>
5:13 pm - Sunday April 20, 3541

የሄነከን ቢራ ዘረፋ ምስጢር በኢትዮጵያ ሲጋለጥ [ክንፉ አሰፋ]

ቢራ ዘረፋ ምስጢር - Kinfu Assefaየሆላንድ ዜምብላ[1] ጋዜጠኞች የኦሮሞ ጸሃፊው የሆነውን ያሶ ካባባን ይዘው ወደ ጊንጪ ያመራሉ። እግረመንገድ ላይ የሚያገኟቸው ገበሬዎችም ሲጠይቋቸው በምስሉ ይታያል። እነዚያ በቀያቸው ማረፍያ እንኳን የሌላቸው ገበሬዎች የጋዜጠኞቹን መኪና ከብበው እንዲህ ሲሉ ይደመጣሉ። “መሬታችንን ቀምተው ለነጮች ሰጡብን። እኛንም በታተኑን…”

በገዛ ቀያቸው ስደተኛ የሆኑ እነዚህ ወገኖቻቸን ሰቆቃቸው የከፋ ነበር። በመጨረሻ ተሰባሰቡና መከሩ። ሰባት ሺህ የሚሆኑ የጊንጪ ተወላጆች ሆ! ብለው ወጥተው ይህንን የሁለት ሚሊዮን ዩሮ (ሃምሳ ሚልዮን ብር) ንብረት በሰኮንዶች ውስጥ አወደሙት። ምስላቸውን ለካሜራ ሳይደብቁ፣ ስሜታቸውን እና የወደፊት እቅዳቸውን ይናገራሉ። “ከአንባገነን መንግስት ጋር አብሮ ከመስራት ይልቅ የአካባቢው ነዋሪዎች ሊጠቀሙ በሚችሉበት መንገድ መስራት እንደሚችሉም።” ለፈረንጆቹ ይመክራሉ። “ይህ ካልሆነ ግን ማውደሙን እንቀጥልበታለን!” ሲሉ አስጠንቅቀዋል። ይህ ማስጠንቀቅያ ግዙፉ አለም አቀፍ ኩባንያ የሆነው ሄነከን ቢራንም ይመለከታል።

ባለፈው ሳምንት በሆላንድ ብሄራዊ ቴለቭዥን የተላለፈው ዜምብላ ፕሮግራም የሚሊዮኖችን ቀልብ ስቧል። ለዚህም ምክንያቶች አሉት። አንደኛው ምክንያት፤ የዜምብላ ፕሮግራም በምርመራ ጋዜጠኞች የሚሰራ በመሆኑ እጅግ የሚፈራ እና በሃገሪቱ ፖለቲካ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ማሳደሩ ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ በኢትዮጵያ እየወደመ ያለው ይህ ንብረት የተቋቋመው በሆላንድ መንግስት ድጎማ ሲሆን፣ ይህ ደግሞ የእያንዳንዱ ሆላንዳዊ ግብር ከፋይ ገንዘብ በመሆኑ ነው።

የሆላንድ የልማትና ትብብር ሚንስተር ለድሃ ሀገሮች እርዳታ ከመለገስ ይልቅ ወደ ንግድ ድጎማ ፊቱን ባዞረ ግዜ፣ 130 አትራፊ የንግድ ድርጅቶች ድጎማ እየተቀበሉ ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል። ከነዚህ ውስጥ ትልቁን የድጎማ ድርሻ የወሰደው ሄነከን ቢራ ነው። ሄነከን ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ የሆላንድ መንግስት አንድ ቢሊየን ዩሮ ድጎማ አድርጓል። እንደ ሆላንድ መንግስት እሳቤ፣ ይህንን የልማት ትብብር ገንዘብ በእርዳታ መልክ ከመስጠት ይልቅ ይህንን አትራፊ ተቋም አበራትቶ ስራ በመፍጠር እና በንግድና በስራ ታክስ ሃገሪቱ ተጠቃሚ እንድትሆን ማድረግ ነበር። የሆነው ግን በተቃራኒ ነው።

የዜምብላ ቴሌቭዥን ዘገባ ያጋለጠው ጉዳይ በእጅጉ ያስደምማል። እንዲህ ነው የሆነው። እ.ኤ.አ. በ 2011 ሄነከን ወደ ኢትዮጵያ እንደገባ የቢራ ስራ አዋጭ መሆኑን ስለተገነዘበ ስመ ጥሮቹን በደሌ እና ሃረር ቢራን ገዛቸው። ስራውንም በእጅጉ አስፋፋ። በአኢትዮጵያ የቢራ ተጠቃሚዎች ቁጥር በእጥፍ እንዳደገም ዘገባው አስምሮበታል። ትርፉም እንደዚያው አደገ።

በደሌ ቢራ ከመሸጡ በፊት አንድ ነጥብ አምስት ሚሊየን ዩሮ ግብር ይከፍል ነበር። ሄነከን ከገዛው በኋላ ግን የከፈለው ዘጠኝ መቶ ሺህ ዩሮ ብቻ ነው። አንድ ሚሊየን ዩሮ ግብር ይከፍል የነበረው ሃረር ቢራም አሁን ሁለት መቶ ሃምሳ ሺህ ዩሮ ብቻ ነው ያስገባው። ትርፉ ከእጥፍ በላይ እያደገ፣ ግብሩ ከእጥፍ በላይ የመቀነሱ ምስጢር ምን ይሆን?

