>
9:19 pm - Wednesday February 8, 2023

ኖርዌይ ኦስሎ:- ታላቅ የስላማዊ ስልፍ ጥሪ !

Demonstration in Norway Oslo 18-12-2015ሰሞኑን በሃገራችን የተለያዩ ግዛቶች በኢትዮጵያዉያን ላይ እየደርሰ ያለዉ ጥቃት ከመቼዉም ጊዜ በላይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሶአል።ሕዝባችን ይኸዉ ከወያኔ የሚደርስበትን ጥቃት በመቋቋም ተቃዉሞዉንና አልገዛም ባይነቱን በገሃድ በተለይ በመላዉ ኦሮሚያና በጎንደር የተለያዩ ወረዳዎች እያሳየ ይገኛል።
ይህ የወገኖቻችን የአልገዛም ባይነትና የዲሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብት ጥያቄዎችን ህወሃት/ወያኔ በተለመደዉ የእብሪተኛ ድርጊቱ የሕዝቡን ድምጽ ለማፈን ተማሪዎች በሚማሩበት የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤቶችና ዩንቨርስቲዎች ድረስ ዘልቆ በመግባት በመግደል፤በመደብደብና በማሰር የሕዝቡን ቁጣና ብሶት በሃይል ለማፈን ቢሞክርም ዉጤት ሳያገኝ ማፈን ከማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሶአል።ተቃዉሞዉም ከእለት ወደ እለት እየተባባሰ የሄደ ሲሆን የወያኔም ጥቃት ከእለተ ወደ እለት አስከፊ ደረጃ ላይ እየደረሰ ይገኛል።
የአዲስ አበባን ከተማን ለማስፋት በሚል ህወሃት/ወያኔ ድብቅ አጀንዳዉን ከአንድ ዓመት በፊት ባቀደዉ የማስተር ፕላን በርካታ ወገኖቻችን ለሞት፤ እንግልትና እስር ምክንያት በመሆን ሂደቱ ቢጠናቀቅም በእብሪት የተሞሉት የህወሃ/ወያኔ ዘረኛ ቡድን እናስተዳድርሃለን በሚሉትና በኢትዮጵያ ሕዝብ ይሁንታ ነዉ የተመረጥነዉ የሚለዉን ሕዝብ ምርጫዉ ባለቀ ማግስት የዘረኛ መሪዎቹ ቁንጮ በማን አለብኝነት ማስተር ፕላኑን የሚቃወሙትን ልክ እናስገባችኋለን በማለት በአደባባይ ለሕዝባችን ያላቸዉን ጥላቻና ንቀት በግልጽ አሳይተዋል።
እብሪተኛዉ የህወሃት/ወያኔ ቡድን ይህን ማስተር ፕላን የሚለዉን እቅድ ከመነሻዉ የቀደዉና የነደፈዉ እዉነት የከተማዋ መስፋት አስፈላጊነት ለሕዝቡ የሚሰጠዉ ጥቅምና ጉዳቱ ሕዝብ ተወያይቶበትና መክሮበት ሳይሆን በሙስናና ብልሹ አሰራር ለተዘፈቁት የህወሃት ሹመኞችና የእነሱ ቡችሎች በከተማዋ በሕገወጥ መንገድ ከያዙት ንብረት በተጨማሪ ሌላ ንብረት ለማስገኘት ሆን ተብሎ ታስቦ የተሸረበ ድብቅ ሴራ እንደሆነ ድርጅታችን ያምናል። ህወሃት/ወያኔ ትላንት በአቃቂ በሚገኙት የአቡ ጨፌ፤ገላን፤ቂሊንጦና ቀርሳ እንዲሁም በቦሌ ቡልቡላ የረር በርና ጎላ ሰፈር የነበሩትን ወገኖቻችንን በማፈናቀል የፈጸሙት በደልና የዘር ማጥፋት ድርጊት ቁስላችን ሳይሽር በድጋሚ ይህንኑ ለመፈጸም የሚደረገዉን ሕገ ወጥ ድርጊት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በፅኑ ሊያወግዘዉ ይገባል።
በሌላ በኩል በዘረኛነትና የተለከፈዉ ሥልጣን በሃይል የያዘዉ የህዋሃት/ወያኔ ቡድን በሕግ ጥላ ስር በጎንደር እስር ቤት ታስረዉ በሚገኙ ወገኖቻችን ላይ በእስር ቤቱ ላይ በተነሳዉ የእሳት ቃጠሎ እስረኛዉ የታሰረበትን ክፍል በመቆለፍ በእሳት ያስፈጃቸዉ ሲሆን ከእስር ቤቱ ሕይወታቸዉን ለማትረፍ የሚወጡ እስረኞችን ዙሪያዉን ከቦ በጥይት ፈጅቷቸዋል። ይህ የወያኔ ድርጊት በሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ወቅት ፋሺስቶች እንኳን ያልፈጸሙትን ይህ ዘረኛ ቡድን በወገኖቻችን ላይ ይህን አሰቃቂና የጭካኔ ድርጊት ፈጽሞአል።
