>
7:31 pm - Tuesday January 31, 2023

ህገ ወጥ ጦር መሳሪያ ማዘዋወር ክስ ….. ከዚያስ? [ግርማ ሰይፉ ማሩ]

Ato Girma Seifu Maruነሐሴ 30 2008 የዓመቱ ማለቂያ ብቻ ሳይሆን የመንግሰት ሹሞች በቴሌቪዝን የሚደሰኩሩትን መልካም አስተዳደር ብሎ ነገር ጫፍ ለማስያዝ እንኳን አቅም እንደሌላቸው አስመስክረዋል፡፡ ፈይሳ ለሊሳ ማራቶን ሮጦ ሁለተኛ ሲወጣ ከሀብታሙ አያሌው ጋር አብረን እያየን ነበር፡፡ ከወርቅ በላይ ያስደሰተኝ ግፋችንን ለዓለም ማሳየቱ ነበር፡፡ ቀደምኩሁ የሚለኝ ካልተገኘ በስተቀር ሰደስታዬን በመግለፅ አንደኛ ነበርኩ፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ እንደሌሎቹ ፎቶ መለጠፍ ሳያስፈልገኝ ወሬውን ብቻ ነበር የለጠፍኩት፡፡ ዛሬ ጠዋት ደግሞ በኢሳት እንዴት ልቡ እንደራሰ ፍስሃ ተገኝ ሲያስረዳ እየሰማው ደስታዬ እንደ አዲስ ሲሰማኝ ነበር፡፡ የዚህ ደስታ ዋናው ምንጭ ነሐሴ 29 ማታ እኔ ኤሊያስ እና ዳንኤል ሸበሺ ቀኑን ሙሉ በቂሊንጦ እሳት ጉዳይ ምንም መረጃ ባለመኖሩ ስንቃጠል ውለን ማታ ብሶታችንን ለመግለጽ በምሽት ፎቶ መነሳታቸን ሊሆን ይችላል፡፡ ይህን በማድረጋችን ግን እንዲህ ወርደው ይዋረዳሉ ብዬ አላሰብኩም፡፡

ነሐሴ 30 እንደ ወትሮ ከቤቴ በጠዋት አልወጣሁም ምክንያቱም የቤተሰብ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ነበር የፍስሐ ተገኝን ትንተና ከመቲ ጋር መስማት የቻልኩት፡፡ አርፍጄ ቢሮ ብገባም ቢሮ መብራት የለም፡፡ ሰለዚህ የፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴን “ የሀብተጊዮርጊስ – አባ መላን” መፅሃፍ ሳነብ ቆየው፡፡ መኪናዬን ጋራዥ ለማሳየት በዘጠኝ ሰዓት ቀጠሮ ስለአለኝ ወደዚያው ቀረብ ብዬ ምሳ ለመብላት መስቀል ፍላወር አካባቢ መኪናዬን ለአጣቢ ሰጥቼ ከጓደኞቼ ጋር ምሳ እየበላሁ እያለ ስልኬ ጮኽች መኪና አጣቢዬ ነበር፡፡ “መኪናዋ በፖሊስ ትፈለጋለች” አለኝ፡፡ ለምን? ስለው “ወንጅል ተሰርቶበታል” እያሉ ነው አለኝ፡፡ ጉዳዬን ስጨርስ እንደምመጣ ነገሬው በፌስ ቡክ ጉዳዩን ፖስት አደረኩ፡፡ ነገር ሊፈልጉኝ ካልሆነ እኔ ካልሆንኩ መኪና ወንጀል አይሰራም፡፡ እኔ ደግሞ እንኳን ከእነርሱ ጋር እየተጋፈጥኩ ተፈጥሮየም ወንጀል ይጠየፋል፡፡ መኪና አጣቢው መልሶ ደውሎ “የተሰረቀ መኪና ነው” አለኝ አለ፡፡ አሁን ነገሩ ፍንትው ብሎ ገባኝ፡፡ ትላንት ምሽት በቂሊንጦ ስለተፈጠረው ግፍ የተነሳነው እና ለህዝብ ይፋ ያደረግነው ፎቶ እንደሆነ፡፡

