>
5:16 pm - Wednesday May 23, 3184

ቡናውን ማን ጠጣው⁉️ (ካሳ አምበሳው)

ቡናውን ማን ጠጣው⁉️
ካሳ አምበሳው
የማወራው ሰለ አንድ እፍኝ ቡና አይደለም፤ በሁለት ቀን ውስጥ ጭልጥ ተደርጎ ስለተጠጣው 29 ሺህ ቶን ወይም 29 ሚሊየን ኪሎ ግራም ቡና ነው፤ አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ጠጥቶት አይደለም ለአይኑ አይቶት ስለማያውቀው ደረጃ አንድ ለአለም ገብያ የተዘጋጀ 29 ሚሊየን ኪሎ ግራም ቡና፤  በገንዘብ ሲተመን ከ150 ሚሊየን ዶላር በላይ የሚያወጣ ቡና፤
የተጠጣው የኢትዮጵያን ምርት ገበያ ድርጅት (ECX) ተብሎ በሚጠው ድርጅት ውስጥ ነው፤ ቡናውን አፍልታ ስታበቃ አቦሉን ራሷ ልፋ ጀሌዎቿን ቶና እና በራካውን ያጠጣችሁ እሌኒ ገ/መድህን ናት፤ እሌኒ ማን ናት? የኢትዮጵያን ምርት ገበያ ድርጅትስ?
ሙሉ ስሟ እሌኔ ዘውዱ ገ/መድህን ይባላል፤ የተወለደችው አዲስ አበባ ሲሆን በዜግነት ሲዊዘርላንዳዊ (Swiss) ነች::
በስታንፎርድ፣ በሚችጋን እና በኮርኔል ዩኒሸርስቲዎች ትምህርቷን ተከታትላለች፤ ኢትዮጵያ ከመግባቷ በፊት ለአለም ባንክ ሰርታለች፤ የእሌኒ ሙሁራዊ አቅም ተጠየቅ ውስጥ የሚገባ አይደለም፤ እውቀቷን የተጠቀመችበት መንገድ ግን ታሪክ ይቅር የሚለው አይደለም፤ በደፋናው ለክፉ መንፈስ ተላለፋ የተሰጠች ጭንቅላት ተሸክማ የምፆር ሴት ናት፤ ቮን ብራውን (Von Braun) የመሰሉ የምጡቅ አዕምሮ ባለቤቶች ለጀርመኑ ናዚ የቀኝ እጅ እንደነበሩ ሁሉ እሌኒ ገ/መድህን ኢትዮጵያን እግር ከወርች አስራ በወያኔ [እንደ ጥገት ላም] አሳልባታለች፤
ወደ ሀገር ቤት ያመጣትን ጉዳይ ስትገልጽ <<የኢትዮጵያን የንግድ ስርዓት መልክ እንዳሲዘው ከጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ጥሪ ደረሰኝ>> ትላለች፤ ጥሪውን ተቀብላ ጨርቄን ማቄን ሳትል ወደ አዲስ አበባ አቀናች፤ ጠቅላይ ሚንስቴሩ ጽ/ቤት አንድ ቢሮ ተሰጥቷት ስራዋን ጀመረች፤ የኢትዮጵያን ምርት ገበያ ድርጅት (ECX) ተብሎ የሚጠራው ድርጅት  እሌኒ እና መለስ ቢሮ ዘግተው ጸነሱት፤ ይህ ድርጅት የዛሬ አስር ዓመት በአዋጅ ቁጥር 550/2000 ተወለደ::
