>
5:13 pm - Friday April 19, 5844

ኦርቶዶክስ የጎሳ ከረጢት አይመጥናትም! (ዮሀንስ መኮንን)

ኦርቶዶክስ የጎሳ ከረጢት አይመጥናትም!

ዮሀንስ መኮንን
* ” ብጹእ አቡነ ፋኑኤል ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሳያውቀው፣ ጳጳሳት ሳይባርኩ ከሀገር የወጣን ታቦት የቅርስ ዘረፋ ነው የምንለው!” በማለት የቤተ ክርስቲያኒቱንም የራሳቸውንም አቋም ከኢትዮ 360 ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።
 
ከየትኛውም ብሔር የተወለድን የትኛውንም ቋንቋ የምንናገር ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን ቤተክርስቲያናችሁ ከፀሐይ በታች በሚነገሩ ቋንቋዎች ሁሉ አምልኮ መፈጸማችሁን እንደማትቃወም ይልቁኑም በምትችለው ሁሉ እንደምታግዝ መረዳት ይኖርባቾኋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን በጎጥ ፖለቲካ አመካኝቶ ዘጠኝ ቦታ በመሸንሸን ተቋማዊ ክብሯን ለማሳነስ፣ ቅርሶቿን ለመካፈል እና ትምህርተ ሃይማኖቷን ለመበረዝ የሚንቀሳቀሰው “የኦሮሚያ ቤተክህነትን አደራጃለሁ” የሚለው አንጃ በጥፋቱ እንደገፋበት ነው።
ማዘዣ ጣቢያውን ከአሜሪካ ሜኒሶታ ያደረገው በእነ አቶጃዋር የሚዘወረው ይኸው የ”ቀሲስ” በላይ ቡድን የመጀመሪያዋን በጎሳ ፓለቲካ የተቃኘች “የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን” ሜኒሶታ ላይ ለመመሥረት አሜሪካ ገብተዋል።
ሜኒሶታ የሚኖሩ ኦርቶዶክሳውያን በስልክ እንደነገሩኝ በግዛቷ ስድስት አብያተ ክርስቲያናት (የቅድስት ሥላሴ፣ የመድኃኔዓለም፣ የቅድስት አርሴማ፣ የቅዱስ ዑራኤል፣ የቅድስት ማርያም እና ትንሽ ወጣ ብሎ ደግሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ) ህዝበ ክርስቲያኑን እያገለገሉ ቢሆንም ሰሞኑን የእነ አቶ ጃዋር ቡድን ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ አዲስ ቤተክርስቲያን በዚሁ በሜኒሶታ ለመግዛት በማፈላለግ ላይ እንደነበሩ ተነግሯል።
የዚሁ ኦሮቶዶክስን የመሰንጠቅ “ፕሮጀክት” አጋፋሪ ግልገሎቹን ትተን ፊትአውራሪዎቹን ስናነሳ “ቀሳውስቱ” በላይ መኮንን ከሀገር ውስጥ እና ሳሙኤሌ ብርሃኑ ከውጪ ናቸው።
ከዚህ ቀደም በአቶ ጃዋር አዝማችነት በሐረር፣ በባሌ እና በአርሲ ለማተባቸው ሲሉ የታረዱት ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች የፈሰሰው ደማቸው እንኳን ሳይደርቅ “ቀሲስ” ሳሙኤል የተባሉት ግለሰብ አቶ ጃዋር አሜሪካ ላይ በጠራው ስብሰቦ የጉባኤው “ባራኪ” ሆነው በመገኘታቸው ከሀገር ወዳድ እና ኦርቶዶክሳውያን ዘንድ ውግዘት አስከትሎባቸው እንደነበር ይታወሳል።
“ቀሲስ” ሳሙኤልም “በጎሳዬ ምክንያት ከአገልግሎቴ ታገድኩ” ብለው ጉዳዩን በማራገብ ከእነ አቶ ጃዋር የጎፈንድ ቅስቀሳ የ80,000 ዳለር እርጥባን ተሰብስቦላቸው ዋሺንግተን ላይ በኦሮሚፋ ብቻ አምልኮ የሚፈጸምባት የጎሳ “ሰሞነኛ” ቤተክርስቲያን ከፍተው ነበር። “ነበር” ያልኩት በ”ቤተክርስቲያኒቱ” ምሥረታ እለት የጎጥ ፓለቲካ የሚንጣቸው “ምእመናን” ጉባኤው አጨናንቀውት የነበረ ሲሆን በሳምንቱ ለቅዳሴ የተገኙት ግን ሦስት “ምእመናን” ብቻ ነበሩ።
እነ “ቄስ” በላይን በገንዘብ እና በሎጂስቲክስ የሚደግፉት ቡድኖች እና ግለሰቦች እንጥፍጣፊ የሃይማኖት መልክ የሌላቸው ፖለቲከኞች እና ጨርሶውነም የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን በጠላትነት የሚያዩዋት ጽንፈኛ ተቃራኒ ሃይማኖተኞች መሆናቸውን ስንረዳ ዓላማቸው ቁልጭ ብሎ ይታየናል። ቤተክርስቲያኒቱን በጎሳ ከፋፍሎ በማዳከም ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን የሚያስተሳስሩ እሴቶቿን በማዋረድ እና በማሳነስ ለሚመኙት የጎጥ ፓለቲካ ቅኝት መደላድል ማዘጋጀት ነው።
ቅዱስ ሲኖዶስ በጥቅምቱ ምልአተ ጉባኤ “የኦሮሚያ ቤተክህነት አደራጅ ነኝ” የሚለውን ቡድን ከነውረኛ አካሄዱ እንዲመለስ ማሳሰቢያ ቢሰጥም እነ ቀሲስ በላይ የሲኖዶሱ መግለጫ ላይ ከማላገጥ ያለፈ እርምት ሲወስዱ አልታዩም። ይብስ ብለው ከሀገር ውጪ ለሲኖዶስ የማትታዘዝ ከሐዋርያት ቀኖና ያፈነገጠች ቤተክርስቲያን ለመመሥረት ጽላት ይዘው አሜሪካ መግባታቸውን አደባባይ ሚዲያ ዝርዝር መረጃ አስነብባናለች። አሁን ጥያቄውን ወደራሳችን መልሰን ምን እናድርግ? ማለት ይኖርብናል።
 
