>

በኢትዮጵያ ስም ህወሓት ከሻዕቢያ ጋር የመጨረሻውን የጠቅላይ ጨዋታ ጀመረ (ኦባንግ ሜቶ)

* አውቀውትም ይሁን ሳያውቁት “የእምነት አባቶች” የክህደቱ ተዋንያን ናቸው
ኦባንግ ሜቶ

“… ይህ ዜና በተገለበ መልኩ መሰማት ከጀመረ ሰነባብቷል። ዜናው በደባና በተቀነባበረ ሤራ የሚካሄድ ቢሆንም ዜናውን በገደምዳሜ የሚያሰራጩት ክፍሎች ስለ ጉዳዩ የተጨነቁ አይመስሉም። ቅርብ ሆኜ እንደምከታተለው ይህ ዜና አደገኛና ኢትዮጵያን ዳግም ክህደት የሚያከናንባት፤ እንደ አገር የመኖር ኅልውናዋን አደጋ ላይ የሚጥል ነው። ይህንን የሚያውቁ የሃይማኖት አባት መስቀል ተሸክመው የዚህ ሸፍጥ ተዋንያንና አስፈጻሚ መሆናቸው ያሳፍራል። ጉዳዩ በአጭሩ ህወሓት ከሻዕቢያ ጋር በኢትዮጵያ ስም ሊታረቅ ዓለምአቀፍ ዕውቅና የተሰጠው ድርድር መጀመሩ ነው…”

ይህ አጭር ሃሳብ ለጎልጉል ከተላከ የውስጥ አዋቂ ደብዳቤ የተቀነጨበ ነው። ደብዳቤውን የላኩት ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ በኢህአዴግ ውስጥ ከፍተኛ የሚባል ኃላፊነት ያላቸውና ኃይለማርያም ደሳለኝ በሚመራው የህወሓት ድቃይ ፓርቲ ውስጥ ቁልፍ ሚና የሚጫወቱ የደቡብ ክልል ተወላጅ ናቸው።

ሃሳቡ ሙሉውን የሚያተኩረው “ኤርትራና ኢትዮጵያን ለማስማማት” በሚል የተጀመረው የሃይማኖት መሪዎች የሰላም ድርድር አንድ መቶ ሺህ የሚጠጋ አገር ወዳድ ሕዝብ ያለቀበትን ባድመንና አካባቢውን ለኤርትራ ማስረከብን ዋና ዓላማ ያደረገ ነው። “ቁማሩ” እንደ ደብዳቤው “ከሰላሙ በኋላ ሁሉም ወደ ነበረበት ይመለሳል (ትግራይና ኤርትራ አንድ “አገር” ሲሆኑ ባድመም የሁለቱም ትሆናለች)። ኤፈርት በከፍተኛ ደረጃ ያከማቸውን ሃብት ኤርትራ ላይ ኢንቨስት በማድረግ ኢኮኖሚውን በመቆጣጠር ኤርትራን “ማልማት” ይሆናል። ይህንን ዕቅድ እውን ለማድረግ ባድመን አስመልክቶ ለሚነሳው ጥያቄ ወያኔ አይከራከርም። በዚህም ስልት ሻዕቢያ በአሸናፊነት ድርድሩን ይቀበላል”።

የጎልጉል መረጃ ምንጭ እንደሚሉት ደግሞ ህወሓት አሁን ኢትዮጵያ ላይ የሚጫወትበት የፖለቲካ ካርድ ስላለቀና ስለተቃጠለበት ከሻዕቢያ ጋር አስቸኳይ ዕርቅ ማድረግ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ዕርቁን እውን ለማድረግ ጉዳዩን ወደ ኃያላን አገሮች ወስዶታል። በባርነት የሚያገለግላቸው ኃያላን የሚባሉት አገሮች ለዚሁ ተግባር ደፋ ቀና እያሉ ነው።

የምስራቅ አፍሪቃን የፖለቲካ ቀጣና እንደ ምክንያት በመንተራስ አሜሪካ ሁለቱን ተገንጣይ የወንበዴ ቡድኖች (ወያኔና ሻዕቢያን) እንድታስታርቅ ህወሓት በወስዋሾቹ አማካይነት ወደ ፍጻሜው ተዳርሰዋል። ለዚህም ይመስላል የአንዳንድ ተቃዋሚ ኃይሎች ስም ከኤርትራ ጋር እየተነሳ ያለው።

