አብን እና ብአዴን የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች
ከይኄይስ እውነቱ
ከዚህ ቀደም ስለ ኢትዮጵያዊነት እና ዐምሐራዊነት ከጐሣና ነገድ ቈጠራ ጋር ሳይያያዝ ከቆሙላቸው የእሤት ሥርዓቶች አንፃር የማይነጣጠሉና ባማራጭነትም የምንጠቀምባቸው ፅንሰ ሐሳቦች መሆናቸውን በተረዳሁት መጠን አንድ መጣጥፍ ማቅረቤ ይታወሳል፡፡ ይህ ማለት ግን ዐምሐራ በነገዳዊ ማንነቱ በፖለቲካ መደራጀቱ ትክክል ነው የሚል አንደምታ የለውም፡፡ በተቃራኒው ዐምሐራ በነገድ ማንነቱ በፖለቲካ ከተደራጀ በጐሠኞቹ ሥርዓት ወጥመድ መውደቁን ያመለክታል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የዐምሐራ ሕዝብ ላለፉት ሠላሳ ሁለት ዓመታት በነገዳዊ ማንነቱና በእምነቱ የደረሰበትንና አሁንም ያልተቋረጠውን፣ በህልውናው ላይ የተቃጣ፣ ለንግግር እንኳን የሚከብድ ሕጋዊና መዋቅራዊ ግፍና በደል መላው ኢትዮጵያዊ የሚያውቀው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ህልውናውን ለማስጠበቅ የሚያደርገውን ማናቸውንም ዓይነት ትግል ተፈጥሮአዊ፣ ሕጋዊ፣ ፍትሐዊና ማንም ምድራዊ ኃይል ሊሰጠውና ሊነሳው የማይችለው መብቱ መሆኑን አምናለሁ፡፡ ለዚህም የመደራጀት አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ ባይገባም፣ ባይደራጅም ለህልውና መፋለም ተገቢ ነው፡፡ ይህ ህልውናን የማስከበር ትግል ደጋግሜ እንደገለጽሁት ከፖለቲካ ውጭ በሚደረግ ድርጅት (በሲቪክ/ሲቪል ማኅበራት ወዘተ.) መፈጸም አለበት የሚል ጽኑ እምነት አለኝ፡፡
አሁን ያለው የጐሣ ፖለቲካና ሥርዓት አንድ ማኅበረሰብ በጐሣ ወይም ነገድ ማንነቱ ፖለቲካን እንዲያደራጅ በሕግ ይፈቅዳል፡፡ የተፈቀደ ሁሉ ይጠቅማለ ማለት ግን አይደለም፡፡ በተግባር ደግሞ አገዛዙ ካልፈለገው ተቋማቱን (ለምሳሌ ምርጫ ቦርድን) መሣሪያ አድርጎ ሊከለክል ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ አሁን ላይ ለምትገኝበት ሁለንተናዊ ምስቅልቀል ዋናው ምክንያት የጐሣ ሥርዓቱና የፖለቲካ ማኅበራትን ጐሣን መሠረት አድርጎ ማደራጀት መሆኑን አብዛኛው ሕዝባችን ተገንዝቧል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ታዲያ እንዴት ተፈጥሮአዊውን፣ ሕጋዊውንና ፍትሐዊውን ጥያቄ ከሰው በታች የሚያደርገውን ዘረኝነት ተጠቅመን ውጤት ላይ ለመድረስ እናስባለን?
