>
5:13 pm - Wednesday April 19, 7093

የአማራን ሕዝብ እና ጭንጋፉ ብአዴንን ምን አገናኛቸው? (ከይኄይስ እውነቱ)

የአማራን ሕዝብ እና ጭንጋፉ ብአዴንን ምን አገናኛቸው?

 

ከይኄይስ እውነቱ

 

መለያየትን መሠረት አድርጎ እና አንድ ሕዝብ አይደለንም ለማለት በዘመነ ወያኔና ወር ተረኞች ነን በሚሉት የግብር ልጆቹ በሆኑት ኦነጎችና ተረፈ-ወያኔዎች የኢትዮጵያ ሕዝብ በጐሣ/ነገድ ማንነት መጠራት ከጀመረ የአንድ ጐልማሳ ዕድሜ አስቆጥሯል፡፡ ኢትዮጵያ አገራችን ለዘመናት በተገነባ ኢትዮጵያዊነት ተብሎ በሚታወቅ ብሔራዊ ማንነት የተሳሰሩ የብዙ ነገዶች/ጐሣዎች አገር መሆኗ እርግጥ ነው፡፡ ያም ሆኖ ዛሬ ዛሬ የኅብረተሰባችንን አንድ ክፍል በጐሣ/ነገድ ስም ስጠራ የዓሣ አጥንት ጕረሮዬ ላይ የተሰነቀረ ያህል ይተናነቀኛል፡፡  የጐሠኞቹ መንደር የገባሁና በኋላቀር አስተሳሰባቸው ተካፋይ የሆንኩ ያህል ይሰማኛል፡፡ ማኅበረሰቡ ከየትኛውም ጐሣ/ነገድ ይሁን ኢትዮጵያዊ ወገኔ/ዘመዴ ነው፡፡ የአገሩ ባለቤት ኢትዮጵያዊ ዜጋ ነው፡፡ የጐሣ/ነገድ አባል መሆን እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ ወያኔ ትግሬና አሽከሮቹ የኢትዮጵያን ሀገራዊ አንድነት ለማፍረስ እና የሕዝቡን አብሮነት ለመበታተን የአገዛዝ መሣሪያ ማድረጋቸው ግን ሠላሳ ዘመን ያስቈጠረ ድርጊት ነው፡፡ 

ለርእሴ መንደርደሪያ ስለሆነው የአማራ ሕዝብ ጉዳይ አንድ ሁለት ቃላት ላንሳ፡፡ የአማራ ሕዝብ ጐሣ/ነገድ ዘለል ሕዝብ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ከመንግሥትነት ታሪክ እና ከትምህርት (ቀደምት መምህራኑ የአማርኛ ቋንቋ ዐዋቂዎች ከመሆናቸው) ጋር ተያይዞ አማራ ተብሎ የሚታወቀው ሕዝብ የብዙ ጐሣዎች/ነገዶች ድብልቅ ውጤት ሆኗል፡፡ የመንግሥት ሕዝብ በመሆኑም የነገድ ማንነት የለውም፡፡ ማንነቱ ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው፡፡ ቅድምናውን ለመናገር እንጂ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ጐሣዎች/ነገዶች ኢትዮጵያዊ ማንነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ጐሣዊ ማንነትም አላቸው፡፡ በብሔራዊ ማንነት (ኢትዮጵያዊነት) ግን ሁሉም ጐሣ/ነገድ እኩል ነው፡፡ የአገዛዙ ሕጋዊና መዋቅራዊ ድጋፍ ስላለው እንጂ ብሔራዊ ማንነታችንና የጐሣ ማንነት የሚጣላበት ምንም ምክንያት የለም፡፡

