ሶስቱ ነጥሎ መምቻ ስልቶች!

ጌታቸው ሽፈራው

ለ27 አመታት የኢትዮጵያን ተቋማትን በይፋ የተቆጣጠረ ኃይሉን ይዞ ወደ ትግራይ የሸሸው ትህነግ ከዋናው ጦርነት በፊትም ሆነ በኋላ የራሱን ትርክቶች ስልታዊ በሆነ መንገድ በሌሎች ለማስለመድ አቅም ነበረው። በተለይ የደህንነት ተቋማትን ጨምሮ የፕሮፖጋንዳውን ክንፍ የሚመሩ ኃይሎቹ በሌሎች ኃይሎች በኩል የራሱን ትርክት እንዲያራምዱለት አድርጓል። አሁንም ድረስ እንዲያራምዱለት እያደረገ ያለው በድሮው እርሾው ጭምር ነው። በሀሰት የራሱን ትርክት ሲያሰራጭበት ከኖረው፣ ከቀጠለው መካከል አማራው አንዱ ነው። እንደ ምሳሌ ወልቃይቶን ለመነጠል እየሰራባቸው ያሉትን ስልቶች እንመልከት።

1ኛ የቁራጭ መሬት ትርክት

ትህነግ በስልታዊ መንገድ ከዘራቸው የፕሮፖጋንዳዎች መርዞቹ መካከል አንዱ “ቁራጭ መሬት” የምትለዋ ትርክት ነች። ለአመታት የዘር ፍጅት የፈፀመበት ወልቃይት ከሀምሌ አምስት በኋላ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ የታወቀ አጀንዳ ሆኗል። ለውጥ ከተባለ በኋላ ደግሞ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ትህነግ ለምን ወልቃይት ጠገዴን በኃይል እንደጠቀቀለ ከኢትዮጵያ ጥቅሞ አንፃር የተለማመዱበት ሀቅ ሆኗል። የማይካድራን ጭፍጨፋ ጨምሮ ሌሎች እውነቶች ኢትዮጵያውያን ስለ ወልቃይት ጠገዴ ትኩረት እንዲያደርጉ፣ የዘር ፍጅቱን ታሪክና አድማስ ተረድተው የትህነግ የሀሰት ትርክት እንዲቀል ሆኗል። በዚህ ወቅት ታዲያ ትህነግ የገነኑበት የአማራ እውነታዎች ከመከራከር ይልቅ ራሱ ወልቃይትን በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ምንም ለማስመሰል ጥረት አደረገ። “ቁራጭ መሬት” የምትል ፕሮፖጋንዳን አማራ ነን በሚሉ ወገኖች ጭምር አሰራጩ። አማራ የሚያምንበት አስመስለው የትህነግ ሚዲያዎችና ዲጅታል ወያነ ይህን ትርክት ለረዥም ጊዜ ሰርተውበታል። ወልቃይትን ቁራጭ መሬት በማስመሰል የህዝብን ጉዳይ በማቅለል ለአመታት የፈፀሙትን ዘር ፍጅት ከቁራጭ መሬት ጉዳይ ጋር ብቻ አያያዙት። የወልቃይት ጠገዴን ስትራቴጅካዊነትና ሌላውን አቃልለው ኢትዮጵያውያን ትኩረት እንዳይሰጡት “ተራ” ጉዳይ ለማስመሰል ሰሩበት። ወልቃይት በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ለመነጠል ከሰሩት ባሻገር ከአማራም መነጠል ስልት ተከትለዋል። ሁለተኛው ስልታቸው ይህ ነው።

