ታሪክ ራሱን ሊደግም?

“ሀገር አድን” እና “ጽምዶ”

ስንታየሁ ታከለ

በአማራ ትግል ውስጥ ዕድሜየ መሳሪያ ለመሸከም ዝግጁ ከሆነ ጊዜ ጀምሮ በአፍላ ጉልበቴ ተሳትፌለሁ። አቅም በፈቀደ መጠን ሁኔታዎችን በንቃት ተከታትያለሁ።

ምናልባትም የፖለቲካ ትንታኔ ሴራና መሰል ነገሮችን በቢሆን ዕድል ደረጃ በጥናት ላይ የተመሰረተ ትንታኔ ላልጽፍ ላልናገር እችላለሁ። ይህንን የማላደርገውም በዚህ ሙያ ላይ ጊዜአቸውን ሰጥተው ለሚጽፉ ፕሮፌሽናሎች ተንታኞች በመተው ነው። እንዲህም ሆኖ አፍላ የወጣነትነት ጊዜየን ያሳላፍኩበት ትግልና የሕዝብ አጀንዳ በተለይም እንደ እጄ መዳፍ በማውቀው ጉዳይ ስሞግት ቆይቻለሁ።

በዚህም በድጋፍና በተቃርኖ መሀል ብዙ ነገሮችን አይቻለሁ። ምክንያታዊ አስተያየቶችን ስማርባቸው፤ የፍረጃ ምላሾችን ደሞ ንቄ አልፌቸዋለሁ። ሁሉም ጉዳይ አስተምሮኝ አልፏል። ዛሬም የምናገረው በአፍላ ወጣትነት ዕድሜየ ካየሁት የሕይወት ተሞክሮ፤ ካገኘሁት እውነታ ጋር በመቆም ነው።

ሀገር አድን ምስረታና የወቅቱ ፕሮፖጋንዳ

ወቅቱ የዛሬ 10 ዓመት ነበር። ቦታው ደግሞ ኤርትራ ሃሬና በርሃ። በ 2008 የኢትዮጵያ ሁኔታ በተለይም የአማራ ተጋድሎ ተቀጣጥሎ ነበር። ጎንደር ሐምሌ 5 የለኮሰችው ችቦ፣ ሐምሌ 24 ላይ ተቀጣጥሎ በትውልድ ከተማየ ባህርዳር ነሐሴ 1 ቀን በነ አበበ ገረመው መስዋዕትነት ተቀጣጥሏል። ሕዝባዊ አመጹ ወደ መሀል ጎጃም እየተሻገረ ነው። ደመላሿ ወልድያ ለፀረ ህወሃት ትግል እየተነቃቃች ነበር። መሀል ሸዋ የአማራ ብሄርተኝነት በመቃቃት ላይ ነበር።

ይህን ሁኔታ የታዘበው የፖለቲካ ነጋዴው ብርሃኑ ነጋ፣ በኤርትራ በረሃ አንድ የጥምረት አጀንዳ ይዞ ብቅ አለ። የትግል መርህ የማያውቀው ብርሃኑ፣ በአገር ቤት የተቀጣጠለውን መነቃቃት በ “ጥምረት” ስም ለመጥለፍ “ሀገር አድን” የሚል የጉግ ማንጉግ ስብስብ ፈጠረ። ያ ጥምር በአጭር ግቡ ዲያስፖራውን በማነቃቃት በገንዘብ ለማለብ፤ በረዥም ግቡ ደግሞ በአማራ ልጆች መስዋዕትነት ጥሩ የስልጣን ተደራዳሪ መሆን ነበር።

ብርሃኑ ነጋ ይህን እያሰበ በ 2008 ጳጉሜ ወር ጥምረቱን ከኤርትራ በረሃ በይፋ አሳወቀ፦

የጥምረቱ አባላት፦

1) አርበኞች ግምቦት ሰባት
2) ዴምህት (ዴሞክራሲያዊ ምንቅስቃስ ሕዝቢ
ትግራይ)፣
3) አዴሃን፣
4) የጋምቤላ ነጻ አውጭ ድርጅት (ጋነአድ)፣
5) የጉምዝ ነጻ አውጭ ድርጅት (ጉነአድ)፣
6) የኦሮሞ ነጻ አውጭ ግምባር (ኦነግ)፣
7) የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ)፣