Elias Gebiru Girma Seifu Maru Daniel Shibeshiወደ መኪናዬ አመራው፣ ፖሊሶች ቆሻሻ እንዳገኘ ዝንብ ወረውታል፡፡ ከሩቅ ሲያዩኝ አንድ ግዳይ የጣሉ ይመስላሉ፡፡ ቀረብ ስል ፖሊሶቹ በዓይን ያውቁኛል “ለምን እንደሆነ አናውቅም ፖሊስ ጣቢያ መኪናው ከእነ አሽከርካሪው ይፈለጋሉ፡፡” አሉኝ፣ እንሂድ አልኳቸው መኪናዬ ውስጥ ሊገቡ ሲሉ እኔ መኪና ውስጥ አትገቡም አልኳቸው፡፡ በራሳቸው መኪና እንዲሄዱ እኔም መኪናዬን ይዤ እንደምሄድ ነገርኳቸው፣ መኪና ማምጣት አልቻሉም፡፡ በመጨረሻ መሄድ የሚፈልጉትን ፖሊሶች ስንት እንደሆኑ እና ምንም ያለመያዛቸውን አጣርቼ አስገባኋቸው፡፡ እግረ መንገዴንም ለምን እንደዚህ እንደአደረኩ፣ ወረቀት ይሁን የጦር መሳሪያ አስቀምጣችሁ መኪና ውስጥ አገኘሁ ብትሉስ አልኳቸው፡፡ ደነገጡ እንዴት እንዲህ ይደረጋል ብለው ምለው ተገዘቱ፡፡ ለማነኛውም ደህንነት ተብዬው የእነሱን ዩኒፎርም ለብሶ ይህን እንደሚሰራ አስረድቼ የቆምኩለት እና ማነኛውንም ዋጋ የምከፍልለትን ጉዳይ አጥብቄ አስረዳኋቸው፡፡ ላንቻ በሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ጥሩ እንክብካቤ ተደርጎልኝ እንደ አቅማቸው አስተናገዱኝ፡፡

