ሴኩቱሬዎችና የሰሞኑ ዘመቻቸው በወፍ በረር ቅኝት ሲፈተሽ!
ህወሃት ሲኦል ብትወርድ ልደቱ አያሌው ከሲኦል አለ!
ጋዜጠኛ ወንድወሰን ተክሉ
ሶስቱ አንድም ናቸው። ደግሞም ሶስትም ናቸው። አንዳርጋቸው ጽጌ፣ ልደቱ አያሌው ይልቃል ጌትነት ተለያይተውም አንድ የሆኑበትና አንድ የሚሆኑበት ጉዳይ አላቸው። ሶስቱም በአማራ ሕዝብ ዋጋ ከፋይነት የትግራዩን ህወሃት ዳግም ወደ አራት ኪሎ እንድትጋዝ እጅግ የፈለጉ ናቸው። ሶስቱም ዛሬ ላይ ለህወሃት ያላቸው ፍቅር እኩል ሲሆንም በጣም በሚገርም ሁኔታ ሶስቱም የህወሃት ባለውለታዎች ነን የሚሉ የህወሃት ግርፍ ፖለቲከኞች ነን ባይ ናቸው።
ዘመኑ ይለያያል እንጂ ሶስቱም ከፖለቲካው ጋር የተዋወቁት በህወሃት ነው። እናም ሰሞኑን አንድ ገና ስላልተወለደ ጽንስ ብለው ሶስቱም በየተራና በየፊናቸው እየተናበቡና እየተቀባበሉ በታላቁ አርበኛ እስክንድር ነጋ ላይ ሲዘምቱና ሲረባረቡ ታይተዋል። በአርበኛው ላይ ሊዘምቱ የቻሉበት ምክንያት ሶስት አበይተ ምክንያቶች አሉአቸው።
1ኛ-የህወሃት አሁናዊና መጻኢ የስልጣን ህልውና እጅግ አስጨንቃቸዋል
2ኛ- ቀደም ብሎ ጽምዶ፣ ለጥቆም ጥምረት/ትብብር/አጋርነት የሚል ስም የተሰጠው ጽንስ ቶሎ እንዲወለድ በእጅጉ ጓጉተዋል። ይህ ያልተወለደውና ገና ሳይወለድ አንዴ ጽምዶ አሁን ደግሞ ጥምረት የሚል ስም ያወጡለት ጽንስ ካልተወለደ የህወሃት ስልጣናዊ ህልውና ብቸኛ ባቡር ነው ብለው በመቀበላቸው ይህ ህወሃትን ወደ ስልጣን በመመለስ ድርጅታዊ ህልውናዋን ዳግም ለስልጣን አብቅቶ ማስቀጠል የሚችል ኃይል አለው ያሉት ጥምረት/ጽምዶ ብለው የሰየሙት ጽንስ ካልተወለደ ህወሃት ለዝንተ አለሙ ከስልጣን የተባረረች ሆና ትቀራለች ብለው ገምግመዋል። እናም ይህ ጥምረት የተባለውና በጽንስ ውስጥ ያለ ጽንስ ይወለድ ዘንድ የማያደርጉት ነገር የለም።
3ኛ- ጽንሱ ሳይወለድ ሊጨነግፍ ይችላል ብለውም በእጅጉ ሰግተዋል፣ በእጅጉም ተጨንቀዋል። የዚህ ጽንስ አጨናጋፊ ታላቁ አርበኛ እስክንድር ነጋ ነው ብለውም ብለው ደምድመዋል። ከአንድ አለም አቀፍ የምእራባዊያን ሚዲያ (DW) ጋር ከሳምንት በፊት ባደረገው እጅግ አጭር ቃለ ምልልስ ታላቁ አርበኛ ለመወለድ ተቃርቦ በነበረው የጽምዶ ጽንስ ላይ ባሳረፈው ጡጫ ጽምዶ ሊጨነግፍ ችላል ብለው ያምናሉ። በጽምዶ ምትክ የተተካውና እናትና አባቱ ተመሳሳይ የሆኑት የጥምረት ጽንስም በተመሳሳይ ሁኔታ በታላቁ አርበኛ የእውነት ቡጢ ሳይወለድ ጨንግፎ ይሞታል ብለው እጅግ ሰግተዋል። እናም ሶስቱም እናታቸውን ህወሃት የስልጣን ህልውናን ለመታደግ አደጋ ደቅናል ባሉት ታላቁ አርበኛ ላይ የተናበበ ተኩስ ሊከፍቱበት ቻሉ።