የአማራ ሕዝብ ባለፉት ሦስት ዐሥርታት የደረሰበትና አሁንም እየደረሰበት ያለው መጠነ ሰፊ ጥቃት በዚሁ ኢትዮጵያዊ ማንነቱ ምክንያት ነው፡፡ አገራችን፣ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በሚጠሉና ለማጥፋት ሌት ተቀን በሚሠሩ የጥፋት ኃይሎች እጅ በመውደቋ፡፡ ይህ ሕዝብ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ውሱን ቦታ፣ የተከለለ ድምበር የለውም፡፡ ዛሬ ወያኔና ኦነግ በፈጠሩት የሐሰት ትርክት በአገሩ ባይተዋር ሆኗል፤ መጻተኛም አስመስለውታል፡፡ ዝርዝሩን ለመረዳት የምትፈልጉ ‹‹የኢትዮጵያ ተጠሪ ማነው?›› በሚል የኢትዮጵያዊው ሊቅ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌን እና ሌሎች መጣጥፎች ያሰባሰበውን መጽሐፍ እንድታነቡ እጋብዛችኋለሁ፡፡ 

ከዚህ በላይ የተናገርኩት ቃል የሚያስቆጣችሁ ጥቂት የማትባሉ ወገኖቼ እንዳላችሁ ይሰማኛል፡፡ ጽዋው ሞልቶ ከተረፈ ግፍና በደል የተነሳ ወደ ‹ጐሠኝነት› አስተሳሰብ የተገፋችሁ እንዳላችሁ ይገባኛል፡፡ ለዚህ መፍትሄው በፖለቲካ ሳይሆን በማኅበረሰብ ድርጅትነት ተደራጅቶ ራስን መከላከልና መብትን ማስከበር ነው፡፡ በዚህ መልኩ ተሰባስበናል የሚሉ አካላት በአገር ውስጥም ሆነ በውጩ ዓለም እንዳሉ ብንሰማም ከመግለጫ ባለፈ ሕዝቡን በመንግሥት መዋቅር ከታገዘ የጐሠኞች ጥቃት የታደገ አልተገኘም፡፡ አንዳንዶች ለዚህ ሕዝብ ቀንደኛ ጠላት ከሆነው ብአዴን ከሚባል ቅጥረኛ ድርጅት ጋር ለመሥራት ስትከጅሉ÷ እንደ ሕዝብ ወኪልም ስታዩት ታዝበናል፡፡ 

የአማራ ሕዝብነት ኢትዮጵያዊነት ከሆነ፣ ኢትዮጵያዊነት ደግሞ የብሔራዊ ማንነት ወይም የዜግነት መገለጫ ከሆነ፣ ለዜግነት የሚመጥን የፖለቲካ አደረጃጀት ያስፈልጋል፡፡ ይኸውም አንድ ዓይነት ዓላማ፣ ተልእኮ እና ግብ ያላቸው ዜጎችን አሰባስቦ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚናፍቀውን መንግሥተ ሕዝብ የሚያቆም ሥርዓት ዕውቀትን መሠረት አድርጎ አማራጭ አሳቦችን የሚያቀርብ የፖለቲካ ማኅበር ማደራጀት ነው፡፡ 

በኢትዮጵያ ምድር በነውረኛነቱ እስከ የሌለው የ‹ፖለቲካ ድርጅት› እንደ ብአዴን አልተፈጠረም፡፡ እውነቱን ለመናገር ይህንን ጭንጋፍ ድርጅት ስሙንም ለማንሳት፣ ሲጠራም ለመስማት ፍላጎት የለኝም፡፡ ብአዴን ራሱን አክስሟል፣ ‹በልጽጓል›፤ የሌለ ድርጅት ለምን ታነሣለህ የምትሉ አትጠፉም፡፡ መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ እንዲሉ ‹በለጸግኹ› የሚለው ኢሕአዴግ አልከሰመም፡፡ ስም ቀየረ እንጂ፡፡ የዚህ ነውረኛ ድርጅት ደጋፊዎችና ተጠቃሚዎች እንዲሁም ግለሰብ አምላኪዎች ካልሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ በዚህ ማጭበርበሪያ እንደማይታለል ተስፋ አለኝ፡፡ የኦሮሞ፣ የደቡብ፣ የሶማሌ፣ የአፋር ወዘተ. ‹ብልጽግና› ማለት ትርጕሙ ምንድን ነው? 

አሽከርነት የባሕርይው የሆነው ብአዴን ወያኔና ግብርአበሮቹ በጐሣ መልክ ሊያደራጁ ያሰቡትን፣ ማንነቱ ኢትዮጵያዊነት የሆነውን የአማራ ሕዝብ ወክሎ አያውቅም፣ ሊወክልም አይችልም፡፡ በእኔ እምነት የአማራ ሕዝብ ለደረሰበት ግፍና መከራ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው የዚህ ጭንጋፍ ድርጅት ፈጣሪ ወያኔ ትግሬ ሳይሆን ሎሌው ብአዴን ነው፡፡ በግል የብዙኃን መገናኛዎች ጭምር በየክፍለሀገራቱ ያሉት የኢሕአዴግ ድርጅቶች ያዋቀሯቸው ምክርቤቶች አባላትን የሕዝብ ተወካዮች አድርገው ሲያቀርቡ ከመስማት የበለጠ ምን የሚያሳዝን ነገር አለ? አምነውበት ከሆነ እጅግ ያስደነግጣል፡፡ በዘመነ ወያኔ ኢሕአዴግ የይስሙላ ካልሆነ በቀር ምርጫ አልነበረም፡፡ ከማዕከላዊው ‹መንግሥት› ጀምሮ ‹ክልል› እስከተባሉት ክፍላተሀገራት የሕዝብ ተወካዮች አልነበሩም፣ አሁንም የሉም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እስካለንበት ጊዜ (በ1997 ዓ.ም. ቅንጅትን ከመረጠበት አጋጣሚ በስተቀር) ይወክሉኛል የሚላቸውን የፖለቲካ ማኅበራትም ሆነ ግለሰቦች በነፃነት መርጦም÷ ሰይሞም አያውቅም፡፡ ዐቢይ በቂ የምርጫ ተሞክሮ አለን ሲል በመዓዛ ሬዲዮ ላይ ሲሳለቅ ሰምተነዋል፡፡

በተለያዩ አስተያየቶቼ ደጋግሜ እንደገለጽኹት ወያኔ ኢሕአዴግ የሚባል የዘረኝነት ምንጭ የሆነ ሰንኮፍ ተነቅሎ ካልጠፋ ኢትዮጵያ ሰንበትን አታደርግም፡፡ ወደ መንግሥተ ሕዝብም ልትሸጋገርም አትችልም፡፡ ከሰንኮፉ የከፋው ደግሞ ብአዴን የሚባለው ጭንጋፍ ነው፡፡ የምንናገረው ስለ ድርጅቱ እንጂ ግለሰቦች አይደለም፡፡ ያም ሆኖ፣ የዚህ የተወላገደ ድርጅት አባል መሆን በራሱ በሽታ ይመስለኛል፡፡ አገዛዙ አዳከመው፣ ተረኞቹ አጠፉት እያልን ከ30 ዓመታት በኋላ ለድርጅቱም ሆነ ለአመራሩ ሰበበ መፈለግ በራሱ ባለአእምሮነት አይመስለኝም፡፡ ለምን ድራሹ አይጠፋም!!! ለኢትዮጵያ መድኅን የሚሆናት ግን ኢሕአዴግ የሚባለው (የ4ቱም ድርጅቶች) ጥላ ብን ትን ብሎ ሲጠፋ ነው፡፡  

ታዲያ ይህንን ወራዳ ድርጅት ከአማራ ሕዝብ ጋር አያይዞ ማንሳት ታላቅ ንቀትና ስድብ ነው፡፡ ስለዚህ ድርጅት የምታወሩ ወገኖች የሞተም ዘመድ የላችሁ?

Filed in: Amharic