ዱላ አታቀብሉ፣ አታጋግሉ!!! (አንዱዓለም መኮንን)

ዱላ አታቀብሉ፣ አታጋግሉ!!!

አንዱዓለም መኮንን
የኦነግ አመራሮች አቀባበል ያማረ እንዲሆን እና የኦነግ ደጋፊ የሆኑ ወንድሞች ደሥ እንዲላቸው ማገዝ ተገቢ ነው። ከፀቡ በፊትም በሰከነ መንገድ ተነጋግሮ መግባባት መልመድ አለብን። አላሥፈላጊ የሆነ ፉክክር እና ብሽሽቅ አያሥፈልገንም።

ለወጣቱ ለባለፉት 27 ዓመታት ሲሰበክለት የኖረው ልዩነት እንጅ ወንድማማችነት እና መተባበር አይደለም። ሥለዚህ በትንሽ ነገር ወደፀብ ለማምራት ቀላል ሆኗል። ጦር ለማወጅም ማሰላሰል አያሥፈልግም። ሞባይልን ወጣ አድርጎ መተኮሥ ነው። ሃላፊነት የማይሰማው እና ቢራ እየጠጣ “አትነሳም ወይ” የሚል ብዙ ነው። የእብድ ገላጋዩ እና ዱላ አቀባዩ የትየለሌ ነው። የሚመክር እና አንተም ተው፣ አንተም ተው የሚል ነው የሚያሥፈልገን።

በዚህ የተነሳም ሰፊው መንገድ ይጠበናል። የምንፈልገውን ባንዲራ ለመሥቀል ሌላውን ማውረድ ተገቢ አይደለም። ሌሎችም የሚፈልጉትን እና አርማየ ነው የሚሉትን ቢሰቅሉ የሌላውን መብት እሥካልነኩ ድረሥ መብታቸው ነው። ሥንተባበር ሁሉም ቀላል ይሆናል። ሆደ ሰፊነት ያሥፈልጋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.