>
5:13 pm - Monday April 18, 2557

ጥያቄያችን ሁሉን አቀፍ ይሁን! (ቹቹ አለባቸው)

ጥያቄያችን ሁሉን አቀፍ ይሁን!
ቹቹ አለባቸው
 
በመንግስት እና በግለሰብ ደረጃ የተፈጸሙትን ስህተቶች፤ እንዲሁም ንጹሁን ንጹህ ካልሆነው ሰው በለየ መልኩ መሆን አለበት፤ ነገሩ ሁሉ ከተደበላለቀ፤ መፍትሄ አይገኝም፡፡ እውነተኛ መፍትሄ ከፈለግን፤እንደ መንግስት የተፈጸሙትን  ስህተቶች ከመንግስት ጋር፤ እንደ ግል የተፈጸሙትን ስህተቶች ደግሞ ህጉን ተከትለን ከግለሰቦች ጋር ማድረጉ ይሻላል ባይ ነኝ!!!
 
አንዳንዴ መቸ እንደምንግባባ ይጨንቀኛል፡፡ ትልቁንና ግንዱን  ነገር ትተን በቅርንጫፎች ላይ መንጠልጠል ላይ ዛሬም እመለከታለሁ፡፡ዋናው ተላት እያለ፤መለስተኛው ላይ እንረባረባለን፡፡ ይህ አካሄድ የእለት ስሜታችንነ እንድናበርድ ሊጠቅመን ካልሆነ በስተቀር፤ለዘለቄታ ድል እንደማያበቃን መታወቅ አለበት፡፡ ለዛሬው ጽሁፌ መነሻ ሆነኝ ትላንት ጎንደር ከተማ ውስጥ የተፈጠረው ሁኔታ ነው፡፡ ይሄውም በትላልትናው እለት ወንድማችንን ጎቤ መልኬን አስገድሏል ተብሎ ሲታማ የከረመውን ፤የአርማጭሆውን ተወላጅና፤ ከመምህርነት እስከ ወረዳ አስተዳደሪነት ያገለገለውን አቶ እያሱ ይላቅን፤በቁጥጥር ስር አድርገነዋል፤ ገቢ አድርገነዋል የሚል ዜና በስፋት ሲሰራጭ ተመለከትኩ፡፡ ነገሩ በምን እንደተቋጨ ባላውቅም፤የከፋ ነገር ግን የደረሰ አልመሰለኝም፤እኔ ግን ፈርቸ ነበር፡፡
ለሁሉም፤እያሱ ይላቅን፤ እኔና ጓደኞቸ አርማጭሆ እያለን ወደ ድርጅት አባልነት ያመጣነው በወቅቱ የማሰሮ ደንብ አመራሮች የነበርነው የብአዴን ሰዎች ነን፡፡ በወቅቱም አርማጭሆ ውስጥ ተኪ አመራር ይሆናሉ ብለን ተስፋ ጥለንባቸው ከነበሩት የአርማጭሆ ልጆች መካል አንዱ ይህል ልጅ ነበር፡፡ ይህ በዚህ እንዳለ፤እኔ በ1993 ዓ.ም አካባቢውን ከለቀቅኩት በኃላ፤ወደ አመራርነት መምጣቱን ሰማሁ፤ደስም ብሎኝ ነበር፡፡ በሂደት ደግሞ ዋና አስተዳደሪ ደረጃ መድረሱን ሰማሁ፡፡ ይሄም ጥሩ ነበር፡፡
ነገር ግን የሳንጃ ወረዳ አስተዳሪ ከሆነ በኋላ፤ በተለይም የ2008 ዓ.ምን አመጽ ተከትሎ የያሱ ስም ክፉኛ ሲነሳ ሰማሁ፡፡ በተለይም ከጎቤ መልኬ ግድያ ጋር በተያያዘ  የሚነሳው ነገር ጎላ ብሎ ይሰማ ነበር፡፡  እኔም እንደ ትልቅ ወንድም  ጉዳዩን አንስቸለት ነበር፡፡ እሱ የሚለው  ነገር ሌላ ነው፤ሰዎች የሚሉት ደግሞ ሌላ፡፡ ለሁሉም ዋነኛው ገዳይ፤እንዲሁም ስምሪቱን በቀጥታ የሰጡት የደህንነት ሰዎች ዛሬም በሂዎት ስላሉ፤ዛሬ ባይሆን ነገ እውነቱ መውጣቱ አይቀርም፡፡ ያኔ እውነተኛውን አስተያየት እንሰጣለን፡፡ይሄም ሆኖ ግን ለታሪካዊነቱን እውነቱን ከማወቅ የዘለለ ሌላ ጥቅም አይኖረውም፤ምክንያቱም ጎቤ የተገደለው፤በግለሰቦች ፈቃድ ብቻ ሳይሆን በመንግስት ውሳኔ ነው፡፡መንግስትን ወደዚህ ውሳኔ እንዲደርስ የገፋው ደግሞ፤በወቅቱ ስርአተ-መንግስቱን ይዘውር የነበረው ህወሀት ነው፡፡ ህወሀት አቶ ኃ/ማሪያምንና ሲራጅ ፈርጌሳን እንዲሁም አንዳንድ የኛን ሆድ አደር ሰዎች ተጠቅማ፤የሰራችው  መንግስታዊ ድራማ ነው፡፡ ስለሆነም፤ጉዳዩ መታየት ያለበት እንዲህ ነው፡፡ ለዚህ ደረጃ ያበቃን ዋናው ጠላታችን ህወሀትና ሌሎቹ ወደሎች እያሉ አሸከሮቹ ላይ ማትኮራችን ጥቅሙ ጎልቶ አልታየኝም፡፡