በመሆን ሀገር አድን የሚባል የጋራ ድርጅት መስርተናልና እወቁልን አሉ።

በወቅቱ በኢሳት ቴቪም ሆነ በሌሎች ሚዲያዎች አጀንዳው ወደ ኢትዮጵያ ህዝብ ተላከ። ህዝቡም የአንድ ሀገር ዜጎች ሁነው ለምን አንድ ሁነው አይታገሉም በማለት ጥያቄ ያነሳ ስለነበር ለጥያቄው ምላሽ ስለተሰጠው ፕሮፖጋንዳው ጫፍ ወጥቶ በአንድ ወር ውጊያ በወቅቱ የነበረውን መከላከያ ደምስሶ መሀል አዲስ አበባ የሚከሰት አስመስሎት ተስፋ ያደረገ አልጠፋም ነበር።

ለሀገር አድን ጥምረቱ እውነተኛ አርበኞች ፍላጎትና ስሜት ነበራቸው። ሆኖም ከጥምረቱ ጀርባ የነበረው ከኢትዮጵያ ህዝብ የተደበቀ በፕሮፖጋንዳ ብቻ የተሸፈነ ፍላጎት ስለነበር ሁኔታዎች በቀናት ልዩነት ይገለጡ ጀመር። ጳጉሜ 3 አንድነቱን አውጀው ጳጉሜ 5 የዴምህት ሊቀመንበር በኋላም የጥምረቱ ምክትል ሊቀመንበር ሞላ አስገዶም በደረቅ ሌሊት የድርጅቱን የቡድን መሳሪያ ታጥቆ በኤርትራ ምዕራባዊ ግዛት ኦምሃጀር/ስኩትር ደርሶ ከሻቢያና ከእኛ ጓዶች ጋር ተኩስ ከፈተ።

የተኩሱ ዓላማ ሽሽት ነው። ተዘጋጅቶበት ስለነበር ማንም ሊያስቆመው ባለመቻሉ፣ ከድንበር ማዶ በሱዳን በኩል የሚጠብቁትን የወያኔ ደህንነቶች ሂዶ ተቀላቀለ። “ሞላ ለወያኔ እጅ ሰጠ” የሚል ዜና በማለዳው ሰማን። እዚህ ላይ የጨዋታውን ቀመር ማስታወስ ያስፈልጋል። ጥምረቱ በአላማ ፈጽሞ የማይገናኙ አንድ ነን ያሉት በሻቢያ ተገደው እንደነበር ትልቁ ማሳያ የሞላ አስገዶም ታሪክ ነው።

ከጥምረቱ ጀርባ የነበረውን የፕሮፖጋንዳ ሂደትና የጥምረቱን ሰራዊት እኔ ከነበርኩበት ድርጅት ውጭ ያሉትን ሻቢያ በሚሰጣቸው ሎጅስቲክስ የሰው ብዛታቸውን ግምት ውስጥ በማስገባትና ከነሱ ከድተው ወደኛ አርበኞች ግምቦት ሰባት የተቀላቀሉት በሚሰጡት መረጃ ተነስተን ኤርትራ ውስጥ ከነበሩት ከፍተኛውን ሰራዊት ይመራ የነበር ዴምህት 3ሺህ አካባቢ ጦር ያለው ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 90% ሰራዊቱ በትግራይ ጠረፋማ አካባቢዎች እና በማዕድን ማውጫ ቦታዎች በግዳጅ እየታፈሰ የሚመጣ እንደሆነ ይታወቃል።

ከነዚህም ውስጥ በያኔ በወረራ ተይዞ በነበረው ሁመራ አካባቢ ገጠራማው ክፍል ሰርግ ይደረግ በነበረ ጊዜ ሙሽሮችን እና ሚዜዎችንና አጠቃላይ የሰርጉን ታዳሚ ጨምሮ አፍሶ መጥቶ በግድ ታጋይ ናችሁ በማለት አሰልጥኖ ታጋይ አድርጓቸው ነበር።

