>
5:13 pm - Wednesday April 19, 6502

የጌታቸው ረዳ ነፍስያ...!!! (ጌታቸው ሽፈራው)

የጌታቸው ረዳ ነፍስያ…!!!

ጌታቸው ሽፈራው

…ዘመን ብዙውን ነገር ከንቱ እንደሚያደርግ ታዩታላችሁ። ድንጋይና ግንድ እያላተመ፣ መሬት እየቆረጠ ሲደነፋ የነበረ ውሃ፣ ደቃቃዋ አሸዋ ውስጥ ይደበቃል። የጌታቸው ነፍስ ወራት ባቀዘቀዘው ወንዝ ውስጥ ልትደርቅ ወራት እንደቀራት ጭላጭ ውሃ ነው የታየችኝ…!
 
የትህነግን ያህል መግለጫ ሲያሽጎደጉድ  የከረመ የለም።  የመግለጫው ብዛት ብቻ ሳይሆን ያዙኝ ልቀቁኝ ማለቱም በርትቶበት ባጅቷል። በደንብ መደንፋት ሲያምረው ጌታቸው ረዳን አሰልፎ ጠረጴዛ አስደብድቧል። አሁን ያዙኝ ልቀቁኝ የሚለው ጌታቸው የለም።
ትናንት በትግራይ ቲቪ የሰጠውን መግለጫ ያየ የጌታቸው ረዳ ነፍስ ከፍተኛ ጭንቀት ላይ ነች። በሀምሌ መጨረሻ አካባቢ ከአፍ እስከገደፉ ሞልቶ ግንዱንም፣ ድንጋዩንም፣ አፈሩንም እያገላበጠ ሲደነፋ የነበረን መለስተኛ ወንዝ ሕዳር አጋማሽ ላይ ብታዩት ያሳዝናችኋል።  ውሃዋ ጭልጭል እያለች አብዛኛውን ክፍል አልጌ ግጥም አድርጎ ይይዘዋል። ትንንሽ ወፎች ተንደፋድፈውበት ይዝናኑበታል። ሳርና ቅጠል ይወዳድቅበታል። ጉንዳን ሳይቀር ውሃው ላይ ጣል ያለች ሳርን ተጠቅሞ ይሻገርበታል።
ዘመን ብዙውን ነገር ከንቱ እንደሚያደርግ ታዩታላችሁ። ድንጋይና ግንድ እያላተመ፣ መሬት እየቆረጠ ሲደነፋ የነበረ ውሃ፣ ደቃቃዋ አሸዋ ውስጥ ይደበቃል። የጌታቸው ነፍስ ወራት ባቀዘቀዘው ወንዝ ውስጥ ልትደርቅ ወራት እንደቀራት ጭላጭ ውሃ ነው የታየችኝ።  ከዛ ሁሉ ድንፋታ ጭል ጭል የምትል ቀጭን ነፍስ ነው የምትታየው። እጅግ ደክሞታል። ወይ የሚወደውን መጠጥ አጥቷል። አሊያም በተስፋ መቁረጥና በንዴት በጣም እየጠጣ ነው።  ወይ የሚወደውን አደንዛዥ አጥቷል አሊያም ከሚገባው በላይ ለመደንዘዝ ሲል ነፍሱን እያሰቃያት ነው። ምግብ መቸም የማይታሰብ ነው። ወልቃይትና ራያ ጠላት በሚሉት ሕዝብ ተይዞ ምላሱ እንዴት ምግብ ያንከባልልለታል? ጉሮሮው እንዴት ይውጥለታል? እንቅልፍስ ቢሆን እንዴት ይታሰባል?
ሰፈር አላስወጣ፣ አላስገባ ብሏችሁ የሚያውቅ ውሻ የለም? የሆነ ጊዜ አርጅቶ ወይ ታሞ ብቻ ጊዜ ጥሎት ለመነሳት ደክሞት፣ እንደድሮው መደንፋት አቅቶት ግን እንደምንም ቢሎ ከሚቀር ካለፋችሁም በኋላ አለሁ ለማለት የሚያሰማት ቀጭን ድምፅ አለች። ቀጭን ድምፅ፣ ብቻ ሳትሆን ስስት ያለች መከራዋን ያየች ነፍስ። ከሞትም ከመኖርህ መሃል የምትንከላወስ! ጌታቸው መግለጫ ሲሰጥ ከዛ ግዙፍና ውድቀት ያዛባው ሰውነቱ ላይ የምትንቦጫቦጭ የተሰቃየች ነፍሱ ታስታውቅበታለች። መጠጥም ውሸትም ሊያለመልማት ያልቻለች ደቃቃ ተስፋ ያጣች ነፍስ።