3ኛ አመቱን በያዘው የአማራ ሕዝብ የህልውና ትግል ጸረ አማራዋ ህወሃትና ኦነግ በአንድ ላይ ተጣምረው በጋራ የብልጽግናን አገዛዝ ይታገሉ የሚለውን ሀሳብ ሻእቢያ እንዳፈለቀ ይነገራል። ይህንንም የጋሪዮሽ የትብብር አንድነት መጀመሪያ ጽምዶ ብለው ያስተዋወቁት ሲሆን ለጥቀውም ጥምረት በማለት በማለት ይገልጹት ጀምራል።
ጽምዶም አሉት ጥምረት ግን በገሀዱ አለም የሌለ ገና በምናብ ደረጃ ያለ የሰባት ታጣቂ ኃይሎች ህብረታዊ ጥምረት የመጠሪያ ስም ነው ተብሎ ተገልጾልናል። ሆኖም በአለም ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ይህ የታሰበው እቅድ ነፍስ ዘርቶ ድርጅት ሆኖ ሳይወለድና ሳይታወቅ ገና በሀሳብ ደረጃ ላይ እያለ አንዴ ጽምዶ- ሲጨነግፍ ደግሞ ጥምረት በማለት ስም ያወጡለትና ይህ ስምም ካልተወለደው ድርጅት በፊት በአየር ላይ እጅግ ተጋኖ ስሙ እንዲጠራ የተደረገ በሀሳብ ደረጃ ያለ ጽንስ ነው።
እንደነዚህ አፍቃሬ ህወሃት ሴኩቱሬዎች አገላለጽ ጽምዶ ወይም ጥምረት ማለት ልክ በ1980ዎቹ መግቢያ ላይ የደርግ ኢሰፓን መንግስት ለመገርሰስ ህወሃት፣ ኢሕዴን/ብአዴን፣ ኦህዴድና ደህዴህ ሆነው የኢትዮጲያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኢህአዴግ) ተብሎ እንደተደራጀው ጸረ ደርግ ኢሰፓ ዛሬ የኤርትራው ሻእቢያ፣ የሱዳኑ አልቡርሃን፣ የትግራዩ ህወሃት፣ የአማራ ፋኖው አፋብን፣ የኦሮሞው የኦሮሞ ነጻንት ሰራዊት (OLA) የቤኒሻንጉሉ የጉምዝ ታጣቂና የአፋሩ አፋጉጉ ሆነው የፈጠሩት ጸረ ብልጽግና ጥምረት ነው ባይ ቢሆንም ጥምረቱን ስጋ፣ ደምና አጥንት ይዞ እንደተወለደ ልጅ ድርጅታዊ ቅርጽና ይዞታ ይዞ ገና ሳይወለድ በሀሳብ ደረጃ (በጽንስ ውስጥ እያለ) ልክ እንደተወለደ ህጻን – ማለቱም ጥምረቱ እንደተደራጀ ድርጅት አድርገው ስሙን ከድርጅታዊ ህልውናው መበሰር እጅግ ቀድመው ያስተዋውቁት ጀመር።
ይህ ጸረ አቢይ ጥምረት ያልተወለደና ያልተፈጠረ በሀሳብ ደረጃ ያለ ጽንስ ነው የምንልበት ምክንያት አንድን ድርጅት ፣ ድርጅት ሆናል የሚያስብሉትን :-
1ኛ- የጥምረቱ አባል ድርጅቶችም ሰባቱም በውስጣዊ ስምምነት ወደ መጣመሩ ለመጋዝ በየድርጅታቸው በአብላጫ ድምጽ ወስነው ከጨረሱ
2ኛ- የጥምረቱ አባል ድርጅቶች የእንጣመርን ውሳኔ ካሳለፉ በኃላ የጥምረቱን ጠቅላላ ጉባኤ ጠርተው:-
