የአብዮቱ ሃምሳ ዓመትና ሶስቱ ቡችሎች
ሃይሉ አስራት
ፕሮፌሰረ ላሬቦ ዕውቀትና ዕውነት ላይ የተመሰረተ ሀሳብ ሲሰጥ አቢዩ የሚባል ቦርኮ ኢሕአፓ ደግሞ በበከተ የአብዮቱ ዘመን ፕሮፓጋንዳ ላይ የተመሰረተ ቅራቅንቦ አስተሳሰቡ የተማሪ እንቅስቃሴ፣ ታክሲ ነጂ፣ ነጌሌ ቦረና ወዘተ እያለ ዝባዝንኬውን ከ50 ዓመት በኋላ ሲያነበንብ ሰማሁት፡፡ ምን ዓይነት ደደቦች ጭምር ኢሕአፓን ሲመሩት እንደነበሩ ማረጋገጫው ይኸው ነው፡፡ ቦርኮ ኢሕአፓዎች እየጠራ ማንትስ በሚባል ቴሌቪዥን የሚያደነቁረን የጨርቆስ አራዳው ያነሰን ይመስል አንድ ሌላ የወሬ ቱቦ ውስጥ ጉድ የሚያሰኝ ወሬ ብሰማ ለአሁኖቹ ትምሕርት ይሆን እነደሁ ብዬ ይችን ጽሁፍ ሞነጫጨርኩ፡፡
ማን ነበር ኢሕአፓ አዲስ አበባ ላይ ከተሸነፈ በኋላ አብቅቶለታል ያለው? በመሰረቱ ኢሕአፓ ማለት በተለይ በአዲስ አበባ የወጣቶቹ ሊግ ነበር፡፡ ጌታቸው ማሩ የሰራው የመጀመሪያው ስህተት የአዲስ አበባውን አብዮት በዝቅተኝነት ቅናት (ኮምፕሌክሳሞች) ከሚነዱት ስብስብ ከነበረው ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ጋር ወስዶ ማደባለቁ ነበር፡፡ እንዴት ሰው ያውም የኢሕአሠ መሪ የነበረ ከ50 ዓመት በኋላ ፕሮፓጋንዳን መሰረት አድርጎ ውሸት ይነዛል? ተቦርነ የተባለውም ሆነ 66 ላይ የተቸነከረው አቢዩ ስለራስ መስፍን ማወቅ ካለባችሁ በታሪክ ባለሙያው ፋነታሁን እንግዳ የተጻፈውን ታሪካቸውን መጀመሪያ አንብቡ፡፡ የደርግን ፕሮፓጋንዳ እንደ ዕውቀት ቆጥራችሁ አታነብንቡ፡፡ ላሬቦ ትክክል ነው አቢዩ የሚባለው ቦርኮ ኢሕአፓ ከዚያም ነጠቅ ከዚህም ነጠቅ እያደረገ ጥልቀት የሌለው ነገር እያነሳ መዘባረቅ የዚያ ትውልድ ዋነኛ ችግር መሆኑን በሚገባ ገልጧል፡፡ በትክክል ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ ስለ መሬቱ ስሪት ወዘተ ምንም ዕውቀቱ አልነበራቸውም፡፡
ይሄ ወደ ሰሜን ያለ የደደቢትና የአሲምባ ውሃ፣ አየሩ ይሆን ወይስ የሚበላው እንዴት አዕምሮን እንደሚያቀነጭር አብዩ የሚባለውን ሰው የቀነጨረ አስተሳሰብ በመረዳት ብቻ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ለዚህ ነው ለካ ኢሕአፓም እንደቀነጨረ የተሸነፈው፣ ደግሞስ በቀነጨረ አስተሳሰብ እንደ አብዩ ዓይነቱ መርቶት የት ሊደረስ? ይህ የአዕምሮ መቀንጨር በልጅነት የሚከሰት ቢሆንም ከአቢዩና መሰል ቦርኮ ኢሕአፓዎች የምንረዳው ግን ቅንጨራው በወጣትነትም በጉልምስናም ሊከሰት የሚችል ያውም ባህር ማዶም ተሻግሮ ዩኒቨርስቲም ተገብቶ የማይለቅ በሽታ መሆኑን ነው፡፡ ለነገሩ ስንቱ የአዲስ አበባ አራዳ ገብረጉራቻን ወይ ሰንዳፋን ሲያልፍ በዚያው ቀንጭሮ እንደቀረ ከያሬድ ጥበቡ በላይ ምስክር የለም፡፡
