>
7:16 am - Tuesday December 6, 2022

ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ - የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ ጉድህን ስማና ከተደገሰልህ ዕልቂት ራስህን አድን! (ይነጋል በላቸው)

ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ – የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ ጉድህን ስማና ከተደገሰልህ ዕልቂት ራስህን አድን!

ይነጋል በላቸው 

ሰዓቱ ብዙ የሚወራበት አይደለም፡፡ ጊዜው የጦርነት ነው፡፡ የአሁኑ ጦርነት ከመጪው ጦርነት ቀለል ያለ ዋጋ የሚያስከፍል ቢሆንም ጦርነት ያው ማስፈራቱ አይቀርምና ጦርነት ላይ ነን፡፡ አሁን የምንገኝበት ጦርነት ሥነ ልናቦዊ ጦርነት ነው፡፡ የተደገሰልንን ዕልቂት ለማስወገድ ሁላችንም የምንችለውን ሁሉ የምናደርግበት ከፍተኛ ፍልሚያ ልናካሂድበት የሚገባን ጦርነት ውስጥ እንገኛለን፡፡ ችግራችን ከእንጭጭነት አልፎ ጎርምሶና ጎልምሶ ሊውጠን ተቃርቧል፡፡ “ሟርት ነው!” ከሚል የመዘናጊያ ወቅት ካለፈ እጅግ ቆዬ፡፡

ኢማኪዩሊ ኢሊባጊዛ ትባላለች፡፡ ብዙ ሰው ያውቃታል፡፡ ከሩዋንዳ የዘር ፍጅት በተዓምር የተረፈችና ግሩም መጽሐፍ ጽፋ ለንባብ ያበቃች ዕድለኛ ሴት ናት፡፡ አሁን በአሜሪካ ሀገር ትኖራለች፡፡ የዚህችን ልጅ መጽሐፍ ወጣቱ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ መምህር መዘምር ግርማ በ2008ዓ.ም ወደ አማርኛ መልሶ ለንባብ አብቅቶታል፡፡ የልጅ ዐዋቂ፡፡ ይባረክ፡፡ ስንቱ ጎምቱ ተጋድሞ ዕንቅልፉን ሲደቃና በዓለም ዘጠኝ ሲምነሸነሽ እርሱ ግን ይጨነቃልና ከፍላቱ ያውጣው፡፡ ጥያቄው ግን “ተጠቀምንበት ወይ?” ነው፡፡ በወቅቱ ያነበብኩትንና ከተርጓሚውም ከኢሊባጊዛም በመገናኛ መስመሮች ተገናኝቼ እኔም እንዳቅሜ የደከምኩበትን ይህን ጉዳይ ዛሬ ማንሳት የወደድኩት የሀገራችን ነገር አድሮ ቃሪያ እየሆነ መጥቶ ሩዋንዳን ያጨራረሱ በተለይ የታዳጊ ሀገራት ጠላቶች በአጠቃላይ ደግሞ የአዲሱ የዓለም መንግሥት አራማጆች ኢትዮጵያን ከምድረ ገጽ የማጥፋት የዘመናት ህልማቸው እውን እንዳይሆን ከዚህ መጽሐፍ ቀጣዩን ዋና ሃሳብ ለማስታወስ ነው፡፡ 

በዚህ መጽሐፍ አንድ የዘር ፍጅት ከመካሄዱ በፊት የሚከተሉትን ቅድመ ሁኔታዎች ያሟላል፡፡ በኛ ሀገር ያለው ሁኔታም እነዚህን ስምንት ቅድመ ሁኔታዎች በሚገባ አሟልቷል፡፡ እነዚህ ነገሮች አንዳቸውም ሳይቀሩ ተሟልተው ሳለ ተግራዊነቱ ለምን እንደዘገዬ በጣም የሚገርም ነው፡፡ ምናልባት የማናውቀው ኃይል እየጠበቀን እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡ ወደዚያ አንገባም፡፡ ጊዜ የለንም፡፡ በነገራችን ላይ ከችግር ፈጣሪ መፍትሔ ሊፈልቅ አይችልምና አውሮፓውያንና አሜሪካኖች ከውድመት ያድኑናል ብሎ ተስፋ ማድረግ ቂልነት መሆኑን መረዳት አለብን፡፡ የሩዋንዳን ዕልቂት አስቀድመው ያውቁ ነበር፡፡ ራሳቸውን እኮ ቀድመው አሽሽተዋል፡፡ ደግሞም ለኢትዮጵያ? የርሷ መጥፋትማ ለነሱ ሠርግና ምላሽ ነው፡፡ ውዱን የኖቤል ሽልማታቸውን ሳይቀር የገበሩበትን ጉዳይ እንዲህ በቀላሉ ሊያዩት? አይደረግም!