2ኛ ወልቃይትን እንደ ጥቂት ቡድኖች ፖለቲካ

የወልቃይትን በተለየ የአማራ አፅመ ርስቶችን አጀንዳ እንደ አጠቃላይ ከአማራው የፖለቲካ አጀንዳም ለመነጠል የተጠቀሙት ጉዳዩ የተወሰኑ ኃይሎች ፍላጎት እንጅ የአማራ ህዝብ ፍላጎት እንዳልሆነ በማስመሰል ነው። የአማራ ርስቶች ጉዳይ የአማራን ቀርቶ የኢትዮጵያ ህዝብን ትግል ጭምር ያበረታ እንደሆነ ሆዳቸው ቢያውቅም የድሮ የፕሮፖጋንዳ ሰንሰለታቸውን ተጠቅመው ጉዳዩ የአማራ እንዳልሆነ ለማስመሰል አሁንም ድረስ እየሰሩበት ይገኛሉ። አሁን በየሚዲያው የሚያስጮሁት የሰሊጥ ጉዳይን ጨምሮ የሚያሰራጯቸው ፕሮፖጋንዳዎች ወልቃይት ጠገዴን ከአማራ አፅመ ርስትነት አጀንዳ አውርደው አማራው የተወሰኑ ኃይሎች አድርጎ እንዲመለከተው ስለፈለጉ ነው። በየቀኑ ከግለሰብ እስከ ፀጥታ ተቋም ላይ የሚደረገው የተናበበ ዘመቻም የአማራን አፅመ ርስት ከአማራው ነጥሎ ለማጥቃት ነው። ትህነግ አርሶ አደሩን አፈናቅሎ በድርጅት ተቋም በኩል ሰሊጥም ሆነ ሌላውን ሲያመርት ኖሯል። በቅርብ አመታት ትህነግ አርሶ አደሩን አፈናቅሎ የያዘው መሬት ወደሱዳን ጭምር ተሰድደው ለነበሩ ባለንብረቶቹ ተመልሷል። ይህ በሆነበት የድሮው የእሱ ወንጀል ሳይሆን ባለንብረቶቹ የሚያመርቱት ሰብል እንደ ወልጀል ተቆጥሮ እንዲሰራጭ የሚደረገው የወቅቱ ፕሮፖጋንዳ እውነታው ሳይሆን ነጥሎ ማጥቂያ ስልት ስለሆነ ነው። ወልቃይት ጠገዴን ግን ነጥለው ማጥቃት የሚፈልጉት ከአማራ ማንነቱ ብቻ አይደለም። ከኩታ ገጠም ወረዳና ዞኖቹ ሰፋ ሲል በታሪክ እንደ አማራ የመጀመሪያ ክሩ ከሚሳብበት ከጎንደር አማራም ጭምር ነው። ወልቃይትን ከዳባት፣ አርማጭሆ፣ ግማሹን “ፀገዴ” ብለው ከጠገዴና መተማ ጭምር ነው መነጠል የሚፈልጉት።