እኔ በበኩሌ፤ ይሄንን ጉዳዩ በዝምታ ማለፍ እንደሚሻል መርጨ የነበረ ቢሆንም፤ እንደገና ተነሳስቸ እንድጽፍ ያደረገኝ ምክንያት ግን አለ፡፡ ይሄውም፤ አንድ ትግል ስንጀምር  እይታችን ሰፊ ከመሆን ይልቅ፤ ጠበብ እያለ ስላስቸገረኝ ነው፡፡ እውነት ነው ጎቤ የተገደለበትና የአገዳደሉ ሚስጥር፤መቸም ቢሆን ሊረሳ የማይችል ጥቁር ታሪክ ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ መልኩ የተገደለው ጎቤ መልኬ ብቻ ነውን?  እንዲሁም በጎቤም ሆነ በሌሎቹ ያላግባብ ተገድለዋል ተብሎ በሚነገርላቸው ሰዎች ግድያ ላይ፤ ከላይ እስከታች የነበሩት / አሁንም ያሉት፤በተለይም  የመንግስት  የጻጥታ መዋቅር አመራር/ አካለት ተሳትፎ አልነበራቸውንም? ነገሮችን በዚህ መልኩ ነው መመልከት ያለብን፡፡በዚህ መልኩ ካልተመለከትነው፤ነገሩ ማቆምያ አይኖረውም፤እንደዛ ከሆነ እማኮ፤ ትላንት ከላሽ ታጥቀው የወልቃይትን ጥያቄ ለምን ታነሳላችሁ ብለው የባ/ዳር ወጣቶችን ሲያሳድዱ የነበሩ ሰዎች ዛሬ በከፍተኛ አመራር ቦታ ተመድበው እየተመለከትን ነው፡፡ እኔ እነሱን ብሆን፤ቢያንስ ለሞራሌ ስል በፍቃዴ ስልጣን እለቅ ነበር፤ነገር ግን እነሱ አላደረጉትም፤የዚህ ምክንያታቸው ደግሞ ግልጽ ነው፤በወቅቱ ይህን ያደረጉት የመንግስትን ህግ ለማስከበር ነው ብለው ስለሚያምኑ ነው፡፡
ስለሆነም፤ በዚህ በኩል ምክሬ ግልጽና አጭር ነው፡፡ ይሄውም ትግላችንና ጥያቄዎቻችን፤ በመንግስት እና በግለሰብ ደረጃ የተፈጸሙትን ስህተቶች፤ እንዲሁም ንጹሁን ንጹህ ካልሆነው ሰው በለየ መልኩ መሆን አለበት፤ ነገሩ ሁሉ ከተደበላለቀ፤ መፍትሄ አይገኝም፡፡ እውነተኛ መፍትሄ ከፈለግን፤እንደ መንግስት የተፈጸሙትን  ስህተቶች ከመንግስት ጋር፤እንደግል የተፈጸሙትን ስህተቶች ደግሞ ህጉን ተከትለን ከግለሰቦች ጋር ማድረጉ ይሻላል ባይ ነኝ፡፡ ከዚህ ውጭ በስሜት ውስጥ ሁነን የምንወስዳቸው  እርምጃዎች፤ሌላ ዋጋ ሊያስከፍሉን ይችላሉ፡፡ ልብ በሉ የትላንቱ ነገር በሰላም ባያልፍ ኖሮ፤ እያሱ እንዲሁ በቀላ እጁን ይሰጥ ነበር? እንዲሁም በሆነ አጋጣሚ እያሱ ላይ አደጋ ደርሶ ቢሆንስ፤በዚህ ጉዳይ ሚከፉ ሰዎች አይኖሩም ይሆን? መጨረሻውስ ምን ይሆን ነበር? በእኔ እምነት፤ይህ አካሂያድ ፤ትኩረታችንና ሙሉ አቅማችንን ዋናዋና አጀንዳዎቻችንንና ጠላታችን ላይ ከማድረግ ይልቅ፤ እርስበርሳችንን የሚያባላ፤አቅማችንን የሚያዳክም መሆኑ አይቀርምና በተረጋጋ መንፈስ ብንቀሳቀስ ጥሩ ነው ስል እመክራለሁ፡፡