ወደጥቅሱ ገባሁ፤ በቅንፍ የምሰጠው ሃሳብ የራሴ ነው፡፡

  1. መከፋፈል (Classification) – እኛና እነሱ ብሎ በመከፋፈል ለየት ይላሉ ተብለው የሚታሰቡትን የኅብረተሰብ ክፍሎች በቀልድም ጭምር በማንቋሸሽ በሰዎች መካከል ያለውን ልዩነት አለማክበር፡፡
  2. የሚታይ መገለጫ መስጠት (Symbolization) – ይህ የጥላቻ ግልጽ መገለጫ ሲሆን ይሁዲዎች በናዚ ጀርመን ቢጫ ኮከብ ያለበት ልብስ እንዲለብሱ እንደተደረገው ነው፡፡
  3. ከሰውነት ክብር ዝቅ ማድረግ (Dehumanization) – ይህ ተግባር ከራስ የተለዩትን ሰብኣዊ ክብርም ሆነ መብት በመንፈግ ይፈጸማል፡፡ በሩዋንዳ አክራሪ ሁቱዎች የቱትሲ ዘውግ ተወላጆችን ‹በረሮ› ይሏቸው እንደነበረው መሆኑ ነው፡፡ (እኛም ጋ ‹ነፍጠኛ፣ ትምክህተኛ…› በሚል መፈረጅና ከሰውነት ተራ የማውጣት አዲስ ፈሊጥ አለ)፡፡ ይህ ሂደት ገዳዮቹ “እየገደልን ያለነው ሰው አይደለም፤ ታዲያ ድርጊታችን ምኑ ላይ ነው ጥፋትነቱ” እንዲሉ መንገዱን ይጠርግላቸዋል፡፡ (እነአባ ቶርባ የአማራ ልጆችን አግተው ሲጫወቱባቸው እንደሰው እንደማይቆጥሯቸው ዓይነት ነው፡፡ እነዚህን ነጥቦች ሁሉንም በሀገራችን እያየን እንደሆነ መካድ የአክራሪዎችን ጭፍጨፋና ግድያ በፀጋ እንደመቀበል ይቆጠራል፡፡)
  4. ማደራጀት (Organization) – በጥላቻ ላይ የተመሠረቱ መንግሥታት አንድን ሕዝብ የሚያጠፋላቸውን ኃይል ያሰለጥናሉ፡፡ ( የ“ዶ/ር” አቢይ መንግሥት አማራው ጥቂት ልጆችን ሚሊሻዎች ማሰልጠኑን አይቶ ደሴ ላይ “ምን እናድርግ – በጀታችሁን ወታደር በማሰልጠን ትጨርሳላችሁ…” እያለ ለአሽሙርና አግቦ ብቻ የተፈጠረ በሚመስለው  መልኩ እንዳፌዘውና በደንገጡር የአማራ ባለሥልጣን ተብዬ ቅምጦቹ መሀል እንደቀለደባቸው በሌላ በኩል ግን አንዳችም ይሉኝታና ሀፍረት ሳይሰማው የራሱን ክልል በብዙ ሽዎች አሰልጥኖ በአደባባይ ማስመረቁን ለዚህ ነጥብ በዋቢነት መጥቀስ ይቻላል – ይህ ነጥብ ብቻውን  በአማራ ጥላቻ የተሞላው የአቢይ ዘረኛ መንግሥት አንዱን ገዳይ አንዱን ሟች አድርጎ የፌዴራል ተብዬውን መንግሥት ማዋቀሩን ያሳያል፡፡ አምባገነኖችና ዘረኞች የይሉኝታን ድንበር ሲደረምሱ ቅንጣት አይሰቀጥጣቸውም – ሁለመናቸው የታወረ ነውና፡፡ 
  5. በተቃራኒ ጎራዎች ማሰለፍ (Polarization) – ሕዝቡ በዘውጉ ከጨፍጫፊውና ከተጨፍጫፊው ወገን ሚናውን እንዲለይ ይደረጋል፡፡ በብዛት ይህ የሚሆነው በጥላቻ ቡድኖች ውትወታ በመገናኛ ብዙኃን የጥላቻውን መርዝ በመርጨት ነው፡፡ አንዱን ዘውግ ከሌላው ለይቶ በማውጣት ጠላት ነው ብሎ ማወጁ ጀርመኖች ይሁዲዎችን ከመፍጀታቸው በፊት በምዕራብ አፍሪካ በሄሬሮች ላይ የ20ኛውን መቶ ክፍለ ዘመን አሰቃቂ ጭፍጨፋ ሲፈጽሙ፣ ይሁዲዎች