የዚህ ድርጅት ዋና ተግባር በመላ ኢትዮጵያ የሚመረቱትን የቡና፣ ጥራጥሬ እና የቅባት እህሎችን ለውጭ ገበያ አቅራቢዎች ማጫረት ነው፤ በመጀመሪያ የቡና፣ ጥራጥሬ እና የቅባት እህሎች ተሰብስበው ECX መጋዘን ይገባሉ፤ በመቀጠልም የጥራት ደራጃ ይወጣላቸዋል፤ በመጨረሻም የመነሻ ዋጋ ይሰጣቸውና የድርጅቱ አባል የሆኑ ላኪዎች እንዲጫረቱ ይደረጋል፤ ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጥ ላኪ አሸንፏል ተብሎ ጨረታው ይዘጋል፤ የዚህ ድርጅት አባል እና ተጫራቾች የህወሓት እና የህወሓት አጋፋሪዎች መሆናቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፤ በብሉንበርግ (bloomberg) ዘገባ መሰረት የኢትዮጵያን የብና እና የቅባት እህሎች በዋነኝነት ለውጭ ገበያ እያቀረበ ያለው የኢፈርቱ ጉና ትሬዲንግ ነው፤ ከዚህ ተነስተን ECX የጉና መጋዘን ነው ብንል ከእውነቱ አንርቅም፤ የሀገሪቱን ጠቅላላ የውጭ ንግድ በዚህ መልኩ በአንድ እዝ አስገብታ ስታበቃ ህወሓትን እነሆ በረከት አለችው፤ ECX ምን ያህል በሙስና የነቀዘ መሆኑን ለመረዳት ከስር በተራ ቁጥር 1 ላይ የተሰጠውን ማስፈንጠሪያ ተከትለው ያንቡ::
የይስሙላው ጨረታ ሳያያቸው የውሃ ሽታ የሆኑ ምርቶች ቁጥር ስፍር የላቸውም፤ የዛሬ 8 ዓመት ገደማ 10 ሺህ ቶን (10 ሚሊየን ኪሎ) ቡና ከECX መጋዘን ጠፋ ተባለ፤ በአንድ ጀንበር 10ሺህ ቶን ቡና ግጥም ተደርጎ ተጠጣ፤ ይህ ያበገናቸው ውስጥ አዋቂዎች ጉዳዩን ለግል ጋዜጦች ሹክ አሉ፤ በአለም አቀፍ ደረጃም መነጋገሪያ ሆነ፤ ይህን ጊዜ መለስ ዜናዊ በቴሌቪዥን ብቅ ብሎ <<ያለፈው አልፏል ከንግዲህ መደገም የለበትም>> ብሎ ፋይሉን ዘጋው፤ ከስር በተራ ቁጥር 2 ያለውን ማስፈንጠሪያ ተከትለው የመለስን መልስ ይመልከቱ::
የዛሬ አመት ደግሞ 19 ሺህ ቶን (19 ሚሊየን ኪሎ) ቡና እጣን ሳያጨሱ ጠጡት ድምጽ ሳያሰሙ እሌኒ መጋዘን ጠጡት፤ ይህን አስመልክቶ አዲስ ዘመን ጋዜጣ የሰራውን ሪፖርት ከስር በተራ ቁጥር 3 ያለውን ማስፈንጠሪያ ተከትለው ያንቡ፤ ከሁሉ የሚገርመው ለይስሙላ እንኳን ህግ ፊት የቀረበ ሰው አለመኖሩ ነው፤ እንግዲህ እነዚህ ለሚድያ የበቁ ዘረፋዋች ናቸው፤  ዛሬ ሌላ ቀን፤ የሚዲያ ብርሀን ያላያቸው ብዙ ጉዶች መውጣታቸው አይቀርም፤ በአልማዝ የተንቆጠቆጡ ብራስሌቶችን ብቻ የሚያውቀው የእሌኒ እጅም ከካቴን ጋር መተዋወቁ አይቀሬ ነው፤
የፎቶ መግለጫ፤
በግራ በኩል ደረቱን ሰጥቶ የሚታየው ጀበና  10 ሺህ ቡና መቀቀል የሚችል ሲሆን የቆመው መቀሌ ነው፤ አንድ ዛላ ቡና የማታበቅለው መቀሌ 10 ሺህ ኪሎ ቡና በአንዴ መቀቀል የሚችል ጀበና ሰርታለች፤ በቀኝ በኩል ያለው ፎቶ እሌኒ ከአዲሱ ለገሰ እና ከመለስ ዜናዊ ጋር ስትሞዳሞድ ያሳያል፤
Filed in: Amharic