በዚህም ጉዳይ ዶቼቬለና ቪኦኤ በወቅቱ ዜና አድርገውት ነበር። የዴምህት ሰራዊት በዚህ መልኩ በግድ የተሰበሰበና ከማሽላ አጨዳ ውጭ የውጊያ ላይ ተሳትፎ የሌለው ድርጅት ነበር። በአጭሩ የዴምህት ስብስብ ለትጥቅ ትግል ሳይሆን ለግብርና ሥራ የሚቀርብ ነበር።

እኔ ወደ ነበርኩበት አርበኞች ግምቦት ሰባት ስንመጣ አጠቃላይ የሰው ሀይሉ ሁለት መቶ ሰባ ብቻ ነበር። የአዴሃን ሶስት መቶ የሚጠጋ ነበር። ኦነግም እንዲሁ ተቀራራቢ ከ250-300 አይበልጥም። አብዛኛዎቹ የኦነግ ሰዎች ምኞታቸው ሳውድ አረቢያና ዱባይ ገብቶ መነገድ ነበር። ኤርትራ በረሃ ላይ ከመቀመጥ የመን አሳ እያሰገሩ መኖር የሚመርጡም አይጠፉም።

ከነዚህ ጋር ጥምረት ፈጠርኩ ያለው የቤንሻንጉል ጉምዝ ነጻ አውጭ ግምባር አምስት አባላት ብቻ ያሉት ሲሆን፤ ይህ የአንድ ቤተሰብ ስብስብ ከድርጅት ተርታ ተሰልፎ አሟሟቂ ነበር። የሚገርመው ነገር ከአምስቱ ውስጥ በስልጣን እርስ በእርስ ተጣልተው ሁለቱ ተገዳደሉ። ሶስት ብቻ ቀርተው ከእኛ ካምፕ አጠገብ ዘውትር ከፍየሎቻቸው ጋር ሲንቀሳቀሱ እናያቸው ነበር። ቀለባቸውን የሚሰፍርላቸው ኮሎኔል ፍጹም (ሌኒን) ነበር።

ዋናው ጉዳይ ያ ሀገር አድን የተባለው ድርጅት በተመሰረተ በሁለተኛ ቀኑ የተበተነው በአስገዳጅ ሁኔታ ስለተሰባሰቡ ነው።
በሻቢያ በኩል ቀጭን ትዕዛዝ መጣ። አንድ ካልሆናችሁ ትጥቅም ስንቅም የለም ተባሉ። ከመሞት መሰንበትን መረጡና ሀገር አድን ጥምረት ብለው መጡ። የብርሃኑ ነጋ ስሌት ደግሞ ሌላ ነበር።

የኢሳት ፕሮፖጋንዳ ሰማይን የመቧጠጥ ያህል ነበር። ውስጡ ስትገባ ግን እንኳን አንድ ላይ ሊታገሉ አንዳችን ከአንዳችን ድንገት መንገድ ላይ ብንገናኝ ተተኳኩስን እንገዳደላለን ወይም ከአርበኞች ግምቦት ሰባት ወደ ዴምህት እዚያው በዚያው በምርኮ ዝውውር የሚፈፀምበት ሁኔታ ነው የነበረው።

በዚህ ድራማ መሀል ግን አሁንም ፕሮፖጋንዳው ይጦዝ ነበር።

በመጨረሻም የአማራ ተጋድሎ እየበረታ በሌሎች አካባቢዎችም ሕዝባዊ ትግሎች፣ አድማና አመፅ ተካሂዶ ኢህአዴግ ፍርክስክሱ ወጣ። “ታጋዮች ነን የምንለውን” ሕዝቡ ነጻ አውጥቶን “ለውጥ” የሚባለው መጣና ለጎሪጥ እየተያየን ወደ ኢትዮጵያ ተበታትነን ገባን።

የአሁናዊ የጽምዶ ጉዳይ

ጽምዶ 9 ድርጅቶች አንድ ላይ ሁነን ልንታገል ነው እያሉን ነው። ዋና ዋና ጽምዶዎችን ብናይ ወያኔ በአስር ሺህዎች የሚቆጠር ሰራዊትና ሜካናይዝድ የሆነ ሰራዊት ነው። ፋኖን ብንመለከት ህዝባዊ ትግል በመሆኑ ለቁጥር የሚያስቸግር ሆኖ እናገኘዋለን። ኦነግ ሸኔን በሚመለከት የሁለቱን ያህል ባይሆንም ተቀራራቢ ሀይል አለው ነው።

