>
4:38 pm - Thursday December 2, 7097

''አታምጣው ስልው አምጥቶ ቆለለው!'' (አቤ ቶክቻው)

The shadow of a supporter of Ethiopia's Unity for Democracy and Justice party (UDJ) is seen through an Ethiopian flag during a demonstration in the capital Addis Ababaትላንት ለንደን ነበርኩ። እኔ ካለሁበት ማንችስተር ከተማ ለንደን ለመሄድ ወደ ስምንት መቶ ሰው ጭኖ በሰዓት እስከ ሁለት መቶ ኪሎ ሜትር ድረስ በሚወነጨፈው ቨርጂን ባቡር የፈጀውን ይፍጅ ብዬ ከተሳፈርኩ ሁለት ሰአት ከ ሃያ ደቂቃ ብቻ ነው የሚወስድብኝ።

የፈጀውን ፈጅቶ በሁለት ሰዓት ከሃያ ደቂቃዎች ለንደን አናቷ ላይ ጉብ አልኩ። ወድያው የገጠመኝ ታድያ አናት የሚያዞር ሙግት ነበር። አናት አዟሪው ሙግት፤ ማንም መገመት እንደሚችለው የሀገራችን ፖለቲካ ነበር። በምድር ላይ ከእንክርዳድ ቀጥሎ አናትን እነደበሶ የሚበጠብጥ ጉዳይ ቢኖር የኢትዮጵያ ፖለቲካ ነው። በተለይ የብሄር ነገር ካለበት ከእንክርዳድም አልፎ አጠፋሪስ (እጸ ፋሪስ) እንደገባበት ጠላ ”አብሾ” ሆኖ ቀውስ ሊያደርግ ይዳዳዋል።

ቢሆንም ግን አናት ያዞራል ተብሎ ሳይጠጣ አይዋልምና ከወዳጄ ጋር በኮስታ ካፌ ቁጭ ብለን ፖለቲካችንን መጠጣት ጀመርን።

የለንደኑ ወዳጄ ትንሽ ከተንደረደረ በኋላ የኢትዮጵ ህዝብ ዋና ጠላት ትግሬዎች ናቸው! ሲል ፈረጠም ብሎ ነገረኝ።

በሆዴ (የመድሃኒያለም ቁጣ!) እያልኩ በአንደበቴ ህውሃትን ማለትህ ነው ወይስ ጠቅላላ ትግሬዎች… ስል ጠየኩት። እርሱም፤ ”ህውሃትን ለዚህ ያበቃው የትግራይ ህዝብ ነው። ዛሬ ህውሃት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የሚፈጽመውን በደል እንዲፈጽም የልብ ልብ ያገኘው ከትግራይ ህዝብ ነው!” አለኝ። ….እንዲህ እንዲህ እያለ በርካታ ማስርጃ የሚላቸውን ነገሮች እየጠቃቀሰ የትግራይ ህዝብ ከሌላ የኢትዮጵያ ህዝብ ተለይቶ እንዴት የበርካታ ጥቅማ ጥቅሞች ባለቤት እንደሆነ፣ ትግራይ ክልል ከሌላው ተለይታ እንዴት እንደበለጸገች እና እንዳማረባት፤ የነ ኦልማ እና አልማ ኪሳራ እንዲሁም የ ትልማ ውጤታማነት፣ የነ ኢፈርትን ትርፋማነት፣ ዲንሾ እና መሰል የሌሎች ክልል ኩባንያዎች ክስረት፣ የወታደሩ ቤት በጅምላው በትግራይ ጀነራሎችን መሞላቱን በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ትልልቅ ሀብቶች እና ትላልቅ ሹመቶች በሙሉ በትግራይ ተወላጆች እጅ መያዛቸውን አጠቃላይ የትግራይ ህዝብ ታላቋን የትግራይ ሪፐብሊክ ለመመስረት እነ መለስ ዜናዊ የነደፉለትን ትልም ይዞ ሌላው ህዝብ ሲነደፍ ዝም ብሎ የሚያይ መሆኑን… በስሜት ተውጦ ነገረኝ። ከነገረኝ በኋላ ”…እነርሱ… ህ…ም!” ብሎ ውሃውን ተጎነጨ።