በነገራችን ላይ እንዲያው አጋጣሚ ሆኖ እንጅ፤ ህወሀት በዝች ምድር እስካለ ድረስ፤ በተለይም አርማጭሆና ጠገዴ ውስጥ የጎቤ መልኬና ደጀኔ ማሩ ( ደጀኔ ተርፏል)፤እንዲሁም ኮ/ል ደመቀ በዘች ወቅት ዳንሻን ለቆ ጎንደር ባይገባ ኖሮ፤ በህወሀት ስኳድ የመገደላቸው ጉዳይ አይቀሬ ነበር፡፡ ነገር ግን የወንድማችን ጎቤ ግድያ  ለጊዜውም ቢሆን ለህወሀት በሚያመች መልኩ መፈጸሙ ብቻ ያናዳል፤ እንጅ የነዚህ ጀግኖች ሞትማ ቀድሞ በህወሀት ተወስኖ ያደረ የነበረ መሆኑን  እናውቀዋለን፡፡
ስለሆነም፤የኔ ሃሳብ ምንድን ነው፤በተለይም የ2008 ዓ.ምን አመጽ ተከትሎ የተፈጠረውን ችግር  በተመለከተ፤ ግለሰቦችን በማሳደድ የምንፈታውና ዘላቂ መፍትሄ ምንሰጠው ሆኖ አይሰማኝም፡፡ ምክንያቱም አብዛኛው ጥፋት  የተፈጸመው በመንግስት አካት ታስቦበትና ታቅዶበት፤ትልቅ በጀት ተመድቦለት ነው፡፡ ስለሆነም፤ እንደ ግለሰብ የሚጠየቅ ካለ፤ እሱን ሳንረሳ፤ መንግስት በፈጠረው ችግር ተመርተው ስህተት የፈጸሙትን ግለሰቦችን ከማሳደድ ወጥተን፤ ሰፋ ባለ መልኩ መንግስትን በተከተልከው  የተሳሳተ አካሄድ ሰዎች ያላግባብ ተጎድተዋል፤ስማቸው ጠፍቷልና፤ ተገቢውን ካሳ ክፈል ብንል ጥሩ ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ፤ ካልተሳሳትኩ በስተቀር፤በ2009 ዓ.ም መሰለኝ፤መንግስት በራሱ ሚዲያ በሰ/ጎንደር ብቻ ከ600 በላይ “አሸባሪዎችን” ገድያለሁ ብሎ ማወጁን እናስተውሳለን፡፡ ሁላችንም ቆየት ብለን እንደሰማነው ደግሞ፤ “አሸባሪ ሆኖ የከረመው መንግስት ነው”፤ሲል መንግስት በራሱ ላይ መስክሯል፡፡ ይሄ ማለት ደግሞ፤ጎቤም ሆነ ሌሎች 500/600 ወገኖቻችን የተገደሉት፤ እውነትም አሸባሪ ሆነው ሳይሆን፤ህወሀት አማራን በተለይም በአርማጭሆና ጠገዴ የሚገኙትን አናብስት ለማጥፋት እንደ ስልት የተጠቀመበት ነገር ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
ስለሆነም፤በዚህ ወቅት ተገደሉ የተባሉት ወገኖቻችን፤ሁሉም ንጹህ ነበሩ ወይ?፤በዚህ  ወቅት ባይገደሉ ኖሮስ በሰላም የመኖር ተስፋ ነበራቸው ወይ?፤በአጠቃላይ፤ከህዝባዊ አመጹ ጋር በተሳሰረ መንገድ ነው ወይ የተገደሉት?፤ሌላ የግል ችግር ኖሮባቸው፤ይሄንን አጋጣሚ ለመጠቀም በመሞከራቸው አብረው የተገደሉ አሉ ወይ? ወዘተ… የሚሉትን ጭብጦች  በተገቢው ከተጣራ በኃላ፤ መንግስት፤ ከለውጡ ጋር በተያያዘ ለተጎዱ ወገኖች ( በጦርነትም ጭምር ቢሆን) አስፈላጊውን ማስተካከያ እንዲያደርግ ነው ትግላችን መሆን ያለበት፡፡ ለምሳሌ በዚህ በኩል መንግስት የሚከተሉት እርምጃዎችን እንዲወስድ መጠየቅ እንችላለን፤
1.የ2008 ዓ.ምን የአማራ አብዮትን መቀጣጠል ተከትሎ፤ጎቤ መልኬም ሆነ ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ፤አማራዎች  በተደገደሉበት ወቅት “አሸባሪ” ነበሩ ተብሎ  መገለጹ፤ ስህተት እንደነበር፤ለዚህም ተጠያቂው መንግስት እንደሚሆን፤በመግለጽ ስማቸውና መለያቸውም፤ለአማራ ክብር ሲባል ዋጋ የከፈሉ  አማራ ጀግኖች ተብሎ እንደገና እንዲታደስ መጠየቅ አለብን፤
