ከይኄይስ እውነቱ
‹‹ካልእ ፍጥረት›› በሃይማኖት የትርጓሜ መጻሕፍትና ባንዳንድ ባህላዊ ትረካዎች እንደምናነበው የሰው እና የአውሬ መልክ ያለው ልዩ ፍጥረት ነው፡፡ ‹ሰበድአት› በመባልም ይታወቃል፡፡ ካልእ የሚለው ቃል በግእዙ ልዩ ኹለተኛም ማለት ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ አግባብ ልዩ እንግዳ ከተለመደውና ባብዛኛው አስተዋይ/አመዛዛኝ/ምክንያታዊ ሰው ከሚቀበለው ወጣ ያለ በሚል ፍቺ ተጠቅሜበታለሁ፡፡
አንዳንዶች ፈሪሃ እግዚአብሔር ካለመኖር እና ጭርሱኑ ከሕሊና መለየት ይሁን፣ ሆዳቸውን አምላካቸው አድርገው ይሁን፣ ከዐቅም ማነስም ይሁን፣ አከርካሪ አልባ ከመሆንም ይሁን፣ እንደ ብአዴን ሞቶ የተወለደ (stillborn) በመሆንም ይሁን፣ ‹የባላገር ፖለቲከኛ›በመሆንም ይሁን፣ የሥልጣን ጥማት ዐቅላቸውን አሳጥቶት ይሁን፣ ወዘተ. ኢትዮጵያ አገራችንን በወሳኝ ሰዓት እየተነሡ የሚፈታተኗት ‹ካልእ ፍጥረታት› አሉ፡፡ አለመታደል ሆኖ አገራችን የእነዚህ ‹ካልእ ፍጥረታት› ደሀ ሆና አታውቅም፡፡
እነዚህ የተጠቀሱት ጉዶች ለምን ይሆን ልቡሳነ ሥጋ አጋንንት መሆንን የመረጡት? ለምን ይሆን ሕይወቱን በሙሉ ከሰው በታች በግፍና በበደል ውስጥ ለኖረ ሕዝብ ጥፍጣፊ ርኅራኄና ሰብአዊነት ያጡት? በባዕድ አገር መሼጦ ሆነው ሲያበቁ አገር ቤት ያለ ሕዝባችንን ሰቆቃ የሚያራዝሙት? በኢትዮጵያዊነት፣ በዐምሐራነት፣ በክርስትና ስም እየነገዱ፣ በባዕድ አገር የሚኖረውን ወገን እያጭበረበሩ ርጥባን በመሰብሰብ ‹የአንጋሽነት› አባዜ ተጠናውቶአቸው ሕይወታቸውን አስይዘው ለትግል የወጡትን በመከፋፈል የተጠመዱት? ርእሰ መጻሕፍቱ እነዚህን ‹ካልእፍጥረታት› የአምልኮ መልክ ያላቸው ኃይሉን ግን የካዱት ብሎ ይገልጻቸዋል፡፡ እንዴት ዓይነት መረገም ቢሆን ነው ከወያኔ ሕወሓት፣ ከኦነግ (በግልባጩ ኦሕዴድ/‹ብልግና›) እንዲሁም ከነዚህ ፈጣሪ ሻእቢያ ጋር ብአዴናዊ አሽከር ሆነን ካልሠራን ሞተን እንገኛለን ያዙኝ ልቀቁኝ እያሉ የሚሟገቱት?