‹‹ኢትዮጵያዊነትን ሳይለቅ›› ማንኛውም ጐሣ ወይም ነገድ የፖለቲካ ማኅበር አቋቁሞ ከጐሠኞቹ ሥርዓት ራሱን ነፃ ያውጣ የሚለው አካሄድ እጅግ መሠረታዊ ስሕተት ይመስለኛል፡፡ ጐሠኞቹ ጐሣዊ ማንነታቸው ከእምነታቸው በልጦባቸው የተለያዩ እምነት ተከታዮች ኦሮሞዎች በመሆናቸው ብቻ አገዛዙ ለተልእኮው የመለመላቸውና ከኢኦተቤክ ኑፋቄ ፈጽመውና ቀኖና ጥሰው ያፈነገጡ ሕገ ወጦች ስለሰበሰቧቸው ዐምሐራውያን ፖለቲካን በነገድ እንዲያደራጁ ምክንያት ይሆናል ብዬ አላምንም፡፡ መርህን ለሚከተል ሰው እዚህ ላይ እሾኽን በእሾኽ ወይም ከየትም ፍጪው ዶቄቱን አምጪው (the end justifies the means) የሚሉት አባባሎች አይሠሩም፡፡ በጐሠኛነት መንገድ የሚመጣ ውጤት ቢኖር እንኳን ዘላቂ ሊሆን አይችልም፡፡ ‹መርህ› ሲባል ላንዳንዱ ቅንጦት ሊመስለው ይችላል፡፡ መርህን ያነሣሁት ከህልውና ጥያቄ ጋር አያይዤ አይደለም፡፡ ህልውናው አደጋ ላይ የወደቀን ማኅበረሰብ ለመታደግ ከፖለቲካ ማኅበርነት ውጭ የሚደራጁ ሌሎች ማኅበራት የማኅበረሰቡን ህልውና ለማስከበር በሚያደርጉት ትግል ከቀሪው ኢትዮጵያዊ ወገኖቹ ጋር ባንድነት በመተባበር የጐሣ ሥርዓቱን/አገዛዙን ሊያስወግዱ ይችላሉ፡፡ በዚህ ረገድ ካገር ውስጥም ሆነ ውጭ የሚገኙ አደረጃጀቶች ተቀናጅተውና ማናቸውንም ሀብት አሰባስበው ጊዜ ሳይወስዱ ህልውናን ወደማስከበር ተጋድሎ መግባት ያስፈልጋል፡፡ በዚህም የጐሣ ሥርዓቱን ከነ ሕጉና መዋቅሩ በማስወገድ ለጤናማ የፖለቲካ ሥርዓት መደላድሉን ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡ ከዚያ ውጭ የትም ፍጪው ዶቄቱን አምጪው መጥፎ ምሳሌነትን (bad precedence) ሊፈጥር እንደሚችል መገንዘብ ያሻል፡፡ እዚህ ላይ በስደትና በመከራ የምትገኘውን የኢኦተቤክንን በምሳሌነት ማንሣት ይቻላል፡፡ ቤተክርስቲያኒቱ ከአጥቢያ ቤክ እስከ ጠቅላይ ቤተክህነት የተዘረጋ ነባር መዋቅር አላት፡፡ አገዛዙ ልክ እንደ ዐምሐራው ሕዝብ የህልውና ፈተና ደቅኖባታል፡፡ ከአገዛዙ ጋር ተደርሷል የተባለው ‹ስምምነት› ተግባራዊ እንዳልሆነ ከብፁዓን አባቶቻችን መገለጫ ተረድተናል፡፡ አልፎ ተርፎም አገዛዙ በአገር ክህደት የሚፈጽመውን ወንጀል ሁሉ እናንተ ትእዛዝ ሰጥታችሁ ያመጣችሁት ነው በማለት እነሱን ለመክሰስና ቤተክርስቲያኒቱን ያለ መሪ ለማስቀረት ዳር ዳርታውን እናውቃለን፡፡ በኃይል የተያዙት አብያተ ክርስቲያናትንና መንበረ ጵጵስናዎችን አገዛዙ ለባለቤቷ ለመመለስ ፈቃደኛ እንዳልሆነ በተግባር እያሳየን ነው፡፡ በመሆኑም አባቶቻችን በጸሎታቸውና መደበኛ በሆነው መስመር ከአገዛዙ ጋር የጀመሩትን ግንኙነት መቀጠላቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እኛ ልጆቻቸው ግን ትእዛዝ በመጠበቅ እጃችንን አጣጥፈን የምንቀመጥበት ጊዜ የለንም፡፡ በየቀኑ በየሰዓቱ አገርና ቤክ የማፍረስ እኩይ ተግባር ቀጥሏል፡፡ አሁን ካልተንቀሳቀስን ኋላ ጥፋቱን መቀልበስ የማንችልበት ሁናቴ ይፈጠራል፡፡ ጩኸቱም የማይጠቅም ይሆናል፡፡ ስለዚህ ባገር ውስጥም ሆነ በውጭ የምንገኝ አማኞች ያለንን ውጤታማ የሆነ መዋቅር ተጠቅመን ማኅበረ ካህናት፣ ማኅበረ ምእምናን እና የማኅበራት አደረጃጀቶች ባስቸኳይ የቤተክርስቲያናችንን ህልውና እና ተቋማዊ ልዕልና ማስከበር አለብን፡፡ ጎበዝ! አገዛዙ አገር ለማፍረስ 24/7 ሲሠራ፣ እኛ የአገራችንን እና የቤተክርስቲያናችንን ህልውና ለማስጠበቅ እንዴት ተኝተን እናድራለን?