ኸርማን ኮሆንም ቢሆኑ ፈራ ተባ እያሉ ሲጠቃቅሱ የነበረውን ሁለቱን “አገራት” የማስታረቅ ጉዳይ አንገብጋቢ መሆኑንን በይፋ አመላክተዋል። እኚሁ ለወንበዴው የህወሓት ቡድን ኢትዮጵያን በገጸበረከትነት ያስረከቡ ሰው፤ በሃሳባቸው ምን ያህል እንደሚገፉበት ባይታወቅም በመርህ ደረጃ ሁለቱን አካላት ለማስታረቅ ከየአቅጣጫው አረንጓዴ መብራቶች መኖራቸውን የጎልጉል ታማኝ ምንጮች ያረጋግጣሉ። በዓለምአቀፍ ደረጃ የሃይማኖት መሪ የሚባሉትም ሰዎች የዚሁ ፖለቲካ አካል ናቸው።

በተለይ ህወሓት የዓለምአብያተ ክርስቲያናት ምክርቤትን ጠጋ በማለት አጀንዳውን ካስጀመረ ቆይቷል። ም/ቤቱ በአገራት መካከል ሰላም ለማስፈን የሚጥርና ተገቢውንም ሁሉ የሚያደርግ በመሆኑ ጉዳዩን በዚሁ መልኩ መመልከቱ የሚያስጠረጥረው አይደለም። ሆኖም በኢትዮጵያና ኤርትራ ስም ህወሓት ከበስተጀርባው ስምምነቱንና ዕርቁን በትግራይና በኤርትራ መካከል ለማድረግ ደፋ ቀና እያለ እንደሆነ ለጎልጉል የደረሰው መረጃ ያመለክታል። በምክርቤቱ ያሉቱ ከዓላማው ቅዱስነት አኳያ የህወሓት መሠሪነት ብዙም ትኩረት የሰጡት አይመስልም።

በአገር ውስጥ ያለው ሁኔታ እየተወሳሰበና መፍትሔው እየጠፋ ባለበት ባሁኑ ወቅት ህወሓት በማኒፌስቶው ላይ እንዳሰፈረው ትግራይን ሪፑብሊክ የማድረግ ዕቅዱ ከታሰበው ጊዜ የቀደመበት ይመስላል። ለኢትዮጵያ የመቶ ዓመት የቤት ሥራ ሰጥተናል እያለ ሲፎክር የነበረው የህወሓት ፈጣሪና ጌታ ሻዕቢያም “ተስፋው” ግቡን አልመታለትም። ከዚያ አልፎ በኢትዮጵያ አንጡራ ሃብትና በህወሓት ተላላኪነት ኤርትራን ሲንጋፖር የማድረግ ሕልሙ ከህወሓት ጋር በከፈተው ጦርነት ቅዠት ሆኖ ቀርቷል። ከነዚህ ሁሉ ጉዳዮች በመነሳት ሁለቱ የወንበዴ ቡድኖች ስምምነት የማድረግ ፍላጎታቸው ባሁኑ ሰዓት ቢነሳሳ የሚገርም እንዳልሆነ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።

ከበረሃ ጀምሮ ችግር ያልተለየው የወያኔና የሻዕቢያ ወዳጅነት ተበጠሰ ሲባል እየተቀጠለ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ የደረሰው በህወሓት ውስጥ ባለው መስመር የለቀቀ የኤርትራ ተቆርቋሪነት እንደሆነ ይታወቃል። የመለስ ዜናዊ ሬሣ ወደ ከርሰመቃብር በወረደበት ጊዜ አዲሱ ለገሰ በስንብት ስነ ስርዓቱ ላይ ስለ መለስ ባነበበው ሰፊ ጽሁፍ የኤርትራን ጉዳይ አንስቶ መለስን እንዲህ በማለት አወድሶት ነበር፤ “መለስ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት መካሄድ የለበትም” የሚል የጸና እምነት እንደነበረው ከገለጸ በኋላ “በድምጽ ብልጫ ተሸንፎ የገባበትን ጦርነት በብቃት መርቷል” በማለት የኤርትራና የመለስን ወዳጅነት ስንብቱ ላይም ህዝብ ልብ እንዲል መናገሩ ይታወሳል።

በባድመ ጉዳይ ከኢሳያስ ጋር ያልተፈለገ የከረረ ግጭት ውስጥ የገባው የመለስ ህወሓት፤ ኤርትራን ለዓለምአቀፉ ኅብረተሰብ በማሳጣት ለማዕቀብና ስቃይ ሲዳርጋት መቆየቱ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። በሌላው በኩል ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ የኤርትራ ተቃዋሚ ድርጅቶችን አሰባስቦ ለኤርትራ የሽግግር መንግሥትና ሕገመንግሥት መለስ ሳይሞት አዘጋጅቷል። ይህንን የመለስ ሤራ ሻዕቢያና ኢሳያስ ጠንቅቀው የሚያውቁት ነው። ከዚህ ሁሉ በላይ ግን የዝምድና ጉዳይ በማይበጠስ ገመድ ስላስተሳሰራቸው ነበር እነ ስብሃት ነጋ፤ ኤርትራ ጦርነት ቢነሳባት ከህዝቧ ይልቅ እኛ ቀድመን እንዋጋለን በማለት በአደባባይ ሲናገሩ የኖሩት።

