አሻግሬ መሸሻ
በ1994ዓም በህወሃት ውስጥ የተፈጠረው መሰንጠቅ /አንጃነት/ ተከትሎ በአሸናፊነት የወጣው የመለስ ቡድን ተንበርካኪ አባል ድርጅቶቹን በመጋለብ በቤተሰባዊነት (ቦና ፓርቲዝም) ደዌ የተመታው ድርጅታችን ፈውስ ያሰፈልገዋል በማለት የመለሰ ድርሰት የሆነውን የአብዮታዊ ድሞክራሲን ትርክት በአዲስ ራዕይ መፅሄት የቆረጣ ጉዞ (የመታደስ አብዬት) ጠላቱን በመንሽ ጠራርጎ ከቡድን አምባገነንነት ወደ ግለሰብ አንባገንነት የመሸጋገሩ ጉዞ ስሙር ሆነ።
ያንን ተከትሎ መንጋው የስም አመራር መለሰን እንደ ድርጅት መሪ ብቻ ሳይሆን እንደ ፈጣሪ ቆጥሮ አጎንባሽ በመሆን ባሰገሩት መንገድ ሽምጥ የሚጋለብ የመነዳት ጉዞ የመጋለብ ዘመንን በፀጋ የተቀበለ ወዶ ገብ ሎሌ መሆኑን አረጋገጠ ።
ቅድመ መለስ ድህረ መለሰ የሚል የታሪክ አውድ ከመትከል በቀር በአመታት ውስጥ በዝርፊያ ክህነት ማህሌት ከመቆም በቀር አገርን ባልተንሸዋረረ ነፅሮት መቃኘት የተሳናቸው በዘመን መካከል የተከሰቱ የፖለቲካ ድኩማኖች ሊበዘብዙን እና በስቃያችን ላይ ዳንኪራ ሊመቱ ጊዜ ለነሱ አዘነበለ።
ዋና ዋና ሜጋ ፕሮጀክቶችን በእነርሱ የበላይነት በተያዘው ኢፈርት፣ ሜቴክ፣ ትልማ፣ ማረት፣ የህወሓት የዝርፊያ ማሳለጫ ኩባንያዎች ያለ ሃግ ባይ ለተራዘሙ አመታት ለመበዝበዝ ዋነኛ መሳሪያዎች ሆነው ለማገልገል አልቦዘኑም ።
ለዚህ የበላይነትና ፈላጭ ቆራጭነት ደግሞ የብሔራዊ ደህንነቱ፤ የመከላከያ፤ የፊደራል ፖሊስ፤ የልማትና የዲፕሎማሲ ተቋማት በህውሓት ዘራፊዎች መያዙ ትልቅ ፋይዳ ነበረው።
የኋላ ኋላ በ2008ዓ.ም. ላይ የጀመረው የአማራና የኦሮሚያ ክልል የህዝብ አመፅ እየጠነከረ በመምጣቱ ወያኔ መራሹ ኢህአዴግ እንደ ለመደው ድርጅቱ የበሰበሰ ስለሆነ ጥልቅ ተሀድሶ ያስፈልገኛል በማለት በለመደው የማነሁለያ መንገዱ ከመሬት በላይና ከሰማይ በታች ያላየነው የለም ችግሩን መንግስት ተቀብሏል በማለት ለማስመሰል ሞከረ። ይሁን እንጂ የህዝብን መሪር አብዮት በሚገባ የተገነዘበው የቲም ገዱና የቲም ለማ ቡድን የሞት ሽረት ትግል በማድረግ ዶ/ር አብይ አህመድን ጠ/ሚር አድርጎ በማስመረጥ እውነተኛውን የህዝብ ጥያቄ ወደ አደባባይ ይዞ ብቅ በማለት የብዙሃኑን ቀልብ ለመግዛት ቻለ ።
ይህ አካሄድ ያልተመቸው ያልታደሰው ቁሞ ቀር ቡድን ለውጡን ለማደናቀፍና ከዚያም ከፍ ሲል ጠቅላይ ሚ/ሩን ለመግደል ከመሞከር አንስቶ በተለያዩ ክልሎች ፤ሶማሌ ቤንሻጉል፤ ወለጋ፤ አዋሳ ፤ በጎንደር (ቅማንት ስም)፤ በቡራዩ እና በመሳሰሉት ሆድ አደር የፖለቲካ ድኩማኖችን ተጠቅሞ የዘረፈውን ገንዘብ እየረጨ ብሔረሰብን ከብሔረሰብ በማጋጨት የብዙ ንፁሐን ደም በከንቱ እንደፈስ ማድረግን እንደ ክፉ ጋኔን ምሱ ሲያደርግ ከርሟል ።
ይህ ሳይበቃ የትግራይ ክልል የፖለቲካ ጥገኝነት የሚሰጥ ይመሰል ያኮረፈውና ከስልጣን የወረደው ቡድን መንግስት በአዲስ አበባ የሰጣቸውን ቤት ትተው መቀሌ ላይ በመመሸግ ሴራቸውን መዶለት ቀጠሉ ከወደቁ ወድያ መፈራገጥ እንዲሉ መሆኑ ነው ።
ሰሞነኛው ወሬ ደግሞ ሜቴክ የተሰኘው የጀነራል ክንፈ ዳኘው የዘረፉ ተቋም ቅኝት፤ እሱን ስንሻገር ደግሞ የጌታቸው አሰፋ የሰቆቃ አፈፃፀም ታሪክ በራሳቸው አንደበት የሚተረክበት ጊዜ ሆነና ጆሯችን ሲግል ከረመ ፤ የማያልቅ የግፍ ዜና የሚዘገንን የሰቆቃ ድምፅ ልክ እንደ አዲስ የትዝታ ፈረሱን ጭኖ ሽምጥ ሲጋልበን ሲያንዘፈዝፍ ሲነዝረን ከረመ። ከዚያም የግፉን ሞልቶ መፍሰስ ተከትሎ የእድል ጀንበር ከህወሓት መንደር አዘቀዘቀች። ካቴና ስፍራዋን አገኘች ህወሓት በቁልቁለት ጉዞው ናዳውን መቅደም ተሳነው፤ ብርክ ይዟቸው ለሽሽት ሲራወጡ በየሰርጡ ተይዘው አንገት ሲደፉ አይናችን ለመመልከት በቃ። የቁልቁለት ጉዞ የመነሳት ሳይሆን የመውደቅ የመጠገን ሳይሆን የመሰበር ዘመን። መልካም ቁልቁለት ብለናል !”!
እናም ለኢትዬጵያ ህዝብ መጪው ጊዜ ብሩህ እንዲሆን ከለውጡ ኃይል ጎን በመሆን ካንሰርን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ ግን የምርጫ ጉዳይ አይደለም !!
ቸር እንሰንብት !!