የሶስቱ ዋና አለቃ ራሱ ሻቢያ ነው። ለሎጅስቲክስ ድጋፍ እንድሚመቸኝ ተጣመሩ ባለው መሰረት ያለ ምንም የፖለቲካ ስምምነት “ጠላትን እንጣል” በሚል ብቻ ቸ ፈረሴ እያሉ ናቸው።

በትግል ሂደት ውስጥ ቋሚ ጠላትና ወዳጅ ባይኖርም ቋሚ ጠላቴ ነህ ብሎ እድሜ ልኩን የተደራጀን ሀይል አብሬህ ልሰለፍ ብለህ በራስህ ፍቃድ መሄድ ማለት በአጭር አማርኛ “በስልጣን ዘመናችሁ የገደላችሁንን የበደላችሁንን ሁሉ ምንም እንኳን እናንተ ይቅርታ ባትጠይቁም እኛ ይቅር ብለናችኋል የእናንተም ሚሊሻ መሆንን እንፈልጋለን” እንደማለት ነው።

በፋኖ በኩል ጽምዶ ነን ብለው ይፋ ያደረጉ አካላት አንድ ትንሽ ነገር ጠብቄ ነበር።

እሱም “በህውሓት/ኢህአዴግ የአማራ ህዝብ የተገደለው፣ የታሰረው፣ የተሰደደው፣ በቆሰለውና በደማው እኛ ምክንያት በመሆናችን የአማራን ህዝብ ይቅርታ እንጠይቃለን” ያስብሏቸዋል ብዬ ነበር። አልሆነም።

በ2008 ዓ.ም ነሀሴ1 በባህር ዳር ከተማ ከ120 በላይ ወጣትን በጥይት የጨረሰው የወቅቱ የመከላከያ የምዕራብ ዕዝ አዛዥ ጄኔራል ፍስሃ ኪዳኑ (ፍስሃ ማንጁስ) ነበር።

ታዲያ በምን አግባብ ነው የፋኖን ትግል እንዲመራ አሳልፈህ የምትሰጠው?

ይህ ብቻውን ከህዝብ አይነጥልም ወይ?

እነዚያ በወያኔ ጥይት የተገደሉትኮ ወንድሞቻችን ናቸው። የግልጽነት ጥያቄ ብንጠይቅ ብልጽግና ልትሉን ነው? በፍጹም!

ኤርትራ የተመሰረተው “ሀገር አድን” ድርጅት “ወያኔ ይውደቅ እንጂ ሌላውን እንነጋገርበታለን” ተባለ። ወያኔም ወደቀና የባሰ መጣ።

የአሁኑም ጽምዶ አይኑን ጨፍኖ “ብልጽግና ይውደቅ እንጂ ሌላውን እንነጋገርበታለን” እያለ ነው። ይህ ሀሳብ ብቻውን ከወያኔ ሚሊሻነት ያለፈ ምንም ነገር የለውም። ጽምዶው የሚሰዋለትን አላማ ከብልጽግና መውደቅ ውጭ ሌላ ማሳየት ያልፈለገው የተደበቀ ነገር ምን አለ?

የትግራይ ወጣት አልዋጋም ብሎ እየሸሸ ባለበት የአማራን ወጣት ያለ ማንም ተቆርቋሪ በስመ ጸረ ብልጽግና ትግል እየማገዱ ማስጨረስ ተገቢ አይደለም። የተጻመዳችሁበትን ዝርዝር ምክንያት ለህዝብ ሳታሳውቁ በግል ስልጣንና በቡድን ጥቅም ስሌት ብቻ አይታችሁ ለመሸወድ መሞከር ፍጻሜው ኪሳራ ነው። በኔ የትግል ግምገማ ጽምዶ ለአማራ የባርነት ካምፕ ነው! ለገዳይ የማገልገል ክፉ አመል ነው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.