>
5:14 pm - Friday April 20, 6159

ኢሰመኮ መግለጫ ትግራይ፡ የማይካድራ ሲቪል ሰዎች ጭፍጨፋ የግፍና ጭካኔ ወንጀል ነው! 

ኢሰመኮ መግለጫ

ትግራይ፡ የማይካድራ ሲቪል ሰዎች ጭፍጨፋ የግፍና ጭካኔ ወንጀል ነው!
 
የተጎዱትን ማቋቋም እና የአጥፊዎችን ተጠያቂነት ማረጋገጥ ይገባል፡፡

 

በትግራይ ክልል ምዕራባዊ ዞን በምትገኘው የማይካድራ ከተማ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በወቅቱ በስልጣን ላይ በነበረው የአካባቢው መስተዳድር የጸጥታ መዋቅርና ሳምሪ በተባለ ኢ-መደበኛ የወጣቶች ቡድን የተፈጸመው ጥቃት፤ ግድያ፣ ጉዳትና ውድመት፤ ጠቅላላ ድርጊቱና ውጤቱ ግፍና ጭካኔ የተሞላበት በሲቪል ሰዎች ላይ  የተፈጸመ የጭፍጨፋ ወንጀል (atrocious crime of massacre against civilians) መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገለጸ፡፡
ይህ የተገለጸው ኮሚሽኑ ከሕዳር 5 እስከ ሕዳር 9 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ በማይካድራ ከተማ እንዲሁም በአብርሀጅራ፣ በሳንጃ፣ በዳንሻ፣ በሁመራ እና በጐንደር ከተማ ተዘዋውሮ ባደረገው ምርመራ የደረሰበትን ግኝቶች ይፋ ባደረገበት የመጀመሪያ ደረጃ ቀዳሚ ሪፖርት ነው፡፡ ይህ ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል (crimes against humanity) እና የጦር ወንጀል (war crime)  ሊሆን እንደሚችል የሚያመለክት ስለሆነ ኮሚሽኑ ዝርዝር ማስረጃዎቹን እና ወንጀሉን የሚያቋቁሙትን የሕግና የፍሬ ነገር ትንተና በሙሉ ሪፖርቱ ላይ በዝርዝር አጣርቶ የሚያቀርብ መሆኑን አሳውቋል፡፡
በቀዳሚ ሪፖርቱ እንደተመለከተው በአካባቢው የነበረው የሚሊሽያና የፖሊስ ጸጥታ መዋቅር በፌዴራሉ አገር መከላከያ ሰራዊት እርምጃ ሸሽቶ አካባቢውን ለቅቆ ከመውጣቱ በፊት ሳምሪ ከተባለ መደበኛ ያልሆነ የትግራይ ወጣቶች ቡድን ጋር በማበርና በመተባበር በተለይ ‹‹አማሮችና ወልቃይቴዎች›› ያሏቸውን የአካባቢው ነዋሪ ሲቪል ሰዎች ከቤት ቤት እየዞሩና በየጐዳናው ላይ በገመድ በማነቅ፣ በስለት በመጥረቢያ በዱላ በመደብደብ ገድለዋል፣ የአካል ጉዳት አድርሰዋል፣ እንዲሁም ንብረት አውድመዋል፡፡ ኢሰመኮ ከአካባቢው ምንጮች እስከ አሁን በአገኘው መረጃ በአነስተኛ ግምት እስከ 600 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ትክክለኛው ቁጥር ከዚህ ሊበልጥም እንደሚችል በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡
ሳምሪ የሚባለው የትግራይ ወጣቶች ቡድን በዚህ ከባድ ወንጀል ላይ ቢሰማራም፤ በአንጻሩ የትግራይ ብሔረሰብ ተወላጅች የሆኑ ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች አጥቂው ቡድን ሲያሳድዳቸው የነበሩ ሲቪል ሰዎችን በቤታቸው፣ በቤተክርስቲያን እና በእርሻ ቦታ ደብቀው በመሸሸግ ሕይወታቸውን እንዳተረፉላቸው ኢሰመኮ ያነጋገራቸው ምስክሮች አረጋግጠዋል፡፡
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ‹‹በማይካድራ ከተማ በአነስተኛ ጽንፈኛ ቡድን የተፈጸመው በብሔር ማንነት ላይ የተመሰረተ እጅግ ዘግናኝ ኢሰብዓዊ ወንጀል ልብ ሰባሪ ቢሆንም፤ በአንጻሩ ኢትዮጵያውያን በብሔር ሳይለያዩ አንዱ የሌላው ጠባቂ ሆነው መታየታቸው ልብ ይጠግናል፤ ስለ ወደፊት በሰላም አብሮ መኖርም ተስፋ ይሰጣል›› ብለዋል፡፡ አክለውም ‹‹የተጐዱ ሰዎችን እና አካባቢዎችን መልሶ ከማቋቋምና ከመጠገን በተጨማሪ፤ በዚህ ከባድ የሰብዓዊ መብቶች ወንጀል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የተሳተፉ በየደረጃው ያሉ ጥፋተኞችን በሕግ ፊት ተጠያቂነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል›› ብለዋል፡፡
የኮሚሽኑን የመጀመሪያ ደረጃ ቀዳሚ ሪፖርት ከዚህ ጋር ተያይዟል፡፡
Filed in: Amharic