ይድረስ ለቀድሞ የህወሃት ታጋይ ጓዶቼና መሪዎች‼️
አታክልቲ አብረሃ! የቀድሞ የህወሃት አባል
* … የእናንተ ስህተት አርቆ ማሰብ አለመቻል ማለቂያ የለውም ፡፡ ብላችሁ ብላችሁ የአገሩ አልበቃ ብላችሁ ወደ ሰው አገር ሮኬት በመተኮስ የአለም አቀፍ ትብብር ለማግኘት ሞከራችሁ ፡፡ አሁንም ማሰብ ብትችሉ ከትብብር ይልቅ ውግዘት እንደሚያመጣ ታውቁ ነበር ፡፡ ግን ማሰብ ካቆማችሁ ሰንብታችኋል ፡፡ ዘመናት አልፈዋል ፡፡ እባካችሁ በደመነፍስ የትግራይን ህዝብ ስቃይ አታብዙበት !!! አቁሙ !!! በቃችሁ !!! ህዝቡን ተዉት!!! ይኑርበት!!!
ባለፉት 3 አመታት ከነገ ዛሬ ከእንቅልፋችሁ ትነቃላችሁ ብዬ ስጠብቅ ነበር ፡፡ የትግራይ ህዝብ ከሌሎች አጋር ብሄሮች ጋር ተጋድሎ ያስገኘውን የትግል ውጤት ባለፉት 30 አመታት አንድ እርምጃ ወደፊት ሁለት ደግሞ ወደኋላ እያላችሁ ስትጓዙ እነዚህ ሰዎች ቀስ እያሉ ይማራሉ እያልኩ እጠብቅ ነበር ፡፡ በአንድ በኩል በአንድ ወቅት እምልበት በነበረው በህውሀት ድርጅት መሰረት የገባሁትን ቃል ላለማጠፍ ስለ አመራሩም ሆነ ስለ ድርጅቱ ምንም መጥፎ ቃል ሳይወጣኝ በምጥ ተጨንቃ መፍትሄ እንዳጣች ነፍሰጡር ለብቻዬ እየተጨነኩና በሀዘን እየተሰቃየሁ የማውቀውን ሁሉ ለራሴው ብቻ በባዶ ቤት እየተናገርኩ ቆየሁ አሁን ግን የተስፋዬ መጨረሻ ስለደረሰ እና የእናንተም አመራር ያመጣው ውድቀት መጠን ስሜቴን መቆጣጠር ከምችለው በላይ ሆኖ አስጨነቀኝ። የድሮ የትግል አጋራችን አሁን ደግሞ ወደ መቀሌ የሚገሰግሰውን የፌደራል ጦር እየመሩ ያሉት ጀነራል አበባው እንዳለው ያበጠው ይፈንዳ ብዬ ለወገኔ ለትግራይ ህዝብ ለወንድሞቼ እና ለእህቶቼ ለአባቶች እና ለእናቶች ህይወት እና ደህንነት በማሰብ ይህን ፅሁፍ አውጥቻለሁ ፡፡
እኔ በረሀ ስወጣ ውቅሮ የሚገኙት ቤተሰቦቼ በተባበሩት መንግስታት እህል ከአሰብ በመኪና ተጭኖ እየመጣ እየተከፋፈለ ነበር የሚረዱት ባለፈው ሳምንት የተባበሩት መንግስታት ከ 600 ሺህ በላይ የትግራይ ህዝብ አሁን በሚካሄደው ጦርነት ምክንያት የምግብ እርዳታ እንደተቋረጠበት ስሰማ በጣም የገረመኝ ። የእናንተ ዘመዶች በብዙ ሚሊዮን ብሮች የሚቆጠሩ የፎቅ ቤቶች ባለቤት ሲሆኑ የትግራይ ህዝብ ግን እስከ ዛሬ ከልመና ያውም ከምግብ ልመና ለማውጣት አለመቻላችሁ ነው ፡፡ ነገር ግን ስሜቴን መቆጣጠር ያላስቻለኝ ያ ብቻ አይደለም ፡፡ ዋናው እና አንደኛው ምክንያት ይህን ቀላል ጥያቄዎች መመለስ አለመቻሌ ነው ፡፡ ጥያቆዎቹም እነዚህ ናቸው “እነኢህ ሰዎች ምንያህል አርቆ ማሰብ ቢሳናቸው ነው በየቀኑ የተሳሳተ ውሳኔ እየወሰኑ እራሳቸውን ከአገር አስተዳዳሪነት ፣ የጦር መሪነት ፤ የሴኪዩሪቲ ሀላፊነትን ከፖሊስ ሀይል አዛዥነት አንስተው ተመልሰው ከ30 አመት በፊት ወደነበሩበት የጎሬላ ተዋጊነት የተመለሱት ?” በነዚህ መሪዎች ነው የትግራይ ህዝብ ሲመራ የኖረው ? ማሰብስ መቼ ነው ያቆሙት ? ባለፈው 3 አመት ውስጥ የወሰዳችኋቸውን ውስኔዎች መለስ ብዬ ሳይ አንዱም ውሳኔ አርቆ አሳቢነት ያልተሞላበት ፊትለፊታችሁ ያለውን እንኳን ማየት እንደማትችሉ ያለጋገጣችሁበት ነው ፡፡ ለመሆኑ አብይ አህመድን እጃችሁን አውጥታችሁ ስትመርጡ ድርድር አድርጋችሁ ነወ ወይስ በደመነፍስ ? እንዲሁ በራሳችሁ ችሎታ በመተማመን ? የራሳችሁን ችሎታስ በደንብ አውቃችኋል ? ወይስ ለራሳችን ስንነግር የምንውለውን ውሸት እየደጋገማችሁ ስትናገሩ እውነት መሰላችሁ ፡፡ ይህን ያህል ዘመን በስልጣን ላይ ስትቆዩ ይህ ሊመጣ እንደሚችል አውቃችሁ ያዘጋጃችሁት ምንድን ነው ? በፌደራል ጦር ላይ ጦርነት መክፈት እንደምርጫ ቆጥራችሁ በፌደራል ስልጣን ላይ የቆያችሁ ጉዶች ያንን ሁሉ ስልጣን ያለምንም ፕላን ለቃችሁ ወደ ዋሻ ተመልሳችሁ የትግራይን ህዝብ እንደገና ተዋጋና ጥለን ወደመጣነው ስልጣን መልሰን ስትሉ አታፍሩም ? ምን ጉዶች ናችሁ ? ለትግራይ ህዝብ እንደገና ጦርነት እንደገና እልቂት ያውም ስትመሩት ከነበረው ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ስታደራጁት ከነበረው ከፌደራል ጦር ጋር እንደገና ተዋጋ ጠላትህ ነው ስትሉ አታፍሩም ?
እስከአሁን የወሰዳችሁትን ውሳኔዎች ሁሉ እስኪ መለስ ብላችሁ እዩ ፡፡ ስልጣን ለአብይ አስረክባችሁ ያለ ምንም ድርድር ለቀቃችሁ፡፡ የፖለቲካውን ለውጥ እንደግፋለን አላችሁ ግን ከመደገፍ ይልቅ ለማደናቀፍ ሞከራችሁ ፡፡ ከዛ ተያይዛችሁ ትግራይ ገባችሁ ያ ምን የሚጠቅም መስሏችሁ ነው ? የትግራይ ህዝብን እንደገና ለጦርነት ለማዘጋጀት መሞከር እብደት እንደሆነ ለመረዳት እንዴት አቃታችሁ ? ከዛስ በኋላ ምርጫ ብላችሁ የማይረባ የልጅ ጨዋታ እናንተው ስልጣን ላይ ሆናችሁ እናንተው ተመረጣችሁ ፡፡ በህዝቡ ማሾፍ እንጂ መንግስት መቼ ትግራይን አትምሩ አለና ፡፡ ምንም ለውጥ ያላመጣ ምርጫ አድርጋችሁ ነፃ አገር የመሰረታችሁ መስሏችሁ ከሆነ የሚገርም ነው ፡፡ ያን ሁሉ በትዝብት አለፍኩት አብረውን የተዋጉትን ያስተባበሩንን እነ ስዬ አብርሀን እና ገብሩ አስራትን ስታባርሩ ዝም ብዬ እንዳየሁ አሁንም ዝም አልኩ ፡፡ ያ አልበቃ ብሎ አርፎ ቤት ውስጥ በተቀመጠ የፌደራል ጦር ላይ ጥቃት በመሰንዘር የማትችሉትን ጦርነት ጀመራችሁ ፡፡ አላማው ምንድን ነው ? ትታችሁ የወጣችሁትን ስልጣን ለማስመለስ ? ያ እንደማይሆን ካልገባችሁ ከገመትኩት በላይ ደደቦች ናችሁ ማለት ነው ፡፡ ያን ካልሆነ ደግሞ ትግራይን ገንጥሎ በብቸኝነት ማስተዳደር ነው ሌላው ምርጫ ፡፡ የቱን ህዝብ ነው ከኢትዮጵያ የምትገነጥሉት ? እኛ እኮ የአሉላ እና የዮሐንስ ልጆች ነን ፡፡ ስማችን ኢትዮጵያ ነው ሌላ ስም ሊኖረን አይችልም ፡፡ በእናንተ ጭንቅላት ነው የትግራይ ህዝብ ተመርቶ ከኢትዮጵያ ተገንጥሎ የሚኖረው ? እዚህ ላይ ነው ዝምታዬ የተሰበረው ፡፡
የእናንተ ስህተት አርቆ ማሰብ አለመቻል ማለቂያ የለውም ፡፡ ብላችሁ ብላችሁ ሶስት ሮኬት በመተኮስ የአለም አቀፍ ትብብር ለማግኘት ሞከራችሁ ፡፡ አሁንም ማሰብ ብትችሉ ከትብብር ውግዘት እንደሚያመጣ ታውቁ ነበር ፡፡ ግን ማሰብ ካቆማችሁ ሰንብታችኋል ፡፡ ዘመናት አልፈዋል ፡፡ እባካችሁ በደመነፍስ የትግራይን ህዝብ ስቃይ አታብዙበት ። አቁሙ ፡፡ በቃችሁ ፡፡ ህዝቡን ተዉት ፡፡ ይኑርበት ፡፡
በሁሉም አቅጣጫ በኢትዮጵያ ሰራዊት ተከባችሃል። የመቀሌን ህዝብ ስቃይ አታብዙበት። እጃችሁ ስጡ ።
የድሮ ጓዳችሁ አታክልቲ አብረሃ