የፈረንሳይ አብዮት የነጻ ግንበኞች ሥራ ውጤት ነው፡፡ ባጠቃላይም ነጻ ግንበኞች የሚሉት ነጻነት፣ ወንድማማችነትና እኩልነት…ነው፡፡ የእነርሱ ሥራ ንጉሳዊ አገዛዝንና በተለይ ደግሞ ክርስትናን በማጥፋት ላይ የተመሰረተ ነውና አሁንም ቢሆን አገሪቱን ማንቁርቷን ይዞ እያስጨነቃት ያለው በመላው ዓለም የተሰማራ የነጻ ግንበኞቹ አደገኛ ቡድንና ይህን ቡድን መጠለያ አድርገው የተነሱ ሌሎችም አጋንንታዊ ዓለሙን የሚዘውሩ ቡድኖች ናቸው፡፡ሰውየው በቀነጨረ አእምሮው ላይ በስተርጅና ተማርኩ ብሎ የጠነዛውን የሜይንስትሪም አስተምህሮ ይዘከዝካል፡፡ ሰውየው ዘንድሮ እንኳ መረጃ በተንበሸበሸበት ዘመን የፈረንሳይ አብዮት እንዴት በማን እንደተመራ አልገባውም፡፡ አቤት አቤት እንዴት ያለው ቀንጨራ ነው ኢሕአፓን ሲመራ የነበረው? በዚህ ሰውዬ ስር ለተመሩ የኢሕአሠ አባላት እጅግ እጅግ አዝናለሁ፡፡ ቦርኮ! ከጭላሎ ተነስቶ ኢትዮጵያን እንደጭላሎ ማሰብን ያህል የተንጫለለ ጨለሌ! ተምሬአለሁ ይላል ያውም በዚህ ዘመን ቢያንስ ወካይ የሆነ ናሙና ሳይወስድ እንዴት የአንድ ጭላሎን መንደር ጉዳይ የሃገር ወካይ አድርጎ ያወራል? ወይ ትምህርት! ከጣሊያን ጋር ይሰሩ የነበሩ ሰዎች ሲናደዱ ባፋን..! ይሉ ነበር፡፡ ምን ዓይነቱ ማፈሪያ ነው?
የፕሮፌሰር ላሬቦ ጥፋት ከዚህ ቦርኮ ጋር በመናኛው መድረክ መገኘቱ ነው፡፡ በጣም የሚያሳስቡ በአገር ደረጃ መነጋገር የሚገባን አጀንዳ ትተው አንዳንድ ቅንጣቢ ተራ ጉዳዮችን፤ የውረፋ፤ የጠላቤትና የአረቄ ቤት ወሬዎችን እያነሱ ከሚቀባጥሩ መናኛ ሰዎች ጋር መቅረቡ ነው፡፡ ያን ትውልድ በአግባቡ መውቀስም ማውገዝም እንደተጠበቀ ሆኖ እንደዚህ ዓይነት የቀነጨረ ቦርኮ ኢሕአፓ ግን ያን ትውልድ ሊወክል አይችልም፡፡
የዘንድሮዎቹ ወጣቶች ከዚህ መማር አለባችሁ ማንም ጠመንጃ ስላነገተ ጥሩ የጦር መሪም ቢሆን እንኳ የአገሪቱን ታሪክ፣ በተለይም ኦርቶዶክስ ተዋህዶንና አማራን የማጥፋት አለም አቀፍ ሴራ ካልተረዳ እንደ አሰግድ ሲሞዳሞድ ከርሞ እጁን ከሚሰጥ፣ እንደ ዘመነ ከአማራ ቀንደኛ ጠላት ብአዴን ጋር ከሚሰራ የውሸት ፋኖና ሌሎችም ወሽካታ በቂ ዕውቀትና የጠነከረ ዕምነት ከሌላቸው ፋኖ ተብዬዎች ወጥታችሁ ወደ ዕውነተኞቹ ፋኖ መሪዎች እንድትቀላቀሉ ነው፡፡ አለበለዚያ መስዋዕትነታችሁ ከንቱ ነው የሚሆነው፡፡ አንድ እንሁን ብሎ ነገር የለም – ዱባና ቅል ለየቅል ነው፡፡ ማንም መናኛ ለፍላፊ ስለለፈለፈ ባንዳና አርበኛ አንድ ሊሆን አይችልም፡፡ የአብዮቱ ጉዳይ በአጭሩ ፕሮፌሰር ላሬቦ ባለው መሰረት የኪሲንጀር – አሜሪካ ፖሊሲ ሲሆን አይሁዶችም ያሉበት፤ በነርሱ የተገፋና በነርሱ በተመለመሉና በስለላ ድርጅቶቻቸው በታገዙ ወታደሮች አማካይነት የተተገበረ ነው፡፡ ተማሪ ቱስ ቱስ አለ እንጂ አብዮት አላመጣም፡፡