የጌታቸው ነፍስ ስልችት ያላት ነች። ሲደነፋበት የከረመው ነገር ውሃ በልቶታል። የተዋከበችው ነፍሱ በአንድ በኩል ደመሰስናቸው እያለች ወዲያውኑ አዳልጧት የመቀሌ መከበብ ጉዳዬ አይደለም ታሰኘዋለች።  “እስካሁን አልተያዝኩም” ብላ እንቅልፍ ያሳጣትን ፍርሃት ትገልፃለች። “መቀሌ ላይ በሄሊኮፍተር ሰው ሊያወርዱ ይችላሉ።” ብላ ዝርዝር ስጋቷን ትናገራለች።    ተሸነፉ ተደመሰሱ ባለችበት “ደርግም ብዙ ከተማ ይዞ ነበር። ከተማ ሊይዙ ይችላሉ። ግን መግዛት አይችሉም።” ብላ ተስፋዋን ትቆርጠዋለች።
 ጌታቸው ረዳ  እንደዛ ሲደነፋ የነበረው በርካታ ፅንፈኞችን መቀሌ እየጠሩ ሲያደራጁ፣ ተልዕኮ እየሰጡ ስለነበር ነው። አሁን ሌላው ፅንፈኛ ቀርቶ አዲስ አበባ ያለው የትህነግ መዋቅር ፍርስርሳው ወጥቷል። መቀሌ በርካታ ፅንፈኛ እየወሰዱ ሲያደራጁ የነበሩት  እነ ጌታቸው ረዳ አሁን ስጋታቸው እነዛ ፅንፈኞች ወደታጎሩበት ቂሊንጦ እንወርዳለን የሚል ነው። ያኔ ጌታቸው ይደነፋ የነበረው የሰሜን ዕዝን እንዴት ወርሰው አዲስ አበባ መግባት እንዳለባቸው በእቅድ ሲመክሩ የሚሰማቸውን ኩራትና ተስፋ እየተመገበ ነበር። አሁን ከዛ የሰሜን ዕዝ ከባድ መሳርያ ተስፋ፣ ሕዝብ ጩቤ ይዞ ይዋጋ ወደሚል ተስፋ ቢስነት ደርሰዋል። አሁን የሰሜን ዕዝን ይዘው አማራን ተራምደው ለማለፍ የነበራቸው ተስፋ በሚያስቆጫቸው መልኩ ከሽፏል። የሰሜን ዕዝ መሳርያ ቀርቶ ልዩ ኃይሉን እስከ አፍንጫው ያስታጠቁት መሳርያ የሚጠሉት ኃይል ሲሳይ  ሲሆን እነ ጌታቸው ድፍረት የሌላቸው ሆነው እንጅ ነፍሳቸውንም ሕዝባቸውንም እንዲህ አያሰቃዩም ነበር።  ያች ስትደነፋ የነበረች የጌታቸው ነፍስ አሁን ተገርፋ ስልል ያለች ድምፅ ብቻ እያሰማች ነው።
የጌታቸው ድካም ገና ቃለ መጠይቁን ሳይጀምር ነው የሚታይበት። ገና በሰላምታ። አመሰግናለሁ ማለት ያቅተዋል። ህፃናት ሳያስቡት እንደሚናገሩት፣ ስላልቻሉ እንደሚገድፉት ነፍሱ ትሳሳታለች። ከአንገት በላይ ያሉት አካላቱ ሳይቀር የኮንፌደሬሽን ያህል አንድነት የላቸውም። ለየብቻቸው  ትንንሽ ምልክት ይሰጣሉ።  አይኖቹ ጎድጉደዋል፣ ምላሱ የሚስቷቸው ቃላቶች ብዙ ናቸው። የትግራይ ቲቪ ኢዴተሮች ብዙ ስህተት እንደለቀሙለት እገምታለሁ። ያም ሆኖ ግን በደንብ ያስታውቅበታል። ሳያስቡት አይኑንም፣ አፍንጫውንም ለመጠንቆል ዘው ብለው የሚሄዱት እጆቹ ጠባቂ ያስፈልጋቸው ነበር።  