>

የሁለት እስረኞች ወግ! [በፈቃዱ ዘ ኃይሉ]

የሁለት እስረኞች ወግ! Befeqadu Z Hailuአዋቂው፣ ዕውቁ እና ተወዳጁ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና ትሁቱ እና ሠላማዊው ፖለቲከኛ አንዱዓለም አራጌን በአካል ያየኋቸው በ2003 መጨረሻ በአንድነት ፓርቲ በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ ነበር። ያኔ በጋራ የምንጦምርበትና ለእስር የዳረገን ዞን ዘጠኝ አልተመሠረተም ነበር። ነገር ግን ጓደኞቼ እና ባልደረቦቼ Soleyana እና Atnaf ሳንተዋወቅ በፊት እዚያ እንደነበሩ ኋላ ስናወራ ሰምቻለሁ። በርካታ ሰዎች በተገኙበት ያ ስብሰባ ላይ ዛሬ ዝዋይ ወኅኒ የተጣለው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝም ተገኝቶ ነበር። ያቺ ስብሰባ እስክንድር ጥናታዊ ንግግር ያቀረበባት ስብሰባ ነበረች። ጥናታዊ ንግግሩ እና ውይይቱ በጥቅሉ በእነአንዱዓለም አራጌ መዝገብ የተከሰሱት 24 ሰዎች ላይ ማስረጃ ሆኖ መጥቷል።

የእነአንዱዓለም አራጌ መዝገብ ብዙ ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኞች የተከሰሱበት መዝገብ ነው። የአዲስ ነገሮቹን ዐብይ ተክለማርያም እና መስፍን ነጋሽ ጨምሮ፣ ከእስክንድር ሌላ አምስት ጋዜጠኞች በዚህ መዝገብ ተፈርዶባቸዋል።

እስክንድርን እና አንዱዓለምን ከዚያ በኋላ ያገኘኋቸው እና የማናገር ዕድል የገጠመኝ ከታሰሩ በኋላ በቃሊቲ (እኔ ራሴ ከመታሰሬ በፊት) ነው። እስክንድር ነጋ ላይ በወቅቱ ለሕወሓት ወገንተኛ የሆኑ ጦማሪዎች ያልጻፈውን ጻፈ እያሉ ሥሙን ሲያጠፉ እውነቱ ምንድን ነው ልለው ነበር የሔድኩት። በኋላ በጥቂት ቀናት ንግግር ብቻ ነፍሴን በቀናነቱ አለመለማት። እስክንድር በጣም ሲመክረኝ ከነበሩ ነገሮች ውስጥ ነውጥ-አልባ (non violent) የትግል ስልት ላይ ፍፁማዊ እምነት እንዲኖረኝ እና ለምሠራቸው ሥራዎች በሙሉ ኃላፊነቱን ለመውሰድ እንድዘጋጅ ነበር። አድርጌዋለሁ/አደርገዋለሁ ብዬ አምናለሁ። ነውጥ-አልባ ፀረ-ጭቆና ትግሌ ይፋዊ የሆነበት እና ወደፊትም የሚሆንበት ምክንያት ለእርሱ ያለኝ አድናቆት እና ክብር የሚገለጽበት መንገድ ስለሆነ ነው።

አንዱዓለም አራጌንም ከዞን ዘጠኝ ባልደረቦቼ እና ሌሎችም ጋር እንጠይቀው ነበር። ስክን ያለ፣ ሃይማኖቱን አጥባቂ እና በመብቱ የማይደራደር ሰው ከገጠማችሁ – እሱ አንዷለም አራጌ ነው። አንዱዓለምን ልንጠይቀው መጀመሪያ የሔድን ግዜ፣ ስለእኛ ጠየቀንና “አዪዪ፣… ይሄ መንግሥት ያስራችኋል” አለን። ያለውም አልቀረ፣ በዓመት ከምናምኑ ታሰርን። አንዱዓለም ከታሰረ በኋላ ሁለት አስገራሚ መጽሐፎች ጽፏል። ‘ያልተሔደበት መንገድ’ እና ‘የሀገር ፍቅር ዕዳ’ የሚሉ ናቸው። መጽሐፍቱን ማንበቡ የአንዱዓለምን ሠላማዊነት እና ባለራዕይነት ማመን ለማይፈልጉት ሳይቀር ያሳምናል።