ይህንን በመንደርደሪያነት ካነሣሁ፣ ወደ ርእሰ ጉዳዬ ስገባ ‹አብን› ራሱን በጐሣ ላይ ያዋቀረ ‹የፖለቲካ ድርጅት› ነው፡፡ በየትኛውም መመዘኛ ሲታይ በኢትዮጵያ በቊጥሩ ብዛት ቀዳሚ የሆነውን የዐምሐራን ሕዝብ የማይመጥንና ሊወክለውም የማይችል ስብስብ ነው፡፡ መደራጀት መብት ቢሆንም የዐምሐራ ሕዝብ እንደ ወያኔ ትግሬና ኦሕዴድ/ኦነግ በዘር ተደራጅተህ ከባርነት ታደገኝ የሚለው የፖለቲካ ማኅበር አይፈልግም፡፡ በነገራችን ላይ በወያኔ ትግሬም ሆነ በወራሹ ኦሕዴድ/ኦነግ በሕግም በተግባርም ያሉት አብዛኞቹ ‹የፖለቲካ ማኅበራት› በጐሣ ላይ የተመሠረቱ በመሆናቸው ተቀባይነትና ተገቢነት ባለው ዘመናዊ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ የፖለቲካ ማኅበራት ተብለው ሊጠሩ አይችሉም፡፡ እነዚህ የጐሣ ማኅበራት በብያኔ ደረጃ እንወክለዋለን ያሉትን ጐሣ መብትና ጥቅም ለማስከበር የተቋቋሙ በመሆናቸው በየትኛውም መመዘኛ
ከአገዛዙ ውጭ ያላችሁ አንዳንድ መደበኛም ሆናችሁ ማኅበራዊ ሚዲያዎችና የሚዲያ ሰዎች እባካችሁ በጎ ተግባራችሁ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አብን እና ብአዴንን እንዲሁም ከእነዚህ ድኩማን ድርጀቶች ጋር ቀድሞም ሆነ አሁን ግንኙነት ያላቸውን ግለሰቦች በመልካም እያነሣችሁ ሕዝብን ከማደናገር ብትጠነቀቁ መልካም ይመስለኛል፡፡ ተልካሻ አደረጃጀት ለሆዳሞች ቢበጅ እንጂ ለሕዝብ ጠንቅ ነው፡፡ ከእንደዚህ ዓይነቱ ድርጅት የጠራ ዓላማ፣ ርእይና ፕሮግራም ያለው ማኅበር ከምንም ተነሥቶ ማቋቋም ይሻላል፡፡ አገዛዙ ሊሄድ የሚችልበትን ርቀት አሁንም ካልገባን ችግሩ የኛ ነው፡፡ እንኳን በጐሣ መሠረትነት ተደራጅቶ ይቅርና የዜግነት ፖለቲካ እናራምዳለን ብለው በንግግርና በጽሑፍ ፕሮግራም ያዘጋጁትና ዛሬ የት እንዳሉ የማይታወቁት የፖለቲካ ማኅበራት ምርጫ ተብዬው ውስጥ ለማዳመቅ ሲሳተፉ አገር አጥፊውን የወያኔ ማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥት› በተግባር የተቀበሉ መሆናቸውን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡
እግረ መንገዴን አንድ ተያያዥነት ያለው ጉዳይ ላንሣ፡፡ ሰሞኑን ከዓድዋ ድል በዓል ጋር ተያይዞ የዐምሐራው ሕዝብ ቀንደኛ ጠላት የሆነው የብአዴን መሥራች አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በሰጠው አስተያየት የተማረኩ ያሉ ይመስለኛል፡፡ ጥያቄው ሰውየው የተናገረው ትክክል ነው/አይደለም የሚለው አይደለም፡፡ ስለ ንግግሩም የምናመሰግንበት አንዳች ምክንያት የለም፡፡ የሚናገር መቼ አጣን፡፡ በአንዳርጋቸውና በጭራቁ ዐቢይ መካከል በመታመን ረገድ ያለው ልዩነት ምንድን ነው? ሰውየው ስንት ጊዜ ነው በአንኳር አገራዊ ጉዳዮች ላይ አቋሙን ሲቀያይር በክህደት የኖረው? የሕዝብ ድምፅ የነበረን ሚዲያ ላገር አፍራሹ ዐቢይ በገጸ በረከትነት መስጠቱ ይረሳል? በኢትዮጵያዊነት አጀንዳ ብቻ ሳይሆን ነገዱን ስንት ጊዜ ነው የቀያየረው? ግልብጥ ሎሌና ‹አማካሪ› አይደለም ወይ? ዛሬ አገዛዙ በፋኖነት ከሚያሳድዳቸው፣ በእስር ከሚያንገላታቸውና ከኤርትራ በርሃ አገር ሰላም ብለው እነሱን ተከትለው ወዳገር ቤት የተመለሱ ወገኖቻችንን ሜዳ ላይ በትኖ ከአገዛዙ ጋር አሸሼ ገዳሜ ማለቱን ዘነጋችሁት? አንድን አጭበርባሪ ፖለቲካኛ ምን ያህል ጊዜ እንዲያታልለን ነው ዕድል የምንሰጠው? መቼ ነው በስሜት መነዳት የምናቆመው? የዐምሐራን ሕዝብ ለአገዛዙ ጭካኔ አሳልፈው ከሰጡ አድርባዮች መካከል ይሄ ግለሰብና ግብረ አበሩ ዶ/ር ብርሃኑ አይደሉም ወይ? እነዚህ አገርን በማይጠገን መልክ እየበደሉና የአገር አፍራሾች ተባባሪ በመሆን እንደ እሥሥት የሚቀያየሩ ግለሰቦች ወቅት ጠብቀው ብቅ በማለት በሕዝብ ዘንድ ያጡትን ተቀባይነት ለማደስ በቀባጠሩ ቊጥር ልባችን ፍስስ የሚል ከሆነ አሁንም አልገባንም ማለት ነው፡፡ ይህ ግለሰብ እኮ እንደ ኦነጎቹ ትውልድን የሚያደናግር የውሸት ትርክት በመጽሐፍ ጽፎ ገንዘብ የሰበሰበ መሆኑን ዘነጋነው? ኢትዮጵያዊ ዜግነት ሳይኖረው ባገር ውስጥ የሚዲያ ሥራ መሳተፍ የማይችለውን ሰው የዓላማው አጋር በመሆኑ ብቻ ‹የአንዳርጋቸው ጽጌ ሕግ› የሚባል የሚዲያ ሕግ እንደወጣለት አታውቁም? እውነትም ጭራቁ ‹ሾርት ሜሞሪ› እያለ የቀለደብን መሠረት የለውም ለማለት ይከብዳል፡፡ ከዚህ በላይ የቀረበው አስተያየት አንዳርጋቸውን ለመሰሉ ሌሎች ሆድ-አደር አድርባዮች ይሠራል፡፡ አዲስ ‹ግልብጥ› ነን ቢሉ በቀላሉ ለማመን አንቸኩል፡፡ እንደ ቂጣ ሲገለባበጡ የኖሩ አሉ፤ ወደፊትም ይኖራሉ፡፡