1ኛ- ጠቅላላ ጉባኤና ማእከላዊ ኮሚቴ ሲያቋቁሙ
2ኛ- የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሲያዋቅሩ
3ኛ- የጥምረቱን ሰብሳቢ፣ ምክትል ሰብሳቢን ጨምሮ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን አመራር ይፋ ሲያደርጉ
4ኛ- የጥምረቱን የጋራ ማህተም፣ሎጎ ቀርጸው ይፋ ሲያደርጉ
5ኛ- የጥምረቱን መተዳደሪያ ሕግና ደንብ ያጸደቁ ሲሆን
6ኛ- የጥምረቱን ፍኖተ ካርታ አርቅቀውና አጽድቀው የመታገያ ድርጅታዊ አይዲኦሎጃቸውን አጽደቀው በእጅ ሲይዙ ድርጅት የተመሰረተ ድርጅት ተብሎ ይጠራል።
ሶስቱ በማንነት ቀውስ ቫይረስ የሚሰቃዩት ሴኩቱሬዎች ግን ጥብቅና ቆመው ስሙን ሊሸጡ የሚጋጋጡለት ጥምረት የሚባለው ስብስብ ከዚህ በላይ የተዘረዘሩትን አንዱንም ሂደት ያልፈጸመ ስለሆነ አንዴ ጽምዶ አሁን ላይ ደግሞ ጥምረት እያሉ የሚጠሩት ድርጅት የተወለደ ሳይሆን ገና በሀሳብ ደረጃ ላይ ያለ ሊወለድም ሆነ ላይወለድ የሚችል ጽንስ ብቻ እንደሆነ ነው ጥምረቱ አሁን ያለበት ሁኔታ የሚያሳየን።
እናም ሶስቱ ሴኩቱሬዎች – ማለትም ልደቱ አያሌው፣ ይልቃል ጌትነትና ሼባው አንዳርጋቸው ጽጌ ይህን ያልተወለደን ጥምረት የተባለን ጽንስ ሊያስጨነግፍ የሚችል ታላቁ አርበኛ እስክንድር ነጋ በ DW ላይ ወጥቶ እጅግ አጭር ቃለ ምልልስ ስለሰጠ ጥምረቱ ጨንግፎ ከመሞቱ በፊት አርበኛው ይሰቀልልን አይነት ዘመቻን ተነጋግረው ይሁን ተናበው በተከታታይ በታላቁ አርበኛ ላይ ሲያዥጎደጉዱ ለመስማት በቃን።
ገና በአፍላ እድሜው በ1980ዎቹ ከአባታችን ፕ/ር አስራት ወልደየስ ጋር ሆኖ በመዐሕድ ድርጅት ለነገደ አማራ ሕዝብ ህልውና መታገል የጀመረውና ከ1985 ዓ ም ጀምሮ “..አማራ ታሪኩን ያድሳል..” በሚል መሪ መፈክር ቃል ላለፉት ሶስት አስርተ አመታት በጽኑ አቋም ለአማራ የታገለውና የህልውናውን ትግል ግንቦት 23 ቀን 2023 E.C የአማራ ሕዝባዊ ግንባር መስርቶ የትግሉን ችቦ “ሀ” ብሎ የለኮሰውን ታላቁ አርበኛን እስክንድር ነጋ እንዴት ለ DW ወጥቶ ስለጥምረቱ ይናገርል በሚል ሶስቱ None Amhara የሆኑት ሴኩቱሬዎች ስሙን የማብጠልጠል ዋልጌ ተግባር ሲፈጽሙ ስናይ የሶስቱን ሰዎች የጤንነት ሁኔታ እንድንመረምር አድርጎናል።
ለመሆኑ በማንነት ቀውስ ቫይረስ የሚሰቃዩት ሶስቱ አፍቃሬ ህወሃት እነማን ናቸው ብለን በመጠየቅ ምላሹን እስቲ እንፈልግ።
1ኛ- የ 73 ዓመት አዛውንቱ ሼባ እንግሊዛዊው አንዳርጋቸው ጽጌ