ሲፈጁና የሩዋንዳ አክራሪ ሁቱዎች ቱትሲዎችን ሲጨርሱ የገዳዩን ዘውግ አባላት በቀላሉ ለማሳመንና ለኅሊናው እንዲቀለው ለማድረግ ተጠቅመውበታል፡፡ (ወያኔዎችና ኦነግ/ኦህዲዶችም በዚህ ዙሪያ የማይናቅ ሥራ እንደሠሩና ታላቅ ድልም እንደተጎናጸፉ መረዳት ይገባል፡፡ ደግነቱ የአማራ ሆደ ሰፊነትና የአምላክ ተራዳኢነት ኑሮልን እንጂ እስካሁንም ቢሆን የከፋ ሁኔታ ሊገጥመን ይችል እንደነበር ከግምት ባለፈ መናገር ይቻላል፡፡)
  6. ዝግጅት (Preparation) – ሰለባዎቹ በልዩነቶቻቸው ተለይተው ይፈረጃሉ፤ የጭፍጨፋው ንድፍ አውጪዎች ሰዎችን በመኖሪያ አድራሻቸውና በሌሎችም መለያዎች ይፈርጁና ለፍጅት ያዘጋጇቸዋል፡፡ (በዚህም ዙሪያ በተለይ ወያኔ በመታወቂያ ላይ ትግሬ አማራ ምናምን ብለው እንዲጻፍ ያደረጉትን ያስታውሷል፡፡ የኛን ለየት የሚያደርገው እንደሁቱና ቱትሲ በአፍንጫ ቀዳዳና በቁመት ዕጥረት የሚለይ ሕዝብ አለመኖሩ ነው – ከላይ የተሰጠን የመዳኛ ፀጋ ሊሆን ይችላል፡፡ እንጂ ባለ ሜንጫው ጃዋር መሀመድ ዐረብ እንደሚመስል ሁሉ የማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ኤርጎጌ ተስፋዬ ምጥምጥ ብትመስል ኖሮ ምን ይውጠን ነበር? ሳይደግስ አይጣላም ምዕመናን!)
  7. ፍጅት (Extermination) –  በታቀደና ሆነ ተብሎ በተመቻቸ ዘመቻ የጥላቻ ቡድኖቹ ሰለባዎቻቸውን ይጨፈጭፋሉ፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በዘር ፍጅት ማንነታቸውን መለየት እስኪከብድ ድረስ ተጨፍጭፈዋል፡፡ (እነወያኔና ኦነግ ይህንንም ቀደም ካለ ጊዜ ጀምሮ እውን አድርገውታል፡፡ እነበደኖን፣ እነአርባጉጉን፣ እነአሰቦት ገዳምን፣ እነዋልድባን፣ እነአሶሳን፣ ስንቱን ጠርተን እንዘልቀዋለን … ብቻ እነዚህንና መሰል የጭፍጨፋ ወያኔ-ኦህዲዳዊ ምኩራቦችን ማስታወስ ነው፡፡ ለነሱ እኮ ለማስመሰል እንደሚናገሩት  መግደል መሸነፍ ሳይሆን መንግሥተ ሲዖልን መውረሻቸውና ምድራዊ መዝናኛቸውም ነው፡፡ “ስንተዋወቅ አንተናንቅ” ይላል የዱሮ አራዳ፡፡)
  8. ክህደት (Denial) – ግድያውን የፈጸሙት ወይንም ቀጣይ ትውልዶች ምንም ዓይት ጥፋት ያልተፈጸመ በማስመሰል ክህደት ይፈጽማሉ፡፡ ( እንደአቢይ ከሃዲ የለም ለምሣሌ፡፡ ልበ ብርሃኑ ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ፀጋየ በቅርቡ ተናገረ እንደሚባለው አቢይ የሚበሳጨው ዜጎች በመጨፍጨፋቸውና በመፈናቀላቸው ሣይሆን ያንን ዕኩይ ኦነግ/ኦህዲዳዊ ድርጊት በሚያጋልጡት ዜጎች ነው፡፡ ይህ ሰው እስፊንክስ እንደምትባለው አንደኛዋ የግሪክ አማልክት ውል-የለሽ ፍጡር ከዕኩይ መንፈስ ለዕኩይ ዓላማ  የተፈጠረ ነው የምንለው ወደን አይደለም፡፡)