አንዳንዴ እንደዚህ ዓይነት ‹ፍጡሮች› መኖራቸውና ከእነርሱ ጋር አንድ ፕላኔት መጋራታችን ከፍተኛ መረገም ሆኖ ይሰማኛል፡፡ ምነው ኢትዮጵያ እንደነዚህ ዓይነቶቹ እሾኽ እና አሜኸላ በብዛት የበቀሉባት አገር ሆነች? ለምንድን ነው ምስጢሩ ያልገባቸው ግለሰቦች፣ አገዛዛዊ ያልሆኑ መደበኛና ኢ-መደበኛ ብዙኃን መገናኛዎች ከነዚህ ‹ካልአን ፍጥረታት ጋር› አንድ ጎራ እንደሆንን እና የሐሳብ ልዩነት ብቻ እንዳለን አድርገው ጉዳዩን የሚያቃልሉት? በእኔ እምነት ውገናቸው ከጠላት እንጂ ከተበደለውና ፍርድ ከተጓደለበት÷ ልዩ ልዩ ጸዋትወ መከራ ሲቀበል ከኖረው እና አሁንም እየተቀበለ ከሚገኘው ሕዝብ ጎን አይደለም፡፡
አዎን! ከእንዲህ ዓይነቱ ምልልስና አተካሮ ርጉም ዐቢይና አገዛዙ እንደሚያተርፍ ጥርጥር የለውም፡፡ ይሁን እንጂ በመልከስከስና በመርመጥመጥ ከመጓዝ ደፍርሶ መጥራት የግድ ይላል፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ ርጉም ዐቢይና አገዛዙ ተጠጋግኖሊቀጥል የሚችልበት ዕድል የለውም፡፡ የተፈጥሮ ሞቱን መሞቱ አይቀሬ ነው፡፡ ርጉም ዐቢይን ስናስወግድ ግን ሌላና የማይጠገን ጥፋት ፈጽመን መሆን የለበትም፡፡ የርጉም ዐቢይ አገዛዝ የመንፈስ አባቱ ወያኔ ሕወሓት ነው፡፡ ኦነግ ‹በአሜባዊ› ቅርፁ ደግሞ ራሱ ‹ብልግና› የተሰኘው ኦሕዴድ ነው፡፡ ሰሞኑን ኦነጋውያን አሜቦች (በብዙ ኢትዮጵያውያን ደም ተጠያቂ የሆነው ጀዋር እንዲሁም ፊደል የቆጠረ የማይመስለው ስንኩል አእምሮ ጸጋዬ አራርሳ ወዘተ.) አገዛዛችን ተናጋ ብለው ሲወራጩ እያስተዋልን አይደለም? ታዝባችሁ እንደሆነ ከአገዛዙም ወገን ይሁኑ በተቃዋሚም ስም እያጭበረበሩ ያሉ በሙሉ በዚህች ሰቆቃ በበዛባት ምድርና የስቃይ ጥግ እያየ ባለ ሕዝባችን የግፍ ዘመንን በዋናነት የሚያራዝሙት ‹ነፃ› በሆነ ባዕድ ምድር የሚገኙ ‹ካልአንፍጥረታት› መሆናቸው ሁሌም ይገርመኛል፡፡ ምን ዓይነት መረገም ቢሆን ነው በ‹ነፃ› ምድር እየኖሩ በስሟ በሚነግዱባት አገራችን እና በስሙ በሚነግዱበት ሕዝባችን በተግባር ባርነት የሚመኙለት?
እውነት ውሎ አድሮ መገለጡ አይቀርምና፣ የዐምሐራ ፋኖእውነቱን የሚጋፈጥበት ሰዓት ዘግይቷል ካልተባለ አሁን ነው፡፡ ‹እውነቱ ምንድን ነው?› የሚል ጲላጦስያዊ ጥያቄ የሚያነሡ እንዳሉ እሙን ነው፡፡ እውነቱ የዐምሐራ ፋኖ ይዞ የተነሣውን ዓላማና ግብ መሠረት ያደረገ ራእይ ያለው ድርጅት አሁንም የለውም፡፡ በነገራችን ላይ ‹አፋብን› እንደ ብአዴን ሞቶ የተወለደ ነው፡፡ ‹እንግዴ ልጅ› ነው፡፡ የዐምሐራ ፋኖን የሚወክልና የሚመጥን ‹አካል› አይደለም፡፡ እንግዴ ልጅነቱም ለወያኔ ለኦነግ ነው፡፡ የነሱም መጠቀሚያ ከሆነ በኋላ ተቆርጦ የሚጣል ነው፡፡ ከጊዜያዊ አመራሮቹ ጥቂቶቹ (ዘመነ፣ ዐሥረስ፣ ምሬ ወዳጆ) አንድም