ከይኄይስ እውነቱ
ደጋግሞ እንደሚነገረው ፖለቲካ ሰፋ ባለ ትርጕሙ አገርና ሕዝብን የማስተዳደር ፍልስምና፣ ጥበብና ሳይንስ ነው፡፡ በዚህ ትርጕም የአንድ አገር ዜጋ በሙሉ ፖለቲከኛ ይሰኛል፡፡ ዜጋ ሆኖ ስላገሩ የማይመለከተው የለም፤ ስለ ሕዝቡ ስለወገኑም የማያሰብ አይኖርም ተብሎ ይገመታልና፡፡ በጠባቡ ደግሞ ባንድ ዓላማ ሥር ሆኖ፣ መርሐግብር ነድፎ፣ እንደ ሁናቴው አሰባሳቢ ርእዮተ ዓለምኖሮት ወዘተ. በማኅበር ተደራጅቶ የመንግሥት ሥልጣን ለመያዝ የሚደረግ ትግል ነው፡፡ በዚህ በኋለኛው ትርጕሙ ፖለቲካ የሥልጣን ወይም የፓርቲ ፖለቲካ ይባላል፡፡ በመርህ ደረጃ በፖለቲካ የተደራጁ ማኅበራት ውስጥ መሳተፍ መብትና ምርጫ ሲሆን፣ ፈላጭ ቆራጭ በሆኑ የሕዝብ መሠረት በሌላቸው አገዛዞች ውስጥ ግዴታ፣ የቊጥር ማብዣና ለተወሰኑትም ‹ልዩጥቅም› ማግኛ ነው፡፡
ርእሰ ጉዳዬ በፖለቲካ ቋሚ ጠላት ወይም ቋሚ ወዳጅ የለም ተብሎ የሚነገረው አባባል ለወሬ ማሳመሪያ የሚነገር ወይም በጥራዝ ነጠቅነት ‹የፖለቲካ ዐዋቂ ነኝ› ለማለት አቋም የሌላቸው ግለሰቦች ወቅቱንና ትግል የሚያካሂዱ ቡድኖችን አዝማሚያ እያዩ በዘፈቀደ የሚናገሩት ሐረግ አይደለም፡፡ ይህንን ዓይነቱን አቋም በአንዳንድ ኢ-መደበኛ ሚዲያዎች እየሰማን እንገኛለን፡፡ በፖለቲካ ቋሚ ጠላት የለም ሲባል ብርቱ ጥንቃቄ ተደርጎና ጠለቅ ያለ ፍተሻና ምርመራ ተደርጎ ከተግባራዊ ተሐዝቦት እና ተለዋዋጭነት ካላቸው ፍላጎቶች ተነሥቶ የተነገረ እንጂ እውነት ነው ብሎ እንደ መርህ ተቀብሎ የሚያናፍሱት የግል ፍላጎት ማስፈጸሚያ የጮሌዎች አባባል አይደለም፡፡ ሐረጉ የሚያስረዳን ፖለቲከኞች የሚጠቅማቸው ሆኖ ሲያገኙት የሚተባበሩበት እንጂ ሁሌም የሚሠራና እውነተኛ አባባል ተደርጎ ሊወሰድ አይገባውም፡፡ እንደ ዓውዱ እና ጠላት እንደተባሉት ኃይሎች ተፈጥሮ፣ ጠባይ፣ የኋላ ታሪክ፣ ዓላማ፣ አቋም፣ አፈጻጸም ወዘተ…የሚመዘን ነው፡፡ በምርጫ ዓውድ ስናየው የዓላማ መለወጥ፣ የኃይል አሰላለፍ ሚዛን መቀየርን በማየት የቆዩ ተቀናቃኞች አንዱ ሌላውን ጠቃሚ አጋር አድርጎ ሊያየው የሚችልበት ሁናቴ ሊፈጥር ይችላል፡፡ ወይም ቀደም ሲል የነበሩ የርእዮተ ዓለም ልዩነቶች ያበቃላቸው ክርክሮች ከሆኑ ለትብብር እንቅፋት ላይሆኑ ይችላሉ፡፡
በሌላ በኩል በአንድ አገር ውስጥ ያሉ ተጻራሪ ኃይሎች ያላቸው ግጭት ሥር የሰደደ ከሆነ፣ ልዩነታቸው መሠረታዊ በሚባሉ እሤቶች ከሆነ፣ መሠረታዊ የህልውና ጥያቄ ከሆነ፣ ወይም የትኛውም ወገን ሊቀይረው ወይም ሊረሳው የማይፈልገው መሠረታው የመርህ ጉዳይ ከሆነ ጠላትነቱ ቋሚ የማይሆንበት ምክንያት የለም፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ ወሳኝ ልዩነት ለጊዜያዊ ትብብርም ክፍተት አይኖረውም፡፡ መሠረታዊ እሤቶች ስንል ለአብነት ያህል ሥር የሰደዱ የሞራል፣ የሃይማኖት እና የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ለጊዜያዊ የፖለቲካ ጥቅም ሲባል የማይታለፉ ቋሚ የጠብ ግድግዳዎችን ይፈጥራሉ፡፡ ባንፃሩም የህልውና አደጋ ስንል ደግሞ በዐምሐራው ነገድ ላይ ካለፉት ግማሽ ምእት ዓመት ጀምሮ የምናየውና በቅርቡ 8 ዓመታት እጅግ ተባብሶ የቀጠለው ጥፋት ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ አንድን ማኅበረሰብ ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ያለመ ግጭት ለሰላማዊ ትብብር ቦታ አይኖረውም፡፡ በመርህ ደረጃ ደግሞ አገራዊ አንድነትን፣ እኩልነትን፣ የሕግ የበላይነትንና በዜግነት ላይ የተመሠረተ ፖለቲካ መቀበልን፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልን ወዘተ አንኳር ጉዳዮች ላይ በጽንፈኝነት ከቆሙ ኃይሎች ጋር የሚኖረው ልዩነት ቋሚ በመሆኑ ለጊዜያዊ ፖለቲካ ጥቅም ሲባል በጋራ ለመሥራት አይቻልም፡፡
ባጠቃላይ የጠላት ማንነትና ዓላማ የሌላው ማኅበረሰብ ጥፋት ላይ የተመሠረት ከሆነ ትብብር ሊኖር አይችልም፡፡ እንዲሁም እጅግ ከባድ ክህደቶችና በተደጋጋሚ የተፈጸሙ ቅንነት የጎደላቸው ተግባራት መተማመንን በመሠረታዊ መልኩ የሚያናጉ በመሆናቸው ሉዐላዊ በሆኑየፖለቲካ አሳቦች (ነፃነት፣ እኩልነት፣ ፍትሕ ወዘተ.) ለወደፊት የሚደረጉ ትብብሮችን የሚዘጉ ናቸው፡፡ በተለይም የአንዱ ወገን ማሸነፍ ለሌላኛው ወገን ሙሉ በሙሉ ጥፋት በሆነበት የዜሮ ድምር ፖለቲካ ጊዜያዊ ተቀናቃኝነት በቋሚ ጠላትነት እንደሚተካ ጥርጥር የለውም፡፡
ከዚህ ትንተና በመነሣት በፖለቲካ ከጠላት ኃይል ጋር የሚደረግ‹ጋብቻ› ወይም ‹ውሽምነት› ሌላ አማራጭ ካለ ባይደረግ ይመረጣል፡፡ የግድ ከሆነም ከፍተኛ ጥንቃቄ ይጠይቃል፡፡ ምክንያቱም ዓላማን ሁሉ ሊያስት ይችላልና፡፡ እንዲያውም ከታሰበውና ከሚፈለገው ውጭ የከፋ ውጤት ሊያመጣ ይችላልና፡፡
ሰሞኑን በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ላይ ቀዳሚ አርእስት ሆኖ እየተናፈሰ ያለው ‹አገራዊ ምክክር› የሚል ታላቅ ፌዝና የዐምሐራ ፋኖ ከአፅራረ ኢትዮጵያ ኃይሎች (ሕውሃት/አነግ) ጋር ስለሚያደርገው አጉል ‹ውሽምነት› ነው፡፡ ቀደም ብሎ ከተሰጠው ቋሚ ጠላት የሚፈጠርበት ትንታኔ አኳይ በእኔ ትሁት እምነት የተጠቀሱት አፅራረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ለኢትዮጵያ ባጠቃላይ ለዐምሐር ሕዝብ በተለይ ቋሚ ጠላቶች በመሆናቸው በኢትዮጵያዓውድ ከነዚህ ኃይሎች ጋር የሚደረግ ጊዜያዊ ‹ጋብቻም› ሆነ‹ውሽምነት› አስፈላጊ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ እስካሁንበተግባር ካየነው አደገኛና አስቀያሚ ያለፈ ታሪክ፣ አፈጻጸም፣ ጠባይ፣ ወዘተ አኳያ የኋላ ኋላ የሚያመጣው መዘዝና ጥፋቱ የከፋእንደሚሆን መገመቱ ስሕተት አይሆንም፡፡
