባልደራስ አባላትና ደጋፊዎች በገፍ ታሰረዋል፡፡ ሌሎችም የባልደራስ አባላትን ፖሊስ በተለያዩ ጊዜያት እያሰረ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ኢትዮጵያና በሌሎችም ክልልሎች እያዘዋወረ የሥቃይ ገፈት እንዲቀምሱ አድርጓል፡፡ ሰሞኑንም የአዲስ አበባ ት/ቤቶች ተማሪዎች የኦሮሚያ ባንዲራን እንዲሰቅሉና የክልሉን መዝሙር እንዲዘምሩ ከተፈጸመባቸው ማስገደድ እና ከተፈጠረው ተቃውሞ ጋር በተያያዘ የባልደራስ አባሎች የሆኑት አቶ ናትናኤል የዓለም ዘውድ እና አቶ ካሳሁን ደስታ ታስረው ከብዙ እንግልት በኋላ ተፈትተዋል፡፡
ኦህዴድ ብልጽግና የባልደራስን ፓርቲ በኢኮኖሚ ለማራቆት ባለው ፍላጎት የባልደራስ ታሳሪዎችን ፍርድ ቤቶች የዋሰትና ገንዘብ አስይዘው እንዲወጡ ሲወስኑና ባልደራስ የዋስትና ገንዘብ እየከፈለ የማስፈታት ሂደት ሲያከናውን፣ ፖሊስ ወደሌላ እስር ቤቶች እየወሰደ በማሰር እንዳይፈቱ ማድረግን የተለመደ ተግባሩ አድርጎታል፡፡ ባልደራስ እስካሁን ለእስረኞቹ ከሚያከናውነው የተለያዩ ወጭዎች በተጨማሪ ለእስረኞች ማስፈቻ ዋስትና ብቻ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ብር ለመንግሥት ካዝና አስገብቷል፡፡
ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ባልደራስ ገና ባለአደራ በነበረበት ጊዜ ‹‹ከባለአደራው ጋር ግልጽ ጦርነት ውስጥ እንገባለን›› ብለው በአደባባይ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡ ከዚያም ወዲህ ገዥው ፓርቲ በተከፋይ የሶሻል ሚዲያ መንጋዎቹ በኩል በባልደራስ ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ በመክፈት፣ እንዲሁም የኦህዴድ ብልፅግና አፍራሽ ሰርጎ ገቦችን ወደባልደራስ በመላክ ፓርቲውን ለማፍረስ ብዙ ጥረት አድርጓል።
ከአምባገነኑ ኦህዴድ ብልፅግና በተጨማሪ የፅንፈኛና አድርባይ ድርጅቶችም ባልደራስ ለዕውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲን ለማስተጓጎል ብሎም ለማፍረስ ብዙ ጥረዋል። ባልደራስ ከእነዚህ ውጫዊ እኩይ ሙከራዎች በተጨማሪም ከዚሁ ከፓርቲው ውስጥ የሥልጣን ጥም ካሰከራቸው እና ትግልን ለኪስ ማድለቢያነት ለማዋል ከሚሹ አመራረሮች እና አባላት ብዙ ፈተናዎች ደርሰውበታል።
ባልደራስ የተጠቀሱትና ሌሎችም ውጫዊ እና ውስጣዊ ተግዳሮቶች ቢገጥሙትም ችግሮቹን በብልሃትና በዘዴ እየተወጣ ሰላማዊ ትግሉን በማካሄድ ላይ ይገኛል። ለዚህም የቀድሞው ፕሬዝዳንት አቶ እስክንድር ነጋ፣ በፅናት እየታገሉ ያሉ አመራሮች፣ አባላት፣ ደጋፊዎቻችን እና ከኢትዮጵያ ውጭ የሚገኙ ድጋፍ ሰጭዎቻችን ትልቅ ምስጋና ይገባቸዋል።
ባልደራስ ለዕውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በበርካታ ጫናዎች ውስጥም ሆኖ እንኳን አንድነቷ የተጠበቀባት እና ዲሞክራሲ የሰፈነባትን ኢትዮጵያን የማየት ህልሙን ለማሳካት ትግሉን አጠናክሮ ቀጠለ እንጂ ከቆመለት ዓላማ ትንሽም እንኳን ዝንፍ ያላለ መሆኑን ለወዳጆቹና ለተቀናቃኞቹ ሁሉ ማሳወቅ ይወዳል።
የባልደራስ ለዕውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የብሔራዊ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
ታህሳስ 24 ቀን 2015 ዓ.ም.
ኢትዮጵያ አዲስ አበባ ባልደራስ