የግብር ማጭበርበር ጥቆማ የደረሳቸው እነዚህ ጋዜጠኞች ጉዳዩን ለማጣራት ወደ ንግድ ሚንስትር ሄዱ። ምኒስትሩ በዚህ የማጣራት ጉዳይ ላይ ሊተባባራቸው ፈቃደኛ አልነበረም። ከዚያም ወደ ጉምሩክ እና ቀረጥ ቢሮ አመሩ። እዚያም ምንም መረጃ እንሰጥም ይሏቸዋል። ምስጢሩን ለማውጣት የጓጉት እነዚህ ጋዜጠኖች ተስፋ አልቆረጡም። በመጨረሻ ወደ ንግድ ምክር ቤት አመሩ። የዚያ ባለስልጣን የሰጧቸው ምላሽ የሚያስቅ ነው። “የንግድና ትርፍ ዘገባ አይደርሰንም።” አሉ። ታዲያ ንግድ ምክር ቤት ይህንን ካልመዘገበ ምን ይሆን የሚሰራው?

የንግድና የስራ ግብር መቀነሱ ብቻ አይደለም። ቀድሞ በሃረር እና በበደሌ ቢራ ቋሚ ሰራተኛ የነበሩ 699 (44%) ሰራተኞችም ከሄነከን ቢራ ተቀንሰዋል። የሆላንድ መንግስት ስራ ፍጠሩ ብሎ ድጎማ ሲያደርግ፣ ይልቁንም ነባሩን ሰራተኛ ከስራው አፈናቀሉት።

በኢትዮጵያ የሄነከን ተወካይ ሆላንዳዊ ነው። የዜምብላ ጋዜጠኖች የዚህን እንቆቅልሽ ለመፍታት እሱን ማፋጠጥ ይችላሉ። ስለዚህም ወደሱ አመሩ። የገቢና ወጪ ዘገባውን እንዲሰጣቸው ጠየቁት። እንቢ እንዳይል ቸገረው። ምክንያቱም በዚያ ዘገባ የሆላንድ መንግስት የድጎማ ገንዘብ ሰላለበት። እሺ ብሎ ይፋ እንዳያደርገው ደግሞ ምስጢሩ ለህዝብ ሊወጣ ነው። እሱም አለ። “የፋይናንስ ሪፖርቱን እሰጣችኋለሁ። እናንተ ግን ለህዝብ ይፋ እንደማታደርጉት ቃል ግቡልኝ።”

ዘገባውን በእጃቸው ያስገቡት እነዚህ ጋዜጠኖች፣ ዶክመንቱን አለም አቀፉ የገንዘብ ተቁዋም አማካሪዎች ጋ ይዘውት ሄዱ። የ አይ. ኤም. ኤፍ. ባለሙያው ወረቀቱን እንዳየ ምስጢሩን ለማወቅ ሰከንዶች አልፈጁበትም። የኢትዮጵያ ህዝብ በታክስ ተዘርፏል። ሰራተኛውም ወገን ከስራው እንዲፈናቀል ተደርጓል።

የመንግስት ባለስልጣን ሃገር ሲዘረፍ እና ወገን ከስራ ሲፈናቀል፣ ጉዳዩን ማፈን መርጠዋል። ምክንያት ቢኖራቸው እንጂ ይህን መረጃ መስጠት ሀገርን የሚጠቅም ነበር። በእርግጥ ይህ የግብር ማጭበርበር ተግባር እነሱ ሳያውቁት ሊሆን አይችልም። “የአባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ!” ነው ነገሩ። እንዲህ እየተዘረፈ ኢኮኖሚው እንዴት ነው በ 11 በመቶ የሚያድገው?

እንግዲህ ይህ በኢትዮጵያ ከዘመቱት 130 የሆላድ የንግድ ድርጅቶች አንዱ ታሪክ ነው። ገቢውና ወጭው በግልጽ የሚታይ፣ ግዙፍ እና አለም አቀፍ ድርጅት። ሄነከን ከገዥው ፓርቲ ባለስልጣናት ጋር በመመሳጠር ይህንን ያህል ከዘረፈ የሌሎቹ – የማይታወቁት ምን ያህ ይሆን?

የቀድሞው የሆላንድ ልማትና ትብብር ሚንስቴር የነበሩት ጃን ፕሮንክ፣ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ከልማት እና እደገት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት ለሌላቸው የንግድ ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ ማድረግን ክፉኛ ይወቅሳሉ። በተለይ መንግስታቸው በልማትና ትብብር ስም፣ በብሄራው ጥቅም ስም የስብአዊ መብት ረገጣን ችላ ማለቱን ያወግዛሉ።

በልማት ስም በሚሊዮኖች እየፈሰሰ ያለው የሆላንድ ግብር ከፋዮች ገንዘብ በኢትዮጵያ ስራ አልፈጠረም። እንደውም ሰራተኞችን አፈናቀለ። ሀገሪቱን በበለጠ የስራና የንግድ ግብር ተጠቃሚ ያደርጋል ይባል እንጂ ግብሩ በ 70 እጅ ያነሰ ሆኗል። ከሁሉም በላይ ደግሞ የገበሬው መሬት እየተነጠቀ ለነዚህ ዘራፊዎች መሰጠቱ የህዝብ ቁጣን አስነስቷል።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት እየተካሄደ ያለው ህዝባዊ አመጽ የገዥው ፓርቲ ችግር ብቻ ሳይሆን የሆላንድም ችግር መሆኑን በመግለጽ ዜምብላ ዘገባውን ይደመድማል።

[1] http://zembla.vara.nl/seizoenen/2016/afleveringen/23-03-2016

 

Filed in: Amharic