“ኤርትራ የትግራይ ናት”፤ “ትልቅ ነበርን ትልቅ እንሆናለን” – ህወሃት በሚል ርዕስ የዛሬ ሁለት ዓመት ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ባወጣው ዘገባ ላይ ስለዚህ የህወሓትና የስብሃት አቋም ይህንን ማለቱ አይዘነጋም፤

“ስለ ኤርትራ ከተወላጆቹ በበለጠ በልበሙሉነትና ባለቤትነት መንፈስ በገሃድ የሚሟገተው የቀድሞው የህወሓት መሪና የነፍስ አባት ስብሃት ነጋ በወቅቱ ይመራው ስለነበረው የሰላምና የልማት ዓለም አቀፍ ተቋም ሲናገር፤ “የሃገሪቱን ገፅታ ለመገንባት የኢትዮ-ኤርትራን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማድረስ የሚያስችሉ ስራዎችን እያከናወነ” ነው በማለት ኢህአዴግ በፓርላማ ስም ለሚመራው የምክርቤት ኮሚቴ መናገሩን ሰኔ 5፣2007 የታተመው የኢቲቪ (ኢብኮ) ዘግቧል። የውጭ መከላከያና ደህንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮቴውም የስብሃትን ዘገባ ካደመጠ በኋላ “ኢንስቲትዩቱ የኢትዮ-ኤርትራ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል” ማሳሰቡ ጨምሮ ገልጾዋል።”

ከዚህ ሁሉ የዓመታት የበስተጀርባ ሥራ በኋላ ነበር በኢትዮጵያ ስም በህወሓትና በሻዕቢያ መካከል ሊደረግ የታሰበው የሰሞኑ የዕርቅ ሃሳብ ይፋ የሆነው። በኅዳር ወር (2010/2017) መግቢያ ላይ ሪፖርተር እንደዘገበው የምሥራቅ አፍሪካ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባዔዎች ማኅበር (አሜሰያ)/Association of Member Episcopal Conferences in Eastern Africa (AMECEA)/፣ ዕርቁን እውን ለማድረግ ከሁለቱም ክፍሎች ይሁንታ አግኝቷል። ከዚህ አስቀድሞ (በየካቲት 18፤ 2007ዓም ወይም 25 February 2015 በታተመው የሪፖርተር ዘገባ ላይ) የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሁለተኛው ካርዲናል ሆነው በቫቲካን የተሾሙት “ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ ሱራፌል የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦችን በማቀራረብ በሁለቱ አገሮች መካከል ዘላቂ ሰላምና ወንድማማችነት ዳግም ለመመለስ እንዲሠሩ” ከህወሓት ጥሪ እንደቀረበላቸው ይታወሳል። በዚህ የዛሬ ሁለት ዓመት በፊት በተደረገ ጥሪ መሠረት ነበር የሰሞኑ የህወሓትና የሻዕቢያ ዕርቅ በኢትዮጵያ ሽፋን መካሄድ የጀመረው።

እገዛታለሁ የሚላትን አገር ፖለቲካዊ ፋይዳ አመናምኖ የገደለው መለስ ዜናዊ በዕቅዱ አለመሳካት “እብድ፣ ያበደ ውሻ፣ ተናካሽ ውሻ፣ አጉራ ዘለል፣ ዱርዬ …” እያለ ኢሳያስ አፈወርቅ ላይ ሲሳለቅ ቢቆይም ዛሬ ህወሓት በኢትዮጵያ ስም የሚጠየቀውን በማድረግ፣ ዳግም ድንበር ሰጥቶ (ባድመን) ለመታረቅ በመወሰኑ የ“ሃይማኖት መሪዎች” የሚባሉት ጉዳዩን ከዳር ለማድረስ እንደማይቸገሩ የዜናው ምንጮች ያስረዳሉ።