አብዮቱ በ66 ይከሰት እንጂ ኢትዮጵያን በመሰረቱ የቀየራትና ጉዞዋን ወደ እልቂትና የጥፋት ጎዳን የከተታት ደግሞ መንግስቱ ሃይለማርያም ሞደሬት የነበሩትን የደርግ አባላት የጨፈጨፈበት ጥር 26/69 ቀን ነው፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም ያለ ቀኝ ተብዬውም ግራውም መሃከሉም ሊያጠፏት የማይተኙላት የእግዚአብሔር አገር በመሆኗ መንግስቱ ሃይለማርያም በህዳር 13/67 የጀመረውን የኢትዮጵያን ባለውለታዎች ጭፍጨፋ እነዚያን የደርግ አባላትና ሌሎችንም አገር ወዳድ ጀግኖች ይሉቁኑም በምስራቅ ጀርመንና ሶቭየቶች የደህንነትና ወታደራዊ እርዳታ አጠናክሮ በመቀጠል አንድ ትውልድ ጨፍጭፎ እስከ ዛሬ ላለንበት ችግር ምክንያት ሆኗል፡፡ በመሰረቱ ኢትዮጵያን የማጥቃትና የማጥፋት ሥራ ከሰሩት እንግሊዝ ፣ ፈረንሳይ፣ ጣልያን፣ ግብጽ፣ቱርክ በቅርቡም አሜሪካ ካደረሱብን ጉዳት ሁሉ እጅግ የከፋውን ኢትዮጵያን የማጥፋት ሥራ የሰሩት ሶቭየቶች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያን አንድ ትውልድ መንግስቱ ሃይለማርያም እንዲጨርሰው ገንዘብ፤ የጦር መሳሪያና ሰላዮችን በመመደብ አገሪቷን ስብርብሯን የማውጣት ስራ የተጀመረው (ልክ የአሁኑ አጋንንታም የአብዮት አህመድ ሥርዓት በምዕራባውያኑ እየተረዳና እየተነዳ እያጠፋን እንዳለው) በሶቭየቶች እርዳታ መሆኑን ኢትጵያዊ ሁሉ ልብ ሊለው ይገባል፡፡
አንግዲህ ስለ ኢትዮጵያ አብዮት ስናወራ ዋናው የአብዮቱ ፍሬ የመንግስቱ ሃይለማርያም ጥር 26/69 ነው፡፡ ትውልዱን ከጥቅም ውጪ አድርጎ፣ ሠራዊቱ ውስጥ ያሉትን ምርጥ ምርጥ ወታደራዊ አዛዦችና መኮንኖች ምንጥር አድርጎ ከጨረሰና በሶቭየቶች እየተደገፈ አገሪቷን አደህይቶ ሶቭየት ሕብረት ሲፈርስ እርሱም የመጨረሻዎቹን ጄነራሎች ረሽኖ መነገዱን በማመቻቸት በመጨረሻም አገሪቱን ለወያኔ አስረክቦ ይኸው እውነተኛው ሞት እንኳን ተጸይፎት 33 ዓመት የቁም ሞት ሞቷል፡፡ የአብዮቱ ሁለተኛው ፍሬ ደግሞ የቀዝቃዛው ጦርነት ማብቂያ በፈጠረላቸው አጋጣሚ ተገፍተው ወያኔ ባንዳዎች ሚኒሊክ ቤተ መንግስት መግባታቸው ነው፡፡ ከዚያም አሜሪካኖቹ ከአፍሪካ የተሻለ አቅም አዳብሮ የነበረውን የኢትዮጵያ ኤሊት ብትንትኑን እንዲያወጡት ያዘዟቸውን ወያኔዎቹ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ በማድረግ ምዕራባውያኑን ሲያገለግሉና ኢትዮጵያን ሲያራቁቱና ሲያጠፉ ከርመው ከ27 ዓመት በኋላ ወደ ቅንጨራ ማዕከላቸው ተመልሰው የትግራይን ህዝብ በምዕተ ዓመታት ሊመለስ ወደማይችል ውርደት፣ ውድመት፣ ቅስም ስብራትና በማንነት ቀውስ ዘፍቀውታል፡፡ ሶስተኛው የአብዮቱ ፍሬ የሆነው የዛሬው ብልጽግና ተብዬ ደግሞ በ21ኛው ክፍለ ዘመን በኦሮሞ ስም ታይቶ በማይታወቅ የጭካኔ፣ አረመኔያዊ ጭፍጨፋ ግድያና አገር የማውደም ስራ ላይ ተጠምዶ አገሪቱን በደም አጨማልቆ ለአጋንንታዊ አዲስ የዓለም ሥርዓት አገሪቱን አሳልፎ በመስጠት ኦሮሞን በክፍለዘመን ሊመለስ በማይቻል የታሪክ አዘቅትና ቅሌት ማጥ ውስጥ ከቶ እንክትክት አድርጎ ሰባብሮታል፡፡ በነሱ ቤት አማራንና ኢትጵያውያንን ሰባብረዋል፡፡ ሀቁ ግን በመንፈሳዊም፣ታሪካዊም ሆነ ባህላዊ ሀብቱ ሊያቆስሉት እንጂ ሊሰብሩ የማይችሉትን አማራንና ኢትጵያውያንን ከተኙበት መቀስቀሳቸውን ነው የሚያስገነዝበን፡፡
በኤርትራም በኩል አብዮቱ በንግድ በኢንዱስትሪ፣ በትምህርት ከፍተኛው የኤሊት አካል የነበሩትን ሰባብሮ ለሻቢያ የተመቻቸ ሁኔታ በመፍጠር ዛሬ ባንዲራ እንጂ እዚህ ግባ የሚባል ሰው የሌለባቸው ከንቱ ወራዳ ለፍላፊዎች አድርጎ አስቀርቷቸዋል፡፡ በትግራይ የነበረውን ተፈጥሯዊ ችግር አማራ እንደፈጠረው ተደርጎ የተነገራቸውን በየጠላ ቤቱ ምድረ ባንዳ ያወራውን ወሬ ጠጥተው ያደጉ በተለይም የታችኛው መደብ አባላት ወያኔዎች ደግሞ ኢትዮጵያን የማጥፋት ሥራውን ለ27 ዓመታት በመሠረታዊ የውጭ ጠላቶቻችን እየተረዱ አከናውነው እውነተኛዎቹን ትግሬዎች ጨፍጭፈው ጨርሰው በመጨረሻም የቀረውን እንደከብት የሚነዱትን ሕዝብ ለአሰቃቂ ጦርነት በመዳረግ ሚሊኖችን በማስጨረስ ታሪካቸው ቢደመደምም የቀረ የአጋንንቱ ዓለም ተላላኪነት ሚሽን ለማስፈጸም ከኢትዮጵያ በዘረፉት ቢሊዮን ዶላር የምዕራባውያኑን እግር እያጠቡ ነው፡፡
የዛሬው ሆድ እንጂ ዕውቀት ቀርቶ ኮመን ሴንስ የሌለው ብልጽግና ተብዬ የደንቆሮዎች ስብስብ ደግሞ የመጨረሻው የአብዮቱ ፍሬ ስለሆነ ፊት ለፊት አፍጥጦ አግጥጦ ኦርቶዶክስ ተዋህዶን፣ አማራን፣ አማርኛን፣ ኢትየጵያንና ኢትጵያውያንን ለማጥፋት ሌት ተቀን ይሠራል፡፡ ኢትዮጵያ እንኳን የልክስክሶቹ ስብስብ ብልጽግና ራሳቸው አሜሪካኖቹ ሊወጓት ቢመጡ የሚዋጋላት አምላክ ያላት አገር ስለሆነች አትጠፋም፣ በመጨረሻ የጠላቶቿን መጥፋት ታያለች እንጂ፡፡
ሲጠቃለል የስድሳ ስድስቱ አብዮት በሃምሳ ኣመት ዕድሜው ሶስት ጸረ ኢትዮጵያ ቡችሎች ነው የፈለፈለው፣ ደርግ ወያኔና ብልጽግና፡፡ የስድሳ ስድስቱ አብዮት ሌላው ዋነኛ መገለጫ ደግሞ ኢትዮጵያ እስከ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ጊዜ ድረስ በራሷ መሪዎች የምትደዳደር አገር ነበረች፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ደርሶ መሪ በመምሰል መንግሰቱ ኃ/ማርያም በሶቭየቶች፣ መለስ ዜናዊ ደግሞ በአሜሪካኖቹ እንዲሁም የዘንድሮው አጋንንታም ደግሞ በአዲሱ ዓለም ሥርዓት ሰይጣናዊ ቡድኖች የሚነዱ አሻንጉሊቶች መሆናቸው ነው፡፡