 

ወገኔ ሆይ! ወደድህም ጠላህም እውነቱ ይሄውና ይሄው ብቻ ነው፡፡ ለመሞት ተዘጋጅተሃል? በየቀኑ ወደ አዲስ አበባ በድብቅ በሚጎርፈው ሜንጫና ገጀራ አንገትህን ለመሰየፍ ዝግጁ ነህ? ወይንስ እንደብልጧ ዐይጥ የምታመልጥበትን ጉድጓድ ምሰሃል? የአዲስ አበባ ወጣት ደኅና ነህ? እንዴነህ?… “የተዘጋጀልህን ወጥመድና የዕልቂት ድግስ ዐውቀህ ራስህን አደን!” እያልኩ መሆኔን ተረዱልኝ፡፡ ሌላ ዓላማ በፍጹም የለኝም፡፡

ማሽላ ሲያር ይስቃል፡፡ በኃጢኣት የተነከራችሁ የሃይማኖት አባቶ”ቼ” በአፋጣኝ ከዚያ እርኩሰት ውጡና ንስሃ ገብታችሁ ምህላ ያዙ፡፡ እርግጥ ነው – አብያተ ክርስቲያን የሚጸዱበት አበቅቴ ከፊት ለፊታችን ተደቅኗል፡፡ ልብ ያለው ካህንና ጳጳስ ግን የወንድምን ምክር ሰምቶ ራሱን ይፈትሽና ሀገር እንድትድን የበኩሉን ያደርጋል – ማን ያውቃል – ፈጣሪ ራሱ መጥቶ አያናግርም፤ የመሰለውን ልኮ ያናግራል – ሲልክ ደግ የፈለገውን እንጅ በሰው መሥፈርት አይደለም፡፡ እንኳንስ ስሙን አዘውትሬ የምጠራውን ኃጥዕ ወአባሲ የሆንኩ እኔን መሰል የሰው ልጅ  ይቅርና ድንጋይና አለቶችን የሚያናግር ጌታ ነው፡፡ ይሰማል እነ ፓትርያርክ? ጥምጣምን በማሳመርና መስቀልን ደረት ላይ በማንዠርገግ ቢሆን ኖሮ ይሄኔ ኢትዮጵያ በመለኮት ሠይፍ ትጣጠርና ጃዋርና ዳውድ ኢብሣ የኢትዮጵያን የአየር ድንበር ተሻግረው ባልመጡ፣ በዚያ አርጅተውም ወደ ቤርሙዳቸው በወረዱ፡፡ ከእውነቶች በላይ የሆነ እውነተ ልንገራችሁ – በእናንተ ዳፋ እግዜር ተቆጥቶ ነው ይህን ሁሉ መቅሰፍት ፊታችን ላይ የደቀነው፡፡ የኖኅን ዘመን የውኃ ጥፋት እናስብ፤ የሎጥን ዘመን ሦዶምና ገሞራ እናስብ፤ ነነዌን እናስብ … እነዚህ ቅጣቶች ሁሉ የኃጢኣት ፍሬዎች ነበሩ፡፡ ቅጣት መነሻ እንጂ መጨረሻ የለውምና ይሄውና ደጃችን ላይ ቆሞ እያንኳኳ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ብዙ መናገር ይቻላል፡፡ ግን ምን ይጠቅማል? ለማንኛውም በሩን ከፍቶ የማለቅም፣ በሩን ሳንከፍት በንስሃና በጸጸት አልቅሰን በራችን ላይ ተገትሮ እያንኳኳብን የሚገኘውን መከራ መመለስም የኛው ምርጫ ነው፡፡ … ሦዶምና ገሞራ እኮ የጠፉት ከሎጥ ውጪ አንድም ፃዲቅ ሰው በመጥፋቱ ነው … ሚስቱ ሳትቀር ለምን የጨው ዓምድ እንደሆነች ታውቃለህ? ወደ አንዱ ዐውደ ምሕረት ሂድና ስማ፡፡ ሆድህን ይቁርጠው እንጂ እዚህ አልናገር! አንድ ሣምራዊና አንዲት ሣምራዊት እንኳን እንጣ???…

 

EMAIL:  yinegal3@gmail.com

Filed in: Amharic