ይህ ሲሆን ከኢትዮጵያም ከአማራም ከጎንደር አማራም ተነጥሎ የሚመቱበት መንገድ ነው።
ሶስተኛው ስልታቸው ይህኛው ነው።

3ኛ “ወልቃይት አማራም ትግሬም አይደለም” ቅስቀሳ

ይህን ስልት የጌታቸው ረዳው ክንፍ ትህነግ በቅርቡ በስፋት እየሄደበት ነው። ሰሞኑን እነ አሉላ ሰለሞን በሚዲያ ብቅ ብለው የወልቃይት ጠገዴ ነባር አማራ ላይ የደረሰውን በደል ያመኑና ግማሽ መንገድ የመጡ በመምሰል ብቅ ያደረጉት ፕሮፖጋንዳ ይህ ከሁሉም ነጥሎ የመምታት ስልት ነው። የመቀሌው ትህነግም ይህን ስልት ከፊት አድርጎ ባይጠቀምበትም የጌታቸው ቡድን የሚያራምደው ይህ ስልት ነጥሎ የመምቻ መንገድ እስከሆነ ድረስ በሆነ መንገድ ይጋራዋል። ይህ ወልቃይትን አማራም ትግሬም ነው ሳንል መፍትሔ እንስጠው የሚለው ከትህነግ ዋና መነጠያ ስልቶች የተቀዳ ነገር ግን ሲፈልጉ “ቁራጭ መሬት” ሲፈልጉ የሰሊጥ እርሻ ያህል ወልቃይትን ሲያቃልሉላቸው ለነበሩ ለሌሎች ኢትዮጵያውያን አንዳንዴ ለአማራውም ቢሆን እንደ መፍትሔ አስመስለው የሚያቀርቡት ሆኗል። የአማራን ርስቶች አጀንዳ የሚደፍቀው ብልፅግና ጋር የተጠጉት እነ ጌታቸው ረዳ ለራሳቸው ፖለቲካ ሲባል የድሮውን አማራን በ”ፀ” እና በ”ጠ” ፖለቲካ ነጣጥሎ ማጥቃት ስልቶ ለማጠናከር የዚህ ፖለቲካ ዋና ምንጭ ከሆነው መለስ ዜናዊ ሚስት አዜብ መስፍን ጨምሮ፣ አማራ ርስቱን ማግኘት ከጀመረ ለእኛም ያሰጋናል የሚሉ የብልፅግና ኃይሎችን ጭምር ይዘው እየሰሩበት ይገኛሉ። አሉላ ሰለሞን ያን ንግግር ሲያደርግ ቆርጦ ለጌታቸው ረዳም ሆነ ለእነ አዜብ መስፍን እንደሚልክ እናውቀዋለን። ይህ ስልት በአማራው በጠና በፀ በነሏቸው ዞኖችና ወረዳዎች ብቻ ሳይሆን ወልቃይትማ በምንም ተአምር ከአማራ ተነጥሎ ሊቀመጥ አይችልም በሚሉና እነ ጌታቸው ረዳም ሆነ እነ አዜብ መስፍን በሚጨቀጭቋቸው የወልቃይት ጠገዴ አመራሮች፣ የተከዜ ዘብ ሆነ ሌላው መካከል አለመተማመንና ጥርጣሬ ፈጥረው እስከ መጨረሻው አተራምሰውና ለያይተው ነው ማንም የማይቆምለት ቀጠና አድርገው በቀላሉ እንረከበዋለን የሚሉት። ይህን አካሄድ እነ ጌታቸው ረዳ ስልታዊ አድርገው፣ የመቀሌው ረዥምና አድካሚ ነገር ግን ከተሳካ አጨብጭቦ የሚቀበለው አድርጎ የሚወስደው ነበር። እስካሁን ወልቃይት ጠገዴንና ህዝቡን ሲያጠቁባቸው የነበሩትን ስልቶች ደርበው፣ ከብልፅግና እስከነ አዜብ መስፍን ያሰለፉበት ይህ ስልት ትህነግ ግማሽ መንገድ የመጣበት ሳይሆን የመጨረሻ ካርዴ ብሎ እየተጠቀመበት የሚገኘው ነው።

የወልቃይትን ጉዳይ በቁራጭ መሬትነት በኢትዮጵያውያን ፊት ለማቅለል ሞክረዋል። አማራውን ርስትህ ሳይሆን የተወሰኑ ቡድኖች የሚጠቀሙበት ነው እያሉ እየዘመቱ ነው። አሁን ደግሞ ዋናው የዘር ፍጅታቸው የሚጋለጥበትን አማራነት፣ ዋናው የማንነት ጥያቄ የሚያጠነጥንበትን መሰረቱም ጋር አቋርጠው ብቻውን ነጥለው ለመምታት ሶስተኛውን ስልት ጀምረውታል። ሶስቱ የተለያየ ደረጃ ቢኖራቸውም ማንነትን ክዶ ለቀጣይ ዘር ፍጅት ማዘጋጀት ነው። አማራውን ከወገኑ ነጥሎ በማጥቃት አፅመ ርስቶቹን መልሶ የመረከብ ያረጀ ያፈጀው የትህነግ መንገድ ነው! የአዋጭነት ደረጃ ላይ እንጅ እነ ደብረፅዮንም ውጤት ካመጣላቸው ከእነ ጌታቸው ረዳ የማይለዩበት ስልት ነው። በተለይ ራሱን፣ ርስቱንና ወገኑን ሰድቦ የሚነጠል፣ የሚነጣጠል ካገኙ በእነዚህ ርስቶቹ ላይ ብቻ ሳይሆን መላው አማራ ላይ ለቀጣይ የሚተግብሩት ነው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.