>
5:13 pm - Monday April 20, 2865

ህወሃት ከ80ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን ያለቁበትን የባድመን ጉዳይ ለብቻው መምከሩ ቁጣ ቀሰቀሰ (በወንድወሰን ተክሉ)

የህወሃት ከፍተኛ አመራር አካል በመቀሌው ዝግ ስብሰባ በባድመ ጉዳይ ለብቻው መምከሩ ሀገራዊ ክህደት ነው ሲሉ ኢትዮጵያዊያን ተቃውሞዋቸውን አሰሙ።

የህወሃት ማእከላዊ ኮሚቴ በመቀሌው ዝግ ስብሰባ ላይ ድርጅቱ አጋጥሞታል ያለውን የህልውና አደጋ ለመከላከል ከነደፋቸውና ከመከረባቸው የመፍትሄ ሀሳቦች ውስጥ አንዱ ከኤርትራ ጋር ያለውን No war,No Peace ላይ ያለውን ግንኙነት ማሻሻል ነው የሚል ሲሆን ይህንን አላማውን እውን ለማድረግም ከ80ሺህ በላይ ህይወት ያለቀበትን የባድመን ጉዳይ ለኤርትራ በመስጠት ዙሪያ መምከሩን አፍሪካ ኢንተለጀንስ መዘገቡ ይታወቃል።
በዚህ  በህወሃት አመራር  ባድመን ሰጥቶ እርቅ ለመፍጠር በሚለው እቅድ ላይ በተደረገው የተናጠል ድርጅታዊ ምክክር ጉዳይ ያነጋገርናቸው ኢትዮጵያዊያን 〈በሀገርና በህዝብ መስዋእትነት ላይ የተቃጣ ክህደት ነው〉ሲሉ በጽኑ ኮንነውታል።

〈የባድመ ጦርነት መንስኤ የራሱ የህወሃት ሚዛናዊ ያልሆነው የውጭ ፖሊሲ ውጤት ሆኖ ሳለ በሻእቢያ ወረራ ተፈጸመብን ብሎ በወተወተበት ወቅት ትልቁን መስዋእትነት ከፍሎ የታደገው ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው ያሉን〉 ሲሆን አክለውም 〈ይህንን ሀገር አቀፍ ዋጋ ያስከፈለን ወሳኝ ጉዳይ እንደግል ጉዳዩ በመቁጠር በመንግስት ደረጃ ሳይሆን በፓርቲ ደረጃ ያውም ለድርጅታዊ ጥቅም ታስቦ ምክክር ማድረግ የኢትዮጵያን ህዝብ ከመናቅ የመነጨ ክህደት ነው〉ሲሉ አስመረውበታል።
አፍሪካን ኢንተለጀንስ ድረ-ገጽ የህወሃት ማእከላዊ ኮሚቴ በውጭ ጉዳይ ምኒስትሩ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ መሪነት ስር አምባሳደር ብርሃኔ ገ/ክርስቶስ፣ዶ/ር ተቀዳ ዓለሙ እና አቶ ሞገስን ባካተተ ኮሚቴ  የተዘጋጀ አዲስ የውጪ ፖሊሲ መረቀቁን የዘገበ ሲሆን በረቂቁ ላይም ህወሃት የባድመን መሬት ለኤርትራ በመስጠትና ብሎም በኢትዮጵያ ያሉትን የኤርትራ ተቃዋሚዎችን ማስታጠቅና ማሰልጠንን በማቆም የኤርትራን ወዳጅነት በመመለሱ አስፈላጊነት በረቂቁ ላይ መስፈሩን ዘግባል።

ከኤርትራ ጋር  በተካሄደው ጦርነት መክፈል የማይገባንን ታላቅ መስዋእትነትና  ዋጋን በህወሃት ጀብደኛና እንዝህላል ፖሊሲ መሰረት ከፍለናል የሚሉት ኢትዮጵያዊያን 〈ዛሬ ደግሞ ይህንን ታላቅ መስዋእትነት የከፈለውን ህዝብ ያላካተተ የመፍትሄ ሀሳብ ተብሎ በህወሃት ብቻ ለምክክር መቀርቡ ድርብ ክህደትና ወንጀል ነው〉 ሲሉ ይናገራሉ።
በመቀሌው የህወሃት ማእከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ እጅግ አከራካሪውና አነጋጋሪው አጀንዳ ተሰብሳቢው የህወሃት ማእከላዊ ኮሚቴ  ድርጅቱ ያጋጠመውን ድርጅታዊ መበስበስና መሰነጣጠቅ  እንዴት እንጠግን በሚል አጀንዳ  ላይ ሆኖ ሳለ እንደመፍትሄነት ያገለግላሉ ተብለው ለመወያያነት የቀርቡት ነጥቦችም ድርጅታዊ ቅርጽና ይዘት ያላቸው ተግባሮች መሆን ሲገባ ድርጅቱ ግን ሀገራዊ ጉዳይን ለድርጅታዊ ጥቅም ብሎ በተናጥል ሁኔታ ባድመን መስጠት ወይም አለመስጠት ብሎ መወያየቱ ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው ብለዋል።

ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉና በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የታሪክ ምሁር የሆኑ ምንጫችን እንዳሉት “የህወሃት በባድመ ጉዳይ በዝግ መምከሩ ድርጅቱ ከተዘፈቀበት የህልውና አደጋ አንጻር እንደመውጫ የሚያገለግሉትን ሁሉ በመሞከር አኳያ ያደረገውና  ያሰበው የሚጠበቅ ነው” ያሉ ሲሆን አክለውም “ለተጋፈጠው የህልውና አደጋ መውጪያ ብሎ የባድመን ጉዳይ በድርጅት መልክ ሊጠቀምበት መምከሩ ግን የፈራውን መፈራረስ የሚያፈጥንለት እንጂ የሚያስቀርለት አይደለም “ሲሉ ተናግረዋል።

ሌላው ምሁር ደግሞ “የህወሃት በባድመ ጉዳይ ለብቻው በዝግ ስብሰባ መምከሩ የታወቀበትን በትግራይ ህዝብ ላይ ብቻ የመመካትን አባዜውን ያሳየበት ነው “ብለዋል። እንደምሁሩ አገላለጽ ድርጅቱ ከትግራይ ህዝብ ጋር በጉዳዩ ላይ ከተስማማ ከተቀረው ክፍል የሚያሰጋኝ ተቃውሞ አያጋጥመኝም የሚልን ስሌት ይዝ ነው ሲሉ ይናገራሉ።

〈የባድመ ጉዳይ የትግራይ፣ወይም የህወሃት ጉዳይ ብቻ አይደለም〉 ያሉት እኚህ ምሁር 〈በባድመ ጉዳይ ትልቁን ዋጋ የከፈለው የኢትዮጵያ ህዝብ  ሲሆን ወሳኙ እና ብቸኛው  ባለቤትም  ህዝቡ ነው ብለዋል።

Filed in: Amharic