ግለሰቦች በተለይም በተጨማለቀው የዚህ ዘመን የሥልጣን ፖለቲካ ውስጥ ሲያቦኩና ግዙፍ ጥፋቶችን ሲፈጽሙ ቆይተው በዐደባባይ ይቅርታ ጠይቀው ተመልሰናል ቢሉ እንኳን በቂ ጊዜ ወስዶ ለስልት የሚደረግ ጊዜያዊ መመለስ ይሁን ወይም ዘላቂ ከፍሬአቸው መመዘን ይገባል፡፡ እውነት ቢሆንም እንኳን ፈጥኖ አምኖ ለታላቅ አገራዊ ዓላማ በተደራጀ ስብስብ ውስጥ ማሳተፍ አይገባም፡፡ እነሱም ባደራጁት ውስጥ ዘሎ መግባት አይገባም፡፡ ቢያንስ ከክፉዎች ጋር አለመተባበርም እኮ በራሱ አስተዋጽኦ ነው፡፡ ያም ሆኖ ትክክል ነው ብለው አምነው ወይም ተሳስተውና ተታልለው፤ አሊያም ለከርሳቸው/ለጥቅም አድረው ኅብረታቸውን ከአጋንንታዊው አገዛዝ ጋር አድርገው የነበሩ ግለሰቦች/ቡድኖች በነቁበትና በባነኑበት ሰዓት ከልባቸው ወደ አእምሮአቸው/ቀልባቸው የተመለሱ ካሉ በጎ አድርገዋል፡፡ መቼም እንደ ጠፉ ይቅሩ አንልም፡፡ ጥንቃቄ ግን ያስፈልጋል፡፡ ባንፃሩም ሰዎች አይለወጡም ወይ ብለው የሚጠይቁ አሉ፡፡ በመደበኛም ሆነ በማኅበራዊ ሚዲያዎች አንዳንድ ሰዎች ስለ ለውጥ ደጋግመው ሲናገሩ ተፈጥሮአዊ መሆኑን እና ማንኛውም ሰው ለበጎ ወይም ለክፉ ሊለወጥ እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ ይህ አባባል በጥቅሉ ሲታይ ትክክል ነው፡፡ ባንፃሩም ለማናቸውም ነገር አጠቃላይ ሕግ/ደንብ/ልማድ/ዕድር (the general rule) እንዳለ ሁሉ ለዚህ አጠቃላይ ሕግ/ደንብ/ልማድ/ዕድር ደግሞ ልዩ ሁኔታዎች (exceptions to the general rule) መኖራቸውን መዘንጋት የለብንም፡፡ በዚህ ረገድ የዚህ አስተያየት አቅራቢ ኢሕአዴግ ከሚባለው የአጋንንት ስብስብ በተለይም ብአዴን ከሚባለው የዐምሐራ ሕዝብ ደመኛ ጠላት ከላይ እስከ ታች ባለው ‹አመራር› ‹ሰው› ይወጣል ብዬ አልጠብቅም፡፡ ይሄ አጠቃላይ ሕጉ/ደንቡ/ልማዱ/ዕድሩ ሲሆን፤ ምናልባት በሠላሳ ዓመታት ውስጥ ያልተደረገ ተአምር ከተፈጠረ ‹ሰው› የሚሆኑ አንድ/ሁለት ግለሰቦች ከተገኙ እንደ ልዩ ሁኔታ (exception) አድርጌ እወስደዋለሁ፡፡ ይሄ አባባል ከብአዴን ጋር የአንድ ሳንቲም ሌላኛው ገጽታው ለሆነው ለአብንም ይሠራል፡፡ ተጨማሪ ስሕተት መሸከም የማንችልበት ደረጃ ላይ የምንገኝ መሆኑን እናስተውል