ብአዴናዊ መሠረት ያላቸው÷ ወዲህም በክህደት የታወቁ ፈጣሪያቸው ወያኔ ‹የሚናፍቃቸው› ‹የባላገርፖለቲከኞች› ናቸው፡፡ የዐምሐራ ፋኖ በተለይ የዐምሐራ ሕዝብ ባጠቃላይ እውነቱን መጋፈጥ አለብህ፡፡ በጎጥ በቀዬ በወንዝ መሸጎጡን አቁመህ የሕዝብህን ህልውና እና ትልቁን አገራዊ ሥዕል ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ በሽታውን የደበቀ መድኃኒት የለውም እንዲሉ ውስጥ ውስጡን የሚንተከተከተው ማልጎምጎም ይፋወጥቶ ኹነኛ መፍትሔ ያሻል፡፡
‹ካልአን ፍጥረታት› ላልናቸው ዓይነተኛ ምሳሌዎች ካስፈለገን ያወቀ መስሎት እንደ ነሐስ የሚንሿሿው ለጥፋት ብቻ ሲሆን ብቅ የሚለውና ‹የፖለቲካዊ ስቶኮልም ሲንድረም› ሰለባ የሆነው ልደቱ እና የዕድሜ ብቻ ሳይሆን የአስተሳሰብ ‹ጀምበሩ› እየጠለቀችበት ያለው፣ በማንነት ቀውስ እና በብአዴናዊ ጭንጋፍነት የሚታወቀው አንዳርጋቸው አሉልን፡፡ በኢ-መደበኛ ሚዲያዎች የሚወራጩ ተከታዮችም አበጅተዋል፡፡ ሲያልቅ አያምር አሉ!!!
አንዳንዶች በክብር ጀምረው በኀሣር/በውርደት ያጠናቅቃሉ፡፡ ሊቃውንት አባቶች ሲናገሩ ያለፈ ጽድቅ አይጠቅምም፤ የዛሬ ማንነት እንጂ፡፡ ደግሞ ደጋግሞ እንደ እሪያ መጨማለቅ ሰውነት አይደለም፡፡ እንደዚህ ዓይነቶቹ ተደጋጋሚ አጥፊዎች በመሆናቸው ሊቃውንት የማይፈወሱ ድውያን÷የማይመለሱ ጊጉያን (በዳዮች) ይሏቸዋል፡፡
ወገኔ! ኢትዮጵያዊ ከወገኑ ጋር ሕዝብ ለሕዝብ በሚደረግ ግንኙነት ረገድ ጊዜው ሲፈቅድ ለመነጋገር ችግር የለበትም፡፡ እንደ ሕዝብም‹ነፃ አውጪ› አንጠብቅ፡፡ ዐቅማችን የፈቀደውን የየራሳችንን ድርሻ እንወጣ፡፡ በስንፍና መና ከሰማይ እንዲወርድልን አንጠብቅ፡፡ ኢትዮጵያን የሚታደጋት ‹ነፃ አውጪ› ድርጅት አይደለም፡፡ ከግማሽ ምእት ዓመት በላይ ለኢትዮጵያ ጠንቅ በሆኑት ‹ነፃ አውጪ› ተብዬ ድርጅቶች (ሻእቢያ፣ ሕወሓት እና ኦነግ፤ በሕፅን ዘላለማዊው አሽከር ብአዴን ሳይረሳ) እንወቅባቸው፡፡
ጨለማ ከብርሃን ጋር ኅብረት እንደሌለው ሁሉ ከነዚህ አጋንንታዊ ድርጅቶች እና ልጣቸው ከራሰ ጉድጓዳቸው ከተማሰ አለቆቻቸው ጋር ኅብረት የለንም፡፡ ላገራችን ኢትዮጵያ እና ለሕዝቧ ዘላቂ ሰላም የምንሻ ከሆነ ከየትም ፍጪው ዶቄቱን አምጪው (the end justifies the means) ከሚል የስንፍናና ድንቊርና አካሔድ ባስቸኳይ ልንላቀቅ ያስፈልገናል፡፡ ሕገ ወጥ አቋራጭ መንገድ የትም አያደርስም፡፡ በድቡሽት ላይ ቤት አይገነባም፡፡ የወደፊቱን መልካም ሊጥ በብአዴናዊ፣ ሻእቢያዊ፣ ሕውሓታዊ እና ኦነጋዊ የገማ የሸተተ እርሾ ለማብኳት እና ለመጋገር አንሞክር፡፡ ውጤቱ ሳይታለም የተፈታ ነውና፡፡ የሚወጣ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል እንዲሉ፡፡




