እኔም በበኩሌ በወዳጄ ውስጥ የሚንቀለቀለው የእልህ ስሜት ምን ያህል ኢትዮጵያውያን ውስጥ ይሆን ያለው… እያልኩ እያንሰላሰልኩ፤ ህዝብ በጅምላው በዳይ በጅምላውም ተጠቃሚ ነው ብሎ መደምደም ደግሞ ደጋግሞ መገምገም ያለበት ሀሳብ መሆኑን፤ በዘመዶቹ አጥፊነት የተነሳ አንድን ህዝብ ለይቶ ”እነርሱ… ህ…ም!” ብሎ ጥርስ መንከስ በቀጣይ ለምናስባት ኢትዮጵያ ከፍተኛ አደጋ መሆኑን፤ እንደ ሁላችን ሁሉ፤ በትግራይ ውስጥ በርካታ የህውሃት ብልግና አስተዳደር ሰለባዎች መኖራቸውን ለአብነት ያህልም እነ አብርሃ ደስታ፣ እነ አስገደ ገብረስላሴ ከነቤተሰባቸው፤ ወይዘሮ አረጋሽ እና ሌሎችም ስማቸውን የማናውቃቸው በርካታ ትግሬዎች የሀውሃት ነገር ”ወይ አነ ግዲ….!” እያሰኛቸው ገሚሱም ከነ ትድሄም ጋር ጠብመንጃ ይዞ፤ ገሚሱም ከነ አረና ጋር በሰላማዊ ትግል ሀውሃትን እና መላው ኢህአዴግን ሉጋም ሊያበጅ ከሌላው ኢትዮጵያዊ እኩል አበሳውን እያየ መሆኑን ተናገርኩ።

ይሄን ሁሉ ብዬ የለንደኑ ወዳጄ ያለኝ ነገር ”አንተ የዋህ ነህ… ልጄ! እንደዚህ እያለን ነው እየታሸን ያለነው” የሚል መልስ ነው።

ይሄ ያልኩት ነገር የዋህነት ከሆነ፤ እንግዲያስ እላለሁ ለዝች ሀገር የወደፊት እጣ ፈንታ የሚያወጣው የዋህ መሆን ነው። ህው ሃትም ሆነ መላው ኢህአዴግ እርስዎ ትግሬ ቢሆኑም ኦሮሞ ቢሆኑም ከተመቹት ይመቻል ከደሉት የደላል። እርስዎ አነስተኛ እና ጥቃቅን ለመሆነ ከተዘጋጁ ኢህአዴግዬ አነስተኛ እና ጥቃቅን ድጎማ ማድረጉ አይቀሬ ነው። ኢህአዴግዬም ሆነች ህውሃት አንቺ ያልሽው ብቻ ትክክል መገን ባንቺ መጀን! ብለው ድቤ ከመቱላት ዱቤ ታበላለች ነጻ ታጠጣለች!

በጥቅሉ ኢህአዴግ ዘመድ የለውም የኢህአዴግ የስጋ ዘመዶች ስጋቸውን የወደዱ ሆዳችን ከራሳችን ይበልጣል ያሉ ናቸው። እንዲህ ብሎም በጅምላ መናገር አይቻልም ይሄኔ አንዳንድ ወገኖች የኢህአዴግዬ የፖለቲካ መስመር ለሀገሪቱ ጥቅም ይበጃል በሚል የዋህነት ከመንግስት የተዛመዱ ሊሆኑም ይችላሉ።

እና፤ በጅምላ መጥመድ እና በጅምላ ማረስ የደቦ እርሻን ያሳምር እንደሆነ እንጂ የሀገር ፖለቲካን አያቀናም! እንላለን!

ብዬ ፖስት ላደርግ ስል በፌስቡክ ገጼ የውስጥ መስመር፤ Robel Alex የተባለ ሰው እንዲህ የሚል መል ዕክት አስቀምጦልኝ አገኘሁ።

Robel Alex
Oct 3rd, 1:44pm
abe zeregna leba feri ensisa neh. mechem mechem mechem ye tigray hizb ayitefam yatefehal enji donkoro. feri fertiteh yekobelelk. tigray will live forever forever forever forever forever

”አታምጣው ስልው አምጥቶ ቆለለው!” ይሉዎታል ይሄ ነው!

በመጨረሻም

እነደ Robel Alex ለሚያስቡ ትግሬዎችም እንደ ለንደኑ ወዳጄ የሚያስቡ ሌሎችም፤ ኢህአዴግ የምታሳየንን አበሳ ስፖንሰር የሚያደርጉ ናቸውና ይፈወሱ ዘንድ አብዝⶬ እጸልያለሁ!

”ማነው ሚለየው ሚደፍረው ይሄ ትውልድ ፍም እሳት ነው!”

Filed in: Amharic