በኢትዮጵያ ህዝብ ሲረግፍ፣ ሲታሰርና፣ ሲገረፍ፣ አገሪቱ ወደ ጎሣ ጦርነት ስታመራ፣ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች ሲፈናቀሉ ከጥቂት ታይታዊና ልማታዊ እንቅስቃሴ በስተቀር ዝምታን የመረጡት የሃይማኖት መሪዎች ከሁሉም በላይ ያሳሰባቸው የሻእቢያና የህወሓት ዳግም መወዳጀት ነው። የሃይማኖት አባቶች ለእነ መረራ ጉዲና፣ በቀለ ገርባ፣ አንዷለም አራጌ፣ ኦልባና ሌሊሣ፣ አህመዲን ጀበል፣ እስክንድር ነጋ እና ሥፍር ቁጥር ለሌላቸው የኢትዮጵያ ልጆች ከእስር መፈታት ግልጽ ጥያቄ ማቅረብ ጀምረው ካልተፈቱ ምግብ አንቀምስም በማለት የረሃብ አድማ እስከመምታት ሊደርሱ በተገባቸው ነበር። የሃይማኖት ስብዕናቸው ልዕልና ያጣ በመሆኑ የታዘዙትን የሚፈጽሙ “መንፈሳዊ ካድሬዎች” ሆነዋል በማለት አስተያየት ሰጪዎች ሲማርሩ በየጊዜው ይሰማል።

ካድሬዎች የወረሩት የሃይማኖት ተቋም መስቀል ይዞ ወደ አደገኛ የክህደት ጠረጴዛ ሲያመራ ሌሎች አካላት ዝም ማለታቸው በርካቶችን ያሳዘነ ጉዳይ ሆኗል። ይህንን ከላይ የተቀመጠውን ሃሳብ የላኩልን ተቆርቋሪ እንዳሉት የአገር ዕርቅ ከሆነ ጉዳዩን ህወሓት በምሥጢር ሊይዘው አይገባም። በሕዝብ መካከል ጸብ የሌለ በመሆኑ ገለልተኛ ወገኖች ዕርቁን ሊተገብሩት ግድ ነው። ዕርቁ በኢትዮጵያ ስም ከሆነ በዓለምዓቀፉ የእምነት ተቋማት ውስጥ ያሉት የህወሓት ሰዎች ከማስማማቱ ስራ ሊታቀቡ ይገባል። ለዕርቅ የቀረበው እጅ መንሻ ከህወሓት ብቸኛ መዘውር ወጥቶ ቢያንስ በኢህአዴግ ደረጃ ሊመከርበት ይገባል። ይህንን ሲያልፍ ደግሞ ጉዳዩ የሕዝብ እንደመሆኑ ሕዝብ በገሃድ ሊያውቀውና ሊመክርበት የግድ ይላል።

መቀሌ ላይ ሲሰዳደብ የከረመው የህወሓት ወንበዴዎች ቡድን የሚፈልጋቸውን ከመራረጠ በኋላ መግለጫ አውጥቶ ነበር። ለሕዝብ ይፋ ያደረገው ያቋም መግለጫ ላይ ከኤርትራ ጋር ሊያካሂድ ስላሰበው ስምምነትም ይሁን ግጭት ምንም ትንፍሽ ያለው ነገር አለመኖሩ አሁን በኢትዮጵያ ስም በህወሓትና ሻዕቢያ መካከል እየተሠራ ላለው “እኩይ ዕርቅ” አስረጅ ሆኖ ቀርቧል።

በማሕበር ገስገስቲ ብሄረ ትግራይ /ማገብት/ አዋላጅነት በሻዕቢያ የተደቀለው የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግምባር /ህወሃት/ በነጻ አውጪ ስም አገር መግዛት በጀመረበት ጊዜ ለእርሱ የበረሃ ራዕይ የሚለውን፤ ለኢትዮጵያ ግን ትውልድ የሚጨርስ ነቀርሳ የሆነውን ችግር ተከለ። ራሱን መሪ አድርጎ በሾመው መለስ ለማኝነት በዓለም እስካሁን ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የተባበሩት መንግሥታት ፊት ቀርቦ አገር እንድትገነጠል በይፋ ለመነ፤ ሰዎችን እንደ እህል በዘር ጆኒያ ሰፈረ፤ በሰላም አብሮ የኖረን ሕዝብ እርስበርሱ አጋጨ፣ ነዋሪዎችን ከመኖሪያቸው አፈናቀለ፤ መሬት ነጠቀ፤ ዜጎችን አዋረደ፣ አሰረ፣ ገረፈ፣ አሰቃየ፣ ገደለ፣ ጨፈጨፈ፣ … በመላው ኢትዮጵያ የማይጠፋ እሳት ለኮሰ፤ አሁን እሳቱ ራሱን የሚበላበት ሰዓት ላይ ደረሰ! ስለዚህ የዘረፈውን ይዞ፣ ሱዳንና ኤርትራን ወዳጅ አድርጎ፣ አገር መስርቶ “በሰላም” ወደሚኖርበት የ“ዕርቅ” አቅጣጫ እየተጓዘ ነው። “የሚያሳዝነው” ይላሉ የጎልጉል መረጃ አቅራቢ “ለዚህ እኩይ ዕርቅ አውቀውትም ይሁን ሳያውቁት የሃይማኖት አባቶች ሽፋን መሆናቸው ነው።”

***************************

Filed in: Amharic