አንዳንድ ነገሮች (ከአቢይ አፈወርቅ) May 9, 2014 አንዳንድ ነገሮች ፣ . . . ዕጹብ ድንቅ ናቸው ፦ እንደ ንጋት ጸሀይ ፣ መንፈስ የሚያሞቁ ፤ እንደ አመሻሽ ጀምበር ፣ ውበት የሚያፈልቁ ፤ የልብ የሚያደርሱ ፣ ለነፍስ የቀረቡ ፤ ከኮተኮቷቸው ፣ ሁሌም የሚያብቡ። አንዳንድ ነገሮች ፣ . . . ግዙፍ እልፍኝ ናቸው ፦ ሁሉን ያካተቱ ፣ ከባህር የሰፉ ፤ ሁሉ የኔ ‘ሚላቸው ፣ በፍቅር የፋፉ ፤ ውብና ፀዓዳ ፣ ልዩ አዳራሽ ናቸው ፤ እልፍኝ አስካልካዩ ፣ ካላጠበባቸው ። አንዳንድ ነገሮች ፣ . . . ልዩ ፍቅር ናቸው ፦ እንደ ዓይን ብሌን ፣ እንደ ህጻን ገላ ፤ ወድቆ እንደሚሰበር ፣ እንደልዩ ሸክላ ፤ የሚሳሳላቸው ፣ ለትልቅ ትንሹ ፤ ሁነኛ ተመልካች ፣ ተሟጋች የሚሹ። ጉድፍ አራጋፊ ፣ ቢያጠፉ መካሪ ፤ የምር ካገኙ ፣ ዓይን ከፍቶ አፍቃሪ ፤ አንዳንድ ነገሮች ፣ ሁሌም ህያው ናቸው ፤ ማደግ ማበብ እንጂ ፣ ሞት የማያውቃቸው:: አንዳንድ ነገሮች ፣ . . . መገበዝ አያውቁም ፦ ቢያጠፉ እንዳላየ ፣ ቢስቱ እንዳልሰማ ፤ በዝምታ አርጩሜ ፣ በ‹ዕውር ፍቅር› ሳማ ፤ ክቦ ከሚያሳንስ ፣ እልፍ ስሜተኛ ፤ ፍቅር ይደረጃል ፣ በአስር ዕውነተኛ።