ቅዱስ ሲኖዶስ
ይህን ዐይን ያወጣ ደረቅ ወንጀል እና ኑፋቄ ቅዱስ ሲኖዶስ ለምን በቸልታ እንደሚያየው ግራ ያጋባል። ለመመሪያው የማይታዘዙ እና በመንፈሳዊ መዋቅሩ የማይገዙትን አገልጋዮች (አንዳንድ አፈንጋጭ ጳጳሳትን ጨምሮ) ክህነታቸውን (ካላቸው) በመያዝ አውግዞ መለየት ይጠበቅበታል። ምእመናን በምታገኙት አጋጣሚ ሁሉ ቅለዱስ ሲኖዶስ መረጃ መሰጠት እና ለውሳኔ ማትጋት ይኖርባቾኋል።
ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን
ከየትኛውም ብሔር የተወለድን የትኛውንም ቋንቋ የምንናገር ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን ቤተክርስቲያናችሁ ከፀሐይ በታች በሚነገሩ ቋንቋዎች ሁሉ አምልኮ መፈጸማችሁን እንደማትቃወም ይልቁኑም በምትችለው ሁሉ እንደምታግዝ መረዳት ይኖርባቾኋል።
ከዚህ ውጪ ያለውን የጎጥ ፓለቲከ አካሄድ ግን በሀገር እና በቤተክርስቲያኒቱ ላይ እየተጎነጎነ ያለ ሰይጣናዊ ሤራ መሆኑን በመገንዘብ ከዚህ መሰል የይሁዳ መንገድ እንድትጠበቁ አደራ እላለሁ። ኦርቶዶክስ የጎሳ ከረጢት አይመጥናትም! ምክንያቱም የተወለድነው ከማይጠፋው ሰማያዊ ዘር ከክርስቶስ ኢየሱስ ነውና!
Filed in: Amharic