ይህ ግለሰብ በ60ዎቹ አመቱ ውስጥ በስተርጅና የትውልድ ዘር ግንዴን እስከሰባት ድረስ በመቁጠር ኦሮሞነቴን አገኘሁ ያለን ሲሆን አማራ የሚባል ነገድ እንደ ሕዝብ ፈጽሞ የለም ብሎ ህልውናችንን የካደ የአለማችን ቁጥር አንድ ጸረ አማራ Opportunist የሆነ ሰው ሲሆን ዛሬ የፖለቲካ Constituency የሌለው ተንሳፋፊ ሰው በመሆኑ ያ የለም ላለው የአማራ ሕዝብ ገና በአፍላነቱ ጀምሮ ላለፉት ሶስት አስርተ አመታት ለነገደ አማራ ሕዝብ ሲታገል እዚህ ከደረሰው ታላቁ አርበኛ እስክብድር ነጋ ይልቅ እኔ ለንደን ያለሁት እንግሊዛዊ ሽማግሌ የተሻለ አስባለሁ ሊለን እየዳዳ ያለ ሀፍረተ ቢስ ቅሌታም ሽማግሌ ነው።
2ኛ- ህወሃት ሲኦል ብትገባ ከህወሃት ጎን የማይጠፋው ልደቱ አያሌው
ትውልዱ በወሎ ቤተአምሃራ ሆኖ እሱ ግን እኔ አማራ ሲባል የማውቀው ክርስቲያን የሆኑትን እንጂ እንደ ነገድ አማራ የሚባል ሕዝብ ስለመኖሩ አላውቅም በማለት የራሱን ነገዳዊ ማንነት በመካድ አንዲትም ቀን አማራ ነኝ ብሎ ለአማራነቱና በአማራነቱ ተሳትፎና አስተዋጾኦ አድርጎ የማያውቀው ሰው ወዳጁን ህወሃት ለመታደግና በአማራ ህዝብ ዋጋ ከፋይነት ለአራት ኪሎ ለማብቃት ለአማራ ከታላቁ አርበኛ እስክንድር ነጋ ይበልጥ አሳቢ መስሎ በመቅረብ በአርበኛው ላይ የጭቃ ጅራፉን ለማሳረፍ ሲታትር የታየ ሰው ነው ልደቱ ማለት።
የህይወት ዘመኑ ሻእቢያን ጠላቱ አድርጎ አምርሮ ሲያወግዝ የሚታወቀው፣ ከሰላማዊ ትግል ውጪ በትጥቅ ትግል ፈጽሞ አላምንም ባዩ ልደቱ አያሌው ህወሃት ከሻእቢያ ጋር ስትታረቅና በትጥቅ ትግል ወደ ስልጣን ለመመለስ ስታንጋጥጥ እሱም የሻእቢያ ወዳጅና የትጥቅ ትግል ደጋፊ በመሆን “..ጥምረቱን መደገፍ ምርጫ የሌለው ውሳኔ ነው…” በሚል አቋም ለአማራ ሕዝብ ላለፉት አራት አመት በጫካ ውስጥ ካለው ከታላቁ አርበኛ እስክንድር ነጋ ይልቅ እኔ አስብለታለሁ በሚል ብልጣብልጥነት ጥምረቱን ያልተቀበለ የብልጽግናን አገዛዝ የሚደግፍ ነው ብሎ እስከመፈረጅ ደረጃ ያደረሰን ድፍረት ይዞ ብቅ ያለ በማንነት ቀውስ ቫይረስ ተይዞ የሚሰቃይ ህመምተኛ ሰው ነው።
3ኛ– በአማራይቱ ጎጃም ምድር ተወልዶ እኔ አማራ የሚባል ስም ለመጀመሪያ ግዜ የሰማሁት ዩንቨርስቲ ውስጥ ነው፣ አማራ የሚባል ሕዝብ ስለመኖሩ የማውቀው ነገር የለም ብሎ ህልውናችንን የካደውና የፖለቲካ ህልውናው በህወሃት ከታቢነት የተከተበው ይልቃል ጌትነት በአማራነቱ ጸንቶ ለነገደ አማራ ሕዝብ በመታገል ከሶስት አስርተ አመታት በላይ ከሆነው ታላቁ አርበኛ እስክንድር ነጋ ይልቅ እኔ ነኝ ለአማራው የምቀርበውም ሆነ ለአማራው የማስበበ በማለት እንደ እብድ እያደረገው ታላቁን አርበኛ ሲሳደብ ልንሰማ ችለናል። የዚህም ሰውዬ – ማለትም የይልቃል ከፍያለ ምኞት፣ ፍላጎትና አቋም ጸረ አማራዋ ህወሃት በአማራ ሕዝብ ዋጋ ከፋይነት ህወሃትን ወደ አራት ኪሎ በመመለሱ ሂደት ላይ የመጋጋዣ ባቡር የሆነውን ጥምረት ያልተቀበለው ታላቁ አርበኛ እስክንድር ነጋን ጨምሮ ሁሉም የብልጽግናን አገዛዝ የደገፉ ናቸው የሚል መሀይማዊና ህወሃታዊ ፍርጃን ከአቻዎቹ ጋር ሆኖ ሲያስተጋባ የተሰማ ሌላው በማንነት ቀውስ ቫይረስ የሚሰቃይ ህመምተኛ ሰው ነው።
እነዚህ ሶስት በማንነት ቀውስ የሚሰቃዪ አፍቃሬ ህወሃት እኛ የምናመልከውን ሁሉ- ሎሲፈርም ቢሆን የማያመልክ እርምጃ ሊወሰድበት የሚገባ ነው እያሉ ሲቀደዱ ትንሽም ቢሆን ስቅጥጥም አላላቸው።
ታላቁ አርበኛ እስክንድር ነጋ ባለፈው ሳምንት በእለተ ሰኞ ከ DW ጋር ባደረገው አጭር ቃለ ምልልስ የአማራ ሕዝብ የህልውና ትግል ከአቻ ኢትዮጲያዊያን ታጣቂና ጸረ ብልጽግና ኃይሎች ጋር ጥምረት ማድረግ የሚገባ መሆኑን ገልጾ ከህወሃትና ከOLA ጋር ተደረገ ስለተባለው ጥምረት ግን :-
1ኛ- የአፋብን ሰራዊት የማያውቀው መሆኑን
2ኛ- የአፋብን ፖሊት ቢሮ መክሮበትና ዘክሮበት በአብላጫ ድምጽ ያሳለፈው አለመሆኑን
3ኛ- ከጸረ አማራ ኃይሎች ከሆኑት ህወሃትና OLA ጋር የሚደረጉ የጥምረት ትብብሮች በድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ፣ በሰራዊቱ ቀጥተኛ ተሳትፎ በአብላጫ ድምጽ አልፎ የተወሰነ መሆን እንዳለበት በመጥቀስ – አማራው ለህልውናው ለመታገል ጫካ የገባው ከእነዚህ ከጸረ አማራ ኃይሎች ጋር ለመታገል እንደመሆኑ መጠን ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ ከእነዚህ ጸረ አማራ ኃይሎች ጋር የሚፈጠር ጥምረት ሊኖር አይችልም በማለት የመርህ፣ የአካሄድና የህግና ደንብ ሁኔታዎችን በመግለጹ እነዚህን ሶስቱን በማንነት ቀውስ የሚሰቃዪትን አፍቃሬ ህወሃትን ጨምሮ በደርዘን የሚቆጠሩ አማራ ነን ባይ አፍቃሬ ህወሃት ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች እየተቀባበሉ ሊረባረቡበት ቢችሉም ለነገደ አማራ ሕዝብ ህልውና ምቾትና ቤተሰቡን ትቶ ጫካ የገባው ታላቁ አርበኛ ከአቋሙ ስንዝር ያህል ፈቀቅ ለማለት እንዳልፈቀደላቸው ነው ማየትና ማወቅ ነው የቻልነው። አበቃሁ።



