ለሶስት ደቂቃ  ያህል የግራ እጁ ኪሱ ውስጥ ነበር። ቀኝ እጁ እየተንቀሳቀሰ ግራው ደክሞት መሰለኝ ኪሱ ውስጥ አረፍ ብሎ ነበር። ከመዛሉ የተነሳ አካላቱም እንደዛው  በየፊናቸው የሚሆኑበት ጊዜ ብዙ ነው።  ውጨኛው አካሉ ጠውልጎ ከሚታየው በላይ ነፍሱ ልትደርቅ መቅረቧ  ይታወቅበታል።
እየተናገረ መሃል ላይ የሚረሳቸው ነገሮች አሉ። “ደመሰስናቸው” ብሎ ጭልጥ ያለ ሀሳብ ውስጥ ይገባል፣ ፈጀናቸው ብሎ በስሜት የሚነጉድበት ክፍል አለ። ውሸቱን ሳይጨርስ “እውነት ቢሆን ኖሮ” ብሎ በምናቡ ድል ለመቀዳጀት እያሰበ ይመስለኛል። ያሰቡትና እየሆነ ያለውን ማሰብ የምርም ያሰቃያል። ያ ሲፎገሉበት የነበረውና አሁን እየተደበቁበት ያለው ሁኔታ ውሃና እሳት መካከል የሚከት ነው። የሚያሰቃይ።  እሳት ውስጥ ገብቶ የቆየ ብረትን በቀጥታ ውሃ ውስጥ ስታስገቡት የሚኖረውን ስሜት ታውቁታላችሁ። የጌታቸው ነፍስ እንደዛ ከጋለው ስሜታቸው ውሃ ውስጥ እንደገባ ብረት “ትሽሽሽሽሸሽ” ብላ  የተሰቃየች ነች።
የሰሜን ዕዝን ትጥቅ ይዘው፣ ወታደሩን አሳምነው፣ በተለይም እነ ጃዋር ሳይታሰሩ ከእነሱና ከሌሎች ጋር ሆነው፣ አማራውን አበጣብጠው፣አዳክመውና አዘናግተው ሰላሌን በሳምንት ውስጥ ጉብ እንልበታለን ሲሉ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ተከዜን ወደኋላ ሲሻገሩ እነ ጌታቸው ረዳ ድሮ ያሰቡትንና አሁን የገጠማቸውን አስበው መጠጥ የተደረደረበት ጠረጴዛ ተደፍተው ሁሉ የሚያለቅሱ ይመስለኛል። ከቃለ መጠይቁ እንደታዘብኩት የጌታቸው ነፍስ በድንፋታ እና በለቅሶ መካከል መከራዋን የምታይ ነች። ኢትዮጵያ ያላትን ከባድ መሳርያ ይዘው፣ ጦሩን አሰልፈው በቀጥታ ቤተ መንግስት ከመግባት ቅዠት  ሲነቁ፣ መቀሌ በከባድ መሳርያ ተከብባ የሚለው እውነት የሞቀን ብረት እጅግ ቀዝቃዛ ውሃ ውስጥ ከማስገባት በላይ ለነፍስ የሚያሰቃይ ነው። ሀምሌ መጨረሻ ላይ ምንም አይቅረኝ እያለ ሲደነፋ የነበረው ወንዝ አካል የሆነች ውሃ ስትጠራርገው ከነበረው ጥቃቅን አሸዋ ስር ተደብቃ ፀሃይን ልታመልጥ እንደምትደክመው አይነት  ልፋት በጌታቸው ነፍስ ላይ ይታያል። “ነፍስ ውጭ ነፍስ ግቢ” እንደሚባለው ነው።  በውሸትና በመራራው እውነት፣ በድሮው ተስፋ እና በወቅታዊ ስጋት መካከል ወዲያና ወዲህ እያለች ትሰቃያለች።
Filed in: Amharic