2. በዚህ  የመንግስት ስህተት ለተፈጠረው የሂዎት መጥፋት፤ የአካል መጉደልና ንብረት ውድመት ፤ መንግስት ተገቢውን ካሳ እንዲከፍል፤ የተወሰደባቸው መሳሪያም ካለ ለቤተሰቦቻቸው እንዲመለስ መጠየቅ እንችላለን፤
3. አጠቃላይ ችግሩ ከመንግስት ስህተት የመነጨ ቢሆንም፤ሙሉ ኋላፊነቱን መውሰድ ያለበትም መንግስት መሆኑን ባምንም፤ በአንጻሩ ደግሞ የግሉን ፍላጎት ለማሳካት ሲል፤ወንጀል የፈጸመ ግለሰብ ካለ፤በመንግስት ስህተት ተሸፍኖ እንዳያልፍ፤በግሉ በህግ አግባብ እንዲጠቅ ማድረግ፡፡ ለምሳሌ ሰሮቃ ላይ በደጀኔ ማሩ ቤተሰቦች ላይ የተፈጸመው ድርጊት ከጠገዴ-አርማጭሆ  ባህል ያፈነገጠ በደልና ግፍ ነው፡፤ ይህ ሁኔታ በግለሰቦች ፍላጎት ላይ የተመሰረተ እንጅ፤የመንግስትን ትእዛዝ ለማክበር ስንል የወሰድነው እርምጃ ነው ሊባል አይችልም፡፡ ሌሎች ጉዳዮችም ይኖራሉና  በዚሁ አግባብ መመልከት ተገቢ ነው፡፡
—–
ማጠቃለያ፡-
ለሁሉም ዛሬም፤ብንደማመጥ፤ብናስተውልና ፤ወደ ሆነ ውሳኔ ላይ ከመድረሳችን በፊት ነገሮችን በጥልቀትና በብስለት ብን መረምር ጥሩ ነው፡፡ ስለሆነም፤በቀጣይ ይሄንን ነገር እንደባህል ብናዳብር እላለሁ፡፡ ቀጣይ የምናካሂደው ትግልም፤በዚሁ አግባብ ቢመራ፡፡ ካልተሳሳትኩ በስተቀር፤ መንግስተ በ2008 ዓ.ም የተከሰተውን ቀውስ ተከትሎ ለተፈጠረው ችግር ይቅርታ ጠይቆ፤ለተጎጅዎችም ካሳ የሰጠ/ ለመስጠት የወሰነ ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን ይሄ ይቅርታ ጥያቃና ካሳ የመክፈል ሁኔታ ሁሉ አቀፍ አልመሰለኝም፡፡በከተሞች አካባቢ የታጠረና ከሰልፎች ጋር ተያይዞ በተከሰተ ችግር ለተጎዱት ወገኖች ብቻ መሰለኝ( ከተሳሰትኩ እታረማለሁ)፡፡ አሁን መሆን ያለበት ይህ የመንግስት ይቅርታ መጠይቅና ካሳ የመክፈል ውሳኔ፤ ለማንነታቸው ብቻ ሲሉ (በግሉ የሸፈተውን ሁሉ ማለቴ አይደለም) ጫካ ገብተው፤ መንግስትን በመሳሪያ ጭምር ሲፋለሙ የሞቱትን ሁሉ ማካተት አለበት ባይ ነኝ ፡፡ምክንያቱም፤እነዚህ ሰዎች ለዚህ ችግር የተዳረጉትና ጦር ሰብቀው መንግስትን ለመፋለም የተገደዱት፤መንግስት በፈጠረው ችግር የተነሳ ስለነበረ ነው፡፡
ስለዚህ መንግስት በዚህም በኩልም የጀመረውን ኋላፊነቱን የመወጣት ስራ ወደዚህ ደረጃም ከፍ አድርጎ እንዲመለከተው  እንጠይቅ፡፡ የሚጠቅመን ይሄ አካሄድ ነው፤መንግስት በዘረጋው ስርአት ውስጥ ሁነው፤የተሳሳተም ቢሆን መንግስት ያወጣውን ህግ ለማስከበር ሲንቀሳቀሱ ችግር የፈጠሩ ግለሰቦችን በማሳደድ የምናገኘው አንዳች ጥቅም የለም፤ምን አልባት ርስበርሳችን ተባልተን፤ለህወሀት ደስታ እንስጠው ይሆናል፡፡
Filed in: Amharic