ላንቻ ፖሊስ ጣቢያ ለአንድ ሰዓት ተኩል በቁጥጥር ስር ቆየው፡፡ በመጨረሻ በጠብ መንጃ ታጅቤ እኔ በሾፌርነት ልደታ ፖሊስ መምሪያ እንድሄድ ኮማነደር በጋሻው ለኮማንደር ወጋየሁ አስተላለፈኝ፡፡ ልደታ ፖሊስ መምሪያ ስደርስ ጉዳዬ ከትራፊክ አደጋ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ተነግሮኝ እንድጠብቅ ተነገረኝ፡፡ ችግሩ ቀላል መሆኑን ይህች ቂሊንጦ መታሰቢያ ፎቶ ቢያንስ በትራፊክ ወንጀል ልታስከስሰኝ መሆኑን ገመትኩ፣ ፖሊሶች ከዚህ እዚያ ይሯሯጣሉ፣ ድንገት እኔ ያለሁበት ክፍል ውስጥ አንድ ሰው ተደውሎልኝ ነው ብሎ ገባ፡፡ ተከታትለው ሌሎችም ሰዎች መጡ፡፡ ነገሩ በደንብ ገባኝ፡፡ እነዚህ ሰዎች በእኔ ላይ ምስክር ሊሆኑ እንደመጡ ተረዳሁ፡፡ በዓይነ ቁራኛ ተከታተልኳቸው፡፡ ዓይኔን ማየት አፈሩ፡፡ ፖሊሶች በተለያየ ጊዜ ይመጡና ሙሉ ስሜን ይጠይቁኝና ሄደው ለአንድ ሲቪል ለለበሰ ደህንነት ሰራተኛ ይነገሩታል እርግጠኛ ነኝ ሰሜ ያስጠኗቸውል፡፡ በመጨረሻ ትራፊክ ጉዳይ መሆኑ ተቀየረ እና ሁከት መፍጠር የሚል መሆኑ ተነገረኝ እና ቃሌን እንድሰጥ ጥያቄ ሲቀርብ ፈቃደኛ እንዳልሆንኩ ገልጬ መርማሪዎቼ ፋይሌን ይዘው ወደ ኮማንደር ቢሮ ሄዱ፡፡ ከጥቂት ቆይታ በኃላ ተመልስው ጉዳያቸውን ከባድ ስለሆነ በሚል ለውይይት ወደ መመሪያው ሃለፊ ኮማንደር ወጋየሁ ጋር ቀረብኩ፡፡ አስገራሚው ነገር በፍፁም አግኝቼው የማላውቀው የእህቴ ባለቤት አብሮኝ ተከሳሸ ሆኖ አገኘሁት፡፡ የመጣው ግርማ ታሰረ ሲሉት ባለቤቱን ተከትሎ ነው፡፡ በቃ ተከሳሽ ሆነ፡፡ ክሱ ደግሞ ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር/መያዝ ሆኖ ደረጃውን አሳደገ፡፡ እነ ዶክተር ታዬ፣ ፕሮፌሰር አስራት በዓይነ ህሊናዬ መጡ፡፡ በሄድኩበት መስመር የሞተ ወይም የተገጨ ስው ሳይገኝ ሲቀር፣ ሁከት ፈጠራ ሲያንስባቸው ለማስፈራሪያ ከፍ ያለ ነገር የተገኘው “ህግ ወጥ መሳሪያ ዝውውር ሆኖ” በደህንነት ትዕዛዝ ተሰጥቶዋል ማለት ነው፡፡ በነገራችን ላይ ክስ ሲመሰረትብኝ ምስክር ሆነው የቀረቡ ሶሰት አዳፍኔዎች መጥተዋል፡፡ ግምቴ ልክ ነበር አስተኳሽ የሚባሉት ቀርበው መስክረዋል፡፡ አንፀባራቂ የፓርኪን ልብስ ለብሰው ከእኛ ቲፕ እየተቀበሉ ሆዳቸውን ይሞላሉ፤ እኛ ላይ በሀስት ምስክር የሚሆኑት ደግሞ እነዚሁ ዜጎች ናቸው፡፡ እነዚህ ከመሆን መሞት በስንት ክብሩ እንደሚሻል ማን ይንገራቸው፡፡ አንደ እናቱን ያስቸገረ ልጅ እናቱን “እኔ መቼ ነው ሰው የምሆነው?” ቢላቸው “ሰትሞት” አሉት፡፡ ሲሞት ሰው ሞተ ተብሎ ዕድር ሰለሚቀብረው፡፡ እነዚህን ሰዎች ከመሆን ሞተው የሰፈራቸው ዕድር ሰው ሞተ ቢላቸው ይሻላቸው ነበር፡፡ እነዚሁ ሰዎች የእኔን መታሰረ ስምተው የመጡ ቤተሰቦቼን አዩኝ፣ ፎቶ አነሱኝ፣ ወዘተ እያሉ ለፖሊሶች ያቀርባሉ፡፡ ፖሊሶቹም እነርሱ የሚሉትን ያዳምጣሉ፡፡ መሞት ይሻላል፡፡
ለማነኛውም ከኮማንደር ወጋየሁ እና የስራ ባልደረቦቹ ጋር በነበረን ውይይት እኔ ነፃነቴን ከማንም የማልጠብቅ ዜጋ መሆኔን አስረዳኋቸው፣ በቂሊንጦ በተፈጠረው እሳት መንግሰት በእጁ ያሉትን እስረኞች ቆጥሮ አደጋ የደረሰባቸውን ሰዎች ለህዝብ አለማሳወቁ መንግሰት ተጠያቂ እንደሆነ እና ኃላፊነት የማይሰማው መንግሰት እንደሆነ ለማስረዳት እጄን አጣምሬ ይህን ግፍ ለመግለፅ እና በዚህ ጉዳት ለደረሰባቸው ጉዳት አጋርነቴን ለመግለፅ ይህን ማድረጌ እንደ ወንጀል እንደተቆጠረ ይህን ደግሞ መቼም የማደርገው እና ከማንም ለዚህ ፈቃድ እንደማልጠይቅ አስረድቻቸው ተለያይተናል፡፡ ለጥቂት ደቂቃዎች ለብቻቸው ካደረጉት ውይይት በኋላ በዋስ እንድለቀቅ ከምሸቱ 3፡00 ሠዓት መወሰኑን ተነግሮኝ በማግስቱ ከጠዋቱ በ4፡00 ሰዓት እንድገኝ አብሮኝ መናጆ ከሆነው የእሀቴ ባለቤት ጋር ተለቀናል፡፡ ከጥናቱ ላይ ተነስቶ ተደናግጦ የመጣው መናጆዬ ነገ ፈተና አለበት፡፡ ፈተናው ላይ የሚፈጠርበት ጫና ምን እንደሚሆን አላውቅም፡፡ ለማነኛውም እኔ ወድጄ በማደርገው እርሱ ዳፋ መግባቱ አሳዝኖኛል፡፡

ኢትዮጵያችን እንዲህ ነች መሰዋዕትነት ልንከፍል መዘጋጀታችንን ዋጋ የማይሰጡ ህግ አስከባሪዎች፣ መብታችንን ወንጅል ለማድረግ ምስክር የሚሆኑ ሆድ አደሮች፣ ሶሰት ሺ አምስት መቶ የሚጠጉ እሰረኞች በምን ሁኔታ እንዳሉ የማያውቁ የእስረኛ ቤተሰቦች ሰሜት የማይረዱ የመንግሰት ሾሞች እና ለዚህ ምንም ግድ የማይሰጣቸው ሰዎች፣ ወዘተ … በተቃራኒው ደግሞ ኮሽ ሲል የትግል አጋርነታችውን የሚገልፁ ጥቂትም ቢሆኑ ምርጦች አቅፋ በአንባገነን ስርዓት መዳፍ ውስጥ የምትገኝ ሀገር፡፡ ሆ ኢትዮጵያ ሆይ ይህንን ግፍ መዝግቢው ……

Filed in: Amharic