ህወሃት/ወያኔ በዉልደቱ ጊዜ የነበረዉን በመርዝ የተለወሰ ጥላቻ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዉያን ላይ ከመቼዉም ጊዜ በላይ እየረጨ የሚገኝ ሲሆን ይህ እኩይ ቡድን ሃገሪቷን ለመገነጣጠልና ታላቋን ትግራይ ለመመስረት ያለዉን የቀን ቅዠት ለመፈጸ ሲል የመጨረሻዉን ካርድ በመሳብ በወልቃይትና ጠገዴ ሕዝብ ላይ ጦርነት የከፈተና የቅማንትን የማንነት ጥያቄ አስከትሎ ግዙፍና ለም የሆነዉን የሃገሪቷን ዳር ድንበር ለባዕዳን/ለሱዳን አሳልፎ ለመስጠ ዝግጅቱን አጠናቆ በዚህ በያዝነዉ ወር ለማስረከብ ቃል ገብቷል።የሃገራችን ዳር ድንበር ጉዳይ እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ሊያሳስበዉና ሊያስጨንቀዉ የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ድርጅታችን ያምናል።
ዉድ ኢትዮጵያዉያን ዛሬ በኦሮሚያ በአማራና በተለያዩ የሃገሪቷ ክልሎች በህወሃት/ወያኔ የሚፈጸምብንን ጭካኔ የተሞላበት እኩይ ድርጊት በጋራ ልንቃወመዉና ልናወግዘዉ የሚገባንና የተደገሰልንን ሃገርንና ሕዝብን የማፈራረስና የመበታተን አደጋ ማስወገድ የምንችለዉ ሆ!ብለን በአንድነት መነሳት ስንችል ብቻ ነዉ።በኦሮሞዉ ላይ የሚፈጸመዉ የእስር፤ድብደባና እንግልት አማራዉን፤ትግሬዉን ፤ከንባታዉን፤ ሐረሪዉን፤ጋንቤላዉን፤ወላይታዉን የሚመለከት ሲሆን እንዲሁም በአማራዉና በሌሎቹ ብሄረሰቦች ላይ የሚደርሰዉ ጥቃት የእኔም ጥቃት ነዉ በሚል በአንድነት መነሳት ያለብንና የተደቀነብንን ጥቃት በጋራ መመከቻዉ ጊዜ አሁን ነዉ ብሎ ድርጅታችን በጽኑ ያምናል።
የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊያን ችግር ህወሃት/ወያኔ ሲወገድ ችግሩም አብሮ እንደሚወገድና አንድነታችን ቀድሞ ወደነበረዉ ቦታ የሚመለሰዉና የቀደመዉ ገናና ስማችንና እኛነታችን እንዲሁም አንድነታችንን የምናስመልስበት ጊዜዉ እሩቅ እንደማይሆን ድርጅታችን ዲሞክራሲያዊ ለዉጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ሰጪ ድርጅት በኖርዌይ እምነቱ የጸና ሲሆን ይኸዉ ህልማችን እዉን ይሆን ዘንድ ሁሉም ብሄር በአንድነት መቆምና መተባበር ጊዜ የሚጠይቀዉ ሃገራዊ ጥሪ ነዉ።
ስለዚህ ኢትዮጵያዉያን በሃገራቸዉ ዳር ድንበርና በመላዉ ሕዝባችን ላይ የሚቃጣዉን ማናቸዉም ጥቃት በጋራ መክቶና ተከላክሎ ጠላትን አሳፍሮ አንገት በማስደፋት መመለስ የሚችል ሕዝብ መሆኑን ታሪኩ የሚያስተምረን ሲሆን ይህን የትላንቱን አንድነታችንን በበለጠ በማጠናከር የሃገራችንንና የሕዝቦቿን ጠላት የሆነዉን ወያኔን ለማስወገድ የሚደረገዉን ትግል አጠናክረን እንድንቀጥልና ትግሉን በመቀላቀል የሃገራችንን ትንሳኤ እዉን ይሆን ዘንድ ድርጅታችን ጥሪዉን ያቀርባል።
ወያኔ በማስወገድ የሃገራችንን አንድነትና ዳር ድንበር እናስከብር!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!
Filed in: Amharic