የፌዴራል ፖሊስ በኢቶሪካ አልበም ያሰራቸውን ማህሌት ሰለሞን እና የሱፍ ያሲንን ፍርድ ቤት አቀረበ

ጋዜጠኛ ወንድወሰን ተክሉ

የፌዴራል ፖሊስ ዛሬ የእውቁን አርቲስት ቴዲ አፍሮን ቃለ አቀባይ እና ምክትል ማናጀር ማህሌት ሰለሞንን እና የረጅም ግዜ ጋደኛ ዩሱፍ ያሲን ፍርድ ቤት አቅርቦ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ እንደጠየቀ ምንጮቻችን ገለጹ።

ሜክሲኮ አደባባይ በሚገኘው ማእከላዊ እስር ቤት የታሰሩት የእውቁ አርቲስት ቴዲ አፍሮ ቃለ አቀባይና ምክትል ማናጀር ማህሌት ሰለሞን እና የረጅም ግዜ ጋደኛው ዩሱፍ ያሲንን ዛሬ በድንገት ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ የተደረገ ሲሆን ፖሊስ የተከሳሻን ከሕግ ጠበቃዋ ጋር የመነጋገር መብት አግዶ ከተካሳሽ ጋር ሳያገናኝ ወደ ፍርድ ቤት ሊያቀርባት የቻለ ቢሆንም የተከሳሻ ጠበቆች ግን በግላቸው ባደረጉት ጥረት ከተከሳሻ ጎን መገኘት መቻላቸውን ማወቅ ተችላል።

በከሳሽ ፖሊስ በኩል በተለይም ማህሌት ሰለሞን የአርቲስት ቴዲ አፍሮ አዲስ አልበም ኢቶሪካን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳንሰጥ ታግደናል በማለት በሀሰት ዜና አሰራጭታለች እና በአርቲስት ቴዲ አፍሮ ስቱዲዮ ሽጉጥ ስላገኘን ይህ የጦር መሳሪያ መኖሩን ታውቃላች በሚል የከሰሰ ሲሆን በተጨማሪም ክሱን ለማጥበቅ በዚህ ምርጫ ሰአት ሆን ብላ አመጽ ለማነሳሳት በማህበራዊ ሚዲያ መልእክት አስተላልፋለች የሚሉና መሰል ክስ ማክበጃዎችን በመጠቀም ክስ በማቅረብ ለተጨማሪ ምርመራ የ 14 ቀን ቀጠሮ እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን ጠይቃል።

በተከሳሽ ጠበቃ በኩል ደንበኛቸው ምንም አይነት ወንጀል ያልፈጸመች መሆኑን በመግለጽ እና ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ እለት ሊሰጡት የነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ታግዶ መሰረዙ የሚታወቅ ሲሆን ዛሬ በዋለው ችሎት ላይ ግን ፖሊስ ጋዜጣዊ መግለጫውን አላገደም በማለት ለፍርድ ቤቱ ሲናገር ተደምጣል።

በተያያዘ ዜና በትናንትናው እለት CMC አካባቢ ባለው የአርቲስት ቴዲ አፍሮ ስቱዲዮ የፌዴራል ፖሊስ ነን ያሉ ታጣቂዎች ሰብረው ገብተው ዘረፋ ከመፈጸማቸውም በላይ የጥበቃ ሰራተኛውን ጨምሮ ስምንት ሰራተኞች ታፍሰው መታሰራቸውን ማወቅ ተችላል።

ፍርድ ቤቱ በፖሊስ በኩል የቀረበለትን የ14 ቀን ቀጥሮ የፈቀደ ሲሆን የዩሱፍ ያሲንን ክስ እና ከስቱዲዮው የታፈሱትን ስምንቶቹን ክስ ጉዳይ በስፋትና በዝርዝር የምንመለስበት ይሆናል።

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.