አንዱዓለም የሁለት ወንድ ልጆች አባት ነው። በአንደኛው መጽሐፉ መግቢያ ላይ እንዲህ ይላል፣ ‘በ1998 ስታሰር [ያኔ ትዳር አልያዘም ነበር] ሳልወልድ ታሰርኩ እያልኩ ሲቆጨኝ ነበር፤ ተፈትቼ አግብቼ ከወለድኩ በኋላ ደግሞ መልሼ ስታሰር የማላሳድጋቸውን ልጆች ወልጄ እያልኩ እቆጫለሁ’ በማለት ቁጭት የማይቀር መሆኑን እና እያንዳንዱ ባለራዕይ መስዋዕትነት እንደሚከፍል ይነግረናል።

Ethiopian mother Serkalem Fasil with her child Nafkotጋዜጠኛ እስክንድርም የአንድ ልጅ አባት ነው። ጓዳው የማይጎድልበት እስክንድር ብልጭልጭ ነገር ሳያሸንፈው ያለውን ሁሉ እውነትን ለጉልቤዎች በመናገር (speaking truth to power) አሳልፎ የሰጠ ሰው ነው። እስር ቤት የተወለደው የታላቁ እስክንድር አንድያ ልጁ ናፍቆት እስክንድር እና ጋዜጠኛ ባለቤቱ ሰርካለም ፋሲል አሁን ሁለቱም ለስደት ተዳርገዋል።

ለአዲስ ዓመት ከግፍ እስር የተፈታው ‘የሙስሊሞች ጉዳይ’ ጋዜጣ አዘጋጁ ጋዜጠኛ ዩሱፍ ጌታቸው ስለ እስክንድር ነጋ አውርቶ አይጠግብም። ቃሊቲ አብረው በታሰሩበት ወቅት የተመለከተውን ሲነግረኝ፣ “እንደሱ ሥነ ስርዓት ያለው ሰው የለም። ሁሉን በዕቅድ ይመራል። እስር ቤት ውስጥ ስፖርት የሚሠራበት፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያነብበት እና እያንዳንዱን ነገር የሚያደርግበት የማይዛነፍ ሰዓት አለው። ከፅዳት ሠራተኞቹ ጋር በሳምንት ሁለቴ ቤት ያፀዳል። ከሰዎች ጋር አብሮ የበላበትን ሰሀን የሚያጥበው እሱ ብቻ ነው…” ~ ሽብርተኛ ተብሎ የ18 ዓመት ፅኑ እስራት የተፈረደበት እስክንድር ነጋ።

እስክንድር ሌላ ቢዝነስ እየሠራ ወይም ተሰድዶ ‘የተደላደለ’ ኑሮ መኖር ሲችል፣ ስለእውነቱ እና እምነቱ የእኔ እና የእናንተን ዕዳ ደርቦ እየከፈለ ነው። አንዱዓለም ከዐሥር ዓመት በፊት በኢትዮጵያ የተከሰተ ድርቅን አስመልክቶ ለተጎዱ ወገኖች መንግሥት በአስቸኳይ እንዲደርስላቸው ሲል ብቻውን ሠላማዊ ሰልፍ የወጣ ዜጋ ነው። በቲፎዞ መኖር አለመኖር፣ ጥቅም ቀርቶ ያላቸውን በማጣት እና ባለማጣት የማይሸበሩት እኒህ ፍፁም ሠላማዊ የትግል አውራዎች የማይገባቸውን ፍርድ ተሸክመው በወኅኒ፣ በአስቀያሚ አያያዝ ተጥለው ይገኛሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው መንግሥት እነዚህ መሰሎቹን ንፁኃን ነፍሶች በማሰር እና በማሰቃየት የማይቀረውን ነውጥ እና መከፋፈል ሲጠራ ኖሯል። ዛሬ (ዘንድሮ) ለዚህ ሕያው ምስክር ነች።

ዛሬ፣ መስከረም 3, 2009 ሁለቱ ንፁኃን ከታሰሩ እነሆ አምስት ዓመታቸው።

Filed in: Amharic