>
5:18 pm - Thursday June 15, 0851

ዶ/ር አብይ ኢትዮጵያን ለምሳ ሲያስቧት አብዲ ኢሌ ለቁርስ አድርጓት ነበር! (ስዩም ተሾመ)

Seyoum Teshome

ዶ/ር አብይ ከዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋር ባደረገው ስብሰባ ለተነሱት ጥያቄዎች አጥጋቢ ምላሽ ሰጥቷል። ሆኖም ግን አንድ ጥያቄን በአግባቡ ለመመለስ ተስኖት ነበር። ይህ ጥያቄ የሱማሌ ተወላጅ በሆኑ ሁለት ምሁራን የቀረበ ነው። በተለይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑ አንድ የሱማሌ ተወላጅ መምህር:

“አያቴ ካራማራ ተራራ ላይ ለሀገሩ ሞቷል! አባቴ ከቤታችን በር ላይ በታጣቂዎች ተገድሏል! ሁለት ወንድሞቼ በአብዲ ኢሌ ታስረው ይሰቃያሉ? እኔ ወደ ተወለድኩበት ጅግጅጋ ከተማ ሄጄ መኖርና መስራት እየፈለኩ ማድረግ አልቻልኩም። አዕምሮው ጤነኛ ያልሆነ ሰው (አብዲ ኢሌ) እንዴት የአንድ ክልል ፕረዜዳንት ይሆናል? አሁን ዶክተር እኔ የምጠይቆት አንድ ጥያቄ ብቻ ነው። እሱም “ሶማሌ ኢትዮጵያዊ አይደለም ወይ?” የሚል ነው። በእርግጥ ሶማሌ ኢትዮጵያዊ ከሆነ እንዴት ህዝቡን የዚያ እብድ መጫወቻ እንዲሆን ትፈቅዳላችሁ? በእውነት ሶማሌ የኢትዮጵያ አካል ከሆነ ዶ/ር እንዴት ይሄ እንዲሆን ትፈቅዳለህ?”

በእውነቱ የመምህሩ ጥያቄ በጣም ልብ የሚነካ ነበር። በተመሳሳይ የቀብሪደሃር ዩኒቨርሲቲ ፕረዜዳንት “እኔ በሕይወቴ ላይ ቆርጬ ነው የምናገረው” በማለት “የሶማሌ ህዝብ መቼ ነው ከእዚህ ሰውዬ (አብዲ ኢሌ) የሚገላገለው?” ሲሉ ጠይቀዋል። ለሁለቱም ምሁራን ጥያቄ ታዳሚዎች ከፍተኛ ድጋፍ ተሰጥቷቸዋል። ጥያቄው የሁለቱ ብቻ ሳይሆን የሁሉም የሀገሪቱ ምሁራን ጥያቄ እንደሆነ በአሳዩት ድጋፍ ገልፀዋል። ከዚህ አንፃር ዶ/ር አብይ ተጨባጭ እርምጃ ከመውሰድ ውጪ ምርጫና አማራጭ እንደሌለው የተገነዘበ ይመስለኛል።

ይህን ተከትሎ ዶ/ር አብይ አብዲ ኢሌን ለማስወገድ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ የቀጠለ ይመስለኛል። በዚህ መሃል አብዲ ኢሌ ሊመታ እንደሆነ በህወሓቶች በኩል ሹክ ይባላል። ዶ/ር አብይ ከአሜሪካ ጉዞ መልስ አዲስ አበባ እንዲመጣ ለአብዲ ኢሌ ቢልኩበትም ሰውዬው አሻፈረኝ ብሎ ይቀራል። በእርግጥ አብዲ ኢሌ የተጠራው ከፌደራል መንግስት ባለስልጣናት እና ከጸጥታና ደህንነት ኃላፊዎች ጋር በክልሉ እየተባባሰ ስላለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለመወያየት ነበር።

አብዲ ኢሌ ደግሞ ወደ አዲስ አበባ የመጠራቱ ሚስጥር ለስብሰባ ሳይሆን ከዚያም በላይ ለከፋ ነገር እንደሆነ በመገመት ወደ ነፍስ አባቶቹ ስልክ ይደውላል። እነሱም ዶ/ር አብይ ከስልጣን ሊያስወግደው እንደሆነ ይነግሩታል። በዚህ መሰረት ሁለት ዓይነት ምክር ይሰጡታል። የመጀመሪያው በክልሉና በአጎራባች አከባቢዎች ሁከትና ብጥብጥ እንዲያስነሳ ነው። ይህን ተከትሎ በተለይ ባለፉት ሁለት ቀናት ራሱን ለመከላከል ደጋፊዎቹን ከያሉበት ወደ ጅግጅጋ ከተማ እንዲመጡ ያደርጋል። ትላንት ደግሞ የተወሰኑ የልዩ ኃይል አባላትን ውደ ድሬዳዋ በመላክ ሁከትና ብጥብጥ ለማስነሳት ይሞክራል። ነገር ግን፣ ሙከራው በመከላከያ ሰራዊት ይከሽፋል።

የአብዲ ኢሌ ነፍስ አባቶች ሁለተኛው ምክር በአንቀፅ 39 መሰረት የሶማሌ ክልልን ከኢትዮጵያ መገንጠል ነው። በዚህ መሰረት አብዲ ኢሌ የክልሉን ምክር ቤትና ካቢኔዎች ስብሰባ ይጠራል። ይህ ደግሞ ከፌደራል መንግስት ጆሮ ይደርሳል። ዶ/ር አብይ አብዲ ኢሌ የጠራውን ስብሰባ ሰርዞ ከፌደራል መንግስት ኃላፊዎች ጋር ስብሰባ እንዲቀመጥ ይነግሩታል። አብዲ ኢሌ ግን አሻፈረኝ ብሎ ዛሬ ጠዋት ሰብሰባውን ማካሄድ ይጀምራል። ዶ/ር አብይ ገና እያጠመደው ሳለ አብዲ ኢሌ ዘልሎ ሊያመልጥ ሆነ። በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 39 መሰረት የአንድ ብሔር የራሱን እድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል “መብቱ በማንኛውም መልኩ ያልተገደበ ነው”። ስለዚህ አብዲ ኢሌ ይህቺን እድል ተጠቅሞ ለማምለጥ ሙከራ እያደረገ ሳለ የመከላከያ ሰራዊት ወደ ስብሰባ አዳራሹ ዘው አለ። አብዲ ኢሌ ጎትቶ አስወጣው ስብሰባውም ተበተነ። ከዚህ ቀጥሎ የሚሆነውን አብረን የምናይ ይሆናል።

 

Filed in: Amharic