ፕሮፌሰር ላሬቦ ትክክል ነው፣ ያለቦታው ነው የተገኘው፡፡ ከማይመጥኑት ሰዎች ጋር ነው ጊዜውን ያጠፋው፡፡ በደርግ ቱልቱላ ፕሮፓጋንዳ ተኮትኩቶ ያደገው ተቦርነ የሚባለው ሰውየ ራስ መስፍን አርሲን የሚያህል መሬት ነበራቸው እያለ ከ50 ዓመት በኋላ ይቀደዳል፡፡ አብዩ የሚባለውም አብሮ ይሄን የጠጅ ቤትና ጠላ ቤት ወሬ ይዞ ያናፍሳል፡፡ ስለ ራስ መስፍን አፍን ከመፍክፈት በፊት የዘመናችንን ምርጥ ምርጥ መጽሃፍት ማንበብ ያስፈልጋል፡፡ ለመሆኑ እነዚህ ሁለት ሰዎች ሙሉጌታ ሉሌ ‹ሀብታሙን ራስ መስፍንን ላነጋግር ሄጄ ድሃውን ራስ መስፍንን አነጋግሬ ተመለስኩ› ብሎ በዚየው ዘመን የጻፈውን እንኳ አልሰሙም? ቦርኮ ሁላ፡፡
የራስ መስፍን ነገር እጅግ ገራሚ ነው፡፡ የራሳቸው ቤተሰብ እንኳ (እሳት አመድ ይወልዳልና) ዕውነተኛው ታሪካቸው እንዳይወጣ ታሪክ ፀሃፊውን ፋንታሁን እንግዳን እስከ ማገድ የተረባረቡበት ግን ደግሞ ታሪክ ፀሃፊው በጀግንነት የራስ መስፍንንም በአጠቃላይ አማራው ላይ ከ1953 መፈንቅለ መንግስት ጀምሮ ምርጥ ምርጦቹን የመፍጀትና አማራን የማጥፋት ሴራ ተንትኖ ከሃዲዎቹ አማራ ፈጅ የንዋይ ልጆችን ታሪክ ጭምር ቁልጭ አድርጎ አሳውቋል፡፡ በታህሳስ 53 እና በህዳር 67 ለተረሸኑት አማሮች ነው መጽሀፉንም መታሰቢያ ያደረገው፡፡ አማራ ነኝ የምትል ሁሉ በተለይም ፋኖዎች ይህን መጽሃፍ አንብቡ፡፡ የአብዩ አይነቶቹ ቦርኮዎችም ምንም እንኳ አሲምባ ላይ ስለተቸከሉ ቢያነቡም ሊለወጡ ባይችሉም ቢያንስ አርሲን ያህል ስፋት ያለው ውሸት ከመዋሸት ይታቀባሉ፡፡
ማንም የዚያ አብዮት ቡችላ ሁላ እየተነሳ የራስ መስፍንንና ምርጥ አርበኞቻችንን እና አባቶቻችንን ስም እያነሳ አፉን የሚከፍተው ምርጥ አርበኛና ለንጉሰ ነገስታቸው ስለዚህም ለሃገራቸው ታማኝ በመሆናቸውና በወስጠ ታዋቂ ደግሞ አማራ በመሆናቸው ነው፡፡ ራስ መስፍንን ማዋረድ በእግረ መንገድ የኢትዮጵያን አርበኞች በሙሉ ማዋረድ በመሆኑ ሌሎችም ክፍሉ ታደሰን ጨምሮ በመጽሃፍ ጭምር ‹ መሬትዎ ይወሰዳል ሲባል ሮጠው መጥተው እጅ ሰጡ › ብሎ ውሸት የጻፈው፡፡ ሀቁ ግን ራስ መስፍን ከአዲስ አበባም አልወጡ፣ የሄዱትም ጃንሆይ ስላስገደዷቸው ልጃቸው እየነዳ ታችኛው የጃንሆይ ቤተ መንግስት ነው፡፡ ልዑል አስፋወሰን አስራተ ካሳ እንዳሉት ታላላቆቹ የንጉሱ ባለስልጣናትና ወታደራዊ አዛዞች እስከመጨረሻው ድረስ ለንጉሰ ነገስታቸው ታዛዥ በመሆናቸው ነው ለእስር በቅተው የተፈጁት እንጂ የበታች መኮንኖቹ ደርጎች ችሎታም ሆነ እውቀት በልጠዋቸው አይደለም፡፡ በመጨረሻም የወሬው ቱቦ ተመችቶኛል ብላችሁ የምታናፉ የአብዮቱ ሶስት ቡችላዎች ተከታዮች ሁሉ እና አብዩም ሆነ ተቦርነ አርሲን የሚያህል መሬት ነበራቸው እያላችሁ አርሲን የሚያህል ውሸት አትዋሹ ታሪክን መጀመሪያ መርምሩ፡፡