ኦነግ እና ሕወሓት እንደ ቅደም ተከተላቸው ከሃምሳ እና አርባ ዓመታት በላይ ራሳቸውን ‹ነፃ አውጪ›› ብለው በዚሁ ስያሜ የቀጠሉ አፅራረ ኢትዮጵያ ኃይሎች መሆናቸው የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ይህንኑ በኢትዮጵያና ሕዝቧ ላይ ያላቸውን የጠላትነት አቋም በአፍም በመጣፍም በተግባርም ያስመሰከሩ ኃይሎች ናቸው፡፡
እነዚህ ከኢትዮጵያ አንድነት በተፃራሪ የቆሙ ዘረኛ ኃይሎች በዓላማ አንድነት የሚቀራረቡት ርጉም ዐቢይ ከሚመራው የኦሕዴድ-ኦነግ አገዛዝ ጋር መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ ኦነግ የሻእቢያ ውሉድ ሲሆን፣ ‹ብልግና› የሚባለው የርጉም ዐቢይ አገዛዝ ደግሞ የሕውሓት ውሉድ ነው፡፡ ሕወሓት ጽንፈኛ የትግራይ ጐሠኞችን ያሰባሰበና ትግራይን ነፃ አገር ለማድረግ የሚታገል ድርጅት ነበር ሳይሆን አሁንም ነው፡፡ የርጉም ዐቢይ አገዛዝ ደግሞ በሕወሓት የዘረኝነት ሥርዓት ላይ ተመሥርቶ ጽንፈኛ ኦሮሞ ነን የሚሉ ለኦሮሞ ሕዝብ ያልቆሙ በኢትዮጵያ ጥላቻ የሰከሩ አረመኔ አጭበርባሪዎችን የያዘ ቡድን ነው፡፡ ዓላማውም ወያኔ ሕውሓት ከ40 ዓመት ወዲህ የፈጠረለትን‹ኦሮሚያ› የሚባል ተምኔታዊ ግዛት ነፃ አገር ለማድረግ ሲሆን፣ ይህንንም አፍራሽ ተልእኮውን በኢትዮጵያ መቃብር ላይ ለማሳካትኢትዮጵያንና ሕዝቧን በማያቋርጥ ‹መንግሥታዊ› ሽብር እየናጠ ያለ የልቡሰ አጋንንት ስብስብ ነው፡፡
ስለሆነም የዐምሐራ ፋኖ በኢትዮጵያ አንድነት ከሚያምኑ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ኃይሎች ጋር የሚያደርገው ስትራቴጂካዊ ትብብር እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ቋሚ ጠላቶቹ ከሆኑት ከሕወሓት እና ከኦነግ ጋር ለጊዜያዊ የፖለቲካ ጥቅም በትብብር መሥራት የግድ አያስፈልገውም የሚል አመለካከት አለኝ፡፡ ፋኖ አንድነቱን ካጠነከረ፣ ድርጅታዊ አሣሩንና ዐቅሙን ካጎለበተ፣ ዓላማውን አጽንቶ ከያዘ የሕወሓት እና የኦነግ ዘላለማዊ አሽከር የሆነውን በድኑን ብአዴን ያለ ርህራኄ ካስወገደ ከእነዚህ የጥፋት ኃይሎች ጋር ጊዜያዊ ‹ጋብቻ› በጭራሽ አያስፈልገውም፡፡ ባለቀ ሰዓት የሚጸጽተንን አደገኛ ስሕተት መፈጸም ብዙዎች የተሠዉለትን እና እየተሠዉለት ያለውን የህልውና ትግል ከንቱ እንዳያደርግ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ አሁንም በትዕግሥት ደግሞ ደጋግሞ መምከርና መደማመጥ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ቊልፍ ጉዳይ ለጥቂት አመራር ነን ለሚሉ የሚተው ሳይሆን ኢትዮጵያን አገሬ ሕዝቧን ወገኔ የሚል የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ መላው የዐምሐራ ሕዝብ እና መላው የዐምሐራ ፋኖ ያገበዋል፡፡






















